Saturday, 03 November 2018 15:39

ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 • የፍትሃ ብሄር ችሎት ወደ አዲስ ህንጻ መዛወሩ ቅሬታ አስነስቷል
      • ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ህንጻ ግንባታ 50 ሚ. ብር ተፈቅዷል   

    የዛሬ 50 ዓመት ገደማ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ወደ ህንድ ለጉብኝት ባቀኑበት ወቅት የአንድ ዲስትሪክት ፍ/ቤትን ይመለከታሉ፡፡ በፍርድ ቤቱ አሰራር በመማረካቸውም በአገሬ እንዲህ ዓይነት ፍርድ ቤት እንዲገነባልኝ እፈልጋለሁ አሉ፡፡ በዚህም መሠረት፤ ላለፉት ከ40 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና  ልደታ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንፃ  በህንድ ባለሞያዎች እንደተገነባ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም ከዋናው ህንፃ ጀርባ የሚገኙት የፍትሃ ብሔርን የወንጀል ችሎት ማስቻያ ህንፃዎች ከእድሜያቸው መግፋት የተነሳ ተደርምሰው አደጋ ያደርሳሉ የሚል ጥናት በመቅረቡ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በተለይ የፍትሀ ብሔር ችሎትን ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኝ ባለ ሰባት ፎቅ አዲስ ህንፃ ተከራይቶ ለማዛወር ተገድዷል፡፡
የዚህ ችሎት መዛወርን ተከትሎ ግን  ተገልጋዮች ቅሬታ እያሰሙ ነው፡፡ ለመሆኑ ቅሬታቸው ምንድን ነው? የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ለዘለቄታው ምን አቅዷል? በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያሉበት ፈተናዎችስ ምንድን ናቸው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ  ቤት ፕሬዚዳንት ከአቶ በላቸው አንሺሶ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡


     መቼ ነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት? እርስዎ ወደ ሃላፊነት ሲመጡ የተቋሙ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ወደዚህ ኃላፊነት የመጣሁት በ2008 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ገደማ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችግሮች ምን ምን ናቸው የሚለውን ለመለየት ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ የመጀመሪያውና ቀዳሚው ችግር ሆኖ ያገኘነው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ማለቴ ነው፡፡ ይህንን የዳኝነት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ዋናው ነገር ሰራተኛን ማዘጋጀት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ትልቅ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የስራ ስፋትና ብዛት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ብዙ ባለጉዳዮች የሚስተናገዱበት ነው።  በቀን ከ1 ሺህ በላይ ባለጉዳዮች፣ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሁለት ሺህ ባለጉዳዮችም ይስተናገዱበታል፡፡ ቀጥታ ባለጉዳዮች አሉ፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተዘዋዋሪ የሚገናኙ ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸውም የሚመጡበት ነው፡፡ ስለሆነም ቀዳሚው ተግባር ሆኖ ያገኘነው፣ ይህንን ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥና በርካታ ህዝብን የሚያስተናግድ ተቋም በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በስነ ምግባርና በተነሳሽነት የሚያገለግል ባለሙያ ማዘጋጀት በመሆኑ ለባለሙያዎቻችን ተከታታይ ስልጠና ሰጥተናል፡፡ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር፣ ለዳኞችና ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ስልጠና እንዲሰጥ አድርገናል፡፡
በጥናቱ ትልቅ ችግር ሆኖ ያገኘነው የስራ ባህል አለመዳበር ነው፡፡ በዚህ የስራ ባህላችን ላይ እንደ እነ ዶ/ር ምህረት ደበበ ያሉ ትልልቅ ምሁራንን በመጋበዝ፣ የስራ ባህላችን ምን ይመስላል? ድክመታችንን እንዴት እንቅረፍ? በሚለው ዙሪያ ለፍ/ቤቱ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ለዳኞች በተለያዩ ምሁራን ስልጠና ሰጥተናል፡፡
በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ዳኞች እየሰሩ ይገኛሉ?
እኔ ወደዚህ ኃላፊነት ስመጣ፣ በስነ ምግባር ጉድለትም በራሳቸው ምክንያትም ከለቀቁት ውጭ 76  ዳኞች ነበሩ፡፡ ይህ የዳኞች ቁጥር ፍርድ ቤቱ ካለው የሥራ ብዛትና ስፋት አኳያ በጣም ጥቂት ነው። የህዝቡም ቁጥር ከ100 ሚሊዮን በላይ ከመድረሱ አንፃር ቁጥሩ አናሳ ነው በሚል ተጨማሪ 46 ዳኞች እንዲሾሙ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ዳኞች ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ፌደራል በሚመጡበት ጊዜ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም ችግሮች በመኖራቸው፣ ከተሾሙት ውስጥ ሁለቱ  ቀርተዋል፡፡
ሰሞኑን ላለፉት 40 ዓመታት ሲያገለግል የነበረውን የፍትሃ ብሄር ችሎት፣ ጦር ኃይሎች በሚገኝ ባለ ሰባት ወለል ህንፃ ላይ በማዛወራችሁ ከተገልጋዮች የተለያዩ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ችሎቱን ልታዘዋውሩ የተገደዳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ህንፃ፣ ከ46-50 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን እስከ ዛሬም ብዙ አገልግሎት የሰጠና በመስጠትም ላይ የሚገኝ ህንጻ ነው፡፡ እንግዲህ በአሁኑ ሰዓት የህዝቡ ቁጥር፣ የንግድና የግብይት እንቅስቃሴውም ሆነ አጠቃላይ የአገሪቱ የእንቅስቃሴ ሁኔታ ሰፍቷል፡፡ የዛሬ 50 ዓመት የነበረው የአገሪቱ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ አሁን ካለው ጋር ፈፅሞ ሊነፃፀር አይችልም፡፡ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚጠቀምበት ህንፃ ግን ያው ከ50 ዓመት በፊት ይሰራበት በነበረው ህንፃ ስለሆነ የችሎት ማስቻያ፣ የቢሮና የመዝገብ ቤት ከፍተኛ ጥበት አጋጥሞታል። የማስቻያ ቦታ በመጥፋቱ በፈረቃ ብሎም በየሶስት ቀኑ የማስቻል ስራ እንድንሰራ ተገደናል፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ መዝገብ በመብዛትና ከቀጠሮ ወደ ቀጠሮ የመንከባለል፣ በዚህም ተገልጋዩ የመጉላላት ችግር ላይ መውደቅና “ፍትህ የለም” ወደ ሚል መማረር ደርሷል። በአጭር ጊዜ እልባት ሊያገኙ ሲገባቸው መዝገቦች ወደ አመትና ከዚያ በላይ እየተንከባለሉ ሲያስቸግሩ፣ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ የሌሎቹ ሦስቱም ፍርድ ቤቶች አመራሮች ምክክር አደረጉ፡፡ ከዚያም በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ ሊከናወኑ የሚገቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀመጥን፡፡  
እስኪ የአጭር ጊዜ እቅዳችሁን ይንገሩኝ--?
የአጭር ጊዜ እቅዳችን፣ ለኪራይ የሚሆን ህንፃ ማፈላለግ ነበር፡፡ በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ ከመንግስት በልዩ ሁኔታ ዘመናዊ ህንፃ የሚገነባበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር የፍርድ ቤቱ ችግር ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ፣ ይሄኛውን ህንፃ (የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋናው ህንፃ ማለት ነው) ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የነበሩት ኃላፊዎች ሲያሳድሱ፣ ከዚህ ህንፃ ጀርባ ያሉ ህንፃዎች ሊታደሱ የማይችሉ፣ በሰው ላይ የመደርመስ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ፣ ዝናብ የሚያስገቡና በሚያመነጩት ሽታ ዳኞችን ለበሽታ እየዳረጉ መሆናቸው የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ በነበሩበትም ጊዜ የተገለፀ ጉዳይ ነው፡፡ ህንፃዎቹ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ጎርፍ እያስገቡ፣ በየጊዜው በጉልበት ሰራተኞች እያስጠረጉ ነበር ሲያገለግሉ የቆዩት፡፡ በኋላ ደግሞ በሰው ላይ የመደርመስ አደጋ ያደርሳሉ ተብሎ በባለሙያዎች ሲገለፅ፣ ህንፃ በአንድ ጀንበር ተገንብቶ ስለማይደርስ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ህንፃ መከራየት ነው፡፡ በእርግጥ ህንፃ መከራየት፣ በመንግስት ወጪ ቁጠባ አቅጣጫ ተከልክሎ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ እኛ ጉዳዩ በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ጠይቀን፣ ህንፃ እንደንከራይ ተፈቀደ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ በኋላ ከዳኞች፣ ከድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችና ከሲኒየር ዳኞች የተውጣጡ አምስት አባላት ያሉት ህንፃ አፈላላጊ ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡ ይህ ኮሚቴ በ2009 እና በ2010 ዓ.ም ጥናት ሲያደርግና ህንፃ ሲያፈላልግ ቆየ፡፡ ህንፃው የተለያዩ መስፈርቶችን እንዲያሟላ መጀመሪያውኑ የተቀመጡ መስፈርቶች ነበሩ፡፡ አንደኛ ለችሎት አመቺ የሆነ፣ ሁለተኛ የቦታ ቅርበት፣ ሦስተኛ ትራንስፖርት እንደ ልብ የሚገኝበት፣ አራተኛ በቂ የመኪና ማቆሚያ ያለውና አምስተኛ በግልፅ ቦታ ላይ የተገነባና የማያምታታ የሚሉ ግልፅ መስፈርቶች ተቀምጠው ነበር፡፡
አሁን የተከራያችሁት ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኝ  ህንፃ እንዴት ተመረጠ?
ኮሚቴው በተቀመጠለት መስፈርትና አቅጣጫ መሰረት፤ ሦስት ህንፃዎችን መርጦ አቅርቧል፡፡ የመጀመሪያው ህንፃ፣ ሳር ቤት አደባባይ አካባቢ የሚገኝ ባለ አምስት ፎቅ  ሲሆን ለፍርድ ቤት ለቢሮዎችና ለችሎት በፓርቲሽን ተከፋፍሎ ቢሰራ ምቾት ሊሰጥ እንደሚችል ኮሚቴዎቹ ገለፁ፡፡ ሁለተኛው አሁን የተከራየነው ጦር ኃይሎች ዋናው መንገድ ላይ የሚገኘው ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ ተከፋፍሎ፣ ለችሎቶች የተመቸ፣ የመኪና ማቆሚያ ያለውና ለትራንስፖርት አመቺ የሆነ ነው የሚል ቀረበ፡፡ እውነትም ይሄ ህንፃ፣ አንድ ሰው ከሲኤምሲ በባቡር ቢመጣ፣ ወርዶ ህንፃው ጋር ለመድረስ ከአምስት ደቂቃ በላይ አያስኬድም፡፡ በታክሲም ለሚመጣ የመጨረሻው ታክሲ ማራገፊያ አካባቢ ስለሚገኝ አመቺ ነው፡፡ ከጀሞም ሆነ ከአየር ጤና ለሚመጣም ዋናው መንገድ ላይ ነው የሚገኘው። ከስድስት ኪሎ፣ ከጊዮርጊስ በባቡር የሚመጣውም እንደዛው መጨረሻ ላይ ወርዶ፣ በአምስት ደቂቃ ችሎት ይደርሳል፡፡ ይሄ ህንጻ በአጠቃላይ በሁሉ ነገሩ አመቺ ነው ተብሎ በሁለተኛነት ቀረበ፡፡
በሦስተኛነት የተመረጠው አፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኝ ህንፃ ነበረ፤ ብዙ ምቹ ባይሆንም እንደ አማራጭ  ቀርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ካወጣው መስፈርት አንፃር፣ ከሳር ቤት አደባባይ ወረድ ብሎ ከኦሮሚያ ቢሮዎች ፊት ለፊት የሚገኘውን መረጥንና፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የበጀት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ ስንጠባበቅ፣ ባለቤቶቹ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አከራዩትና ተቀደምን፡፡ ከዚያ የጦር ኃይሎቹን ህንፃ ለመከራየት ወሰንን፡፡ ከመከራየታችን በፊት ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባለሙያዎች አይተውት፣ መስፈርቱን ሊያሟላ የሚችል እንደሆነ አረጋግጠውና ታምኖበት ተፈቀደ፡፡ ይህንን ሂደት አልፈን ከመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ውል ገባንና የፓርቲሽን ሥራ  ተጀመረ፡፡ የፓርቲሽኑ ስራ ቀጥታ ከአግሮስቶን ግዢ በመፈፀም፣ ህግና ስርአት በተከተለ መልኩ ተከናወነ። ከዚያም በቅርቡ ስራ ጀመረ፤ ሂደቱ ይሄን ይመስላል፡፡
ተገልጋዮች ግን የተለያዩ ቅሬታዎችን እያሰሙ ነው፡፡ አንደኛ፤ ህንፃው ባለ ሰባት ፎቅ በመሆኑ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአቅመ ደካሞችና የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች ምቹ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ አሳንሰር አልተገጠመለትም፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ የለውም፣ ተገልጋዩም ከ40 ዓመት በላይ ከለመደው ቦታ የፍትሀ ብሄር ችሎቱ መዛወሩ ግርታን ፈጥሮበታል … የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ በእነዚህ ቅሬታዎች ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንግዲህ ነገሮችን በቅንነት ብናያቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፤ እዚህ ዋናው ግቢ ያሉት ህንፃዎች ተደርምሰው አደጋ ከማድረሳቸው በፊት እርምጃ መውሰዳችን በበጎ መልኩ ሊታይ ይገባል፡፡ ሌላው ማህበረሰቡን በጥሩ መልክ የሚያገለግል፣ ዘመናዊና የአገሪቱን ገፅታ የሚያንፀባርቅ ህንፃ መገንባት በረጅም ጊዜ እቅዳችን ውስጥ ተካትቶ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2.14 ሄክታር መሬት ተፈቅዶልን፣ ሁለተኛ ዙር የዲዛይን ፍላጎት ጥናት ላይ እንገኛለን፡፡ እርግጥ አንድ ባለሀብት ህንፃ ሲሰራ፣ ለንግድና ለጠቅላላ አገልግሎት እንጂ ለፍርድ ቤት ብሎ አይሰራምና ሰባት ፎቅ መሆኑ ትክክል ነው። ህንፃው ገና አዲስና አገልግሎት ሰጥቶ የማያውቅ በመሆኑ አሳንሰር አልተገጠመለትም ነበር። አሁን ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳንሰር ለማስገባት በሩጫ ላይ ናቸው፡፡ ከ15 ቀን እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ የዘገየው  በውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ባለበት ግቢ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግና የፍትህ ሚኒስቴር ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ የዚህ ግቢ ባለቤት የትኛው ተቋም ነው?
ፍርድ ቤቱ ከውጭ ሲታይ በጣም ትልቅ ይመስላል፡፡ እርግጥ ቦታው 4.4 ሄክታር መሬት ነበር። እንዳልሺው ፍትህ ሚኒስቴርም እዚሁ ግቢ ውስጥ ህንፃ ገንብቷል ግን ካርታ የለውም፡፡ ምክንያቱም የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን እንዲሁም የግንባታ ፈቃድና ሌሎች ስርዓቶችን ባልተከተለ መንገድ ነው ግንባታው የተካሄደው ይባላል፡፡ በእርግጥም ፕላንን ተከትሎ ያልተሰራ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጥበትን ህንፃ ገንብቶ እየሰራ ነው፤ ነገር ግን ካርታ የለውም፡፡ በባለቤትነት የሚታወቀው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ራሱ ካርታ የለውም፡፡
ለመሆኑ የግቢውን የአስተዳደር ሁኔታን በመምራት በኩል ችግር የለውም?
የአስተዳደሩም ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቅድም ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አለ፣ የልደታ ተጠሪ ፍርድ ቤት አለ፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትም አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ፤ ባለቤትነቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሆንም፣ በካርታ ደረጃ ግን ተለይቶ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ በአስተዳደር በኩል የገጠመንን ችግር ልንገርሽ፡፡ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ሲከናወን፣ የዚህን ግቢ አጥር አፍርሶታል፡፡ ያንን አጥር ለማስገንባት የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስንንቀሳቀስ፣ ለየራሳችን ተለይቶ የተሰጠን የባለቤት የምስክር ወረቀት የለንም። እኛ ስንመጣ በቆርቆሮ ነበር የታጠረው፡፡ በወቅቱ የካሳ ክፍያ ተወስዶ አጥሩ መገንባት ነበረበት፡፡ ታዲያ ይህንን አጥር ለመገንባት ከፍተኛ  ውጣ ውረድና ችግር ነበር፡፡
የተለያዩ ተቋማት በአንድ ግቢ ውስጥ ሆነው በመስራታቸው፣ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ አለ?
አንድ ተቋም ስራውን ሲሰራ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ደህንነቱን ከመጠበቅ አንፃር ቀዳሚው አጥር ነው፡፡ ፈትሾ ለማስገባት አጥርና በር መኖር አለበት፡፡ ሁሉም በየስርቻው የሚገባ ከሆነ፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ችግር የደህንነት ስጋት ነው፡፡ ሌላው ፍትህ ሚኒስቴር እዚያ ቦታ ላይ ግንባታ ባይገነባና ቦታው ክፍት ቢሆን ኖሮ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሌላ የመሬት ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገን እዚሁ ህዝብ የለመደው ቦታ ላይ ግንባታ በማካሄድ አገልግሎት እንሰጥ ነበር፡፡ ስለዚህ በቂ ቢሮ በቂ ችሎት ከሌለ፣ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ ግልፅ ነው፡፡ ትልቅ የቀጠሮ መንከባለልና መስተጓጎል ያስከተለው፣ የቢሮና የችሎት እጦት ነው። ለዚህ ነው የፍትሃ ብሄር ችሎትን ወደ ኪራይ ህንፃ በማዛወር ጊዜያዊ መፍትሄ የሰጠነው፡፡  
የተከራያችሁት ህንፃ የሚንከባለሉ መዝገቦችንና ጉዳዮችን ከማቀላጠፍና ቶሎ መፍትሄ ከመስጠት አኳያ ምን ያህል ለውጥ  ያመጣል ይላሉ? ምን ያህል ችሎቶችስ ይኖሩታል?
እዚህ ግቢ በአንድ ችሎት ይካሄድ የነበረው የስራ ክርክር ችሎት፣ በአሁኑ ሰዓት በአዲሱ ህንፃ በሶስት ችሎት የሚስተናገድበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በስድስት ችሎቶች ይካሄድ የነበረው ቀጥታ የፍትሃ ብሔር ክስ ጉዳዮች አሁን ላይ በእጥፍ በ12 ችሎቶች እንዲስተናገድ ሆኗል፡፡ በችሎት እጦት ታጥፎ የነበረው የፍትሀ ብሔር ይግባኝ ጉዳዮች ችሎቶችም ተደራጅተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ በፊት ለረጅም ጊዜ ይንከባለሉ የነበሩ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ የሚቋጩበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን እናምናለን፡፡ ለምሳሌ የስራ ክርክር ጉዳዮች በ60 ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ አለባቸው፡፡ እሱም በመጀመሪያ ደረጃ አከራክሮ በሚወሰን ፍርድ ቤት ነው፡፡ ነገር ግን አራት አመታት ያስቆጠሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህ የማስቻያ ቦታ እጦት፣ አንዱን ጉዳይ አራት ወር አምስት ወር እንዲቀጠር ያደርጋል፡፡ በቦታ ችግር  በአንድና በሁለት ዳኛ ብቻ ነው የሚያስችል የነበረው፡፡ በመጀመሪያ ክርክር በ60 ቀናት ይቋጭ ከተባለ ይግባኙ ከዚያ ባነሰ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ህጉ ታሳቢ ያደርጋል፡፡
አሁን አሁን በአገራችን የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት እየተቋቋሙ ይገኛሉ፡፡ ኢንቨስት የሚያደርጉት ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች እንደመሆናቸው፣ አብዛኞቹ ክርክሮች በፌደራል ፍ/ቤቶች ዳኝነት ሥር የሚወድቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን ሊሸከሙ የሚችሉ ችሎቶች አሁንም መደራጀት አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ህንፃ የተከራየነው። በዚህ ምክንያት ችሎቱ ለምን ወደዚህ ተዛወረ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቹ ተገቢ ቢሆኑም ለውጥ ለማምጣት ነውና ነገሮች ቀስ በቀስ ይስተካከላሉ። እዚህ በችግር ተመቻችቶ ከመቆየት በአዲሱ ህንፃ ጉድለቶች ካሉ እያስተካከልን ነገር ግን የተሻለና ሰፊ አገልግሎት መስጠቱ የተሻለ በመሆኑ፣ ነገሩ  በቀናነትና በበጐ መንፈስ ቢታይ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ቅርስ ነው ብዙ ሰው ያውቀዋል፣ መዛወር የለበትም የሚሉም አሉ፤ ግን አማራጭ በማጣት አዛውረናል። የጤና እክል ላለባቸው፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለነፍሰ ጡሮች ጉዳያቸው በልዩ ሁኔታ ተይዞ፣ አንደኛ ፎቅ ላይ የሚስተናገዱበትን አሰራር አመቻችተናል፡፡ የመኪና ማቆሚያ ከፊት ለፊት 10፣ ከኋላም እንደዛው የሚይዝ ቦታ አለ፡፡ እውነት ለመናገር እዚህም ቢሆን ፓርኪንግ የለንም፡፡ ሰው በየመንገዱ መኪናውን እያቆመ እየገባ ለስፖኪዮና ለመሰል ንብረቶች ዘረፋ ሲጋለጥ ነው የቆየው፡፡ አሁን የተሻለ የመኪና ማቆሚያ ነው ያለው፡፡ ይሄ ጊዜያዊ ነው፡፡ በሂደት የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ህንፃ እንገነባለን፡፡  
መንግስት የፍርድ ቤቱን ችግር ምን ያህል ተገንዝቦታል? ለጠየቃችሁት የቦታና የበጀት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አግኝታችኋል? እስኪ ስለምትገነቡት ዘመናዊ ህንፃም በጥቂቱ  ይንገሩኝ---
ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቂ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የፍትህ አካል ነው፡፡ የአገሪቱ ትልልቅ ጉዳዮች በዳኝነት የሚታዩበት ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በጀት ተፈቅዷል፡፡ የቀድሞው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ልዩ ትኩረት ሰጥተው፣ ለህንፃው ግንባታ 2.14 ሄክታር ቦታ ተፈቅዶ ነበር፡፡ ችካልም ተቸክሎ ርክክብ ለማድረግ በሂደት ላይ እያለን የአመራር ለውጥ ተደረገ፡፡ አዲሱ አመራር አጠቃላይ የከተማዋን መሬት ቆጠራ ጀምሯል፡፡ አዲሱ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን አግኝተን አነጋግረን፣ ቀና ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ የመሬት ቆጠራው ሲጠናቀቅ ቦታውን እንረከባለን፡፡  
የተፈቀደላችሁ ቦታ የት አካባቢ ነው? መንግስት ለግንባታውስ ምን ያህል በጀት ፈቀደላችሁ?
ቦታው ልደታ ክ/ከተማ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማዶ ላይ ቀድሞ ቢታንያ ክሊኒክ የነበረበት አካባቢ ነው። ከጐማ ቁጠባ ወደ ተክለሃይማኖት ስትወጪ፣ በግራ በኩል ያለው ቦታ ነው፡፡ ቦታውን ሄደን አይተናል። በጣም አማካይ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የአገሪቱን ገጽታ የሚወክል፣ ለአካል ጉዳተኞችም ለአቅመ ደካሞችም ለነፍሰ ጡሮችም የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ህንፃ እናሰራለን፡፡ አሁን ጥናቱ ተጠናቅቆ ወደ ስራ ለመግባት እየጠበቅን ነው፡፡ በጀትን በተመለከተ 50 ሚ. ብር ተፈቅዷል፡፡ እንደውም በመጀመሪያው ሩብ አመት የአፈር ምርመራ ተደርጐ ወደ ስራ ልንገባ ስንዘጋጅ ነው የአመራር ለውጥ የተደረገው፡፡ በአጠቃላይ ያለው እውነት ይሄው ነው፡፡ ለተሻለ አገልግሎት ዝውውር ሲደረግ ምቾት ማጣት ሊመጣ ይችላል፤ ነገር ግን ባለጉዳዮቻችን በጣም ሊታገሱት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ባለጉዳይ ለ6 ወርም ለአመትም ሲቀጠር “ፍትህ የለም” እያለም ይታገሳል፡፡ ይህንንም ዝውውር በበጐ መልኩ ተመልክተው መታገስ አለባቸው፡፡ ሚዲያውም ይህን እውነታ ለተገልጋይ በግልጽ የማስተዋወቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ ባለጉዳዮችም በሚኖሩ ክፍተቶች ላይ ከእኛ ጋ እየተወያዩና የመፍትሔ አካል እየሆኑ፣ አብረን ችግሮቻችንን ብንፈታ መልካም ነው እላለሁ፡፡  


Read 6382 times