Saturday, 27 October 2018 10:22

ሕብረት ባንክ ከግብር በፊት ከ706 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

በዕድገት ምጣኔው ከሌሎች ባንኮች ጋር ሲወዳደር 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል


ሕብረት ባንክ አ.ማ ባደረገው ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመትት አምና ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር የ42.8 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 706.98 ሚሊዮን ብር ከግብር በፊት ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ ከትናት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ባካሄደው 10ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ስብሰባና በ20ኛው የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ባቀረቡት የ2010 ዓ.ም ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የተመዘገበው የ211.94 ሚሊዮን ብር ጭማሪ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ካሉ አቻ ባንኮች የዕድገት ምጣኔ ጋር ሲወዳደር በሦተኛ ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጠው ገልጸዋል፡፡
ከግማሽ ዓመት ለበለጠ ጊዜ በአገሪ የተለያዩ ስፍራዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተፈታተኑ ዋና ዋና ተግዳሮቶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት አቶ ዛፉ፣ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ አምና በተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ29.63 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከ17.80 ቢሊዮን ብር ወደ 23.08 ቢሊዮን ብር ከፍ በማድረግ ከአቻ ባንኮች ጋር ያላቸውን የገበያ ድርሻ ወደ 14 በመቶ ማሳደጋቸውንና የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 24.53 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 15.07 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 22 ተጨማሪ ቅርንጫፎች ተከፍተው የጠቅላላ ቅርንጫፎች ብዛት 229 መድረሱን የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ ለደንበኞቻችን ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን በዚህ ዓመትም አዳዲስ ቅርንጫፎች ለመክፈት የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በ2030 በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 5 ታላላቅ የባንክ ተቋማተው አንዱ ለመሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ አራት ትላልቅ ድርጅቶች አንዱ ከሆነው ዲሎይፍት ኮንሰልቲን ጋር መፈራረማቸውን ጠቅሰው ባንኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ ብቁ ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነት ለመወጣት የሚያስችል የቢዝነስ ሞዴል ለመቅረፅ አስፈላጊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት የህብረት ባንክ መስራቾች “የነገረው ተመራጭ ባንክ” ለማድረግ ራዕይ ሰንቀው መነሳታቸውን የጠቀሱት አቶ ዛፉ፣ በ2018/19 በጀት ዓመት እጅግ ከፍ ያለ እቅድ በማውጣት፣ መጪው ጊዜ የቢዝነስ ሞዴላቸውን በማሻሻል፣ የሰው ኃይል አቅማቸውን በማጎልበት የቴክኖሎጂና የአገልግሎት ልቀትን በማረጋገጥ የባንካቸውን ትራንስፎርሜሽን በእነዚህ የስኬት መሰሶዎች ላይ እንደሚያቆሙ ተናግረዋል፡፡ ሰኔ 30 ቀን 2018 ለባንኩ ደንበኞች የተሰጠው አጠቃላይ የብድር ክምችት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 24.53 በመቶ ወይም የ2.97 ቢሊዮን ጭማሪ በማሳየት 15.07 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ከወለድ አልባ ተቀባጭ የተሰበሰበው ገንዘብ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ 85.69 በመቶ ወይም 297.24 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 644.12 መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት አምና በተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው 22.0 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 6.02 ቢሊዮን ወይም የ27.37 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 28.03 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የባንኩ ጠቅላላ ገቢም አምና ከነበረው 2.0 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 889.49 ሚሊዮን ወይም 44.5 በመቶ በመጨመር 2.89 ቢሊዮን ብር መድረሱን የቦርድ ሊቀ መንበሩ አስረድተዋል፡፡
ከምድር በታ ያለውን 4 ወለል ጨምሮ 32 ፎቅ ርዝማኔ ያለው የዋናው ቢሮ ህንፃ ቋሚ መዋቅር (Skeleton work) ይጠናቀቃል ከተባለው ጊዜ በፊት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ጠቅሰው፣ የሕንፃው የማጠናቀቂያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ገልጸዋል፡፡

Read 2209 times