Print this page
Saturday, 27 October 2018 10:25

በላይቤሪያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት በነጻ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ በሁሉም የአገሪቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በክፍያ ሲሰጥ የቆየው ትምህርት በነጻ እንዲሆን መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርገዋል፡፡
በአገሪቱ ትልቁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላይቤሪያን ጨምሮ በአራቱም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽራፊ ሳንቲም ሳይከፍሉ በነጻ ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚችሉ ፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት መልእክት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የክፍያ መቅረት ብስራቱን ያሰሙት በመዲናዋ ሞንሮቪያ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላይቤሪያ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር በተገናኙበት አጋጣሚ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ በወቅቱ ተማሪዎቹ በደስታ ምላሽ መስጠታቸውንና በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የፕሬዚዳንቱን ብስራት በደስታ እንደተቀበሉት ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ዊሃም፤ ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ ያሳለፉትን ውሳኔ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም በአርአያነት ሊከተሉት እንደሚገባ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ ተማሪዎችንና ወላጆችን ክፉኛ ሲያስቆጣና አመጽ ሲቀሰቅስ እንደነበር ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፣ በቅርቡም የአንድ ክሬዲት አወር ክፍያ በግማሽ ያህል መጨመሩ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር አስታውሷል፡፡



Read 1181 times
Administrator

Latest from Administrator