Sunday, 28 October 2018 00:00

“ወርደን እናየዋለን!”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጎረቤታም ገበሬዎች ስለሚዘሩት እህል ይመካከራሉ፡፡
አንደኛው -
“ዘንድሮ ምን ብንዘራ ይሻላል?”
ሁለተኛው -
“በቆሎ ብንዘራስ?”
አንደኛው -
“አዬ በቆሎ አይሆንም፡፡ በቆሎ በቀላሉ በእንስሳቱ ስለሚጫር አያስተርፉልንም፡፡”
ሁለተኛው -
“እንግዲያው ባቄላ ይሁና?”
አንደኛው -
“አዬ እሱማ አልሸሹም ዞር አሉ ነው”
ሁለተኛው -
“ካልሆነ ማሽላ ይሁና?”
አንደኛው -
“ማሽላ ደግሞ ገና ከመሬት ብቅ ሳይል የወማይ ወፍ መጫወቻ መሆኑ ነው፡፡”
ሁለተኛው -
“አሁን እኛን በጣም የሚያስፈራን እህሉ ከመሬት ብቅ ሳይል ተጭሮ መበላቱ ነው እንጂ ከበቀለማ በኋላ ጠባቂ እናስቀምጥለታለን፡፡”
አንደኛው -
“ይልቅ አንድ ዘዴ ታየኝ”
ሁለተኛው -
“ምን ታየህ?”
አንደኛው
“ወጣም ወረደ የሚያስቸግሩን ዝንጀሮና ጦጣ ከሆኑ፣ መንገዳችን ላይ አንዳቸውን ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ያልዘራነውንና ለእነሱ የማይመቻቸውን እህል ጠቅሰን ለምን አናታልላቸውም?”
ሁለተኛው -
“በጣም ድንቅ መላ ነው”
በዚህ ተስማምተው በቆሎ ዘርተው ሲመለሱ፣ ጦጢት ዛፍ ላይ ሆና አገኙዋት፡፡
ጦጢት
“አያ ገበሬ?”
ገበሬ
“እንዴት ከርመሻል ጦጢት?”
ጦጢት
“ዘንድሮ ምን ዘርተህ መጣህ?”
ገበሬ -
“ተልባ፡፡ ተልባ ዘርቼ መጣሁ፡፡”
ገበሩው ይሄን ያለው ጦጣ ተልባ ጭራ ማውጣት እንደማትችል ስለሚያውቅ ነው፡፡
ጦጢትም፤
“ይሁን፡፡ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
***
እኛ ስለ ሌሎች ደካማ ጎን ስናስብ፣ እነሱስ ስለኛ ደካማ ጎን ምን ያስባሉ? ብሎ ማሰብ ከብዙ ስህተት ያድነናል፡፡ አስቀድሞ ነገር በሌሎች ደካማ ጎን በመጠቀም ዕድገትን ማሰብ ተላላነት ነው፡፡ “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚለውን ተረት ማጤን እጅግ ተገቢ የሆነበት ወቅት ላይ መሆናችንን እናስተውል፡፡ ክልልና ክልል፣ ፓርቲና ፓርቲ፣ ድርጅትና ድርጅት፣ ቡድንና ቡድን ቀና ውድድር ቢያደርጉ እንጂ በመሻኮትም ሆነ በመጠላለፍ ከቶም ትርፍ አያገኙም፡፡ ቀና ያልሆነውን መንገድ ለዘመናት እንደማያዋጣን አይተነዋል፡፡ በጠረጴዛ ውይይት ካልሆነ የማይፈቱ አያሌ ችግሮች እንዳሉብን እየታወቀ፤ መልሰን ግጭትና ሴራ ውስጥ መዘፈቅ ውሃ ወቀጣ ከመሆን አይዘልም፡፡
“እኛ ሳንስማማ
እኛ እየተባላን
መቼም ሳንቻቻል
እንኳን ሰማዩና መሬቱም ይርቃል!”
ስለ ሰላም እያወራን፣ ስለ ፍቅር እየሰበክን፣ ስለ እርቅ እያወሳን ወዘተ … መልሰን ከተጋጨን የተጫረው ብርሃን ይጨለመለማል፡፡ የለኮስነው ቀንዲል ይጠፋል፡፡ ያቀድነው ዲሞክራሲ፣ እናጠራዋለን ያልነው ፍትህ ሁሉ
“ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ይሆንብናል፡፡
ምንም እንኳ የተያያዝነው የለውጥ ሂደት ዕድሜው አጭር ቢሆን፣ ገና ዳዴ እያልን ነው ብለን ስህተት እያየን እንደ ፍጥርጥሩ ማለት አንችልም፡፡ ባወጣ ያውጣው ብለን ጥፋትን ሳንዳኝ፣ ችግርን በሰዓቱ ሳንፈታ መጓዝ “ሃማሊያን በሁለት ቆራጣ እግር” እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡ ገና ብዙ ዳገት እየጠበቀን ሜዳው ላይ ከደከምን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆናል፡፡ ከውጪው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ስምምነት መፈራረማችን በጎ ጎናችን የሆነውን ያህል፤ የውስጥ ችግራችንን በወቅቱ አለመፍታት አገርን ስጋት ላይ መጣል ነው፡፡ ችግራችን ከላይ ከላይ እንደሚወራውና የሚለባበስ ነገር አይደለም፡፡ ግልጥ ያለና አስጊ ነው፡፡ እንደ ጦጣዋ “ወርደን እናየዋለን” ማለት ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለእኛው ነውና፣ መሬት የረገጠ ነገር እንሥራ፡፡
ዛሬም፤
“… ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ” ብንል ይሻላል!
ልዩ ልዩ ሹመቶች እየተሰጡና ተቋማት እየተጠናከሩ መሆኑ ደግ ነገር ነው፡፡ ሹመኞች ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ አይወጡም የሚለው መለኪያው ጊዜ ቢሆንም ቢያንስ ሙስና ውስጥ አይዘፈቁም የሚል ዕምነት አለን፡፡ ተስፋችን ትልቅ ነው፤ ጉዞው ጠመዝማዛ ነው - ጥናቱን ይስጣችሁ ማለት የአባት ነው!

Read 7520 times