Sunday, 28 October 2018 00:00

የጎደላቸውን የሚሞሉ ሚኒስትሮች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ሴትና ፈረስ እንደ ኩሬ ውሃ እያደር ማነስ
ሴት ማገዶ ቢቸግራት ምሰሶ ትነቅላለች
ሴት ምን ብታውቅ በወንድ ያልቅ
እነዚህ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ቃል በቃል ባይሆንም በሌሎች  የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙ፣ ሴትን አሳንሰው የሚያሳዩ ሃሳቦችን የያዙ አነጋገሮች ናቸው፡፡ በግልጽ አማርኛ ትንሹም ትልቁም ሴትን የሚንቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ምድር እንደ ወሎዋ ወይዘሮ ወርቂት አይነት አገር የገዙ፣ እንደ እትጌ ጣይቱ ከባለቤታቸው ተስተካክለው መንግሥት የመሩ፣ እንደ ወይዘሮ ላቀች ደምሰው ጦር ያዘመቱ (በጣሊያን ላይ) ሴቶች በታሪካችን ቢኖሩም፤ ከአዲስ አበባ ተነስተን ወደ የትኛውም የሀገራችን አካባቢ እግራችን እንደረገጠ ብንጓዝ የምናገኘው እውነት፤ ሴት ልጅ ስትገፋና ሰትናቅ፣ ሴት የትም ልትደርስ አትችልም እየተባለ አንገቷን እየተያዘች ለባል ስትሰጥ፣ አልችልም አልፈልግም በምትልበት ጊዜም የጉልበት በደል ማለትም ጠለፋ ሲፈፀምባት ነው፡፡
መውለድ ተፈጥሮአዊ ኃላፊነት መሆኑ ታውቆ፣ የወለዱትን ማስተማር ግዴታ ከተደረገ መቶ ዓመት ያለፈው ቢሆንም፣ ቤተሰብ በትምህርት ረገድ ለሴት ልጆች  የሚሰጠው እድል ከወንዱ ጋር  ሲነፃፀር፣ አሁንም ባጣ ቆየኝ ነው ቢባል የተጋነነ  አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን  ጋዜጣ፤ ‹‹ለጆሮ የሚቀፍ ስድብና ሐሜት የሚነገረው በሴቶች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች እንደ አንድ መጠቀሚያ እቃ ዓይነት ግምት ሲሰጣቸው ይታያል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ወንዱም ይሳሳታል፡፡ የእነሱ ስህተት ጎልቶ የሚታየው ለምን ይሆን?›› ብሎ በቁጭት ከጠየቀና ቀጥሎም፤ ‹‹ወንድ ሆኖ መወለዱ ገመናውን ሸሽጎለት መኖሩ ነው እንጂ አንዳንዱ ወንድ ዝርክርክ ነው›› ብሎ ከመሰከረ ሃምሳ አምስት ዓመት ቢያልፍም፣ ዛሬም በሴቶች ላይ የተዘፈዘፈው ሸክም እምብዛም አልቀነሰም፤ እንደተዘፈዘፈ አለ፡፡ ስለ እኩልነታቸው በየአደባባዩ ይነበነባል እንጂ የሚፈጸምባቸውን መገፋት ለማስቆም ብቃ ብሎ የተነሳ የፍትህ አካል አልታየም፡፡
‹‹ሴቶች ድርብ ጭቆና አለባቸው፤መፍትሔ የሚያስገኝላቸው የሶሻሊስት ስርዓት ነው›› ይሉ የነበሩት  ደርግና ኢሕአዴግ፤ የፓርቲያቸው አንድ ክንፍ አድርገው ሲነዷቸው ከረሙ እንጂ፣ በአዲስ መንገድ በፓርቲ ዲሲፕሊን ቀፍድደው አረጥራጭ አደረጓቸው እንጂ ለሴቶች ነፃነት አልሰጧቸውም፡፡ እራሳቸውን እንዲመሩ፣ እንዲያብቡ፣ እንዲጎመሩ አላደረጓቸውም፡፡
በንጉሡ ዘመን የነበረው ፓርላማ፣ ያንን ባላባታዊ ሥርዓት ጥሰው የወጡትን ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን፣ ወይዘሮ መቅደስ ዘለቀ፣ ወይዘሮ ገነት አጥናፉና ወይዘሪት አሥራት ታደሰ የመሳሰሉ ደራሲዎችን የያዘ ነበር፡፡ ዛሬ በፓርላማ እምብዛም በስም የምትጠራ ሴት የታጣችው ትምህርት ሳይስፋፋ ቀርቶ፣ ሴቶች ብቃትና ትጋት አጥተው ሳይሆን በፓርቲ አሰራር ተጠፍንገው ተይዘው፣ ሹዋሚና ሸላሚ ወንዶች በመሆናቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም በዚያን ጊዜም፣ በሀገራችን ዘመናዊ ተብለው ከሚጠሩት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ወ/ሮ ውበት ተስፋ ሚካኤል የመጀመሪያዋ ሴት ረዳት ዳሬክተር ሆነው  የተሾሙት ከ52 አመት በፊት በ1959 ዓ.ም ነው፡፡ ዛሬም አየር መንገድ ውስጥ ሴቶች ከዚህ ደረጃ አላለፉም፡፡ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለመምራት መንገድ አልተለቀቀላቸውም፡፡ ይኸ ደግሞ የሆነው ሙያ አጥተው፣ መልመድ ተስኗቸው ሳይሆን፣ የወንዶች የበላይነት ዘውድ እንደጫነ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡
ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አዲሱን ካቢኔያቸውን አቋቁመዋል። ከካቢኔው 20 አባላት ውስጥም 10ሩን ሴቶች አድርገው ሾመዋል። እነዚህ ሴቶች በልዩ ልዩ መንገድ ሲደቀኑባቸው የነበሩትን እንቅፋቶች እያለፉ እዚህ የደረሱ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ለለውጥ መቆሙን እየተናገረ፣ ምልክትም እያሳየ ላለው መንግሥታቸው፣ ግማሽ የካቢኔ አባላትን ሴቶች በማድረግ፣ ዶ/ር ዐቢይ ለወሰዱት ኃላፊነት አክብሮትም አድናቆትም አለኝ፡፡ ሴቶችም ይህን ፈር ቀዳጅ ጅምር ከዳር ለማድረስ ሃላፊነት ተቀብለው፣ ለመሥራት በመወሰናቸው ከልቤ አበጃችሁ እላለሁ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላትን የመረጡበትን መመዘኛ ማለትም፡- የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ይፋ ማድረጋቸው  ይታወቃል፡፡ ይኼ መልካም ነው፡፡ ችግሩ ግን ከራሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የካቢኔ አባላቱ በጠቅላላ በቅርብ የሥራ ኃላፊዎች የሚከበቡ፣ በእነሱ የሚሽከረከሩና እነሱን የሚያሽከረክሩ ከሆነ ነው፡፡ በአደራጁትና በተደራጀ ቀለበት ውስጥ የሚሽከረከሩ ከሆነ፣ አዲስ ነገር የማየታቸው ወይም ለአዲስ ችግር የመጋለጣቸው ጉዳይ ሊያከትም፣ ነገሮችም ሁሉ በነበሩበት ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ አገርም ወደ መረራት አዙሪት ውስጥ መልሳ ልትገባ ትችላለች፡፡
እኔ፤ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን አገር እንደሚያደንቀው ሁሉ አደንቀዋለሁ፡፡ በአንድ ነገር ደግም ከሌላው በተለየ አደንቀዋለሁ፡፡ ኃይሌ ከየትኛውም ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ በዚህ አይነት ትምህርት ምስክር ወረቀት ወይም ዲፕሎማ አገኘ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በተሰማራባቸው የሆቴልና ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ጥሩ ውጤት አያስመዘገበ ነው። በቅርቡም በእርሻ ሥራ መሰማራቱ ይታወቃል። ኃይሌ በሁሉም  ሥራዎች  ድካሙ ወይም ጥረቱ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ የቻለው፣ የጎደለውን በባለሙያዎች ስለሚሞላ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እራሳቸው፣ ሴቶችም ወንዶችም የካቢኔው አባላት ምን ያህል  የጎደላቸውን  ለመሙላት የተዘጋጀ ልብ አላቸው? ጥያቄዬ ነው፡፡ ማንም ቢሆን የጎደለውን ለመሙላት የተዘጋጀ እንጂ ፍጹም  አይደለም፡፡   
Read 968 times