Saturday, 27 October 2018 10:35

ውዳሴና ክስ! - (ምናባዊ መጣጥፍ)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(3 votes)


የእያንዳንዱ ሰው ህይወት፣ ወጀብና ነውጥ አለበት። በምቾትም ይሁን በችግር የታጀበ ነውጥ፡፡ ያንን በትክክል የሚነግረኝ የግቢያችን ግንብ፣ አጥርና ትንሷ አበባ ናቸው፡፡ ግንቡ አርጅቶ አስር ግዜ እየወደቀ፣ አስር ግዜ ተጠግኖ ይቆማል፡፡ ለመኖር ይታገላል፣ ወድቆ ላለመቅረትና ላለመረታት ይለፋል፡፡ ከመግቢያ በሩ አካባቢ በግንቡ ላይ ያለፈቃዱ የበቀለች ትንሽዬ አበባ አለች:: አበባዋ ያደገችው በግንቡ ላይ ባለች ትንሽ ስንጥቅ ውስጥ በተገኘች አፈር ላይ ነው፡፡ የምታሳዝንና የምታምር አበባ ነች፡፡ ቀጭን ሆና እንደ አንቴና ሽቅብ ተመዝዛ ስታበቃ፣ ከጫፏ ላይ ትንሽዬ አበባ አብባለች። አንዳንድ ግዜ ደግነት ልቤን ሲያቅፈኝ፤ ስወጣና ስገባ በብርጭቆ ውሃ ቀድቼ፣ ፈንጠቅ አደርግላታለሁ፡፡
የዝናብ ወቅት መጣና አገር ምድሩ በአረንጓዴ ተሸፈነ፡፡ መላጣ የነበረው ሜዳ የዝናቡን መምጣት ለመቀበል በሚመስል መልኩ (ንጉሱን በአጀብ እንደሚቀበል ህዝብ) በትንንሽ ሳሮች ተጥለቀለቀ። የበጋውን ድርቅ ተቋቁሞ ይታገል የነበረው እሾሃማ እምቧይ እንኳ፣ ያንን ሁሉ ወጀብ አልፎ ለዚህ በመብቃቱ እየፈገገ ሽቅብ ይመነጠቅ ያዘ፡፡ ጓሯችን ለመዞር እስኪያቅት ድረስ በእነዚህ የክረምት ብቃዮች ተማረከ፤ ከሁሉ የሚገርመኝ ግን እነዚህ በግንቡ ላይ የሚሳቡ ሃረጎች ናቸው፡፡ አጥሩን አረንጓዴ ቀለም የተቀባ ያስመስሉታል፡፡
ከበራችን አካባቢ በስንጥቅ የአፈር ቅንጣት ላይ የበቀለችውን ይህቺን ትንሽዬ አበባ በየቀኑ እከታተላለሁ፡፡ እናም ራሴን እጠይቃለሁ፤ በጣም ታምራለች፣ ውብ ነች ታዲያ እዚያ ግድግዳ ላይ ተጣብቃ ምን ትሰራለች! መሬት ላይ ብትሆን የበለጠ ማማርና ማደግ ታገኝ አልነበረምን? ነቅዬ መሬት ልትከላት ይሆን ወይስ እዚያው ላይ መጨረሻዋን ልይ! ለመሆኑ በበጋው የት እየከረመች ነው ክረምቱን ብቅ የምትለው!
(ይህ ነገር ግን፤ ልክ እንደ ሴቶች ከፍታን ማፍቀር ነው! ልክ እንደ ሴቶች መብረር መፈለግ ነው! ልክ እንደ ሴቶች ሁልግዜ በልጦ ለመታየት መጣር ነው! ልክ እንደ ሴቶች ሲያብቡ (ሲጎረምሱ) ለመታየት መሻት ነው! ወይስ ዝም ብሎ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው! … እያልኩ ከንቱ ፍልስፍናዬን አሰፋለሁ፡፡)
**
ውዳሴ! (በፍቅራችን አበባ ወቅት!)
(…ለአያቴ(እማመይ!)ና ለዝንተ ዓለማችን … (ለዝንተ ዓለም ወዳጅነትና ፍቅራችን!))
አንድ ዕለት እማመይና እኔ በረንዳ ላይ ተቀምጠን እንወያይ ነበር፡፡ ስለ መክሊት ነበር (ስለ ፍቅረኛዬ!)! ብዙ ግዜ ተነጋግረን ልንግባባ ያልቻልንበትን ነገር እየነገርኳት ነበር፡፡ እናም እኔ እንዲህ ስል አጠቃለልኩላት … ‹‹… እማመይ ከመክሊት ጋር ይኸው በአይናችን ከተያየን ወራት ተቆጠሩ፡፡ ወይ አልተጣላን … ወይ አብረን አይደለን! … እንዲሁ ተንጠልጥሎ ያለ ነገር ነው፡፡ ዝም ዝም ተባብለናል፡፡ ኩርፊያው ደግሞ እኔን ያሰቃየኛል፡፡››
አያቴ ትክዝ ብላ ስታበቃ፤ ‹‹…እኔ የአንተን ፊት በማየት ስሜትህን አውቀዋለሁ፡፡ ሃዘንህ ሲከብድ፣ ነገር ሲገባህ እረዳለሁ፡፡ ስለምወድህ … የልብህን አርምሞና መናወጥ እያዳመጥኩ ስላሳደግሁህ በትክክል አውቅሃለሁ፡፡ ይህንን ነገር ቶሎ ፍታ! ተነጋገሩበት፡፡ አብራችሁ ሁኑ ወይ ደግሞ ካልሆነ መለያየት ነው፡፡ መክሊቴ‘ኮ ሸጋ ልጅ ናት ጌታ! … ግን የሆነ የምትደብቀው ጉዳይ አላት መሰለኝ ስውር ናት! አንተ ግን ጉዳዩን ተነጋግረህ ለመፍታት ሞክር! ደስታህን ማየትና ልጅ ወልደህ ማቀፍ ይናፍቀኛል!››
‹‹…አየሽ እማመይ ችግሩ‘ኮ መክሊት እዚህ አገር ላይ የምታየውን ነገር ሁሉ የማንቋሸሽ ልምዷ ደስ አይለኝም (ብዙ ግዜ ያጣላናል!) … ለምሳሌ ታክሲ ሰልፍ ስታይ ደርሶ ለእርሷ ብቻ ይመስል አገሯን መርገም ነው። ዝናብ ከመጣ ማማረር ነው፡፡ በአደባባይ አብሬያት ስታይ ጓደኛ መያዟ እንዳይታወቅ ትፈልግ ይመስል መሸሽ ነው፡፡ ብቻ ምንም አይነት ደስታ እዚህ አገር ላይ እንደማይገኝ አምናለች እናም ደስታዋን ከደመና በላይ በሚበረው ጢያራ ውስጥ አስቀምጣለች፡፡  ልቧ ሁሉ ውጪ መውጣት ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ የአሜሪካ ናፍቆት ደሟ ውስጥ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ተቃራኒዋ ነኝ! … ታዲያ በዚህ ላይ እንዴት መነጋገር ይቻላል…››
‹‹…አንተ ደግሞ ይህንኑ አትነግራትም እንዴ?!››
‹‹…ዋጋ የለውም እማመይ፡፡ እውነት ለመናገር ግን በጣም ናፍቃኛለች፣ ስትጠፋብኝ ይደክመኛል፣ አብራኝ ስትሆን ደግሞ ጭቅጭቁ ያስጠላኛል፡፡››
‹‹….ጌታ! … የምታፈቅራትን ልጅ ማግኘት ጥሩ ነውኮ! አይደለም እንዴ?! እናም እርሷ ደስተኛ እንድትሆን አመቻችላት፡፡ ደግሞ ለሳምንታት ካላየሃት ምን ትርጉም አለው! … ዋ! ብቻ አግብታ እንዳታገኛት! …››  ህመሟና ፈገግታዋ ፊቷ ላይ በአንድ ተጣምረው ያበራሉ፡፡ ስለ እኔ ትታመማለች፡፡ ስስቅ ትስቃለች … ሳዝን ትተክዛለች፡፡
‹‹…እውነቱን ለመናገር የምፈልገው መተው ይመስለኛል፡፡ ብተዋት ደስ ይለኛል‘ኮ ግን ደግሞ ልቤ ወደ ፊት … ወደ ኋላ ይላል፡፡ መቁረጡ ይበጀኛል መሰለኝ…›› አንዳንድ ቀን ድምጼ የራሴ አይመስለኝም፣ አንዳንድ ቀን ስሜ ራሱ የራሴ አይመስለኝም፣ አንዳንድ ቀን ገላዬ ራሱ የራሴ አይመስለኝም፡፡ ግን  እያወራሁ ነበር፤  እኔው ነበርኩ  … አለሁ! በጣም እናፍቃታለሁ፣ በጣም እወዳታለሁ፡፡ አራት አንጓ ያለው ጣቷ መዳፌ ውስጥ የሚያመነጨው ሙቀት ይታወሰኛል፤ ረጃጅም ጥፍሮቿና ደማማቅ ቀለማቸው በአይኔ ላይ ይውላሉ፡፡ የሚያባቡት ከንፈሮቿ ልብ ድካሜን ያመጡታል፡፡
እማማዬ ትክዝ ብላ … ‹‹ጌታ! … ጠንካራ መሆንህን አውቃለሁ፡፡ እንድትሰበርብኝ አልሻም፡፡ የግንቧ ላይ አበባን ረሳሃት እንዴ?! ዝናብና ከፍታ ትወዳለች … ፀሃይ ደግሞ ሲወጣላት ምግቧን ታዘጋጃለች፡፡  ምናልባትም አብባ ታፈራለች፡፡ መሬት ብትሆን ከዚያ ይሻል ነበር እንላለን አይደለምን! …ግን ከፍታው ዕጣዋ ነው፡፡ ራሷን ከዚያ ከፍታ ላይ በቅላ አገኘችው እንጂ ራሷን አልተከለችውም፡፡ ስለዚህ መክሊት ከፍታውን፣ መሄዱን፣ መራቁን፣ የዳመና ናፍቆቱን ራሷ ያመጣችው አይመስለኝም፤ ዕጣዋ ነውና … ከፍታዋ ላይ ራሷን ለመትከል ትታገላለች፡፡  ምናልባት ያደገችበት ቤት ነው ምናልባት የፍላጎቷ ርቀትና ምጥቀትም ነው፡፡ ወደ ከፍታው ይዛህ የምትበር ከሆነ ሞክር ግን እንዳትወድቅ … ብቻዬን ልብረር ካለች ግን ተዋት…››
ከግንባችን ላይ ያለችውን አበባ አተኩሬ አየኋት፡፡ እንባዬ የታገለኝ መሰለኝ፡፡ ፊቴንም በመዳፌ ሸፈንኩ፡፡ አትንቀላት! ለብቻዋ ተዋት አልኩት ለልቤ! ምናልባት በዚያው ታፈራ ይሆናል!… ምናልባት ከዚያ ከወረደች ትከስም ይሆናል፡፡ እባክህ ተዋት!
እናም ለወራት ተውኳት! …
**
ክሴ! (በፍቅራችን ድቅድቅ ጫፍ! …)
… ለመክሊትና  ለመጨረሻዋ ሰከንድ …
አንድ ቀን ማታ አራዳ ጊዮርጊስ አንድ ሱቅ በረንዳ ላይ ቆሜ፣ ከባለ ሱቁ ላይተር ተቀብዬ ሲጃራ እየለኮስኩ እያለ … ከኋላዬ ‹እንቁላል ስጠኝ!› የሚል ድምጽ ሰማሁ። ድምፁን አውቀው ነበር፡፡ ‹‹…የፈረንጅ አድርገው፤ ስድስት … እሱ ይሻላል!!››
ፊቴን ለማዞር ፈራሁ፡፡ ላይተር የያዙ ጣቶቼ ተንቀጠቀጡ፡፡ ቀጥሎ መለኮሻው ከጣቶቼ አመለጠኝና ወደቀ፡፡ አይኖቼን ስጨፍን ጠረኗ ሸተተኝ፡፡ ከየትም በየትም ቦታ ለይቼ አውቃታለሁ፡፡ ልቡናዬን መግዛት አቃተኝ ፡፡ መክሊቴ ነች፡፡ የሹራብ ኮፍያዬን ከጭንቅላት ጎፈሬዬ ላይ ዝቅ እያደረግሁ ስዞር …. ኦ! …. መክሊቴ! (ልቤ ተናወጠች!) …. ለወራት በዝምታ መለያየታችን ውስጥ የታመመች ናፍቆት ለመሞት ወይ ለመዳን ትንፈራገጥ ጀመር፡፡
አተኩራ አየችኝና … ‹‹…አል!…›› አለች ክብ ከንፈሯን በቀስታ ከፍታ፡፡ ስሜ በእርሷ ከንፈር ሲዳሰስ የሚሰማኝ ንዝረት፣ የትም በየትም ቦታ ተሰምቶኝ እንደማያውቅ አረጋግጣለሁ፡፡ ስሜ ሲጠራ ከንፈሩን እንደተሳመ ጉብል ይነዝረኛል፡፡ ምላሴ ከሌሎች ዘንድ ስትንበለበል እንደማትውል ሁሉ፣ ከእርሷ ፊት ለንቋሳ ሆና ከትናጋዬ ስር ትለጠፋለች፡፡
ተንደርድሬ አቀፍኳት፡፡ ጉንጬን በጉንጯ እየዳሰሰች በጆሮዬ … ‹‹…አልኮል ጠጥቻለሁ እንዳይሸትህ!›› ስትል በቀኝ ጆሮዬ ስር አንሾካሾከች። የጆሮዬ ተንጠልጣይ ስጋ የተርገበገበ መሰለኝ፡፡ ደግሞ ሌላውን ጉንጬን (ግራ ጉንጬን!) እየዳሰሰችና በአንድ እጇ ወደ ኋላዋ እያመለከተች … ‹‹…ባሌ ነው አግብቸዋለሁ!…››
ከኋላዋ ራቅ ብሎ የቆመውን ጎልማሳ አላየሁትም ነበር፡፡ ልቤ ዝቅ አለች፡፡ ጎልማሳው በሩቁ በጥርጣሬ አይን ያየኝ መሰለኝና ደነገጥኩ፡፡ አቀርቅሬ ወደ እርሷ ዞርኩ፡፡
ስራና ጤና ከጠየያቀችኝ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ከጎልማሳው ጎን ተሸጉጣና ፌስታሏን አንጠልጥላ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡ (በእርግጥ ዞር ብላ ስታየኝ በእነዚያ ውብ አይኖች ላይ የእምባ መጋረጃ ተጋርዶባቸው ነበር!)፡፡ በሩቁ  …. የጋብቻ ቀለበቶቻቸው በጣቶቻቸው ላይ ያንፀረቀ መሰለኝ፣ (…ነው ወይስ … እምባዬ በሱቁ ተንጠልጣይ መብራት … እንደ ዕንቁ እያንፀባረቀ (!)…) … ትክዝ ብዬ እንደቆምኩ፡፡ ሸምሴ እንዲህ ሲለኝ ባነንኩ …
‹‹…አልዓዛር ታውቃታለህንዴ?! … ሰውየውንኳ ደንበኛዬ ነው…››
‹‹…አውቃታለሁ፡፡ እርሱ ግን ማነው!?…››
‹‹…እዚያ ዳህላክ ገስት ሀውስ ነው ያረፈው። ከአሜሪካ የመጣ ሰው (ዲያስፖራ!) ነው፡፡ አሪፍ ደንበኛዬ ነው…›› (ኦህ … በመጨረሻም!) … ስል አሰብኩ፡፡
በድንዛዜ ወደ ግቢያችን ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ህልም በሚመስል ጉዞ እየተራመድኩ ነበር፡፡ ሲጃራዬን በሃይልና በነውጥ እየመጠጥኩ፣ ወደ ግቢያችን እየተንገዳገድኩ አመራሁ፡፡ (ሲጃራዬ በአናቴ ላይ እንደ ጎጆ ቤት የማለዳ ጭስ እየተንቦለቦለ መሆን አለበት መቼም!) … እናም ገና ግቢያችንን ስረግጥ ያቺን የግምብ ላይ አበባ በሩቁ አየኋት፡፡ ታጋይና ውብ አበባ፣ ከፍታና ዳመና የምትወድ፣ ምኞቷን ሰማይ ዳር ያስቀመጠች ውብ አበባ! … ለደቂቃ ቆዝሜ በተመስጦ ትምባሆዬን ካንቦለቦልኩ በኋላ በድንገት ተንደርድሬ፣ ከግምቡ ላይ ጨመደድኩና መንጭቄ ነቀልኳት፡፡ (አዲዮስ! … አለች ነፍስያዬ!) እናም በደመ-ነብስ ጭብጤን ካጠበቅሁ በኋላ … ስር የሰደደችበትን ጥቂት አፈር ማራግፍ ጀመርኩ፡፡
እማመይ በምሽቱ ከበረንዳ ላይ ቆማ እያየችኝ ነበርና እንዲህ ስትል ሰማኋት … ‹‹እንዴ! እንዴ! … ጌታ! ምነው ነቀልካት?!››
‹‹…ነቀልኳት!…›› አልኩ በለሆሳስ! በብስጭት መሳይ ቃል ደግሜ!  … ‹‹በቃ ነቀልኳት! እማ!…›› በማሳዘንና የእንባዬን እንክብሎች ከጥቁር ልጥልጥ ፊቴ ላይ እየጠራረግሁ!
‹‹…የነቀልከው ሁሉ የሚደርቅ መሰለህ! ሞኝ! አንዳንዱ መልሰህ ብትተክለውም ላይበቅል ይችላል፤ አንዳንዱ ደግሞ ብትጥለውም መልሶ ይፀድቃል ልጄ!…! …›› ስትል ሰማኋት፡፡
**
ስንብት! (በመጨረሻ!…)
… ለትንሷ አበባ! …
ለመሆኑ አንተ የግንቡ መሬት ነህ ወይስ የረገጥከው … ሲል ደመ-ነብሴ ጠየቀኝ፡፡ የነቀልኳት ወደ ትልቁ ልተክላት ነው ወይስ ከትንሹ ላስወግዳትና ላደርቃት፣ ከዚያም ትዝታዋን ለነፋስ ልሰጥ? እውነት ያደረቅሁት አበባ ፀፀት በልቦናዬ አብሮኝ ይኖር አይደለምን? መልስ አልባ ጥያቄዎች ይግተለተሉብኝ ጀመር፡፡ በድንጋጤ ከደረት የሸሚዝ ኪሴ ውስጥ ተጨማሪ የሲጃራ ሰበዝ ዳበስኩ፤ አጣሁም፡፡ ገዝቼ መምጣት ስላለብኝ፣ የአጥሩን በር ድርግም አድርጌ ዘጋሁና ወደ ኪወስኳ አመራሁ። ይሁና ይላል ልቤ፡፡ ነቅዬ የያዝኩትን አበባ ከቱቦ ውስጥ ወርውሬ፣ ቆሜ ለሰከንዶች አየሁት። ተነቅሎ የተጣለ መልሶ ይፀድቅ ወይም ይደርቅ ይሆናል ስል አሰብኩና በጭጋጋማ አይኖቼ እየደበዘዙ የሚሄዱትን ምስሎች ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናበትኳቸው።





Read 1329 times