Saturday, 03 November 2018 15:49

ጅሎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 “ወንድ ልጅ ሲከፋው፤ ውጭ አገር ይመኛል፤
እዚህ ያላደለው፤ እዚያ ምን ያገኛል”
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን፤ የሐገራቸውን ታሪክ ያለ ሚዛን ይዳኛሉ፡፡ በአባቶቻቸው ዓይን የሚያዩትን ጉድፍ ዘወትር አብዝተው ሲያነውሩ፤ እነሱ በዓይናቸው ግንድ ተሸክመው ይዞራሉ፡፡ አባቶቻቸውን፤ ‹‹ብዝሃነትን ማክበር ያልቻሉ ጨቋኞች›› እያሉ በስድብ ጭምር ይኮንናሉ፡፡ ግን እነሱ ብዝሃነትን ማክበር ተስኗቸው የጎሳ ልዩነትን መነሻ አድርገው ዜጎችን ያፈናቅላሉ፡፡ ግብዞች ናቸው፤ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚል ቃል ሰምተው የማያውቁ አባቶቻቸውን፤ በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ክስ ያንገረግባሉ፡፡ እነሱ ግን የተለየ አቋም ያለውን ሰው በዴሞክራሲ አግባብ ማስተናገድ አቅቷቸው እርስ በእርስ ይፋጃሉ፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አባቶቻቸውን በአድሎ፣ በሙስና፣ በፍትሕ ማጉደልና የዜጎችን የፖለቲካ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ባለመቻል ሲከሱ፤ በሚያነሱት ነገር ሁሉ እነሱ ብሰው ይገኛሉ፡፡
ህገ መንግስት ባለበት፣ የህዝቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በዳበረበት፤ ትምህርት በተስፋፋበት፤ ዓለም አቀፍ ሁኔታውም ምቹ በሆነበት በዚህ ዘመን የሚገኙት የሐገራችን የፖለቲካ ልሂቃን፤ ‹‹ዴሞክራሲ ተጓደለ፤ መልካም አስተዳደር ተበደለ፤ ፍርድ ተገመደለ›› የሚል ጥቃያቄ ሲነሳባቸው፤ ‹‹ዴሞክራሲ ጊዜን የሚጠይቅ በተቋም ግንባታ የሚመለስ ሥራ ነው›› እያሉ ሩብ ምዕተ ዓመታት ዘለቁ እንጂ እንደሚያወሩት አልሆነላቸውም፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፤ መላ አፍሪካን ከተቀራመቱት ኃያል የቅኝ ገዢ ኃይሎች መንጋጋ ለማምለጥ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ወደ ደቡብ የዘመቱትን ‹‹ማይም›› አባቶቻቸውን ‹‹የህዝብን ፈቃድ ሳታከብሩ፣ የዴሞክራሲ መርህን ሳትከተሉና የህግ የበላይነትን ሳታረጋግጡ ገዝታችኋል›› ብለው የሚከሱት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሐገራችን የፖለቲካ ልሂቃን፤ አያቶቻቸው ‹‹የማያውቁትን›› ነገር እንዲያደርጉ የሚጠይቁ ፍርደ ገምድሎች ሆነው ሳለ፤ እነሱ የሚያውቁትን ማድረግ የማይችሉ እና በአንዳንድ ሚዛን ደግሞ ከሚከሷቸው፤ ኋላቀር ከሚሏቸው አባቶቻቸው ጭምር የሚያንሱ ናቸው፡፡ ‹‹በረቱበት፤ ይረቱበት›› ማለት እንዲህ ነው፡፡
‹‹እጃችውን ከበትር፤ አፋቸውን ከነገር›› ማራቅ ያቃታቸው አምባገነኖች ስለመሆናቸው እንጂ ለዴሞክራሲ ስርዓት መከበር፣ ለህግ የበላይነት መስፈንና ለመልካም አስተዳደር መጽናት ከልብ የሰሩ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ህዝብ የሚመሰክርላቸው  አይደሉም፡፡ ሐገሪቱን ከድህነት ቀርቶ ከእርስ በእርስ ጦርነት እንኳን ሊያወጧት አልቻሉም፡፡ ‹‹እንባ ሲሻኝ፤ ዓይኔን ጢስ ወጋኝ›› እንዲሉ፤ የዘመናችን ልሂቃን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባቱ እንኳን አቅቷቸው ሲያሳዝኑን፤ ይኸው በድንበር ሰበብ ህዝብን ለግጭትና ለጦርነት ለመዳረግ ዳር ዳር እያሉ ነው፡፡ ህዝቦች በእኩልነት የሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን ሲሳናቸው፤ ‹‹የመገንጠል መብታችንን ለማስከበር እንታገላለን›› እያሉ ነው፡፡
‹‹ወንድ ልጅ ሲከፋው፤ ውጭ አገር ይመኛል፤
እዚህ ያላደለው፤ እዚያ ምን ያገኛል›› አለ ዘፋኙ፡፡
እነዚህ አፈ ጮሌዎች፤ ‹‹የመገንጠል መብታችንን ለማስከበር እንታገላለን›› ይላሉ፡፡ ግን መገንጠል ህዝቡ የሚመኘውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአስማት አያመጣውም፡፡ መከራችንን ያበዛ እንደሆን እንጂ ሸክማችንን አያቀለውም፡፡ ትንንሽ ሐገር ከመሆን የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ከመዘፈቅና በተገነጠልን ማግስት በድንበር ወይም በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሰበብ ለእልቂት ከመዘጋጀት በቀር ሌላ የምናገኘው ነገር አይኖርም፡፡ በማያባራ ግጭት ተጠምደን ለልማትና ለዴሞክራሲ የሚውል ጊዜ እንኳን አናገኝም፡፡ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ማረጋገጥ ያልቻልነውን በእኩልነት የአብሮ መኖር ብቃት፤ በተገነጠለችው ክልል ውስጥ ማረጋገጥ አይቻለንም፡፡ አስቀድሞም የችግሩ መንስዔ አብሮ መኖር ባለመሆኑ፤ መገንጠል መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደኔ ሐሳብ የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ውይይት ነው፡፡ እዚህ መወያየት ካልቻልን፤ እዚያስ በምን ብቃታችን ተወያይተን ችግሮቻችንን እንፈታለን።  
አዎ፤ የግጭት መብቀያ፣ መራቢያና መፈልፈያ የውይይት አለመኖር ነው፡፡ ውይይት ባለበት ግጭት አይከሰትም፡፡ ይህ ሐሳብ ምናልባት ችግር ያለበት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በደንብ ስናጤነው፤ ‹‹ውይይት ባለበት ግጭት አይከሰትም›› መባሉ በጣም ትክክል ነው፡፡  የማይናወጽ እውነት ነው። ግጭት የሚበቅለው፣ የሚራባውና የሚፈለፈለው ውይይት በሌለበት አካባቢ ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ ሰው የሚያስብ ፍጡር ነው፡፡ ህይወቱንና ንብረቱን የሚያጠፋ ችግር ውስጥ እንዲህ በቀላሉ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ችግር ቢኖርም ነገሩን በውይይት መፍታት የሚችልበት ዕድል ካለ፤ ከጦርነት ውይይትን ይመርጣል፡፡ የተፈጠረበትን ችግር ተናገሮ፤ ሰሚ አግኝቶ ችግሩ ከተፈታለትና ጥቅሙ ከተጠበቀለት ለምን ወደ ግጭት ይገባል፡፡ ምክንያቱም፤ ለሰው ልጅ በሰላምና በህይወት ከመኖር የሚልቅ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ህይወቱ ብቻ አይደለም፡፡ በህይወት ለመኖር የሚያስችሉት ሐብትና ንብረቶቹም እንዲጠበቁለት ይፈልጋል፡፡ በእነዚህ ጥቅሞቹ ላይ አደጋ ሲያንዣብብበት መናገር ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በንግግር የሚያልቅበት ዕድል ምቹ ከሆነና ተናግሮም መፍትሔ ማግኘት ከቻለ ግጭት የሚነሳበት ዕድል ዝግ ይሆናል፡፡  
ታዲያ አንዳንዴ ውይይት የመሰለ ነገር ኖሮ ግጭት ሲነሳ ወይም ሲባባስ እንመለከት ይሆናል፡፡ እንዲያውም አልፎ አልፎ ውይይቱ ችግር የሚያባብስ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ውይይት የመሰለ ነገር ኖሮ ግጭት የሚከሰተው፤ ውይይቱ ነጻነት የሌለበት ሲሆን፤ ወይም ውይይቱ ኃይል ባላቸው ሰዎች ተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ፤ ውይይት የሚባል ነገር ኖሮ ሳለ ግጭት ሊባባስ ይችላል፡፡ ሆኖም ትክክለኛ ውይይት የሚኖረው፤ ትክክለኛ ነጻነት ሲኖር ነው፡፡ ውይይቶች ግጭትን ሊያስወግዱ የማይችሉት ወይም ሊያባብሱ የሚችሉት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ወገኖች በነጻነት መወያየት የሚችሉበት መድረክ በተዘጋ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች በነጻነት መወያየት የሚችሉበት መድረክ ክፍት ሊሆን የሚችለውም ዴሞክራሲ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሌለበት ወይም ባልዳበረበት ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡ በአጭሩ የግጭት ማስወገጃ ብልሃት ውይይት ነው፡፡ ስለዚህ እንወያይ፡፡ የይስሙላ ያልሆነ ነጻ ውይይት ለማድረግ እንችል ዘንድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንፍጠር፡፡  
በመሆኑም ግጭቶችን ሲከሰቱ ወይም ለግጭት የመዳረግ አዝማሚያ ሲታይ፤ ቀድመን መፈተሽ የሚገባን፤ ለውይይት ምቹ የሚሆን ነገር መኖር አለመኖሩን ነው፡፡ ነጻ ውይይት ለማድረግ ያስችለናል ብለን ያጸናነው ስርዓት ካለም በስርዓቱ ውስጥ የተከሰቱ ብልሽቶች  መኖር አለመኖራቸውን መመርመር ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ ህገ መንግስታችን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን አጎናጽፎናል፡፡ ሐሳብን በግልጽ ነጻነት የመግለጽ መብትም መረጃ የመፈለግ፣ የማሰባሰብና የማሰራጨት ጉዳዮች እንደሚያጠቃልል በህገ መንግስታችን ሰፍሯል፡፡ ታዲያ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከተለያዩ ወገኖች እንቅፋቶች ወይም ጫናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ እንቅፋቶቹም ውስጣዊ እና ውጫዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚረጋገጠው በሳንሱር አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ የመብቱ ተጠቃሚ በራሱ ላይ የሚጭነው ማዕቀብም ይኖራል፡፡ ስለዚህ ከሌላ ወገን ከሚመጣና ከራስ ከሚመነጭ ሳንሱር ነጻ መሆንን ይጠይቃል፡፡
ሆኖም የነጻነት ጉዳይ ከሌላ ወገንና ከራስ ከሚመነጭ ሳንሱር ነጻ በመሆን ብቻ አያበቃም። መረጃን በመፈለግ፣ በማሰባሰብና በማሰራጨት ረገድ እንቅፋት ካለ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ እክል ይኖራል፡፡ ስለዚህ መረጃን በመፈለግ፣ በማሰባሰብና በማሰራጨት ረገድ የሚኖር ጫና ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ የሚደርስ ጫና ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ነጻ ውይይት ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህ ዓይነት ምህዳር ውስጥ የሚደረግ ውይይት ግጭትን ሊያባብስ የሚችል ውይይት የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም እውነተኛ ውይይት ሊባል አይችልም፡፡ እንዲህ ያለ ውይይት ግጭትን ሊከላከልም አይችልም፡፡ ስለሆነም፤ ‹‹ግጭት እንዳይኖር ማድረጊያው ብልሃት ውይይት ነው›› ሲባል፤ ነጻ ውይይት ማለት እንጂ፤ ጉልበት ያላቸው ወገኖች፤ የደካሞች ድምጽ በአግባቡ እንዳይሰማ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ የሚደረግ ውይይት አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ ውይይቱ የሚካሄድበት አጠቃላይ አውድም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ዓውድ ስንልም የፖለቲካ ባህልና ታሪክን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡
ቀደም ሲል ነጻነት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ብቻ የሚኖር ሐብት መሆኑን ጠቅሰናል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተቋማዊ ባህርይ ያለው የውይይት መድረክ ፕሬስ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተቋም ያለው ጤንነት የውይይቱን ጤንነት ይወስነዋል። ግጭትን  የማስቀረት ሚናውም በዚህ ተቋም ጤንነት ይወሰናል፡፡ ስለሆነም፤ በውይይት ግጭትን የማስቀረት ተግባር፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን ጉዳይ የሚመለከት ሲሆን፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይም በአብዛኛው ከሚዲያ ነጻነትና የአሰራር ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ውይይት የማድረግ ጉዳይ ከፕሬስ ነጻነት ጋር ይተሳሰራል፡፡ እናም ግጭትን በመከላከል፣ በማስተዳደርና በድህረ-ግጭት (ሰላምን መልሶ በመገንባት) ሁኔታዎች ውስጥ የሚዲያ ሚና ትልቅ ነው፡፡ ሚዲያ የውይይት መኪና በመሆኑ፤ ግጭትን በመከላከል ሂደት የዚህ መኪና አሰራርና የባለሙያዎቹ የሥነ ምግባር ሁኔታ ወሳኝ ነው፡፡
ሆኖም የሚዲያውን ሁኔታ ከማየታችን በፊት፤ የሐገራችን ሚዲያ በምን አውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ መመልከት ይኖርብናል፡፡ የሐገራችን የሐሳብ ወይም የውይይት መኪና በምን ዓውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ የሐገሪቱን ታሪክ ዋነኛ ባህርይ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሐገሪቱን ታሪክ ዋነኛ ባህርይም ግጭት ነው፡፡ በአጠቃላይ የሐገራችን የውይይት መኪና ወይም ሚዲያ ለረጅም ዓመታት በግጭት ውስጥ አልፎ በመጣ ህብረተሰብ ውስጥ የሚሰራ መኪና በመሆኑ፤ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ጠንካራ ባህል በሌለው ህዝብ ውስጥ የሚገኝ መኪና ነው (1) (ባህላዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም)፡፡ እንዲሁም የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል በሌለበት ምህዳር የሚንቀሳቀስ መኪና ነው (2) ለዴሞክራሲ ባህል ተቃራኒ የሆኑ አመለካከቶች በሰፊው በሚታዩበት ማህበራዊ ዐውድ የሚሰራ መኪና ነው (3) ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
ከእኛ ሐገር ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የግጭት ምንጭ የሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምላሽ ሳያገኙ ረጅም ዘመናትን ኖረናል፡፡ በዚህ የተነሳ በማያባራ የግጭት ናዳ ስንታወክ ዘመናትን ገፍተናል፡፡ ከግጭት አዙሪት የሚያወጣ መላ ጠፍቶብን ስንታመስ፣ ምዕተ ዓመታትን ዘልቀናል። ረጅሙ የሐገራችን ታሪክ ዋነኛ ገጽታ ግጭት ሆኖ የሚታየው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ አስጎንብሶ ከሚገዛንና ዘወትር ከሚደቀድቀን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት እግር ሥር መውጣት ተስኖን ቆይተናል፡፡ ለረጅም ዘመናት በግጭት ውስጥ ያለፍን በመሆናችን የተነሳ፤ እንዲሁም የድህነትና የኋላ ቀርነት ቀንበር ተጭኖን ዘመናት በመግፋታችን የተነሳ፤ ተቋማዊ የግጭት መከላከያና መፍቻ ብልሃት ውሉ እየጠፋብን ብዙ ጊዜ ተደናብረናል፡፡
ታዲያ ከዘመናዊነት ግፊት ጋር ነባሩ የግጭት መፍቻ ስርኣት እየተዳከመ ከመሄዱ በተጨማሪ፤ ቢኖርም አገልግሎቱ ከመንደር ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶቹ እንደ ሐገር የሚመጣን ቀውስ ለመከላከል የሚያስችሉ አይደሉም። ያም ሆኖ ጨርሶ ከመጥፋት የጠበቀን ይኸው ባህላዊ ስርዓት በመሆኑ ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ይሁንና በዘመናዊ የኑሮ ይትብሃል ለመሄድ የምንሞክር በመሆኑ፤ ባህላዊው የግጭት መፍቻ ስርዓት አጋዥ ከመሆን ያለፈ ሚና ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ዘመናዊው የግጭት መፍቻ ስርኣት (ዴሞክራሲ) በፍጥነት እየተጠናከረ ካልሄደ፤ ከእንግዲህ የግጭት ተጋላጭነታችን ይበልጥ እየሰፋ ሊሄድ ይችላል፡፡
በተደጋጋሚ በሚያጋጥመን ግጭት የተነሳም ኢኮኖሚያዊ አቅማችን ደካማ እየሆነ መጥቶ፣ በልቶ ለማደር የምንቸገር ህዝቦች ሆነናል፡፡ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፤ በልቶ ለማደር የሚያስችል ሥራ ለመስራት ዕድል ለማግኘት ጭምር ነው፡፡ ድህነቱ የከፋ በሆነ መጠንም፤ ለግጭት የምንዳረግበት ዕድል ሰፊ ይሆናል። የግጭት ጉዳይ የሚያሳስበን በዚህ የተነሳ ነው፡፡
የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን አንድ ቁም ነገርም አለ፡፡ በዓለም የተካሄዱ ትላልቅ ወይም ትናንሽ ግጭቶች ሁሉ ብዙ ደም ካፋሰሱ በኋላ የመጨረሻ ማሳረጊያቸው እርቅ መሆኑን ነው፡፡ የዓለም ታሪክ ይህን ሐቅ ያስገነዝበናል፡፡ የግጭቶች ሁሉ ማሳረጊያ ውይይትና ድርድር ከሆነ፤ ለውይይትና ለድርድር በራችንን ሰፋ አድርገን ግጭትን ማራቅ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ዓይን ያጠፋ፤ ዓይኑ ይጥፋ›› ብለን ከማሰብ መውጣት ይኖርብናል፡፡ ማህተመ ጋንዲ ‹‹ዓይን ያጠፋ፤ ዓይኑ ይጥፋ የሚል መርህ ዓለምን የዓይነ ስውራን መኖሪያ ያደርጋታል›› ይላል፡፡ ዓይንን ያጠፋ -ዓይኑ ይጥፋ በሚል አስተሳሰብ ሄደን፤ ያተረፍነው ነገር በድህነት ዓይኑ የጠፋ ህብረተሰብ መሆን ብቻ ነው፡፡ ድህነት ደግሞ የግጭት መራቢያ ወይም መፈልፈያ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ አስተውሉ፡፡ ቀደም ያለውን የታሪክ ምዕራፍ ትተን፣ ከዘመነ መሣፍንት ጀምረን እንየው፡፡ በዘመነ መሣፍንት በየጎጡ ተከፋፍለን እርስ በእርስ ስንጨራረስ ኖረናል፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም ባለው የታሪክ ምዕራፍ ባሳለፍናቸው 300 ገደማ የሚሆኑ ዓመታት ውስጥ የኖረ እና የ300 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው አግኝተን፤ ቀጭ ብሎ የህይወት ታሪኩን ቢያጫውተን፤ እንደ ሐገር ያለፍነውን መከራ ከባድነት በውል እንረዳው ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በፊት ከወጣትነት ዕድሜ የደረሱ ሰዎች ሁሉ የህይወት ታሪካቸውን ብትጠይቋቸው የምትሰሙት አሳዛኝ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ቀደም ባለው ዘመን፤ በዘመቻ ተወልዶ፣ በአገልግል ታዝሎ፣ በየጊዜው በሚነሳ የእርስ በእርስ ግጭት እየተሰደደ፤ በየቤተ ዘመዱ ተጠግቶ፤ መረጋጋት ባጣ ቤተሰብ ያደገ ልጅ ብዙ ነው።  የታላላቅ ሰዎቻችንን የህይወት ታሪክ ተመልከቱ፡፡ የስደት፣ የመከራ፣ የሰላምና የነጻነት እጦት ያጠወለገው የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ሐገሪቱ በየጊዜው በሚነሳ ማዕበል ክፉኛ የምትናጥ ጀልባን ትመስላለች። እንዲህ ዓይነት ችግር በተደጋጋሚ የሚከሰተው፤ ታሪክ ራሱን ስለሚደግም አይደለም፡፡ ጅሎች ታሪክን ይደግሙታል እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም፡፡
የዘመነ መሣፍንቱ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት፤ ወሬና ትንታኔ የሚያሻው አይደለም፡፡ ዘመኑ ራሱን ለመግለጽ የሚሳነው አይደለም፡፡ የሑከት ዘመን ነው፡፡ ይኽን የታሪክ ምዕራፍ ስንዘጋ የምናገኘው አጤ ቴዎድሮስን ነው፡፡ እርሳቸው እንዲሁ እንደዋተቱ የእንግሊዝ ጦር መጥቶ መቅደላ አምባ ሲወጋቸው ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ተከታዩ አጤ ዮሐንስ ናቸው። ለጦርነት ጉራዕ-ጉንደት-አንቺም- መተማ ወዘተ እየዋተቱ፤ አንድ ቀን እንኳን ሳያርፉ ከዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ተከታዩ አጤ ምኒልክ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በጦር ሜዳ አድገው፣ በጦር ሜዳ ጎልምሰው፣ በጦር ሜዳ አርጅተው፤ በመጨረሻ መረጋጋት ያጣ መንግስት ትተው አረፉ፡፡ በዚህ ሁሉ የታሪክ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት አላገኙም፡፡
ምናልባት፤ ታሪኩን በፖለቲካ መነጽር የሚመለከት ሰው፤ ሊነቅሰው የሚችለው ችግር መኖሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ አጤ ምኒልክ ወደ ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ የኢትዮጵያ ግዛት ሲሄዱ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ሽፍታ ያስመረረው ነጋዴ፤ ጎሮዶማን ያስቸገረው አርሶ አደር፤ የአስተዳደሩን ባህርይ ተወት አድርጎ፤ ህግ የሚያስከብር አንድ ኃይለኛ መምጣቱን እንደ ሰላም አዋጅ ይመለከተው ነበር፡፡ ከዝርፊያና ከውንብድና ግፍ የተገላገለው አርሦ አደርና የሲራራ ነጋዴ፤ የአጤ ምኒልክን መምጣት በደስታ የሚመለከትበት ሁኔታ ነበር፡፡
በአጭሩ ከአድዋ እስከ ወልወል ባለው ዘመን፤ ሐገሪቱ ከጦርነት ትንሽ ፋታ ብታገኝም፤ የረባ ነገር ሳይሰራ ጊዜው አለፈ፡፡ ሐገሪቱ በሥልጣን ሽኩቻ ትታመስ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው የሐገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው እንደ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ያሉ ምሁራን፤ መልካም አስተዳደር ሳይሆን የማይረባ አስተዳደር እንኳን ማጽናት አለመቻላችን አሳስቧቸው ይጨነቁ ነበር፡፡ ሐገር የሚለማው በትምህርት በመሆኑ፤ ትምህርት እንዲስፋፋና ስርዓት እንዲጸና ብዙ ወትውተዋል፡፡ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ሐገሪቱን የማዘመን ሥራ ቢጀመርም፤ የተደላደለ ስርዓት መትከል አለመቻሉን እያዩ በጸጸት ይብከነከኑ ነበር፡፡ ሐገሪቱ በውስጥ ችግር እና በዙሪያዋ በሚያንዣብቡ ቅኝ ገዢዎች ሴራ ተወጥራ እያቃሰተች ሳለ፤ ምኒልክ አረፉ፡፡ በእቴጌ ጣይቱ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግስት ዘውዲቱ እና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ደጋፊዎች ሴራና ሽኩቻ የሚታመሰው መንግስት የረባ ሥራ ለመስራት የሚችል አልነበረም፡፡ ሽኩቻው በአጤ ኃይለስላሤ አሸናፊነት ተደምድሞ ስለ ትምህርትና አስተዳደር ማሰብ እንደ ተጀመረ የአድዋን ቂም በመበቀል ስሜት የሚገፋው የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል መጥቶ፤ የሀገር ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ የተማሩ ወጣቶችን ለቅሞ በማጥፋት፤ ሐገሪቱን ክፉኛ አመሳቅሎ፤ ህዝቡንም ጨፍጭፎ ሄደ፡፡
ባለፉት 300 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም ፋታ አላገኘም፡፡ ለጊዜው የሥርዓቱን ባህርይ ወደ ጎን አድርገን፤ ከፋም ለማም ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጀምሮ፤ የተወሰኑ ልጆች ተምረው ለሐገራቸው መስራት ከሚችሉበት ዕድሜ ሲደርሱ፤ ለዕድገት እርሾ የሚሆን ነገር ሳይሠሩ በግጭትና ጦርነት ለሞት ይዳረጉ ነበር። በመጨረሻም፤ ዘውዳዊው አገዛዝ አርጅቶና በስብሶ ሲገረሰስ የተፈጠረው የተስፋ ጭላንጭል በተመሳሳይ ሁኔታ ድርግም አለ፡፡ የተስፋው መዝሙር ወደ ሙሾ ተቀረ፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነቱም ተባብሶ ቀጠለ፡፡
የ1960ዎቹ ኢትዮጵያ የታላቋ ሶማሊያ ቅዠት በነበረው ዚያድ ባሬ መጠነ ሰፊ ወረራና ለ30 ዓመታት በዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ ሞት አፋፍ ተገፋች፡፡ ይህ ሂደት መቋጫ ያገኘው በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ከስልጣን ተወግዶ፤ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲጸና ነው፡፡ ይህን የሚታወቅ ታሪክ የማነሳው ለአጽንዖት እንጂ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማስተማር አይደለም፡፡ የመጣንበት ጎዳና ምን ያህል አስከፊ መሆኑንና ሐገሪቱ ወደ ግጭት እንዳትገባ በብዙ መጠንቀቅ እንዳለብን ለማሳሳብ ነው፡፡ እንዲሁም የሐገራችን ሚዲያ በምን ዓይነት አውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ለማመልከትና ሐገሪቱ እንዲህ ፋታ በሌለው የግጭት ወይም የጦርነት አዙሪት ውስጥ እየተዘፈቀች የምትቀጥል ከሆነ፤ እንደ ሐገር ከስህተታችን እየተማርን፤ የጎደለውን እየሞላን፤ የተጣመመውን እያረቅን፤ የታሰበበት የልማት ዕቅድ መንደፍ ወይም መተግበር እንደማንችል ለማስታወስ ነው፡፡
የሐገር ዕድገትን አስቦ፣ ህጻናትን በትምህርት ኮትኩቶ አሳድጎ፤ በየመስኩ በማሰማራት የህዝቡን ህይወት የሚቀይር ሥራ ለመሥራት፤ ቢያንስ ከ30 ዓመታት የማያንስ የተቀናጀ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ እንደሚታወቀው፤ ሐገራችን ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ዘርግታ ልጆችዋን ማሰልጠን ከጀመረች ከአንድ ምዕተ ዓመት የበለጠ ዘመን መቁጠር አይቻልም፡፡ በዚህ አንድ ምዕተ ዓመት ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት ለመቅሰም የቻሉት ወጣቶች፤ ቀደም ሲል በኢጣሊያ ወራሪ ጦር፤ በኋላም በአፋኙ ወታደራዊ መንግስት ተገድለዋል፡፡ የቀሩትም ሐገራቸውን ጥለው በገፍ ተሰድደዋል፡፡ ሌሎቹም አፋኙን አገዛዝ ለመታገል ጠብመንጃ አንስተው ሜዳ ወጥተዋል፡፡ 30 ዓመታት በፈጀ የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙ የሐገር ሐብትና ውድ ጊዜ ባክኖ ቀርቷል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዕድገት ሊታሰብ አይችልም፡፡
እንግዲህ ያለፉትን 300 ገደማ ዓመታት ያሳለፍነው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው ሐገራችን ከጦርነት አንጻራዊ ፋታ ያገኘችው ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመኙ ዜጎች ሁሉ፤ የመጀመሪያ ሥራቸው ሊያደርጉት የሚገባቸው ጉዳይ ሐገሪቱ ወደ ግጭት የምትገባበትን በሮች ሁሉ ዝግ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ወደ ሌላ ቀውስ መግባት ችግሮቻችን ይበልጥ እየተወሳሰቡ እንዲሄዱና ሊታረሙ የማይችሉ ስህተቶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ግጭቶች በዚህ ዓይነት የምልከታ አንጻር መመርመር ይኖርብናል፡፡ ታዲያ በዚህ ዓይነት አውድ ውስጥ የሚሰራ ሚዲያ ወይም የውይይት መኪና ሊኖረው የሚገባው ሚና ምን መሆን አለበት? ይህን ጉዳይ በሌላ ራሱ የቻለ ክፍል እመለከተዋለሁ፡፡

Read 2219 times