Saturday, 03 November 2018 15:44

የወልቃይት ተፈናቃዮች ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የማንነት ጥያቄ ከሚነሳበት አወዛጋቢው የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ በማንነታችን ምክንያት በደል ደርሶብናል የሚሉት የወልቃይት ተፈናቃዮች፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የፌደራል መንግስት ፍትህ እንዲሰጧቸው ተማጽነዋል፡፡ ከወጣቶቹ መካከል አራቱን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሮ፣ ሃሳባቸውን እንደ ወረደ አቅርቦታል፡፡ እነሆ፡

             “ስቃይና እንግልቱን ማንም አልተረዳልንም”

    አዳነ እሸቴ አደራጀው እባላለሁ፡፡ አርሶ አደር ነኝ። የመጣሁት ከወልቃይት ነው፡፡ ባለትዳር ነኝ፡፡ ልጆች አሉኝ፤ እያስተማርኩም ነው፡፡ 11ኛ ክፍል የደረሰ ልጅ አለኝ፡፡ እሱም በአሁኑ ሰአት እንደኔው በትምህርት ቤት በደረሰበት በደል ተፈናቅሎ ጐንደር እየተማረ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ እንዳይናገር እንዳያነብ በመደረጉ ነው ወደ ጐንደር ተዘዋውሮ ትምህርት የጀመረው፡፡ በነሐሴ 2010 ዓ.ም “ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጠያቂዎች እኛን አይወክሉም” ብላችሁ ለሚዲያ ተናገሩ አሉን፡፡ እኛ ወልቃይት ጠገዴ አማራ እንጂ ትግራይ አይደለንም ብዬ በአቋሜ ፀናሁኝ፡፡ በዚህ የተፈጠረው ልዩነት እየሠፋ መጣ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ”ፋኖ አማራ ሊዋጋ ነው ሠልጥኑ” ብለው በሚሊሻነታችን መሣሪያ ያለንን ሰዎች ማስገደድ ጀመሩ፡፡ መዋጋት አለብን አሉ፡፡ እኛም “አማራ ሆነን አማራን አንወጋም፤ እንኳን አማራን ከትግራይ ጋር አንዋጋም” አልናቸው፡፡ መሣሪያ የያዝነው ለንብረታችን መጠበቂያ እንጂ የህወሓትን ተልዕኮ ለማስፈፀም አይደለም፡፡ አንሰለጥንም አልናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ከአስተዳዳሪዎቹ ጋር በድጋሚ ልዩነት ፈጠርን፡፡ “መሣሪያችሁን ፍቱ” ተባልን፤ እኛም አንፈታም ብለን ዘጠኝ ሆነን በረሃ ገባን፡፡ ህዝቡም ደግፎን ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን መስከረም 17 የመስቀል በአል ሲከበር፣ የአካባቢው ህዝብ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቁን ይዞ በአማርኛ እየዘፈነ እየተጫወተ ሲንቀሳቀስ ተቆጡ፡፡ “እንዴት በአማርኛ ትጨፍራላችሁ?” ብለው በወታደር አስከበቡት፡፡ ሰውም ተገድሏል፡፡ እኛ በረሃ ነበርን፤ በእኛም ላይ ዘመቱ፡፡ አምልጠን ጐንደር ገባን፡፡ የደረሰብን በደል እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በአማርኛ ጮክ ብሎ መነጋገር እንኳን አይቻልም። ወጣቶች ይደበደባሉ፣ ይታሠራሉ፤ ብዙ ስቃይ ነው የሚደርስባቸው፡፡ ከስቃይ ሽሽት ሰዉ በስፋት ተፈናቅሏል፡፡ በተለይ ከመስቀል በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ እዚህ አዲስ አበባ እንኳ የመጣነው ከ170 በላይ ነን፡፡ በርካታ ሚሊሻዎች ለጦርነት ሠልጥኑ ሲባሉ እምቢ ብለው ተሰድደዋል፡፡ ለሕይወታቸው የሰጉት ደግሞ ሰልጥነዋል፡፡
የወልቃይት ህዝብ መከራ ብዙ ነው፡፡ ነባሩ ነዋሪ ሸቃላ ሆኖ፣ በሠፈራ የመጡት ኢንቨስተር ሆነዋል። አማራ የተባሉ በተለየ መንገድ ይገለላሉ፡፡ ስቃይና እንግልቱን ማንም አልተረዳልንም፡፡ አሁን እዚህ የመጣነው ለገንዘብ እርዳታ አይደለም፤ ሃብታችንን ተጠቅመን ብንሰራ ሃብታሞች መሆን የምንችል፣ ሠርተን መብላት የምናውቅ ነን፡፡ የመጣነው ከመንግስት መፍትሔ ለማግኘት ነው፡፡ መብታችን ተከብሮ ወደ ቀያችን መመለስ እንፈልጋለን፡፡ ገለልተኛ የፀጥታ ሃይል መኃላችን መግባት አለበት፡፡ መንግስት ዋስትና ወስዶ ይመልሰን፡፡ ሌላው በህገ መንግስቱ መሠረት የቀረበ ጥያቄ አለ፤ ለሱም አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠን እንላለን፡፡ ሰው ነንና እንደ ሰው መፍትሔ ይሰጠን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መፍትሔ ይሰጡናል ብለን በመተማመን ነው የመጣነው፡፡

--------------

            “የዶ/ር ዐቢይን ቲ-ሸርት ለብሶ


      ስሜ አበበ ወርቁ ይባላል፡፡ የመጣሁት ከዳንሸ ነው፡፡ እስከ 5ኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ ትምህርቴን ያቋረጥኩት አማርኛ መማር አለብን በማለቴ ነው። የአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ አለን፤ ግን በዘፈን ነው የሚያልፈው፡፡ እኛ ደግሞ መማር ስለምንፈልግ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ በዚያ ምክንያት ነው ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ግብርና የገባሁት፡፡ ጐንደር፣ አማራ የሚል ዘፈን ወይም ቃል መናገር አንችልም፡፡ በአማርኛ ማልቀስ፣ በአማርኛ ለሠርግ መዝፈን ክልክል ነው፡፡ በተለይ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ልዩ ትኩረት አድርገው ነው አፈናውን ያጠናከሩብን፡፡
ዘፈን በአማርኛ ስዘፍን ልዩ ሃይል ቤቴ ድረስ መጥቶ ደብድቦኛል፡፡ “አንተ ስለ መለስ፣ ስለ ሃየሎም ታሪክ እንጂ ስለ ዐቢይ ምን ታውቃለህ?” ነው የምንባለው፡፡ በአማራነታችን ተጐድተናል፡፡ እንግልቱ ስቃዩ፣ አፈናው ሲበዛብን ነው የተሰደድነው፡፡ መንግስት መፍትሔ ይስጠን፡፡ አሁንም ጥያቄያችን መፍትሔ ሳያገኝ አንቀመጥም፡፡ መቀመጫም የለንም፡፡ በአማራነታቸው አምስት ጓደኞቼ የት እንደደረሱ አላውቅም፡፡ 281 የማውቃቸው ወጣቶች መሣሪያ ይዘው በረሃ ገብተዋል። አካባቢው የጦርነት ቦታ ነው የሚመስለው። የዶ/ር ዐቢይ ምስል ያለበት ቲ-ሸርት ለብሶ መውጣት ክልክል ነው፡፡ አሸንዳ በትግርኛ ካልጨፈራችሁ ተብለን ተደብድበናል፡፡ እኛ እንደ አማራነታችን ባህላችንን፣ ቋንቋችንን ማበልፀግ መጠቀም ተከልክለን ነው የኖርነው፡፡


-------------


             “ዶ/ር ዐቢይን መደገፋችን ዋጋ አስከፍሎናል”


      ክንፈ ጥላሁን ማሞ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከወልቃይት ወረዳ ነው፡፡ አዲስ አበባ የመጣነውም አማራ ሆነን በወልቃይት መኖር ስላልቻልን ተፈናቅለን፣ ከፌደራል መንግስት መፍትሔ ለማግኘት ነው፡፡ እኛ የወልቃይት ሰዎች አማራ ሆነን፣ በአማርኛ መማር አልቻልንም፤ አማራ ሆነን በአማራ መሬት ነግደን አትርፈን መኖር አልቻልንም፡፡ በቋንቋችን በነፃነት ማውራትም መማርም አልቻልንም፡፡ አማርኛ ከዘፈንኩ ወይ ካወራሁ እታሠራለሁ ወይም እገረፋለሁ፡፡ መኪናዬ ላይ የዶ/ር ዐቢይን ፎቶ ከለጠፍኩ በትራፊክ ፖሊስ ያለ አግባብ እቀጣለሁ፡፡ ሱቅ ላይ ስለ ዶ/ር አብይ የተለጠፈ ነገር ካለ፣ በግብር እያሳበቡ ቅጣት ይጥላሉ፡፡
የአማራነት ነገር ከታየብህ ለእንግልትና ለድብደባ፣ ለእስር መዳረግህ አይቀርም፡፡ በወልቃይት ያለው ችግር ጐልቶ የታየው ዶ/ር ዐቢይ  ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነው፡፡ አማራዎች ዶ/ር ዐቢይን መደገፋችን ለጥቃት አጋልጦናል፡፡ ሰንደቅ አላማ፣ የዶ/ር ዐቢይ ምስል ያለበት ቲ-ሸርት፣ የአፄ ቴዎድሮስ ቲ-ሸርት እንዲሁም ጃኖ የለበሰ ሰው፤ “የአሸባሪ ልብስ የለበሰ” እየተባለ ይደበደባል፤ ይታሠራል፣ ይሰደዳል፡፡ በዚህ መንገድ ተደብድበው የት እንደደረሱ ያላወቅናቸው ጓደኞቻችን አሉ፡፡ እኔ እስከ 10ኛ ክፍል ተምሬያለሁ። የተማርኩት ሳልወድ በግድ በትግርኛ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ከሁለት አመት በፊት ያችን ትምህርትም አጥፍተዋታል። ለበአል በአማርኛ መጨፈር መዝፈን አይቻልም፡፡ ለአዲስ አመት ለመስቀል እኔ ራሴ ተደብድቤያለሁ። “የደርግ ቡችላዎች፣ የደርግ ትርፎች” እየተባልን ነው የምንደበደበው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣነው  መንግስት መፍትሔ እንዲሰጠን ነው፡፡
አሁን ተሰድደንም ወከባውና ክትትሉ አልቀረልንም። ቤተሰቦቻችን እየተንገላቱብን ነው፡፡ እናንተ ናችሁ የላካችኋቸው ተብለው እየተሰቃዩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን መደገፋችን ዋጋ አስከፍሎናል። ለእንግልት ለስቃይ ዳርጐናል፡፡ የፌደራል መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ መንግስት ጥበቃ እንዲያደርግልንም እንፈልጋለን፡፡ ባዶ እጃችንን ምንም ልብስ፣ ገንዘብ ሳንይዝ የወጣን ሰዎች ነን፡፡ አፋጣኝ ፍትህ እንፈልጋለን፡፡


---------------


               “በባህላችን መሠረት ጀግናን ፎክሮ መቅበር አይፈቀድልንም”

   አስፋው ክንፉ እባላለሁ፡፡ እድሜዬ 18 ነው። ከትምህርቴ ተፈናቅዬ ነው የመጣሁት፡፡ 5ኛ ክፍል ነበርኩ፡፡ አማርኛ ቋንቋ እንማር ባልኩ ነው የተሰደድኩት፡፡ አማራነት በወልቃይት እንደ ወንጀል ነው እየታየ ያለው፡፡ “እናንተ እነ ዶ/ር ደብረፅዮንን ነው መደገፍ ያለባችሁ እንጂ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር ዐቢይ፣ ለማ መገርሣ ማለት የለባችሁም” ነው የሚሉን። ምንም አይነት የአስተዳደር ጥያቄያችን ተቀባይነት የለውም። የመኖሪያ ቦታ፣ የእርሻ መሬት እየተከለከልን ነው፡፡ በሚዲያ ቀርበን ብሶታችንን መናገር አንችልም፡፡  
በአብዛኛው የሚያጠቁን በተናጠል ነው፡፡ በጅምላ የሚያጠቁን ሠርግ ላይ ወይም በአል ላይ በአማርኛ ስንጨፍር ነው፡፡ ለቅሶ ላይ በባህላችን መሠረት ጀግናን ፎክሮ መቅበር አይፈቀድልንም፡፡ በአማርኛ በመዝፈናችን፣ ባህላችንን እናሳድግ በማለታችን በደል ተፈጽሞብናል፡፡ እምነት የጣልንባቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ታሪክን መሠረት አድርገው፣ የኛንም እንግልት ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡን ነው የምንፈልገው፡፡ እኔም ካቋረጥኩት ትምህርቴ ተመልሼ ተምሬ፣ ነገ ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ፡፡


------------------


             “የአማራነት መንፈስ አለባችሁ ተብለን ነው የተፈናቀልነው”


    ዲያቆን ላልይበላ መላው እባላለሁ፡፡ ከወልቃይት ፀገዴ ከተፈናቀልን ከወር በላይ ሆኖናል፡፡ የተፈናቀልንበት ምክንያት “እናንተ የአማራነት መንፈስ አለባችሁ፤ አማርኛ ትናገራላችሁ፤ በስልክ አማርኛ ታወራላችሁ፤ አማርኛ ጽሑፍ ያለባቸውን ቲ-ሸርቶች ትለብሳላችሁ” ተብለን ነው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአፄ ፋሲል ግንብ፣ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፎቶ ያለበትን ቲ-ሸርት መልበስ የተወገዘ ነው፡፡ የእነ ለማ መገርሣን፣ የእነ ገዱ አንዳርጋቸውን ቲ-ሸርት የለበሰ ታድኖ ነው የሚደበደበው፤ የሚታሰረው፡፡ የአማርኛ ዘፈን ማዳመጥ አይቻልም፡፡ ክልከላውን የሚያደርጉት አስተዳደሩና የትግራይ ልዩ ሃይሎች ናቸው፡፡
ዱላ የሚለማመዱት እኛ ላይ ነው፡፡ “እነሱ ትግሬ ናቸው” ይሉናል፡፡ ትግሬ ብንሆንማ ባልደበደቡን ነበር። ትግሬ አለመሆናችንን የሚያረጋግጡልን ራሣቸው ናቸው፡፡ እኛ አማራ ነን፤ ስለዚህ ባህላችንን ማጐልበት አለብን ብለን፣ ደመራ በአማርኛ እየጨፈርን እየዘመርን፣ በዓል ለማክበር መሞከራችን ነው ዛሬ ለመፈናቀል ያበቃን፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ነው ማሣደዱ የበረታው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሣይቀር በትግርኛ ነው መሰበክ ያለበት በሚል ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ በተለይ ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ አፈናው ጠንክሮብናል፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ ወጣቶች ትምህርታቸውን፣ ገቢ የሚያገኙበትን ስራቸውን፣ ግብርናቸውን ትተው ነው የተሰደዱት፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ይዘን የመጣነው ጥያቄ እውነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተን ልንደመጥ ይገባል፡፡ ዜጐች ነን፣ በሃገራችን ለምን እንንገላታለን፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ታሪኩ ተጠንቶ፣ ስነ ልቦናው ተጠንቶ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል፡፡ ታሪክ ነው መጠናት ያለበት፡፡  

Read 474 times