Print this page
Saturday, 19 May 2012 10:42

“ውረድ እንውረድ ተባባሉና…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው… እንግዲህ ፕሬሚየር ሊግ ስላበቃ ስለ ራሳችን እናውራ! የምር ግን…የኦሎምፒካችን ነገር እንዴት ነው? እነኚህ እያባሉን ያሉ የ‘ቦተሊካ’፣ የሀይማኖት፣ የዘር ምናምን ነገሮች ሳይኖሩ በአንድ ልብ የምናጨበጭብበት፣ የምንደሰትበት ብቸኛ ነገር ቢኖር እሱንም ልናጣ! የምር ግን… ስንትና ስንት ነገር አልፎ የመጣው አትሌቲክሳችን በአንድ ጊዜ እንዲህ ውዝግብ ሲበዛበት አይገርማችሁም!ሀሳብ አለን…በሩጫውም፣ በኳሱም በምናምኑም መነዛነዙ ከበዛ ለወደፊቱ ለየፌዴሬሽንና ለየስፖርት ኮሚቴው የሚገቡ ሰዎች ስለሚመሩት ስፖርት የፅሁፍ ፈተና ይሰጣቸውማ፡፡ ልክ ነዋ በአንድ ወቅት ይህ ጸሀፊ የ‘ፈረንጅ አፍ’ ጋዜጣ ስፖርት አምድ ሲያዘጋጅ ስታዲየም ገብተው የማያውቁ ሰዎች የክለብ ኮሚቴዎች ውስጥ እንደነበሩ ትዝ ይለዋል፡፡ (በነገራችን ላይ…አሁን ካሉት የስፖርት ጋዜጠኞች መሀል አንዱ ወዳጄን “ኢትዮጵያ ደግሞ መቼ የአፈሪካን ዋንጫ ወስዳ ታውቅና ነው” ምናምን ነገር ብሎታል፡፡ የሩኒ ቅድመ አያትን ታሪክ ግን ሊነግራችሁ ይችላል፡፡

እናላችሁ… በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአንድ ጊዜ እንዲህ የሁላችንም ባህሪ መለዋወጡ አየገርማችሁም! ልክ ነዋ…ከምንም ነገር ይልቅ ለጠብ ቅርብ ሆነናል፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ለጠብ ምክንያትም አያስፈልግም፡፡

ስሙኝማ… በፊት በፊት ለባልና ሚስት መራበሽ ከዋና ምክንያቶች መሀል አማቶች ነበሩ፡፡ አለ አይደል… ወይ የባል እናት በእንግድነት መጥተው ጓዳ ይገቡና “ሽንኩርት ጠቃ አድርጊበት እንጂ! ልጄን ሽንኩርት በሌለው ወጥ አንጀቱን ልታደርቂው ነው እንዴ!”  ምናምን የነገር ጥይት ተኩሰው ጦርነት ያስጀምሩ ነበር፡፡ (አሁን የአማቶች ዋና ተግባር አሜሪካ ሄዶ የልጅ ልጅ ሞግዚት መሆን ሆኗል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)

የአማትነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ለጓደኛው ሲያወራ ምን ይለዋል…“ትናንትና አጋቾች አማቴን አግተው ወሰዷትና ስልክ ደውለው ሀያ ሺህ ዶላር ክፈሉ አሉን፡፡”

“ባትከፍሉስ ምን ያደርጓቸዋል?” ሲል ጓደኛ ይጠይቃል፡ ሰውየው ሆዬ ምን ብሎ መለሰ መሰላቸሁ…

“ባንከፍልማ አማቴን መልሰው እቤት እንደሚያመጧት ዝተውብናል፡፡”

እናላችሁ… ጠብ በዝቷል፣ ክፋት በዝቷል፣ መጠላለፍ በዝቷል፡፡ ስሙኛማ… እንግዲህ እንደ ከተማው ወሬ …አለ  አይደል…ፍቺ በዝቷል፡፡ አርባ ምናምን ዓመት አብረው ቆይተው “በቃኝ፣ ንብረቴን አካፍሉኝ” ሲባባሉ አያሳዝንም፡፡ (“ሚስቴ ሌላ ወንድ ወዳለች…” ብለው ከቤታቸው ወጥተው ውጪ ያሉ ልጆቻቸው በተከራዩላቸው ቤት ስለሚኖሩ የሰባ አምስት ዓመት አዛውንት በዛ ሰሞን ሰምተን ሲገርመን ነበር፡፡ አዎ…አገር እንዲህም እየሆነችላችሁ ነው!)

ድል ካለ ሰርግ በኋላ መንፈቅ ሳይሞላ “ከዚህ ሰውዬ ገላግሉኝ…” ምናምን በዝቷል ነው የሚባለው፡፡ እናማ… አለ አይደል… እንዴት ነው በአጭር ጊዜ ትዳርን የሚያክል ትልቅ ተቋም እንደ ሰኞ ማከሰኞ ጨዋታ በቀላሉ ማፍረስ እንደ ባህል የሆነው አያሰኛችሁም!

እናላችሁ…እዚህ አገር ጥናት የማድረግ ባህል አለመኖሩ ነገሮችን ሁሉ በ‘ይሆናል’ እንድናወራቸው ተገደናል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች በሚኖሩበት ጊዜ ባለሙያዎቻችን “ለምን እንዲህ ሆነ?” ብለው አለመጠየቃቸው ያሳዝናል፡፡ አሀ…እነ ባሮንስና ጎርደን ላይ ጥናት ካስፈለገ እኛ እንበቃለና!

በአደባባይ “የእከሌን ሚስት እኮ አወጣኋት…” እየተባለ ‘የሚፎከርበት’ ዘመን የግድ ሊያሳስበን በተገባ ነበር፡፡ ድሮ “ባሏ ፊልድ ሲሄድ…” ተብሎ የሚዘፈንበት ነገር ሁሉ ቀርቶ ዘንድሮ ነገሩ ሁሉ እንዲህ ‘ፀሀይ ላይ ሲሰጣ’ የምር ያሳዝናል፡፡ (እነ እንትና ከሦስተኛ ፎቅ መስኮት እየዘለሉ በጄሶ መታሸግ ቀረላችኋ!”

ይቺን ስሙኝማ…ሰውዬው ለጓደኛው ምን ይለዋል…“እባክህ አንዱ ሰውዬ ከሚስቴ ጋር ያለህን ግንኙነት ካላበቃሀ ግንባርህን እልሀለሁ ብሎ ሜሴጅ ላከልኝ፡፡”

“ታዲያ መጠንቀቅ ነዋ!”

“እንዴት ልጠንቀቅ!  ስሙን ስላልጻፈ የየትኛዋ ባል እንደሆነ አላወቅሁም!”

እናማ…“የየትኛዋ ባል እንደሆነ አላወቅሁም!” የሚሉ እየበዙ ሲሄዱ በዛው ልክ ጠቡና መበላላቱ እንደሚበዛ ስጉልኝማ፡፡

ደግሞላችሁ…“ተው፣ ይሄ ነገር አይሆንም!” ከምንል ይልቅ “አበጀህ፣ የእኔ እምቦሳ” ባዮቹ በዝተናል፡፡ እናማ…‘መካሪ ሲያሳጣ’ ያኔ ነው ቀይ መብራት፡፡

እግረ መንገዴን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ… ጊዜው በጣም መሽቶም አቶ ባል ገና ቤቱ አልገባም፡፡ ሚስት ሆዬ ስጋት ይገባታል፡፡ በኋላ በከተማው በተለያዩ አቅጣጫዎች ላሉ አምስት ጓደኞቹ ለእያንዳንዳቸው… “ባለቤቴ ከአንተ ጋር ነው?” የሚል ጥያቄ ትልካለች፡፡ አምስቱም ጓደኞች ምን ብለው መለሱ መሰላችሁ…“አዎን ከእኔ ጋር ነው፡፡”

እናማ…“አንተ ትብስ አንቺ” እየቀረ ሲሄድ፣ ከመሳሳም መናከስ ሲቀል…የምር አሳሳቢ ነው፡፡

ሁለቱ ሰዎች ስለ አንድ ጓደኛቸው ነው የሚያወሩት፡፡

“ለመሆኑ ስንት ይከፈለዋል?”

“በሳምንት አምስት መቶ ብር ያገኛል፡፡ ሚስቱም በሳምንት አምስት መቶ ብር ታገኛለች፡፡”

“በጋራ በሳምንት አንድ ሺህ ብር ያገኛሉ ማለት ነዋ!”

“አይ፣ በጋራ አምስት መቶ ብር ብቻ ነው የሚያገኙት፡፡” “እሱም አምስት መቶ፣ እሷም አምስት መቶ ያገኛሉ አላልከኝም እንዴ?”

“እሱ አምስት መቶ ብሩን ተቀበሎ ይመጣና እሷ ደግሞ አምስት መቶ ብሩን ሙሉ ለሙሉ ትቀበለዋለች፡፡”

ይሄ አሪፍ ነገር አይደል! አምስት መቶዋን አምጥቶ የሚሰጥ ባል! “በየትኛው ልብ ወለድ ነው ያነበብኩት!” የሚባልበት ዘመን እኮ ነው፡፡

እናላችሁ…ልክ አሁን፣ አሁን በብዙ ትዳሮች ይታያል እንደሚባለው መበጣበጥ…አለ አይደል… መስማማት ያለባቸው ቦታዎች እየጠፉ ነው፡፡ የማይቧጨቅ ኮሚቴ፣ የኃይማኖት ተቋም፣  አክስዮን፣ ማህበር ምናምን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እንደ አካሄዳችን ጓደኝነት፣ አብሮ አደግነት የመሳሰሉትን ነገሮች ከእንግዲህ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልሞች’ ላይ ብቻ ልንጠብቅ ግድ ሳይለን አይቀርም፡፡ እናማ…እንዴት ነው በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንዲህ ነገረ ሥራችን ሁሉ የተገለባበጠው ማለቱ ደግ ነው፡፡

እናማ… በየቦታው የምትሰሙት ነገር ሁሉ “ተጣሉ!”  “ተራበሹ!”  ”ሳይስማሙ ተበታተኑ!” ምናምን የሚባሉ ነገሮች ስትሰሙ ታዝናላችሁ፡፡ (በነራችን ላይ…ይሄ በኳስ ሜዳዎቻችን አካባቢ እያሰለሰ የሚታየውን መራበሽ ‘ፍሬኑ ሳይበጠስ’ ለማቆም መሞከሩ ይሻላል፡፡)

ስሙኝማ… አንድ ሰሞን ይሄ ቢ.ፒ.አር. የሚባለው ነገር እፎይ አሰኝቶት ነበር፡፡ በየቦታው እኮ ለአገልግሎት ስትሄዱ… “እኔ ምንጣፍ ልሁንልህና ተረማመድብኝ…” ልትባሉ ምንም አይቀርም ነበር፡፡  “የእውነት ይቺ የእኛው ጦቢያ ነች?” የሚያሰኝ ነበር፡፡

አሁን ልጄ… ብዙ ቦታ ግልምጫውና “ለእኔ ስትል ለምን አፍጋኒስታን በእግርህ አታቀጥነውም!” አይነት ነገር ከበፊቱ ብሶበት መጥቷል፡፡ (እነ እንትና…ግምገማ ቀረ እንዴ!) በየሚዲያው የምታነቡት አንዱ አንዱን ሲከስ፣ ሌላው አጸፋዊ ክስ ሲወረውር…ብቻ በአጠቃላይ እውቀት በብልጠት የተተካበት ዘመን ሆኗላችኋል፡፡ አለ አይደል…ጥያቄው “ማነው እውነትን ይዞ የተነሳ!” ከማለት ይልቅ “ማነው ክሱን ማሳመር የሚችል!” ማለት የሆነ ይመስላል፡

የሆኑ ‘ነገር ተበላሽቷል’ አይነት ነገር የሚሉ ወገኖች “የኮሚቴው አመራሮች ሥራ እየበደሉ ነው፣ የራሳቸውን ዳሌ እያሰፉ ነው…” ምናምን አይነት ክስ ያሰማሉ፡፡ የኮሚቴው አመራር አባላት የተከሰሱበትን ከማስረዳት ይልቅ ምን ይሉ መሰላችሁ… “እነሱ ስውር ተልእኮ ይዘው የተነሱ ሰዎች ናቸው…” ምናምን ብለው ነገሩን ‘ቦተሊካ ተች’ ይሰጡታል፡፡ (እግረ መንገዴን…ዘንድሮ በብዙ ነገር ፖለቲካ እስካልነካህ ድረስ እንደፈለግህ ሁን…” አይነት ነገር አልበዛባችሁም! ብቻ ምን ይሁን ምን አንድ አቤቱታ ወይም የአሠራር ችግር ስታነሱ ቶሎ ተብሎ የፖለቲካ ቀለም ይቀባል፡፡ “የትራንስፎርሜሽኑን ሂደት ለማደናቀፍ…” ምናምን ይባልና ምን አለፋችሁ ‘ቴረር በቴረር’ ሊያደርጓችሁ ይዳዳቸዋል፡፡)

ድሮ… ማለት የአውቶብስ ሰልፍ ከመሰለፍ የመስቀል አደባባይ ሰልፍ መሰለፍ ቀላል በሆነበት ዘመን ሁሉ ሰልፎች ላይ የማትጠፋ መፈክር ነበረች፡፡ “የሽግግሩን ቻርተር እንደግፋለን!” አሪፍ ማምለጫ ነበረች አይደል!

እናላችሁ… አሁንም የሆነ “የመንግሥትን ምናምን ለማደናቀፍ…” የምትል ማምለጫ በር አለች፡፡ እናማ…እንዲህ እየተባለ ብዙ ነገሮች የሚባባሱበትና መፍትሄ ለማግኘትም አስቸጋሪ የሆነው ነገሮችን ሁሉ ወደ ‘ፖለቲካ አቅጣጫ’ የመለወጥ ነገር ነው፡፡ እናላችሁ…ነገርዬዋ ሁሉ ‘የአምናን አሼሼ ገዳሜ በዘንድሮ ማሲንቆ’ አይነት ነው፡፡ የዚች አገር መለያ የሆነ የሚመስል አንድ ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ… ነገሮችን በክርክር፣ በማመንና በማሳመን ከመፍታት ይልቅ ቶሎ ብለው ወደ ‘ወንበር ማነቃነቅ ሙከራ’ ማዞር የሚችሉ ሰዎች በየማህበሩ፣ በየኮሚቴው አናት ላይ ጉብ ማለት ሲሳካላቸው!

ታዲያላችሁ…መበጣበጥ እየበዛ ሲሄደ፣ በየቦታው ስምምንት የሚባል ነገር ሲጠፋ፣ አስታራቂ የምንላቸው አባቶች ያሉባቸው ስብስቦች ሳይቀሩ እርስ በእርስ ሲናቆሩ ስናይ… ለይቶለት የእግዚአብሔር ሰላምታ ሙሉ ለሙሉ ከመቅረቱ በፊት ነቃ ማለት አሪፍ ነው፡፡

እናማ… በትንሹም፣ በትልቁም “ውረድ እንውረድ ተባባሉና…” አይነት ነገር እየተባባልን የት እንደሚደረስ አንድዬ ይወቀው፡፡ እሱው ከገደሉ አፋፍ ይመልሰንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 2627 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:34