Saturday, 03 November 2018 15:34

የዓለም ባንክ ከፍተኛውን የብድር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ፈቀደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


    የዓለም ባንክ ከፍተኛ የሚባለውን የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ብድርና እርዳታ ለኢትዮጵያ የፈቀደ ሲሆን ገንዘቡ በሀገሪቱ በተጀመረው ለውጥ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን በቀጥታ የሚውል ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ መገንዘቡን የገለፀው የአለም ባንክ፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም መፍጠሩን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አበረታች እርምጃዎች መውሰዱንና በአካባቢው ሰላምን መሰረት ያደረገ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑን እንዲሁም በመንግስት ተይዘው የነበሩ የልማት ተቋማትን ወደ ግል ዘርፍ ለማዛወር እንቅስቃሴ መጀመሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛውን ብድርና እርዳታ ለኢትዮጵያ ለመስጠት መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በብድርና እርዳታ መልክ የሚሰጠው ገንዘብ በዋናነት ሶስት ጉዳዮችን ለማስፈፀም እንደሚያግዝ የጠቆሙት የአለም ባንክ የፕሮጀክት ቡድን መሪዋ ናታሊያ ሚዮሌንኮ፤ ገንዘቡ በዋናነት ለልማት የሚመደበውን በጀት ለመደጎም፣ የኢንቨስትመንት ግንኙነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት በቀጥታ ይውላል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍም እርዳታና ብድሩ ያግዛል ተብሏል፡፡
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ከፈቀደው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ግማሹ (600 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ) በእርዳታ የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከአለም ባንክ የተገኘውን ብድርና እርዳታ አስመልክቶ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሲናገሩ፤ ዓለም ባንክ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ለማንም የአፍሪካ አገራት ያላደረገውን ከፍተኛ ብድር ድጋፍ ለኢትዮጵያ መፍቀዱን ጠቁመው፣ ይህም በለውጡ ጅማሮ እምነት እንዳለው አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ከ6 ወር በኋላም ተጨማሪ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ዓለም ባንክ መስማማቱ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

Read 6401 times