Print this page
Saturday, 27 October 2018 10:29

የመን የከፋ ረሃብ ተጋርጦባታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


በየመን ለአመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሪቱ በአለማችን የ100 አመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋ ይሆናል ለተባለ የረሃብ አደጋ ልትጋለጥ እንደምትችል ተመድ አስጠንቅቋል፡፡
ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፤በየመን ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ያለው ጦርነት መፍትሄ ካልተገኘለትና በሳኡዲ የሚመራው ጥምር ሃይል የአየር ጥቃት መፈጸሙን ከቀጠለ በመጪዎቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ 13 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች የከፋ ረሃብ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በአገሪቱ ለአመታት የዘለቀው ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ አለማቀፍ ተቋማትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እያስተጓጎለው እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በቀጣይም አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ርብርብ ካላደረገ በርካታ ዜጎች በተለይ ደግሞ ህጻናት በከፋ ረሃብ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የሁቲ አማጽያን ከሶስት አመታት በፊት መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የመን በከፋ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሳኡዲ የሚመራው ጥምር ሃይልም አለማቀፍ እውቅና የተሰጠውን መንግስት በመደገፍ ከአማጽያኑ ጋር ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡


Read 1949 times
Administrator

Latest from Administrator