Saturday, 03 November 2018 16:10

ሉፍታንዛ ከአዲስ አበባ ወደ ፍራንክፈርት ቀጥታ በረራ ጀመረ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በጀርመንና በኢትዮጵያ የተደረገው በረራ 50ኛ ዓመት ይከበራል


    የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ፤ ከአዲስ አበባ ወደ ፍራንክፈርት ቀጥታ በረራ የጀመረ ሲሆን በሳምንት 5 ቀናት ወደ አውሮፓ በረራ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተሻሻለው አዲሱ የቀጥታ በረራ፣ አውሮፕላኑ፣ ጂዳ ላይ ሲያርፍ ይባክን የነበረውን የ2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በማስቀረቱ ወደ አውሮፓ የሚደረገው የበረራ ጉዞ ወደ 6 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ዝቅ ማለቱን አስታውቀዋል፡፡
የባለ 5 ኮከቡ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ዘመናዊ ኤርባስ 340-300 የተለያዩ የምቾት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ 30 ቢዝነስ ክላስ፣ 25 ፕሪሚየም ኢኮኖሚና 221 ኢኮኖሚ ክላስ መቀመጫዎች አሉት፡፡ አውሮፕላኑ በዘመናዊ መሳሪያዎች የተዋቀረና ለተጓዦች ተስማሚ ዲዛይን ያለው ነው ተብሏል፡፡ ለፕሪሚየም ኢኮኖሚ ተጓዦች የተለየ ክፍል ከምቹ ወንበሮች ጋር ያለው አውሮፕላኑ፤ ከኢኮኖሚ ክላስ አንፃር በቦታ ስፋት 50 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ሉፍታንዛና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትብብር ለመሥራት ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ደንበኞች የበረራ ትኬታቸውን እስከ 12 ሳምንታዊ በረራዎች መጠቀም ይችላሉ ያሉት የሉፍታንዛ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋና ሥራ አስኪያጅና የሽያጭ ኃላፊ ሚ/ር ቶቢያስ ኧርነስት፤ መንገደኞች ለተለያዩ በረራዎች ማዕከል ወደ ሆነችው፣ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ከ180 በላይ የበረራ መስመሮች ወዳላት ፍራንክፈርት ከተማ ምቾታቸው ተጠብቆ የቀጥታ በረራ አገልግሎት መስጠት በመጀመራችን የላቀ ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ፍራንክፈርት ለሚጓዙ ደንበኞች አሁን ያለው የበረራ ጊዜ በማጠሩ የቀጥታ በረራው ለእነሱ ምቹ በሆኑ የበረራ መርሐግብሮች ወደ መላው አውሮፓና ወደ ሰሜን አትላንቲክ መዳረሻዎች መጓዝ ያስችላቸዋል ያሉት ሚ/ር ኧርነስት፤ ከፍራንክፈርት ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞችም በበረራው ለመጠቀም በቂ ጊዜ አላቸው፤ ከማክሰኞና ከእሁድ በስተቀር በየዕለቱ ከምሽቱ 5፡45 በረራ ይደረጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
 ሉፍታንዛና ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ አላቸው፤ ሉፍታንዛ ሲኖራቸው ወደ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በረራ ያደረገው እ.ኤ.አ ግንቦት 1969 ዓ.ምነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁና የሽያጭ ኃላፊው፤ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር በጀርመንና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው በረራ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል፡፡
ከሉፍታንዛ አየር መንገድ ባገኘነው መረጃ መሠረት፤ የሉፍታንዛ ግሩፕ አየር መንገድ አውሮፕላኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአራት ክፍለ አኅጉራት፣ በ105 አገሮች፣ በ271 መዳረሻዎች በየሳምንቱ 11ሺ 111 በረራ ያደርጋሉ፡፡

Read 2042 times