Saturday, 03 November 2018 15:55

ከ18ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በፊት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


      ከ530 ሺ በላይ ተሳታፊዎች፤ ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ፤ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ የሽልማት ገንዘብ፤
      ከ4200 በላይ ተሳታፊዎች ከውጭ አገራት፤ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ለበጎ አድራጎት የተሰበሰ


 1. በ2011 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ኤርትራዊው ምርጥ የረጅም ርቀት አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ በክብር እንግድነት ተጋብዟል።  በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው ኡጋንዳዊው ስቲቨን ኪፕሮቲችም ሌላው የክብር እንግዳ ነው፡፡
 2. በሁለቱም ፆታዎች ከ500 በላይ እውቅና ፕሮፌሽናል አትሌቶችን በሚያሳትፈው ዋና ውድድር ላይ ለመፎካከር ከኬንያ፤ ከኡጋንዳ፤ ከኤርትራ  እና ከሌሎችም አገሮች መጥተዋል፡፡
 3. ባለፉት 18 ዓመታት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተዘጋጁ ውድድሮች ብዛት  ከ120 በላይ ይሆናሉ።
 4. በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው የተሳታፊዎች ብዛት ከግማሽ ቢሊዮን አልፏል፡፡ በ18ቱ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች የተሳተፉት ከ530ሺ በላይ ሆነዋል፡፡
 5. 18 የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ለማዘጋጀት ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆኗል፡፡
 6. የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ከ18 ዓመታት በፊት ሲጀመር 10ሺ ተወዳዳሪዎች በማሳተፍ  ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ  የተሳታፊዎቹ ቁጥር ወደ 18ሺ፤ 25 ሺ፤ 35 ሺ ፤ 38ሺ፤   40ሺ ፤  42ሺ ከሆነ በኋላ አምና እና ዘንደሮ 44ሺ ሆኗል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች የተሳትፎ ፍላጎት ከ100ሺ እንደሚያልፍ ያውቃሉ፡፡ ውድድሩን በተሳካ እና በተደራጀ ሁኔታ ለማስተናገድ ሲባል በ44ሺ ተሳታፊዎች ላይ ረግተዋል፡፡
 7. ዘንድሮ በውድድሩ የሁለት ቀናት ክንውን በድምሩ የሚሳተፉት 48ሺ ናቸው፡፡ 3500 በፕላን ኢትዮጵያ የህፃናት ውድድር የሚሳተፉ፤ በዋናው ውድድር 500 ፕሮፌሽናል አትሌቶች እና 44ሺ ስፖርተኞች ናቸው፡፡ በአምባሳደሮች ውድድር የ16 የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፤ በዊልቼር ሽቅድምድም ከ25 በላይ ተወዳዳሪዎች፤ 500 የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች እንዲሁም ከ30 በላይ ታዋቂ ሰዎች እና አርቲስቶች ‹‹ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ›› በሚለው ዓላማ የሚሮጡ ናቸው፡፡
 8. ባለፉት 18 ዓመታት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተዘጋጁ ውድድሮች ላይ ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ የሽልማት ገንዘብ ተበርክቷል፡፡ ዘንድሮ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚያሸንፉም ከ400ሺ ብር በላይ ለሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡
 9. የጎዳና ላይ ሩጫው በሁለት ምድብ በተካፋፈለ አዲስ አሯሯጥ መካሄዱን ይቀጥላል፡፡ የመጀመርያዎቹ በቀይ መነሻ የሚሮጡትና ከ1 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 10 ኪሎ ሜትሩን የሚጨርሱ ሲሆኑ ብዛታቸው 7000 ነው።  በሌላ በኩል በሁለተኛው ምድብ በአረንጓዴ መነሻ ለመሮጥ 37ሺ ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ሲሆን  ውድድሩን ለመጨረስ ከ1 ሰአት በላይ ጊዜ የሚወስድባቸው፤ በፌስቲቫል መልኩ የተለያዩ ትርኢቶችን እያሳዩና እየተዝናኑ የሚሮጡ ናቸው።
 10. የኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ በሱፐር ስፖርት፤ ፋና ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ቃና ቲቪ ሳምንታዊው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ካፒታል እና ሌሎች ከውድድሩ ጋር በተለያየ መንገድ የሚሰሩ የሚዲያ አጋሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኢቢሲ ለውድድሩ  የቀጥታ ሽርጭት ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን ዘንድሮ የዲኤስቲቪው ሱፕር ስፖርት በ52 ደቂቃዎች ልዩ የዘገባ ሽፋን ይሰጠዋል፡፡
 11. በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ላይ ለመሳተፍ ከ25 የተለያዩ አገራት ከ500 በላይ ስፖርተኞች መጥተዋል፡፡  ይህም ባለፉት 18 ዓመታት በውድድሩ ላይ የተሳተፉትን የውጭ እንግዶች ብዛት ከ4200 በላይ ያደርገዋል፡፡
 12. በአሁኑ ወቅት በዓለማችን መሮጥ አለባቸው ከተባሉ 10 የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች  አንዱ ሲሆን የአፍሪካ ግዙፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ተብሎም ይጠቀሳል፡፡ አንድ ቀለም ማልያ በሚለብሱ ተሳታፊዎቹ የአፍሪካ አስደናቂው የአትሌቲክስ መድረክም ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በ2005 እኤአ ላይ የዓለም አቀፉ የማራቶንና የረጅም ርቀት ሩጫዎች ማህበር AIMS   አባል ሲሆን ማህበሩ በ90 አገራት 300 መሰል የሩጫ ውድድሮችን ያሰባሰበ ነው፡፡ በ2013 እኤአ ላይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሚያዘጋጃችው ውድድሮች የሚሊኒዬሙን የልማት ግቦች ለማሳካት ባደረገው አስተዋፅኦ የAIMS የማህበረሰብ አገልግሎት ልዩ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫው ከውድድሩ አያይዞ በሚያነግባቸው መርሆችም ተሳክቶለታል፡፡
 13. በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ10 በላይ የኦሎምፒክ ወይም የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች ውጤታማ ሆነዋል፡፡  በዋናው የአትሌቶች ውድድር በወንዶች ምድብ የመጀመርያው አሸናፊ የውድድሩ የበላይ ጠባቂና መስራች ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሴቶች ምድብ ብርሃኔ አደሬ ነበረች፡፡ በ2ኛው በወንዶች ምድብ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም በሴቶች ወርቅነሽ ኪዳኔ ፤ በ3ኛው በወንዶች ምድብ ስለሺ ስህን በሴቶች ምድብ  ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ7ኛው ማራቶኒስቱ ፀጋዬ ከበደ ከውድድሩ አሸናፊ ታላላቅ አትሌቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ምርጥ የማራቶን ሯጮች መካከል በሴቶች አበሩ ከበደ፤ ድሬ ቱኔ እና ጠይባ ኢርኬሶ እንዲሁም በወንዶች ቻላ ደቻሳ እና ጌቱ ፈለቀ  እንዲሁም የዳመንድ ሊጉ አሸናፊ ሃጎስ ገብረህይወት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪካቸው ወደ ስኬት ለመውጣት ከቻሉት አትሌቶች ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ምድብ በ7ኛ፤ በ8ኛው እና በ14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች በማሸነፍ አትሌት ውዴ አያሌው በታላቁ ሩጫ ልዩ  የድል ሃትሪክ በመስራት ትጠቀሳለች፡፡
 14. በየጊዜው ታላላቅ የክብር እንግዶችን ከውጭ እና ከአገር ውስጥ በማሳተፍም የጎዳና ላይ ሩጫው ስኬታማ  ሆኖ ቆይቷል፡፡  ከ2 ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ3ሺ መሰናል የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችውና በቻይና የናይኪ ክለብ ፕሬዝዳንት የሆነችው የቻይናዋ አትሌት ዢን ዋን እና ታዋቂው የረጅም ርቀት ፤ የማራቶን ሯጭ የሆነው የደቡብ አፍሪካው ሄንድሪክ ራማላ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ በሌሎቹ ታላቁ ሩጫዎችም ፖል ቴርጋት፤ ገብሬላ ዛቦ፤ ካሮሊና ክሉፍት፤ ዴቭ ሞርክሩፍት፤ፓውላ ራድክሊፍ፤ የኒውዮርክ ማራቶን ዲያሬክተር ሜሪ ዊተንበርግ፤ የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት፤ የኬንያዎቹ አትሌቶች  ካተሪን ንድሬባ፤ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ሌሎች የኢትዮጵያ ምርጥ ታላላቅ አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡
 15. ከ10 በላይ ታዋቂ የዓለም አትሌቲክስ ማናጀሮች በ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የሚሰማሩ ሲሆን ዋናው ምክንያት አዳዲስ አትሌቶች ለመመልመል የሚጠቀሙበት አመቺ መድረክ ስለሆነ ነው፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫ የሚመዘገብ ውጤትና ሰዓት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ያስችላል፡፡
  16. ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከአጋር ስፖንሰሮችና ከባለድርሻ አካላትም ጋር በመስራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ እንደቶታል፤ ቶዮታ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አብይ ስፖንሰሮች ሆነው ከሰሩት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያዩ ቁሳቁሶች አቅርቦት፤ በመስተንግዶ እና ሌሎች ተግባራትን በአጋርነት የሚሰሩት ከ50 በላይ ድርጅቶች ሲሆኑ ውድድሩ  በየዓመቱ ከ15 በላይ የተለያዩ ስፖንሰሮችን በአጋርነት የሚያሰባብም ነው፡፡
  17. በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስር ውድድሮችን በማዘጋጀት በሚሰራው ቡድን፤ የሚያስተናግዱ፤ ፅዳት የሚያከናውኑ፤ የሚያስተባብሩና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ብዛት ከ850 በላይ ነው፡፡ በመሮጫው ጎዳናዎች 10 ዲጄዎች እና  የሙዚቃ ባንዶች የሚሰማሩ ሲሆን፤ ሁለት የሻወር እና አንድ የውሃ ጣቢያዎች እንደሚዘጋጁ እና በውድድሩ መነሻ 3ሺ ፊኛዎች ወደ ሰማይ እንደሚለቀቁ ታውቋል፡፡
  18. ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ውድድር ጋር በተያያዘ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡

Read 2135 times