Sunday, 28 October 2018 00:00

በእንተ ነጻነት!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

“መንግስት አባት ሳይሆን አሽከር መሆኑን የሚያምን ህዝብ ሊኖረን ይገባል

    ነጻነት፤ በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ብርቱ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ይሻል፡፡ ነጻነቱ ዋስትና እንዲያገኝለት፣ እንዲበረክትለት የሚሻ ሰው ለሌሎች ነጻነትን ለመስጠት ቸር መሆን ይገባዋል። ለሌሎች ሲሰጡት በመቀነስ ፋንታ የሚበረክት፣ ዋስትና የሚያገኝና የሚበዛ ነገር ነጻነት ነው፡፡ ነጻነትህ እንዲበረክትና እንዲጸና ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ነጻትን ለሌላው ስጥ፡፡
አንዳንድ ምሁራን ‹‹ነጻነት ተፈጥሯዊ ነው›› ይላሉ። የመብት ፍልስፍና አባቶች፤ ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶች›› (Natural Rights) ከሚሏቸው ነገሮች አንዱ ነጻነት (Liberty) ነው፡፡ ይሁንና ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶች›› የሚለው አገላለጽ የሚደብቀው አንድ ቁም ነገር አለ። የመብት ፍልስፍና አባቶች፤ ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶች››  ሲሉ የሚገልጽዋቸው ‹‹በሕይወት የመኖር፣ ደስታን የመሻት፣ ነጻነትን›› ወዘተ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶች››፤ ግኝቶች (Discovery) በመሆናቸው፣ የህብረተሰቡ የፖለቲካ - ኢኮኖሚ ዕውቀት ዝቅተኛ በሆነበት ዘመን ተግባራዊ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ሲጀመር፤ የተጠቀሱት መብቶች የማይገሰሱ፤ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የተቀዳጃቸው ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶች›› መሆናቸውን ለመረዳት ዕውቀት አስፈላጊ ነው፡፡ ‹‹ተፈጥሯዊ መብቶችን›› ለመረዳት ዕውቀት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፤ በመብቶቹ የመጠቀምና መብቶቹን የመጠበቅ ነገርም ዕውቀትን ይፈልጋል፡፡
የስው ልጅ ነጻነትን አጥብቆ የሚሻ ፍጡር ነው። እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣን ፖል ሳርትር ያሉ አንዳንድ ሰዎች፤ ‹‹ሰው ነጻ እንዲሆን የተረገመ ፍጡር ነው›› ይላሉ፡፡ ካርል ማርክስ ደግሞ በአንድ መጣጥፉ፤ ‹‹ጨቋኞች እንኳን በጭቆና ተግባራቸው የነጻነትን አስፈላጊነት ያረጋግጣሉ›› ይላል፡፡ ‹‹ጨቋኞች የሚፈልጉት ያለ አንዳች ገደብ፤ በነጻነት የሌሎችን መብትና ነጻነት መርገጥ ነው፡፡›› ጨቋኝ የሚባለው ሰው፤ በነጻነት የመጨቆን ‹‹መብት›› ለራሱ ለማረጋገጥ የሚፈልግና ይህን ፍላጎቱንም ለማሳካት የቻለ ሰው ነው፡፡ ነጻነትን በዕውቀት ገንዘቡ ያላደረገ ሰው፤ ነጻነት ሲያገኝ ሌሎችን ለመጨቆን ይጠቀምበታል፡፡ ነጻነት ለሌሎች በሰጡት ቁጥር የሚበዛ፣ ዋስትና የሚያገኝ፣ በዕውቀት ገንዘብ የሚደረግና በዕውቀት የሚጠበቅ ውድ ሐብት መሆኑን ያልተገነዘበ ሰው ወይም ነጻነትን በዕውቀት ገንዘቡ ያላደረገ ሰው፤ ነጻነት ሲያገኝ ሌሎችን ለመጨቆን ይጠቀምበታል፡፡
የቮልቴር ቃል ነጻነትን በትክክል ለመረዳት ያግዘናል፡፡ ‹‹እኔ አንተ የምናገረውን ነገር አልደግፍም። ይሁንና ይህን የማልደግፈውን ሐሳብህን እንዳትገልጽ የሚከለክልህ ሰው ቢመጣ፤ ያኔ የአንተ ጠበቃ እሆናለሁ። ከአንተ ጎን ተሰልፌ ነጻነትህን አስከብራለሁ›› ብሏል፡፡ ነጻነት ዋስትና አግኝታ መኖር የምትችለው፣ እንዲህ ያለ የነጻነት ግንዛቤ ያላቸው ዜጎች በበረከቱበት ሐገር ነው፡፡        
የኛ ሐገር ነጻነት ጠንካራ የዜጎች ዋስትና ያላት አልመሰለኝም፡፡ ያለፉት ዓመታት ልምዶች ይህን ሐቅ ደጋግመው አረጋግጠውልናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውም ቋሚ ምስክር ነው፡፡ ለነጻነት ያለን ግንዛቤ እንደ ጨቋኝ ገዢዎች ያለ ነው፡፡ ነጻነታችንን የምናረጋግጠው የሌሎችን ነጻነት በማፈን ነው፡፡ ሌሎችን ነጻነት በመንፈግ ነው፡፡ መብታቸውን በመጣስ ነው፡፡ እንደ ቮልቴር ‹‹አንተ የምትናገረውን ነገር አልደግፍም፡፡ ይሁንና ይህን የማልደግፈውን ሐሳብህን እንዳትገልጽ የሚከለክልህ ሰው ቢመጣ፤ ያኔ የአንተ ጠበቃ እሆናለሁ›› የሚል አቋም ካልያዝን ነጻነትን ጠብቀን ማቆየት አንችልም፡፡ ችግሩም የሚታየው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ነው፡፡
በቅርቡ አንድ የሐገራችን አንጋፋ ፖለቲከኛ በስታዲየም ንግግር ሲያደርጉ፤ ደጋፊዎቻቸው የግለሰብ ሥም እየጠቀሱ ጸያፍ ስድብ ይሳደቡ ነበር። ሆኖም ፖለቲከኛው በቀጥታ ድርጊቱን ማውገዝ ቀርቶ፤ በአኳኋናቸው እንኳን ያለመደሰት ሁኔታ ለማሳየት አልሞከሩም፡፡ ሁነቱ በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት በዓለም ዙሪያ እየተላለፈ መሆኑን በማሰብ፤ ተግሳጽ ብጤ ጣል ቢያደርጉ ክብሩ ለእርሳቸው ነበር። እንኳን ሐገር ለመምራት ተስፋ አድርጎ በህዝብ ፊት የቆመ ፖለቲከኛ፤ የመንደር ሽማግሌም እንዲህ እንዲያደርግ እንፈልጋለን - እንጠብቃለን፡፡ እርሳቸው ሥልጣን ሲይዙ የሚደግፏቸውን ሰዎች ብቻ ሣይሆን የሚቃወሟቸውን ሰዎች መብት የማስከበር የሞራል ብቃት እንዳላቸውና ከሚተቿቸው አንዳንድ የመንግስት ባለሥልጣናት የሚልቁ መሆናቸውን ማሳያ አጋጣሚ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር፡፡ ብቻ ነገሩን ‹‹ጠላትህን ጎርፍ ሲወስደው፤ እንትፍ ብለህ ጨምርበት›› በሚል ስሌት የተውት መሰለው፤ ንግግራቸውን ጨረሱ፡፡
ይህ ፀሐፊ ‹‹ልደት›› ፈቅዶለት የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ልደትን ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም፤ ‹‹የታሪክ አጋጣሚ›› ወይም ‹‹የሕይወት ጥሪ›› ገጥሞለት፤ የሐገሪቱን የፕሬስ ነፃነት በተግባር ለመፈተሽ የሚያስችል ዕድል አግኝቷል፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራ ተሳታፊ በመሆን የፕሬስ ነፃነት ቀዳሚ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ‹‹ተከልክሏል›› የሚል የሳንሱር ማህተም ሳያጋጥመው፤ የብዙ ደራስያንን ልብ የሚያደማው የሳንሱር መቀስ ሳያስደንግጠው ለመጻፍ ችሏል፡፡ ሐሳብን መግለጽ ወንጀል ሆኖ ለእስር ሲዳርግና እንደ በአሉ ግርማ ባሉ ሰዎች ሞትን ሲያመጣባቸው ለተመለከተው ለዚህ ፀሐፊ፤ የፕሬስ አዋጁ ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ ነው፡፡
‹‹ከዛሬ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው›› የሚል አዋጅ በፀናበት ዘመን ኖሯል፡፡ የተለየ ሐሳብን ማራመድ በሚያስረሽንበት ዘመን የህፃንነት ዘመኑን አሳልፏል፡፡ መንግስት ከሚያቀርበው መረጃና ሐሳብ ተቃራኒ የሆነ መረጃና ሐሳብ የሚያስተናግዱ ፕሬሶች በሌሉበት የፖለቲካ ምህዳር በልጅነት ዘመኑ ተመላልሷል፡፡ ይህን የአፈና ስርዓት በመቃወም፤ ሜዳ የወጡ ወጣቶችን ታሪክ እየሰማ የየዋህነት ዘመኑን ዘልቋል፡፡ ይህ የነፃነትን ጣዕም በደንብ ለመረዳት ያግዘዋል፡፡ ‹‹ልደት›› እና ‹‹የታሪክ አጋጣሚ›› ስለ ነፃነት አስረድተውታል፡፡
በአንጻሩ፤ ስለ ነጻነትና ዴሞክራሲ የሚኖረውን አስተሳሰብ የሚጎዱ ውርሶችም ይኖሩታል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ህብረተሰብ ሊነሳ የሚችለው ዝርዝር ብዙ ስለሚሆን አልገባበትም፡፡ ሁላችንም፤ ‹‹ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል›› እና ‹‹ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ዓይነት ብሂሎችን እየሰሙ ከማደግ ጀምሮ ለዴሞክራሲ ስርዓት ባዕድ የሚያደርግ ብዙ ውርስ ተሸክመናል። ስለዚህ ይህን ችግራችንን ተረድተን መስራት ይኖርብናል፡፡
በአንዳንድ አጋጣሚዎች፤ ‹‹እኛ የምንጠቀምበት ነፃነት ችሮታ እንጂ ደመወዝ (earned) አይደለም›› የሚያሰኝ ነገር እመለከታለሁ፡፡ ነፃነት፤ ለህግ እስረኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የህግ የበላይነት እንዲከበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ህግን ለማክበርና ለማስከበር ያልተዘጋጀ ወይም ቀናተኛ ያልሆነ ህብረተሰብ ነጻነቱን አስከብሮ ለመዝለቅ አይችልም፡፡ ነጻነት እንዲህ ዓይት ብቃት ያለው ህዝብን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ጉድለታችን ብዙ ነው፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ‹‹እከሌ የተሰኘውን ጋዜጣ አታንብቡ›› ሲሉ ስንሰማ፤ ‹‹እነዚህ ሰዎች ስልጣን ቢይዙ የማይቀዱትን ሐሳብ የሚያራምድ ጋዜጣ እንዲጠፋ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም›› ብለናል። ሌላው ቀርቶ ብዙ በደል አደረሰብን የምንለው ባለሥልጣን እንኳን፤ ከህግ በወጣ አግባብ ጥቃት እንዲደርስበትና መብቱ እንዲሸራረፍ ባለመፈለግ ነው ነጻነትን መጠበቅ የምንችለው፡፡ ነፃነት ‹‹የጠላቶቻችን›› ነፃነት እንዳይጓደል በመታገል ብቻ ነው የሚጠበቀው። ዴሞክራሲያዊነት ምንድነው ቢሉ፤ የሐሳብ ልዩነትን አለመፍራት ነው፡፡ በተለይ ሓሰብና አስተያየት የሚቀርፁ እንደ ፕሬስ ያሉ ተቋማት፤ የተለያዩ ሀሳቦችን የማስተናገድ ሚናቸውን ሳያጓድሉ በገለልተኝነት መሥራት ካልቻሉ ነጻነት ዋስትና አያገኝም፡፡  
‹‹ሕዝባዊ መንግስት ይኸውልህ፤ ጠብቆ ማቆየቱ ከሆነልህ›› (A republic if you can keep it) የሚል ብሂል አለ፡፡ ብሂሉ ተግሳጽና ምክርን አቀላቅሎ የያዘ ነው፡፡ የነጻነትን ትርጉም መለየት ለተሳነው ትውልድ የተሰነዘረ ምክር ነው፡፡ ‹‹የአሜሪካ ነጻነት በምን ያህል ዋጋ እንደ መጣ የማያውቁ ወጣቶችን ለመቀስቀስ የተነገረ ቃል ነው፡፡
ከ1960ዎቹ ወዲህ ባለው ዘመን የተወለዱ የአሜሪካ ወጣቶች የህገመንግስቱ ገበሬዎች ስርዓቱን ለማጽናት የከፈሉትን መስዋዕነት አያውቁም፡፡ ስለዚህ ነፃነቱ ‹‹ያለ-የነበረ- የሚኖር›› አድርገው ያስቡታል፡፡  They took it for granted ስርዓቱን ለመጠበቅና ጤናማነቱን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችሉ፤ እንዲሁም የስርዓቱ ምሰሶ የሆኑ መርሆዎች ሲጣሱ አይከነክናቸውም፡፡ ‹‹የአሜሪካ መስራች አባቶች››፤ ሪፐብሊካዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዐቱ የቆመበትንና ህያው ሆኖ የሚዘልቅበትን መርሆዎች አስቀምጠው ቢያልፉም፤ ወጣቱ ትውልድ አሁን የሚጠቀምበትን ነፃነት እንደ ተፈጥሮአዊ ስጦታ ቆጥሮታል። ይህ ስርዐት ከዜጎች የሚፈልገው ትጋት፣ ንቃት፣ ተሳትፎ  አለ፡፡ ወጣቶቹ ይህን ኃላፊነት ቸል ካሉት፤ ስርዐቱ ይጠፋል፡፡
አለን ብሉም የተባሉ ፀሐፊ ‹‹የአሜሪካዊ ህሊና መጠርቀም›› (The Closure of American Mind) ሲሉ የጻፉት አንድ መጽሐፍ አለ፡፡ በዚህ መጽሐፋቸው፤ ‹‹የአሁኖቹ ወጣቶች በነጻነት ያምናሉ፡፡ የማንንም ነጻነት ያከብራሉ፡፡ ነጻነትን በማክበር ረገድ ቸር ዝንባሌ አላቸው። ስለዚህ ‹‹መብቱ ነው He has got his right/She has got her right›› ማለት የሚቀናቸው ወጣቶች ናቸው። ሆኖም ነፃነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እሴቶችን የሚደፈጥጡ ነገሮችን በነፃነት ስም ያስተናግዳሉ፡፡ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ስርዐት መርሆዎችን የሚጥሱ ጉዳዮችን በደንታ ቢስነት ያስተናግዳሉ›› ሲሉ ይተቻሉ፡፡
አሁን የሚጠቀሙበት ነፃነት ዜጎች ከፖለቲካ ከተገለሉ፤ ምርጫ የመምረጥ ፍላጎት ከሌላቸው፤ የመንግስትን አሰራር ለመከታተል የሚያስችል ትጋት ከሌላቸው፤ ሙሉ ጊዜአቸውን ሰጥተው በፖለቲካው መድረክ ውርውር የሚሉ ቡድኖች ስርዐቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር እንዳይፈጽሙ ለመከላከል አይችሉም፡፡ ዴሞክራሲ የጥቂት ኤሊቶች ጨዋታ አይደለም፡፡ አብዛኛው የአሜሪካ ህዝብ ፖለቲካውን ለተለያዩ ‹‹ቲንክ ታንክ›› ቡድኖች አደራ ሰጥቶ፤ እነሱ ያሻቸውን እንዲያደርጉ በደንታ ቢስ ስሜት የሚመለከታቸው ከሆነ፤ አሜሪካውያ ወጣቶች ዛሬ በለጋስነት ለሁሉ የሚሰጡት ነጻነት አንድ ቀን ሊጠፋ እንደሚችል አለመገንዘባቸውን፤ አለን ብሉም ይናገራሉ፡፡
ታዲያ የዘመኑ አሜሪካውያን፤ ‹‹ያለ-የነበረ- የሚኖር›› አድርገው የሚያስቡት ወይም for granted ይወስዱት የነበረው ስርዓት፤ በአንድ አጋጣሚ ሊጠፋ፣ ሊፈርስና ሊዛነፍ እንደሚችል በማሰብ ከእንቅልፍ የባነኑት በ9/11 ክስተት እንደሆነ የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ ይህ ክስተት የምርጫ ውድድሩን ፖለቲከኞች የሚዘላለፉበትና የሚጣጣሉበት መድረክ አድርገው የማየት አስተሳሰባቸውን እንዲቀየር ያደረገና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የገዛ ሕይወታቸውን የሚወስን ሁነኛ ጉዳይ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደረገ ነበር፡፡ መንግስት የሚከተላቸው ፖሊሲዎች ህይወታቸውን የሚወስኑ ጉዳዮች መሆናቸውን ለመረዳት ያስቻላቸው ክስተት ነበር። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው፤ እንደ አሜሪካዊ የሚኖሩት፣ በጣም የሚወዱትና ዓለምን የሚያስቀናው የዴሞክራሲ የህይወት ዘይቤአቸውን ሊያጠፋ ወይም ሊያለማ የሚችል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን እንዲያውቁ ያደረጋቸው አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ መስራች አባቶች የሰጧቸውን የዴሞክራሲ ስርዓት ይዘው መዝለቅ እንደማይችሉም ያስገነዘባቸው ነበር፡፡
ወደኛው ጉዳይ ስንመለስ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተመለከትናቸውን ክስተቶች፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማጠናከር እንድንሰራ፤ ችግሮቻችንን በመለየት ለመሥራት እና አካሄዳችንን ለመፈተሸ የሚያነሳሱ ጥሩ አጋጣሚዎች አድርገን ልንወስዳቸው ይገባል፡፡ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ስርዓት የማይስማሙ አስተሳሰቦችን በቶሎ ማስወገድ ያስፈልገናል፡፡ ለምሣሌ፤ ከእነዚህ አስተሳሰቦች አንዱ፤ ‹‹መንግስት አባት ነው›› የሚል አስተያየት ነው፡፡ በዚህ የተመለደ ገራገር ንግግር ውስጥ ነፃነትን ለመጠበቅ፣ ለማጠናከርና ለማሳደግ የማያስችል የአስተሳሰብ ችግር መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ‹‹መንግስት አባት ነው›› የሚል ትውልድ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስት አባት ሳይሆን አሽከር መሆኑን የሚያምን ህዝብ ሊኖረን ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፤ የሲቪክ ተቋማትን ለፖለቲካ ዓላማ እንዲሰሩና በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ታፍነው እንዲገቱ ማድረግ.፣ የህግ የበላይነትን የሚሸረሽር ተግባር ውስጥ መግባት፤ በዲሞክራሲያዊ መድረኮች በንቃት ተሳታፊ አለመሆን፤ ቀበሌ ስብሰባ ሲጠራ አለመሄድ፤ በተደራጀ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከመሞከር ይልቅ፤ በግርግርና በሁከት ለመጓዝ መሞከር፤ የሌሎችን መብት ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆን ወዘተ ችግሮች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ይዘን ስርዓቱን ልንጠብቀው ቀርቶ በአግባቡ ለመጠቀም እንኳን አንችልም። ስለዚህ አንዳንዴ ‹‹አሁን የምንጠቀምበት ነፃነት ስጦታ እንጂ ደመወዝ (earned)  አይደለም›› እላለሁ፡፡
የማህበራዊ ሚዲያው ነገር መታሰብ አለበት፡፡ የማህበራዊ ሚዲያው ነገር፤ ከዓመት በፊት አንድ ጓደኛዬ፤ ‹‹ከዩቲዩብ አገኘሁት›› ብሎ እንድመለከተው በሰጠኝ አንድ ቪዲዮ ሊገለጥ የሚችል ነው፡፡ በተመለከትኩት ቪዲዮ፤ ከአንድ የጦር ካምፕ ወይም እስር ቤት ከሚመስል ግቢ በር ዘብ ሆነው የሚጠብቁ አራት ወታደሮች ይታያሉ፡፡ አካባቢው ጫካ ነው፡፡ የእነሱን ጉርሻ የለመደ አንድ ዝንጀሮ መጣ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ የተቀባበለ ጠብመንጃውን ሰጠው፡፡ ሌላኛው ጓደኛው ይቃወም ነበር፡፡ ግን ሰጠው። ዝንጆሮውም መሣሪያውን እንደነሱ አድርጎ ያዘ፡፡ ወዲያ ወዲህ አለ፡፡ ከዛም አጋጣሚ ሆኖ ጣቱ ቃታውን አግኝቶት ወደ ወታደሮቹ መተኮስ ጀመረ፡፡ አከታትሎ ተኮሰ፡፡ ሆኖም አያያዙ ትንሽ ዘቅዘቅ ያለ ስለ ነበር ጥይቱ ከወታደሮቹ እግር ሥር ሲያርፍ አራቱም እየተሳሳቁ ሸሹ፡፡ ዝንጀሮው እነሱ ሲሸሹ ፊቱን ወደ ተመልካቹ አቅጣጫ መልሶ፤ ድል እንዳደረገ ጀግና፣ በሁለት እጆቹ ክላሹን ወደ ላይ ሲያነሳ ይታያል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያው ይህን ይመስላል፡፡


Read 1488 times