Saturday, 27 October 2018 10:11

ቶም ከርክማን እና ዐቢይ አሕመድ

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(2 votes)

እ.ኤ.አ. በ2016 በአሜሪካው ኤቢሲ ቴሌቪዥን አማካይነት ለዕይታ መብቃት የጀመረው “Designated  Survivor” ተከታታይ ድራማ፣ የአሜሪካን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ድብቅ ሴራዎችን ያሳየ ነው፡፡ በዴቪድ  ጉገንሃይም የተፈጠረውና “24” በተሰኘው የፎክስ ቴሌቪዥን ተወዳጅ ድራማ ላይ “ጃክ ባወር” የተባለውን መሪ ገጸ-ባሕርይ ሲጫወት በምናውቀው ካናዳዊው ተዋናይ ኪፈር ሱዘርላንድ መሪ ተዋናይነት የሚቀርበው ይህ ድራማ፣ ከሳምንት ሳምንት በማይጠበቁ ክስተቶቹ የበርካታ ተመልካቾችን ቀልብ እንደሳበ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተጉዟል፡፡ በዚህ ድራማ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ትርክት በአንዳንድ መልኮቹ ከአሁኑ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አይቼበታለሁ፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡
ቶማስ ከርክማን የተባሉ የአሜሪካ  መንግሥት ባለ ዝቅተኛ ደረጃ  የካቢኔ አባል፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለኮንግረሱና ለሴኔቱ የጋራ ስብሰባ ንግግር የሚያደርጉበት “State of the Union” ተብሎ የሚታወቀው  ዓመታዊ መንግሥታዊ ሁነት በሚከናወንበት ዕለት ማለዳ ላይ፣ ሳይጠበቅ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ከካቢኔ አባልነታቸው ይባረራሉ። ከሰዓት በኋላ በልዩ ጥበቃ ክፍሉ (Secret Service) አማካይነት እዚያው ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባለ ምሥጢራዊ ሥፍራ ከባለቤታቸው ጋር እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ምሽት ላይ ፕሬዚዳንቱ በካፒቶል ሂል (የምክር ቤቶቹ መቀመጫ) ዓመታዊ ንግግራቸውን በማድረግ ላይ እያሉ በከባድ ፈንጂ ሕንፃው ተመትቶ ከነሙሉ ካቢኔያቸው ተገደሉ፡፡ በሕንፃው ውስጥ ንግግሩን ሲከታተሉ የነበሩ የኮንግረስ አባላት፣ ሴናተሮች እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም በፍንዳታው አለቁ፡፡
በምሥጢራዊ ቦታ ተቀምጠው ንግግሩን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ የነበሩት ከርክማን እና ባለቤታቸው፣ ከፍንዳታው በኋላ በፍጥነት ወደ ኋይት ሐውስ ተወሰዱ፡፡ እንደደረሱም ከርክማን ቃለ-መሐላ ፈጽመው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
ከዚህ በኋላ ባለው የድራማው ክፍል ፕሬዚዳንት ከርክማን ከጥቃቱ ማግሥት ባለመረጋጋትና በሥጋት ውስጥ ያለችውን አሜሪካን  ለማረጋጋት፣ አንድነትና ሰላሟን ለማስጠበቅ፣ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያስደነገጠውን የሽብር ጥቃት አድራሽ ለማግኘት፣ እንዲሁም አዲስ መንግሥት ለማቋቋም የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ትግልና የሚያልፉባቸውን አስቸጋሪ እንዲሁም አደገኛ መንገዶች እንመለከታለን፡፡
ድራማው ልብ-ወለድ ይሁን እንጂ መነሻው እውነታን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በተለይም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በሁለቱ ታላላቅ ጎራዎች (በካፒታሊዝም እና ሶሻሊዝም) መካከል በነበረው ፍጥጫ፣ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ በሚያይበት ዘመን፣ አሜሪካ በመንግሥታዊ አስተዳደሯ ላይ ጥቃት ቢደርስ ተተኪ መሪ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ በማመን፣ የጀመረችው ተጠባባቂ መሪ  (Designated Survivor) የማስቀመጥ ሐሳብ ለታሪኩ ነባራዊ መነሻ ሆኗል፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት፤ በዚህ የፖለቲካ ድራማ ታሪክና በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ መመሳሰሎችን ተመልክቻለሁ፡፡  በተመሳስሎዎቹ ውስጥ ልዩነቶችም ይታያሉ፤ እነዚህን መመሳሰሎች (ከነልዩነታቸው) ከወቅቱ የኢትዮጵያ  የፖለቲካ ውጣ-ውረድ ጋር አያይዞ መመልከቱ ላለንበት አስቸጋሪ ወቅት የመፍትሄ መንገዶችን ለማሰብ መነሻ እንደሚሆን በማሰብ የተወሰኑትን ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቤያቸዋለሁ፡፡
የአሜሪካው የ“Designated Survivor “ፕሬዚዳንት ቶማስ (ቶም) ከርክማን እና የኢትዮጵያው የአሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀውስ ጊዜ መሪዎች ናቸው። ሁለቱም ሰዎች፣ አገሮቻቸው በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ የመሪነቱን ወንበር በምርጫ ሳይሆን በባለአደራነት (እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ) ይዘዋል፡፡ እርግጥ፣ ፕሬዚዳንት ከርክማን፣ በድንገተኛ አጋጣሚ፣ ሳይዘጋጁ ነው ፕሬዚዳንት የሆኑት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን፣ የቀድሞው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን አምባሳደር ካሣ ከበደ ለግዮን መጽሔት “ራሳቸው ነገሩኝ” ብለው እንደገለጹት፣ ለቦታው ሲዘጋጁበት ቆይተው ነው፣ ቀዳሚያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣን ሲለቁ ወንበሩን የያዙት፡፡
ሁለቱም መሪዎች ቤተ-መንግሥት ሲገቡ ቀዳሚ ሥራቸው አገር ማረጋጋት ነበር፡፡ አገር ለማረጋጋት ሁለቱም የተጠቀሙት በመሪነት ያደረጓቸውን የመጀመሪያ ንግግሮቻቸውን ነው።  በንግግሮቻቸውም መሪዎቹ አገሮቻቸው ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታ በመግለጽ፣ ችግሮች ቢኖሩም በጽናት እንደሚወጧቸው ለሕዝቦቻቸው ቃል  ገብተዋል።  በውጤት ደረጃ ግን የሁለቱ መሪዎች ንግግሮች ያመጧቸው ውጤቶች ይለያያሉ፡፡ የፕሬዚዳንት ከርክማን ንግግር፣ ከዚያ ጊዜ በፊት  አይተውት በማያውቁት ምስቅልቅል ውስጥ ለገቡት አሜሪካዊያን ብዙም ማጽናኛ አልሰጠም፣ በአንጻሩ፣ ለ27 ዓመታት አንድ ዓይነት ሥርዓት፣ ፖለቲካዊ መሥመርና ተመሳሳይ የፖለቲካ ቋንቋ ሲያይና ሲሰማ ለኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የተስፋና የለውጥ ብልጭታ ያሳየ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ከርክማን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከንግግሮቻቸው በኋላ ያደረጉት፣ ችግር ወዳለባቸው ቦታዎች መሄድና ጉብኝት ማድረግ ነበር፡፡ እዚህ ላይ፣  ሁለቱ መሪዎች በጉብኝታቸው ባከናወኑት ተግባር ይለያያሉ፤ ፕሬዚዳንት ከርክማን፣ በፈንጂ በወደመው “ካፒቶል ሂል” በመገኘት በነፍስ-አድንና በምርመራ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችን አበረታተዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደግሞ ጅግጅጋ ከተማ በመገኘት በእርስ-በርስ ግጭት ውስጥ የነበሩትን የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች አንድ ላይ አስቀምጠው ከሶማሌ የሕዝብ ተወካዮች ጋር በመነጋገር የማረጋጋት ሥራ ሠርተዋል፡፡
ሁለቱም መሪዎች ሥራቸውን ሲጀምሩ ጀምሮ ተቃዋሚ አላጣቸውም፣ በዚህም ብዙ ተፈትነዋል፡፡ ከርክማን፣ “ለፕሬዚዳንትነት ብቁ አይደሉም” የሚሉ ሰዎች ተነስተውባቸዋል፣ በዋናነት፣ ለደረሰው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ያላቸውን ቆራጥነት የተጠራጠሩ ሰዎች ከአስተዳደራቸው ውስጥ ነበሩ (በተለይም የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ሊቀ መንበር በሆኑት ጄኔራል)።  ዶ/ር ዐቢይም፣ ባይበዛም፣ በአመራራቸው ላይ ከጅምሩ አንስቶ ጥርጣሬ ያደረባቸው ጥቂት ሰዎች ሥጋታቸውን ሲገልጹባቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል፣ ለሁለቱም መሪዎች የማይታዘዙ ባለሥልጣናት ነበሩ። የአሜሪካውን መሪ አንዳንድ የክፍለ-ሀገር ገዢዎችና ወታደራዊ አዛዦች፣ የኢትዮጵያውንም በተመሳሳይ የአንዳንድ ክልሎች አመራሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች  ፈትነዋቸዋል፡፡
ከርክማን እና ዐቢይ ጠላት የበዛባቸው ናቸው፤ ሁለቱም በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል (ዶ/ር ዐቢይ በመስቀል አደባባይ የተደረገባቸው ሙከራ በይፋ የሚታወቀው ይሁን እንጂ፣ ሌሎች ሴራዎችም እንደነበሩና እንዳሉ በቅርቡ ተናግረዋል)፡፡ ሁለቱን መሪዎች ከሥልጣን ለማውረድም የተለያዩ ሴራዎች ተጠንስሰውባቸዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የመሪዎቻቸውን ደህንነት በመከታተልና ተስፋ በማድረግ በኩል ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ከርክማን የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ያሉበት ሁኔታ ይፋ እስኪሆን ድረስ አሜሪካዊያን በጭንቀት ተጠባብቀዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በተለይ ከአሜሪካ ጉብኝታቸው ከተመለሱ በኋላ ለቀናት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው በመቆየታቸውና በርካታ ሐሜቶችም በዚህ ምክንያት በመወራታቸው፣ በሚዲያ እስከሚቀርቡ ድረስ ኢትዮጵያዊያን በጭንቀትና በሥጋት ጠብቀዋል፡፡ በመጨረሻም መሪዎቹ ለሕዝብ ሲታዩ የሕዝቦቹ እፎይታ ተመሳሳይ ነበር፡፡
እነዚህን የተመሳሳይነት ነጥቦች ስዘረዝር፣ አንባቢያን “ያኛው ልብ-ወለድ፣ ይሄኛው እውነት፤ምን ያገናኛቸዋል?” ብለው እንደሚጠይቁ እገምታለሁ፡፡ ትክክል ነው፣ ሁለቱ በዚህ ይለያያሉ፡፡ ዋናው ነጥብ ግን በተለይ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን እንማራለን?” የሚለው ነው፡፡
እኔን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው “ታጋሽ” እንደሆንን እንናገራለን፣ ነገር ግን፣ በእኔ ትዝብት፣ አብዛኞቻችን ትንሽ ተስፋ ስናይ (ወይም ያየን ሲመስለን)፣ የተገባው ቃል ሁሉ በአንድ ጀንበር ዕውን የሚሆን ይመስለናል፡፡ ስለሆነም፣ የተባለው ነገር ሲዘገይብን ቶሎ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይ እንደ አሁኑ ዓይነት በችግር የተሞላ ጊዜ ላይ ስንደርስ፣  ችግሮቹን ለመፍታት በሚወሰዱ እርምጃዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በመመልከት፣ እርምጃ ወሳጁ አካል (መንግሥት) ሆን ብሎ እንደሚያደርገው አስበን እንደመድማለን። ወይም ደግሞ፣ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ጊዜ ከወሰደ፣ ለምን ጊዜ እንደወሰደበት ከመመርመር ይልቅ፣ መንግሥትን በዳተኝነት ለመውቀስ እንቸኩላለን፡፡ በ”Designated Survivor” ላይ የምንመለከተው የፖለቲካ ኮሪደሮቹ ውይይት፣ ክርክር፣ ጭቅጭቅና ፍትጊያ፣ በደንብ ካየነው፣ አገር መምራት ምን ያህል ከባድ ሥራ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ ይህንን ድራማ ስንመለከት፣ የአገራችንን ሁኔታ በድራማው ውስጥ ካለው ጡዘት ጋር እያዛመድን ብናጤነው፣ አስተሳሰባችንን በተሻለ ለመቅረጽና እንደ ዜጋም የበኩላችንን ትብብር እንድናደርግ ያሳስበናል ብዬ ስለማምን ነው በንጽጽር ያቀረብኩት። በዚህ መንፈስ በመነሳት፣ በተለይ የፊልም ተከታታይ የሆናችሁ አንባቢያን፣ ይህንን ድራማ እንድትመለከቱት በአክብሮት እጋብዛለሁ፡፡


Read 1365 times