Saturday, 03 November 2018 15:43

የራስ ተፈሪያኖች ኮንፍረንስ በሻሸመኔ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   - “ሻሸመኔ የመላው ጥቁር ህዝቦች የቃልኪዳን ምድር ናት” – ማማ አስካለ ስላሴ
             
     ሁለተኛው የመላው አፍሪካ ራስተፈርያኖች ስብሰባ (All African Rastafrians Gathering 2018) ከትናንት በስቲያ በሻሸመኔ ከተማ የተጀመረ ሲሆን ስብሰባው ለ11 ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡ ልዩ ስብሰባው በትናንትና እለት ለ88ኛው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴና እቴጌ መነን የበዓለ ሲመት በተዘጋጀ ልዩ ክብረ በዓል የቀጠለ ሲሆን በራስተፈርያኖች አህጉራዊ የንግድ ቀጠና እና ልዩ ልዩ ትስስሮች የሚያተኩረው የአምስት ቀናት አህጉራዊ ጉባኤ  ከሰኞ ጀምሮ እንደሚካሄድ እንዲሁም በራስተፈርያኖች አህጉራዊ ምክር ቤት እንቅስቃሴና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ እንደሚመከር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ማማ አስካለ ስላሴ ለአዲስ አድማስ  ገልፀዋል፡፡
በአፍሪካና በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ የራስተፈርያን ተቋማት፤ ሌሎች የማህበረሰብ አባላትን የሚያገናኙ የትውውቅ መድረኮች መኖራቸውን አመልክተው፤ ራስተፈርያኖች በመላው አፍሪካ በሚኖራቸው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አተኩሮ በሚካሄደው የ5 ቀናት ጉባኤ ላይ በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሱ ራስተፈርያን ነጋዴዎች፤ የራስተፈርያን ተቋማትና ማህበራት ከፍተኛ ምክክር እንደሚያደርጉ ማማ አስካለ ተናግረዋል፡፡ በ2ኛው የመላው አፍሪካ ራስተፈርያኖች ስብሰባ፤ የራስተፈርያን ቤተሰቦችን የሚያሳትፉ ምሽቶች፤ የምስጋና እና የከበሮ ጨዋታዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ስነስርዓቶች የሚካሄዱ ሲሆን የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎችን የሚያሳትፍ የ2 ቀናት ባዛርም እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡ በስብሰባው  ላይ  ለመሳተፍ ከ12 የተለያዩ አገራት ከ100 በላይ ራስተፈርያኖች  ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን ከዓመት በፊት በተመሰረተው የራስተፈርያኖች አህጉራዊ ምክር ቤት (The Rastafari Continental Council RCC)  አጀማመር ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡
2ኛው የመላው አፍሪካ ራስተፈርያኖች ስብሰባ በመላው ዓለም የሚገኙ የራስተፈርያን ማህበረሰብ አባላት፤ ተቋማትና ማህበራት በጋራ የሚንቀሳቀሱባቸውን አቅጣጫዎች ያዳብራል ያሉት ማማ አስካለ ስላሴ ፤ በራስተፈርያን የንግድ ማህበረሰብ መጠናከርና በአህጉራዊ የንግድ ቀጠና መስፋፋት ላይ የእውቀት ሽግግሮች የሚፈጠሩበት መድረክ ይሆናልም ብለዋል፡፡  ዘንድሮ በኢትዮጵያ  መንግስት ከ300 በላይ ራስተፈርያኖች  የነዋሪነት ፈቃድ ማግኘታቸውን አስመልክቶ በስብሰባው ላይ የምስጋና እና አድናቆት ስነስርዓት እንደሚኖርም ይጠበቃል፡፡ የራስተፈርያኖችን እንቅስቃሴ በተለይ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ማህበራትና ተቋማት ያስመዘገቧቸው ስኬቶችን የሚዳስሰው ስብሰባው፤ በተመሳሳይ በተለያዩ የካራቢያን አገራት የሚንቀሳቀሱ ራስተፈርያንና ተቋሞቻቸው ያሏቸውን መልካም ተመክሮዎች ያጋሩባቸዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪ በአፍሪካ ዙሪያ ራስተፈርያኖች ያላቸውን የንግድ ትስስሮች በተመለከተ በተለይ ከናሚቢያ እንዲሁም ከምዕራብ አፍሪካ የሚመጡ ተወካዮች የሚያቀርቧቸው ጠቃሚ ልምዶች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
ከራስተፈርያኖች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስብሰባዎች፣ ኮንፍረንሶችና ልዩ መድረኮች ከ1980ዎቹ ሲካሄዱ መቆየታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች ብዙዎቹ በየዓመቱ ቋሚ ሆነው የማይካሄዱና የሚቆራረጡ፤ በተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች የሚጉላሉና ውጤታማ ያልሆኑ መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡ የመላው አፍሪካ ራስተፈርያኖች ስብሰባ  ባለፈው ዓመት ሲካሄድ ግን በተያዙ አቅጣጫዎች ወደፊት ብዙ ለውጦችና ስራዎች እንደሚኖሩ  ተስፋ አሳድሯል፡፡ በዓምናው ስብሰባ በወቅቱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ የራስተፈርያን ድርጅቶችና ተቋማትን የወከሉ ከ100 በላይ  ራስተፈርያኖች ከአንጎላ፣ ቤኒን፣ ካሜሮን፣ ጋና፣ ሲሸልስ፣ አይቬሪኮስት፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ከእንግሊዝ ፤ ከአሜሪካና ከካሪቢያን የመጡት ልዑካኖችም በአፍሪካና በጥቁር ህዝቦች የባህል ሉዓላዊነትት፤ የኢኮኖሚ ነፃነት፤ የባህል ኢንዱስትሪ መዳበርና የፈጠራ ኢኮኖሚን በዘላቂነት ለማነቃቃ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በአፍሪካ የንግድ ቀጠናውን ለማስፋፋትና አፍሪካን እንደ አንድ አገር ለመፍጠር የራስተፈርያኖችን አስተዋፅኦ ለማሳደግም ተወስኗል፡፡ ከአንደኛው የመላው አፍሪካ ራስተፈርያኖች ስብሰባ ስኬታማ ሂደት በኋላ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ለ3 ቀናት በተካሄደ ስብሰባ፤ የራስተፈርያኖች አህጉራዊ ምክር ቤት የተመሰረተ ሲሆን መስራቾቹ ኢትዮጵያ፤ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ አንጎላ፣ ቤን፣ ሌሶቶ፤ ዚምባቡዌ፤ ታንዛኒያ፣ ናሚቢያና ስዋዚላንድን የወከሉ ራስተፈርያኖችና ተቋማት ነበሩ፡፡ ጋናዊው ራስ ኦሁማ ቦስካ የራስተፈርያኖች አህጉራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን የምክር ቤቱ ቀጣይ ስብሰባ በግንቦት ወር በጋና አክራ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ››  ዘመቻ
የመላው ጥቁር ህዝቦችና ራስተፈርያኖች ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ››  ዘመቻ ከ80 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ፤ ሻሸመኔ፤ ባህርዳርና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች  ከ1000 በላይ ራስተፈሪያኖች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሻሸመኔ የሚኖሩ ራስተፈሪያኖች ደግሞ  እስከ 500 እንደሚደርሱ ይናገራሉ፡፡ የራስተፈሪያኖች እና የመላው ዓለም የጥቁር ህዝቦች ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ እንቅስቃሴ እንደሚጠበቀው ባይሆንም በሻሸመኔ በአዲስ አበባ፤ በባህርዳርና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ባለፉት 25 እና 30 ዓመታት ከ2ሺ በላይ ሲኖሩና ሲመላለሱ ቆይተዋል፡፡
በርግጥ የጥቁር ህዝቦችና  ራስተፈሪያኖች ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ››  ዘመቻ ወደ አፍሪካ በመስፋፋቱ ማረፊያቸውን በኢትዮጵያ ብቻ አላደረጉትም፡፡ ወደ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አይቬሪኮስት፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳም እየከተሙ ይገኛሉ፡፡  በሁሉም አገራት የመኖሪያ ፈቃድ እየተሰጣቸው ቢሆንም መሬት የሰጠቻቸው ብቸኛ አገር ግን ኢትዮጵያ መሆኗን መጥቀስ ግድ ይሆናል፡፡  በተለይ ባለፉት 12 ወራት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መኖር ለሚፈልጉ የጥቁር ህዝቦችና ራስተፈርያኖች የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት መጀመሩ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ እየሰጠች የምትገኘው መታወቂያ የመኖሪያ ፍቃድ፣ የነዋሪነት መገለጫና የተለያዩ ህጋዊ መብቶችን የሚሰጥ ሲሆን በአገሪቱ ህገ መንግስት የሁለት አገር ዜግነት የማይፈቀድ በመሆኑ  የዜግነት ፈቃድ ግን አይደለም፡፡
ማማ አስካለ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት በመላው ዓለም የሚገኙ ራስተፈሪያኖች እና ጥቁር ህዝቦች በማናቸውም ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ ጐን የሚቆሙና የሚሟገቱ ናቸው፡፡ ይህን የሚያስገነዝቡትም “ኢትዮጵያውያን ለእኩልነትና ፍትህ ይሟገተሉ፡፡ አንጋፋዎችን፣ አቅም ደካሞችንና ህፃናትን እንዲሁም የተጐዱ ህዝቦችን ይደግፋሉ፤ ቅርስን ይጠብቃሉ የተዘረፈውን ያስመልሳሉ፤ ለሰላም በጋራ ይሠራሉ፤ የአፍሪካን አንድነትና ብልጽግናዋን ለማምጣት በህብረት ይንቀሳቀሳሉ” በማለት ነው፡፡
እንደ ማማ አስካለ አገላለፅ፤ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ወደ ኢትዮጵያ/አፍሪካ ከ600 ዓመታት በፊት መመለስ የጀመሩ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሻሸመኔ ላይ መሬት ከተሰጣቸው በኋላ የመጀመሪያዎቹ ራስተፈሪያኖች የገቡት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ያኔ ደግሞ ከጃማይካ፣ ከትሪንያድ ቶቤጎና ከበርባዶስ የመጡት ራስተፈሪያኖች ይበዛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሻሸመኔ የከተሙ የጥቁር ህዝቦችና ራስተፈሪያኖች አባላት ከ20 የተለያዩ አገራት መሰባሰባቸውን የሚናገሩት ማማ አስካለ፤ “ሻሸመኔ የጃማይካውያን ብቻ አይደለችም። የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የቃልኪዳን ምድር ናት። ሻሸመኔን የጃማይካ ብቻ ያስመሰለው የደርግ ስርዓት ነው፡፡  የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ዝና እና ክብር ለማጥፋት የደርግ አገዛዝ መስራቱን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በዚህ ምክንያትም በራስተፈርያኖች እንቅስቃሴ ላይ የሚፈለገውን ለውጥና እድገት ማየት አልተቻለም›› ይላሉ፡፡ ራስተፈሪያኖች እና ጥቁር ህዝቦች ከምዕራቡ ዓለም፤ ከጃማይካና ከካሪቢያን አገራት ብቻ ሳይሆን ከደቡብ አሜሪካ አገራት፡- ቺሊ ብራዚል፣ ሱሪኒማና ጋይና ለመምጣት ይፈልጋሉም ብለዋል-ማማ አስካለ፡፡


--------


            ማማ አስካለ ስላሴ ማናቸው?

    በመላው ዓለም የሚኖሩ ራስተፈርያኖች ማማ አስካለ ስላሴ በሚለው ስማቸው የሚያውቋቸው ቢሆንም በሙሉ ስማቸው ዮቮኔ ጌይል ተብለው ይጠራሉ፡፡ በዌስት ኢንዲስ ጃማይካ ውስጥ የተወለዱት ማማ አስካለ፤ በራስተፈርያኖች እንቅስቃሴና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርቶች በመስራት ከ45 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ማማ አስካለ ከ10 ዓመታቸው ጀምሮ በኖሩባት እንግሊዝ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በእንግሊዝኛ ስነፅሁፍ፤ በሶሲዮሎጂና በዩናይትድ ኪንግደም ህገ መንግስት፣ በከፍተኛና በአንደኛ ደረጃ መምህርነት፣ በታሪክ ምርምርና ፀሃፊነት እንዲሁም በትምህርት አስተዳደር ከፍተኛ ልምድም ያካበቱም ናቸው። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን በትምህርት የባችለር ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በከፍተኛ የትምህርት ተቋምና በመዋለ ህፃናት መምህርነት በርካታ ሰርተፊኬቶችን አግኝተዋል፡፡
ከትምህርቱ መስክ ውጭ የተከበሩበት ሌላ ሙያ ያላቸው ማማ አስካለ፤  ከታዋቂው እንግሊዛዊ ሪቻርድ ብራንሰን ጋር ለመስራት በቨርጂን ሪከርድስ ዓለም አቀፍ ሙዚቃ አሳታሚ በመቀጠር የጀመሩት ነው፡፡ በታዋቂው ዓለም አቀፍ ኩባንያ በአሳታሚነትና በገበያ ፕሮሞሽን ስራዎች በመቀጠር በሙያ መስኩ የመጀመርያዋ ጥቁር ሴት ሲሆኑ በከፍተኛ አገልግሎታቸው ምስጉን ሆነዋል፡፡ ከዚያ በኋላ  ፍሮንትላይን ሌብል በተባለውና ከበርካታ የጃማይካ ሙዚቀኞችና ፕሮዲውሰሮች ጋር በሰራው የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ ምስረታ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በፍሮንትላይን ሬድዮ እና ሚዲያ ፕሮሞሽን ሃላፊነት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ1972 እ.ኤ.አ ጀምሮ አገልግለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ  ታላቅ አጋጣሚ ተፈጠረላቸው፡፡ በተለያዩ የአሳታሚ መብቶች ዙርያ ከቦብ ማርሌይ ጋር የመከሩበት ግንኙነት ነበር፡፡ ቦብ ማርሌይ ወደ ጃማይካ ተመልሰው የሪከርድና አሳታሚ ኩባንያ የሆነውን Tuff Gong እንዲቀላቀሉ ነበር ያግባባቸው፡፡ በታፍ ጎንግ በሚኖራቸውም ኃላፊነት፤ የቦብ ማርሌይን ሙዚቃ በጃማይካ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በማስፋፋት እንዲሰሩ ጋበዛቸው፡፡ ማማ አስካለ ግብዣውን በመቀበል ወደ ጃማይካ ኪንግስተን ተመልሰው በተራራ ስፍራዎች የራስተፈርያን እምነት እየተቀበሉ፣ በታፍ ጎንግ ስቱዲዮ መስራት ጀመሩ፡፡ በዚህም በቦብ ማርሌይ ታፍ ጎንግ ስር የማርኬቲንግና የፕሮሞሽን ስራዎችን በማከናወን ለአምስት አመታት እስከ 1981 እኤአ ሊሰሩ ችለዋል፡፡
የሬጌው ንጉስ በተመሳሳይ ጊዜ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ተከትሎ ለሱ መስራቱን አልተውትም። በተለያዩ የካረቢያን አገራትና ደሴቶች በመዘዋወር የታፍ ጎንግ የሙዚቃ ስራዎችን በማስተዋወቅ ስኬታማ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ቦብ ማርሌይ የሰጠው ምስክርነት በታፍ ጎንግ ሙዚቃዎች ፕሮሞሽን ብቻ ሳይሆን የኃይለስላሴን ትምህርቶች በማስፋፋትና ፍቅርና አንድነትን በመስበክ  እማማ አስካለ ምስጉን አገልግሎት ሊሰጡ ቆይተዋል፡፡ በጃማይካና በካራቢያን ከታፍ ጎንግ ስቱዲዮ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ከጨረሱ በኋላ ማማ አስካለ በ1982 ወደ አሜሪካ ገብተዋል። ራስ ሬከርድ በተባለ የሙዚቃ አሳታሚ የፕሬስና የህዝብ ግንኙነት ዲፓርትመንት በመመስረት ለ6 ዓመታትም ሰርተዋል፡፡
እማማ አስካለን ወደ አባት አገራቸው ኢትዮጵያ የመመለስ ጥሪ ዳግም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መለሳቸው፡፡ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመግባት በማህበረሰብ ግልጋሎትና በትምህርት መስክ ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በቀጠሉት  ዓመታት በአውሮፓ የተለያዩ አገራት ውስጥ በመዘዋወር የዓለምን ማህበረሰብ በራስተፈርያን እንቅስቃሴና አስተምህሮት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በመገናኛ ብዙሃንና በህዝብ ግንኙነት ስራዎች በመላው ዓለም የተሳሰሩበትን ተዓማኒነትና ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያቸውም የእቴጌ መነን ፋውንዴሽንን ለመመስረት በቅተዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ስራዎቻቸውም የሚታወቁ ሲሆን አንጋፋው ትውልድ በምግብ፤ በልብስና በጤናማ አኗኗር እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል  በሚል መርሃቸውም በትጋት ሰርተዋል፡፡ በ “The EMPRESS MENEN FOUNDATION” ስር በፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ሆላንድ፤ ጀርመን፤ ክሮሽያ፤ ፊንላንድና ዴንማርክ በተደራጀ ሁኔታ ከሌሎች የራስተፈርያን ተቋማት ሰዎች ጋር ሰርተዋል። የእቴጌ መነን ፋውንዴሽን በየዓመቱ ልዩ ካለንደር በማማ አስካለ አዘጋጅነት ማሳተም የጀመረ ሲሆን  በመላው ዓለም ስለ አፍሪካ፤ ኢትዮጵያና ራስተፈርያን ያለውን ግንዛቤ ለማስፋፋት የሚሰራበት ህትመት ነው፡፡ በመጨረሻም ማማ አስካለ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ውድ አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ በእቴጌ መነን መታሰቢያነት ባቋቋሙት ፋውንዴሽን በአውሮፓ የጀመሩትን በልዩ ካላንደሮች የማስተማር ዘመቻን በኢትዮጵያም ሲሰሩበት ቆይተዋል፡፡


Read 1326 times Last modified on Saturday, 03 November 2018 15:51