Monday, 29 October 2018 00:00

ዳንጎቴ ከአለማችን በጎ አድራጊ ባለጸጎች 6ኛ ደረጃን ይዘዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዋረን በፌ በ1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል

የአፍሪካው ቁጥር አንድ ባለጸጋ ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ፤ ከፍተኛ በጀት መድበው ትርጉም ያለው ስራን በሚያከናውኑ የአለማችን ምርጥ በጎ አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥ የ6ኛ ደረጃን መያዛቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ተግባራት በማዋል የሚታወቁ የአለማችን ግለሰቦችን ዝርዝር ይፋ ያደረገው ሪችቶፒያ የተባለ የእንግሊዝ ተቋም፣ በፋውንዴሽናቸው አማካይነት 1.25 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ተግባራት የመደቡት ዳንጎቴ 6ኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1981 ባቋቋሙት ፋውንዴሽን አማካይነት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የመሰረተ ልማት ግንባታና የበጎ አድራጎት ስራ ሲያከናውኑ የቆዩት የ61 አመቱ ናይጀሪያዊ ቢሊየነር ዳንጎቴ፣ ከአጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው ከስምንት በመቶ በላይ የሚሆነውን ለበጎ አድራጎት ተግባር እንዳዋሉም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተቋሙ የምርጥ በጎ አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን በፌ ሲሆኑ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ በሁለተኛነት ይከተላሉ፡፡
እንግሊዛዊቷ ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግስ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ አሜሪካዊቷ የቶክ ሾው አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ አራተኛ፣ የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ኤለን ሙስክ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሪቻርድ ብራንሰን፣ ማርክ ዙክበርግ፣ ጄፍ ቤዞስና ማይክ ብሉምበርግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሌሎች በጎ አድራጊዎች ናቸው፡፡

Read 2592 times