Monday, 05 November 2018 00:00

ፌስቡክ በ3 ወራት 13.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 2.6 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች፣ 33 ሺህ 606 ሰራተኞች አሉት


     ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው መስከረም በነበሩት ያለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ13.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በየዕለቱ የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ቁጥርም 1.49 ቢሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡
የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረጉት መረጃ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ፣ ዋትዛፕ፣ ኢንስታግራምና ሜሴንጀር የተሰኙትን የኩባንያው አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ወርሃዊ ደንበኞች ቁጥር ከ2.6 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡
ፌስቡክ ባለፉት ሶስት ወራት ካገኘው ገቢ 92 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው ከሞባይል ስልኮች ማስታወቂያዎች ያገኘው ገቢ መሆኑን የጠቆሙት ዙክበርግ፣ ኩባንያው ከዚህ ማስታወቂያ 12.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በፌስቡክ የተለያዩ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ ኩባንያዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አስረድተዋል፡፡
በየዕለቱ በፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ሜሴንጀር አማካይነት 100 ቢሊዮን ያህል የጽሁፍና የምስል መልዕክቶች እንደሚላኩ የተነገረ ሲሆን፣ ከ90 ሚሊዮን በላይ ኩባንያዎችም የፌስቡክ ገጾችን ከፍተው ራሳቸውን እያስተዋወቁና ስራዎቻቸውን እያቀላጠፉ እንደሚገኙ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በተጀመረው የፌስቡክ የክፍት የስራ ቦታ ማመልከቻ አፕሊኬሽን አማካይነት በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ ለመቀጠር የቻሉ ደንበኞች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፌስቡክ የሰራተኞቹን ቁጥር 33 ሺህ 606 ማድረሱንንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1227 times