Saturday, 03 November 2018 15:37

ጠ/ሚኒስትሩ የዘንድሮ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረቶችን አስታወቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)


    መንግሥት በያዝነው ዓመት የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውን ዋና ዋና እቅዶች ጠ/ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታን፣ ፍትህና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሻውን ዲሞክራሲ ለማስፈን መንግስታቸው ተከታታይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በዘንድሮ ዓመት እንደሚያከናውን ጠ/ሚኒስትሩ  ሰሞኑን በፍራንክፈርት ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ አብራርተዋል፡፡   
ፍትህና ዲሞክራሲን ሊያሳልጡ የሚችሉ ተቋማትን በመገንባት ላይ እንገኛለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በተጓዳኝም ተቋማቱን በገለልተኝነት የሚመሩ ባለሙያዎችን የመምረጥ፣ የማሰልጠንና የመመደብ ስራዎች ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድን ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ለማድረግ የህግና የመዋቅር ማሻሻያ በመሰራት ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዐቢይ፤ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት በሰለጠነ መንገድ የዜጎችን መብትና ክብር ጠብቀው ስራቸውን እንዲሰሩ ጠንካራ ሪፎርም በመካሄድ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ መከላከያውን የማዘመንና የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡   
የፍትህ ተቋማት በገለልተኝነት የሚሰሩና ለዜጎች መብት ብቻ የቆሙ ለማድረግ፣ ዳኞች በህግ ልዕልናና በህሊናቸው ብቻ የሚዳኙ እንዲሆኑ ማድረግም የዚህ ዓመት ዋነኛ ትኩረት ነው ብለዋል። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በፍትህ ዘርፉ ላይ ተከታታይ የሪፎርም እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አስታውቀዋል፡፡ የፀረ ሽብር ህጉንም ህዝብ እየተወያየበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ፤ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅን የማሻሻል ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡  
የትምህርት ጥራትን የተሻለ ለማድረግም በዘንድሮ ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የሪፎርም ስራ እየተሰራ መሆኑን በፍራንክፈርቱ መድረክ ላይ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ሂደቱ ሲጠናቀቅ የሀገሪቱ የትምህርት ስርአት የሚታማበትን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡  
የኑሮ ውድነትን መቋቋም፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማብረድና የህግ የበላይነትን ማስከበር ጉዳይም የመንግስታቸው የዘንድሮ ዓመት  ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን  ጠ/ሚኒስትሩ  አስታውቀዋል፡፡

Read 11981 times