Sunday, 28 October 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

“ሰላም ማደሪያዋ የያንዳንዳችን አእምሮ ነው!!”

“Try to be yourself,
Be the master of your soul,
Peace comes from within.”
ከላይ ያነበባችሁት እ.ኤ.አ በ2016 በጂብሰን አካዳሚ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ በጃፓን ‹ሃይኩ› የግጥም ስልት ‹Peace› በሚል ርዕስ ባደረጉት የግጥም ውድድር አንደኛ ወጥቶ የተሸለመ ግጥም ሲሆን የ10 ዓመት ህፃን የፃፈው ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊትም (በ2015) በተመሳሳይ ርዕስ የሚያስደንቅ ግጥም ፅፎ 1ኛ በመውጣት ተሸልሟል፡፡
***
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጎልማሳ ራሱን ሊያጠፋ ወደ ሱሉልታ ጫካዎች አቀና፡፡ ከዛፎቹ ባንደኛው ገመዱን አስተካክሎ ቋጠረበት፡፡ ለመሞት እንደተዘጋጀ እንጨት እየለቀሙ የሚተዳደሩ እናት ከሩቅ ሲመጡ ተመለከተ፡፡ ጠበቃቸውና አናገራቸው፡፡
“እማማ”
“አቤት”
“ይህንን ይውሰዱ” አላቸው፤ ሰዓቱን፣ ቀለበቱንና ጥቂት ገንዘቦች!! እማማም ፊቱንና ሁኔታውን በማየት ያሰበውን ተረዱና፤
“አልፈልግም” አሉት፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ፡፡
“ለምን?” ጠየቃቸው፡፡  
“ከሰላም አይበልጥብኝም”  
“ማለት?”
“አየህ ልጄ፤ የሰጠኸኝን ንብረት ባየሁ ቁጥር አንድ ተስፋ የቆረጠ፣ ህይወትን መጋፈጥ ያቃተው፣ ለጠላቶቹ የተንበረከከ ፈሪ ሰው እንዳጋጠመኝ አስታውሳለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ሰላሜን ያደፈርሳል” አሉትና ጥለውት ሄዱ። አጅሬም ተከተላቸው …
“እማማ፤ ሰላም የት ትገኛለች?” በማለት ጠየቃቸው። ጭንቅላታቸውን በጣታቸው እየነካኩ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
***
ሰው ባለበት ሰላም፣ ሰው ባለበት ግጭት አለ፡፡ ሁለቱም የተፈጥሮ አካል ናቸው፡፡ አንዳንዴ ተንኮልና ቅድስና ወይም ክፋትና ደግነት፣ አንዳንዴ ሰብዓዊነትና አውሬነት ወይም ገሃነምና ገነት እንላቸዋለን፡፡ በሁለቱ ተቃራኒዎች ፉክክር ህይወት ትሽከረከራለች፡፡ … ወደ ፊትና ወደ ኋላ፣ ወደ ግራና ወደ ቀኝ!! … የኑሮ ጠመኔ በመንፈሳችን ሰሌዳ ላይ ፍቅርና ሰላምን፣ ጥላቻና ብቀላን ሲፅፍ፣ ሲሰርዝና ሲደልዝ ይውላል፡፡ የህሊና ዳስተራችን ደግሞ የመሰለውን እያጠፋ የመሰለውን ያቆያል፡፡
ወዳጄ፡- እኔና አንተ ጥሩ ሰዎች ስንሆን ቤተሰብ፣ ህብረተሰብ፣ አገርና ምድር ሰላም ይሆናሉ፤ጥሩ ካልሆንን ደግሞ ይታወካሉ፡፡ ውሃ የተሞላ ሳፋ፣ ኩሬ ወይም ባህር ላይ ትንሽ ጠጠር ብትጥል፣ እርጋታው ምን ያህል እንደሚናወጥ ታያለህ፡፡ የእያንዳንዳችን ባህሪም ለአጠቃላይ ሰላማችን፣ ልማትና ጥፋት የሚኖረው አስተዋፅኦ እንደዛ ነው፡፡ ሁላችን በአንድ፣ አንዱም በሁላችን ውስጥ ተወልደን፣ አድገን፣ ተጋብተን፣ ተሳስረን … አገር ሆነናልና!!
ወዳጄ፡- በዓለም በምንኖርበት ጊዜም ሆነ ከህይወት ተፋተን ወደ ነበርንበት ስንመለስ፣ አሻራችን እንደየ ሥራችን ስልጣኔያችን ላይ ታትሞ ይታያል፡፡ ሂትለርና ሙሶሎኒ፣ ማርኮኒና ኤዲሰንን የምናውቀው ባሻራቸው ነው፡፡ ጋንዲና ክርስቶስን ደስቶቭስኪና ማርክስን፣ ዳርዊንና ፍሮይድን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን አላየናቸውም፡፡ ሁሌም ግን አብረውን ይኖራሉ፡፡ ኑሯችን ውስጥ አሻራቸው አለ፡፡ ቢል ጌትስና ማርክ ዘከርበርግ፣ ሃውኪንግና ቦብ ዲለን፣ እኔ፣ አንተ፣ እሱና እሷም ያው ነን፡፡ ስልጣኔ የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ሰላም ደግሞ የቅብብሎሹ ድልድይ ነው፡፡ ድልድይ ከሌለ ታሪክ ይቋረጣል፡፡ አሻራ ይጠፋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ “የአክሱም ሃውልት እንዴት ቆመ? … ላሊበላ እንዴት ታነፀ?” እያልን የምንጠይቀው ለዚህ ነው፡፡ ቅብብሎሹ ስለተቋረጠ ይመስለኛል፡፡
የቅብብሎሹ መቋረጥ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በጥበብ ብቻ ሳይሆን ወጥ የሆነ፣ ተያያዥነት ያለው አሳማኝ የእምነት ታሪክም እንዳይሸጋገር ስላደረገ እምነትም ከተረት፣ ከባህልና ከኑሮ ዘይቤነት አላለፈም። ለዚህ ነው የአምልኮትና የሃይማኖት ልዩነቶችንና ግጭቶችን የምናስተናግደው፡፡ … ለምሳሌ ክርስትናን መሰረት ያደረጉ ትውፊቶች (Mytheology) “ሰው ከሞት ጋር አልተፈጠረም” ብለው ያስተምራሉ፡፡ አዳምና ሔዋን የእባብን ወሬ ሰምተው ተሳሳቱ፡፡ የሃሰት ወሬ ሞትና መከራን አመጣባቸው፡፡ ከገነት ተፈነገሉ ይላል፡፡ ሰው የሚሞተው በገዛ ጥፋቱ ነው ለማለት፡፡ የግሪክ ሚቲዮሎጂም፤ ሞት የመጣው ከሰው ጥፋት እንደሆነ ይተርካል …
“… በወርቃማው ዘመን ዚየስ አምላክ፣ ለወዳጁ ኤፒሜቲየስ፣ ከሰዎች ውስጥ ቆንጆ ሴት መርጦ እንዲያገባት በስጦታ ሰጠው፡፡ … ውቧ ፓንዶራን። ፓንዶራ የአምላክ ሚስት በመሆኗ ሁሉ በጇ፣ ሁሉ በደጇ ሆኖ ስትኖር አንድ ቀን ተሳሳተች፡፡ አማልክቶቹ ማንም እንዳይነካው ብለው አደራ ያስቀመጡትን ሳጥን ስትፈለቅቅ በውስጡ የነበሩት ችግር፣ ህመም፣ ስቃይና የመሳሰሉት መከራዎች አፈተለኩ፡፡ የወርቃማው ሰው ዘመን አበቃ፡፡ ህይወትና ሞት ጎን ለጎን ተሰለፉ” ይላል። ባለቅኔያቸው ሄፂዖድም …
በገነት የነበሩ አማልክት፣
ወርቃማውን የሰው ዘር፣
ህመምና ሞትን ሳያውቅ፣
እንደነሱ ሆኖ እንዲኖር፣
ቢያደርጉትም አላወቀ፣
የአደራ ህግን ስቶ፣
በመከራ ተዘፈቀ፡፡ …. በማለት ፅፏል፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ በነዚህና በመሳሰሉ ሌሎች የእምነት ትርክቶች የ ‹ተረጋገጠው ዕውነት› ሰው ካላወቀ የራሱ ጠላት ይሆናል የሚል ነው፡፡
ወዳጄ፡- ከትዳርህ ወይ ከቤተሰብህ፣ ከጓደኛህ ወይ ከወዳጅህ ብትጣላ ትታረቃለህ፡፡ ከጎረቤትህ ባትግባባ፣ ከዕድርህ ባትስማማ ትሸመገላለህ፡፡ ከአለቃህ ብትጋጭ ስርዓቱ ይዳኝሃል፣ አምላክህን ብታስቀይም ንስሃ ትገባለህ፡፡ ከራስህ ከተጣላህ ሰላምህን የት ታገኛለህ? ራስህን ከገደልከው ማንን ይቅርታ ትጠይቃለህ? “ከራሱ ጋር ሰላም የሌለው፣ ከሁሉም ጋር ጠበኛ ነው!!” ይላሉ ሊቃውንት፤ሰላም የነፍሳችን መዘውር መሆኗን ሲመክሩ፡፡
ወዳጄ፡- ህገ መንግስትም ሆነ ማህበራዊ ስርዓት ያስፈለገው ለሰላም ነው፡፡ የጦርነት ታሪክ ሲገለበጥ የሰላም ታሪክ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ታሪክ የሰላም ታሪክ ነው፡፡ የስልጣኔ ታሪክ የሰላም ታሪክ ነው። የመደብ ትግል፣ የብሔር ብሔረሰብ፣ የዘር፣ የጎሳና የጎጥ ውዝግብ ዞሮ ዞሮ መቋጫው ሰላም ነው። ሰው ለሰላም ይዋጋል፣ ለሰላም ይገድላል፣ ለሰላም ይሞታል፡፡ ሁሉም ግን ሰላም አይሰጡትም፡፡ ሰላም በመግደልና በመሞት አትገኝም፤ ሰላም ማደሪያዋ የያንዳንዳችን አእምሮ ነው!!
***
ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡- እንጨት ሻጭዋ እማማ ቤት ድግስ አለ … ዛሬ፡፡ የመጽሐፍ ምረቃ፡፡ የመጽሐፉ መግቢያ ሲነበብ … “በህይወት መሰላል እንወጣለን፣ እንወርዳለን፤ ነገር ግን ዕድሜያችንን በሙሉ የምንፈተንባቸውን … እኔ ማነኝ? … ሰላም እንዴት አገኛለሁ? እያልን ዘወትር የምንጠይቃቸውን ጥያቄዎች መመለስ አልቻልንም፡፡ የመኖር በረከት የሆነችውን የህይወት ድር ለመበጠስ ግን አፍታ አይፈጅም፡፡ … ቤት ገንብተን፣ የኤሌክትሪክ መብራት ለማስገባት የሚፈጅብን ጊዜ፣ ገንዘብ፣ የዲዛይንና የኢንስታሌሽን ግንባታ ሂደትና ውጣ ውረድ ከባድ ነው፡፡ መብራቱን አጥፍተን ቤቱን ለማጨለም ግን ሰኮንድ ትበቃናለች። አንድ ቦታ መበጠስ ነው፡፡ በስንት መከራ የታነፀችን ህይወትና ሰላም ለማጨለምም የዚህኑ ያህል ቀላል ነው፡፡” ይላል፡፡ … ከ15 ዓመታት በፊት እራሱን ሊያጠፋ የነበረው ጎልማሳ የፃፈውን መጽሐፍ እማማ ይመርቁለታል፡፡ መታሰቢያውን ለስማቸው፣ ሽያጩን ለኑሯቸው ‹ጀባ› ብሏቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ ‹ሠላም› የሚል ስም እወዳለሁ። አሁን ደግሞ የሠላም ሚኒስቴር ተጨመረልኝ፡፡ …. እሰይ!!
ሠላም!!

 

Read 1610 times