Print this page
Saturday, 03 November 2018 15:35

ትግራይን ከአማራ ክልል የሚያገናኘው የአላማጣ መንገድ ተዘግቶ ሰንብቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 ከ250 በላይ የተሽከርካሪዎች ፍሰት ተገትቷል

     የትግራይ ክልልን ከአማራ ክልል የሚያገናኘው የአላማጣ ቆቦ መንገድ ተዘግቶ በመሰንበቱ የትራንስፖርት ፍሰት የተገታ ሲሆን ተሽከርካሪዎች መጉላላታቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
መንገዱ ካለፈው ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ያልተከፈተ ሲሆን ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል ለመግባት የተንቀሳቀሱ ከ250 በላይ የህዝብና የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ቆመው መሰንበታቸው ታውቋል፡፡
መንገዱ በዋናነት ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ ሰቀላ ወንዝ አካባቢ የሚገኝ ነው ያሉት ምንጮች፤ የመዘጋቱ ምክንያትም በአካባቢው ከተከሰተው ተቃውሞና ግጭት ጋር ተያይዞ የሰው ህይወት በመጥፋቱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “የትግራይ ልዩ ሃይል ሊያጠቃን ይችላል” በሚል ስጋት ነው መንገዱ የተዘጋው ብለዋል - ምንጮች፡፡
መንገዱን ለማስከፈት ከአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ትናንት ለቢቢሲ የገለፀ ሲሆን፤ ከውይይቱ በኋላ መንገዱ በአፋጣኝ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

Read 9002 times