Print this page
Monday, 29 October 2018 00:00

የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሐሙስ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ20 በላይ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ

   በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተሰሩና ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኙ ከ20 በላይ ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡበት የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሐሙስ በቫምዳስ መዝናኛ ይከፈታል፡፡ የአውሮፓ አገራት  አምባሳደሮችና የባህል ማዕከላት ዳይሬክተሮች ከትናንት በስቲያ በቫምዳስ የመዝናኛ ማዕከል በሰጡት መግለጫ፤ በፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያዊያን አጫጭር ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡና የአውሮፓና የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የቤልጂየም፣ የቼክ ሪፐብሊክ፣ የዴንማርክ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የሀንጋሪ፣ የአየርላንድ፣ የአዘርባጃንና የቱርክ ፊልሞች የሚታዩ ሲሆን ፊልሞቹ ዘጋቢ፣ ታሪካዊ፣ ኮሜዲና ድራማ ዘውግ ያላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ፊልሞቹ በየአገራቱ ቋንቋዎች የተሰሩና የእንግሊዝኛ ሰብታይትል ያላቸው ሲሆኑ ለእይታ የሚቀርቡትም በነፃ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም መሰረት የፈረንሳዩ “LeBiro” የተሰኘው ፊልም በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ ላይ ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ላይ የሚቀርብ ሲሆን ዓርብ ከቀኑ 8፡00 ላይ የኢትዮጵያ አጫጭር ፊልሞች፣ ከቀኑ 10፡30 ደግሞ የስፔይን፣የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ፊልሞች ለእይታ ሲበቁ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ከቀኑ 5፡00 ላይ የስውዲን የህፃናት ፕሮግራም፣ ከቀኑ 8፡00 የስሎቫኪያ፣ ከቀኑ 10፡00 የዩናይትድ ኪንግደም እና ከምሽቱ 12፡30 የኔዘርላንድስ ፊልም ለእይታ ይቀርባሉ፡፡ እሁድ ከቀኑ 8፡00 ደግሞ የፖርቹጋል፣ 10፡00 ላይ የኢጣሊያ፣ ምሽት 1፡00 ላይ የጀርመን ፊልሞች ይታያሉ ተብሏል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 29 ከቀኑ 10፡00 የቱርክ፣ ምሽት 1፡00 የአዘርባጃን ፊልሞች የሚታዩ ሲሆን ቅዳሜ ህዳር 1 ረፋድ 4፡00 ላይ የሀንጋሪ የህፃናት ፕሮግራም፣ ከቀኑ 8፡00 የቤልጂየም፣ 10፡00 ላይ  የፊንላንድ፣ ምሽት 12፡30 ደግሞ የዴንማርክ ፊልሞች ለእይታ እንደሚበቁ ታውቋል፡፡ እሁድ ህዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም የፌስቲቫሉ መዝጊያ ሲሆን ከቀኑ 8፡00 የአየርላንድ፣ 10፡00 የቼክ ሪፐብሊክ፣ ምሽት 1፡00 ደግሞ የፖላንድ ፊልሞች ታይተው፣ የፌስቲቫሉ መቋጫ እንደሚሆን ታውቋል፡፡  


Read 3693 times
Administrator

Latest from Administrator