Saturday, 27 October 2018 10:46

“ሪተርን ኦፍ ዘ ሌጀንድ” አልበም እሁድ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የእውቁ ድምፃዊ ካህሳይ በረኸ 15 ዘፈኖችን ያካተተው “ሪተርን ኦፍ ዘ ሌጀንድ” የተሰኘ የሙዚቃ ሲዲ ነገ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በኪውን ኦፍ ሼባ ዋሽንግተን ሬስቶንት ይመረቃል፡፡ ድምፃዊው በጤና ችግር የተነሳ ከመድረክ ጠፍቶ የቆየ ሲሆን በህክምና ጤናው መመለሱን ምክንያት በማድረግ፣ ይሄንን 10ኛ አልበሙን “ሪተርን ኦፍ ዘ ሌጀንድ” ሲል መሰየሙን አስታውቋል፡፡ በምረቃው ላይ ድምፃዊውና ሌሎች ድምፃዊያን ሥራቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን አርቲስት ካህሣይ በረኸ፣ አልበሙን አስመልክቶ ንግግር እንደሚያደርግም ታውቋል፡፡ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ለመታደም መግቢያው አልበሙን በ200 ብር መግዛት ሲሆን ከአዲስ አበባ አስመራ ደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬትና ፎቶግራፍ ለጨረታ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል። አርቲስቱ የኢትዮ-ኤርትራን እርቅ ምክንያት በማድረግ ከድምፃዊ ሰለሞን ባይሌ ጋር “ፍቅር አሸነፈ” የተሰኘ ዘፈን በጋራ ያቀነቀነ ሲሆን ስለ እናቱ ያቀነቀነው “አደይ”፣ “ራሂላ”፣ እና ሌሎችም ይበልጥ ይታወቃል፡፡ 10ኛ አልበሙ ከያዛቸው 15 ዘፈኖች መካከል ዘጠኙን ከበፊት ዘፈኖቹ ወስዶ ከውጭ ሙዚቀኞች ጋር በዘመናዊ መንገድ እንደገና አሻሽሎ መሥራቱንና ስድስቱ አዳዲስ መሆናቸውን ድምጻዊ ካህሣይ በረኸ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

Read 2193 times