Saturday, 03 November 2018 16:11

የትዕቢት ደቀ መዝሙር፥ ኒቼ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(2 votes)

 ፍሬድሪክ ኒቼ አወዛጋቢ ከሆኑት ፈላስፎች መካከል የሚመደብ ነው። ሁሉንም የማፈራረስ አባዜ ብቻ ሳይሆን እራስንም የማፍረስ ልክፍት የተጠናወተው ነው። ቋሚ፣ ነባራዊ፣ ዘመን የማይሽረው የሚባል ጉዳይ ለኒቼ ትርጉም ያለው አይመስልም፡፡  
ምናልባትም ለኒቼ ትርጉም ያለው ትምህርት የሚባለው ከቅድመ ሶቅራጥስ ፈላስፎች አንዱ የነበረው ሔራክሊተስ የተባለው ፈላስፋ የሚያቀነቅነው “ሁሉም ነገር መቆሚያ በሌለው ለውጥ ውስጥ ነው…” የሚል ትምህርት ነው፡፡ “አንድን ወንዝ ሁለቴ መሻገር አንችልም” ይለናል ሔራክሊተስ፤ ምክንያቱም ተመልሰን ስንመጣ ውሃው ይለወጣልና። እንዲህ አይነት ቅርጽ የሌላቸው ለውጦች በኒቼ የፍልስፍና ድርሳናት ውስጥ እንደ “ከብት የዋለበት ማሳ” የፍልስፍና ፍሬ፣ ሃሳቡን አተረማምሰውት እናገኛቸዋለን። ‹‹ሁሉም ነገር በቋሚ ለውጥ ውስጥ ነው›› በሚለው ጥቅሱ የሚታወቀው የቅድመ ሶቅራጥስ ፈላስፋው ሔራክሊተስ፤ የማይለወጥ ነገር ቢኖር ለውጥ እራሱ ብቻ ነው የሚለን ይመስላል፡፡
ከሉተራዊያን ቤተሰቦች በጀርመን ሃገር፣ ሮክን ከተማ እንደተወለደ በልጅነቱ አባቱ ስለሞቱበት በእናቱ፣ በእህቱና በአክስቱ ተከብቦ እንዳደገ ይነገራል - ኒቼ። በፊሎሎጂ ትምህርቱ ጀት ተማሪ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በሃያኛ ዓመት አጋማሽ እድሜው ላይ በባዜል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ሆኖ ይሰራ ነበር። “The Birth of Tragedy” የተሰኘው የመጀመሪያ ስራው የተጠበቀውን ያህል አድናቆት አላስገኘለትም፤እንደውም የሰሉ ትችቶች ተሰንዝረውበታል፡፡ የእነ አኪለስንና ሶፎክልስን ድራማዎች ተራራ ላይ ይሰቅልና የአፍላጦንን ስራዎች ግን እመቀመቅ ቀብሮ፤ በእነዚህ ስራዎች የግሪክን መነሳትና መንኮታኮት እያነጻጸረ ይነግረናል - በ”Birth  of Tragedy” ስራው። መርህ ያለው በስነ አመክንዮ የተቀነበበ የአስተሳሰብ መስመር በእነ አፍላጦን አማካኝነት ስትጀምር፣ ግሪክ መንኮታኮት እንደ ጀመረች ለኒቼ ብቻ ይገለጥለታል።
ከፈላስፎች ሁሉ ኒቼን የሚለየው ግልጽና ቀላል በሆነ ቋንቋ እየተጠቀመ፣ የፍልስፍና ስራውን ማቅረቡ ነው፡፡ በተለይም ከእነ ካንት ጋር ስናነጻጽረው፣ ምን ያህል ሐሳቡን በቀላል መንገድ ለማቅረብ እንደተጋ እናስተውላለን። ካንት በጀርመንኛ እየጻፈ አንባቢዎቹ ጀርመኖች እራሳቸው ጀርመንኛውን መረዳት ተስኗቸው፤ ‹‹ይህ ሰው ለምን በጀርመንኛ አይጽፍልንም›› እያሉ ይሳለቁበት እንደነበር ይነገራል። በቋንቋ የተካነውን ኒቼ ሥራዎች ስናነብ ግን ፍልስፍና የምናነብ ላይመስለን ይችላል፤ ድርሰት እንደምናነብ እስኪሰማን ድረስ ከገጽ ወደ ገጽ ስንሻገር እንኳ ልብ አንለውም። እንደ እኛው ዳኛቸው ወርቁ፤ ቀበሌኛና ጠጣር ቃላትን ሳያበዛ በመጻፍ፣ የቃላት መፍቻ መጽሐፍ አስር ጊዜ ከመጎተት አድኖናል - ኒቼ።
“The Birth of Tragedy” የተሰኘው የኒቼ ስራ ሁለት ዋና ማጠንጠኛዎች አሉት። የማህበረሰብና ባህልን ምንነት መመርመር እንዲሁም የምዕራባዊያን ፍልስፍናዊ ነገረ መለኮትን መመርመር ነው፡፡ እዚህ ዓለም ላይ መኖር ይገባናል ወይስ አይገባንም? ባህል ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው? ባህል ምንድን ነው? በምን እና በምን ሁኔታዎች ባህል ይለመልማል? በምን ሁኔታዎችስ ይከስማል? እዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጅ እንዴት እንደመጣና  ምን እንደሚሰራ --- ኒቼ ይፈላሰፋል። ይህቺ ዓለም በእርግጥ ለሰው ልጅ የምትሆን ከሆነ፣ በተድላና በደስታ እንዴት እንደሚኖርባት ቀመር ያወጣል። የሰው ልጅ ባህል ወግና ልማድ ይኑረው ወይስ  እርቃኑን እንደተፈጠረ፣ አኗኗሩም እርቃኑን ይሁን?… ኒቼ ጭንቅላት ውስጥ ተፍ ተፍ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የመጽሐፉ ክፍል፤ እነዚህንና ተዛማጅ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚመራመርበት ነው።
ከሁሉም ጥንታዊያን ባህሎች ለኒቼ የሚመስጠው የግሪካዊያን ባህል ነው። የአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን አቲክ ትራጀዲ (Attic tragedy) ምርጥ የባህል ወኪል ነው- ለኒቼ፡፡ ዳንስን ሙዚቃን፣ ግጥምን ያካተተ ዝግጅት ነው - አቲክ ትራጀዲ። ነገር ግን በዚያ ዘመን ስላልኖረ ትክክለኛውን የአቲክ ትራጀዲ ገጽታ መረዳቱን ለማወቅ ያዳግታል። በእርሱ ዘመን የነበረውን የዋግነር ሙዚቃዊ ድራማዎችን እንደ ማሳያነት ተጠቅሞባቸዋል። ከዳንሱ፣ ከሙዚቃውና ከስነ ግጥሙ ውስጥ የሰውን ልጅ ምንነትና የዚህን አለም የአኗኗር ስልቱን ቀመር በረጃጅም ፎርሙላዎች በኒቼ ጭንቅላት ስሌት ውስጥ ይገባሉ፤ ከዚያም መልሶቹን ያሰምራል።
በአዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች ግራ ተጋብታ የነበረችውን የኒቼ ዘመኗን አውሮጳን ከኒቼ የእለት ተእለት እንቅስቃሴና የሌሊት ቅዠትና ህልም በቀላሉ ልናላቅቃት አንችልም። ኒቼ ዘመናዊነትና ሳይንስ ያናበዘውን ይህንን ዘመናዊ ማህበረሰብ እንዴት ከበሽታው እንፈውሰው ብሎ በ”በርዝ ኦፍ ትራጀዲ” የሚጠይቀው ኒቼ፤ በቀላሉም መልስ ይሰጣል፡፡ በዋግነር ሙዚቃዊ ድራማ መሰረት ላይ አዲስ ትራጂክ ባህል መመስረት ይኖርብናል የሚለው ፈላስፋው፤ በወጣትነት ዘመኑ ከፍተኛ የዋግነር አድናቂና አፍቃሪ እንደነበር ይነገራል።
የሳይንስ ግኝቶች በአውሮጳ እለታዊ ህይወት ውስጥ ጉልህ ተጽዕኖ መፍጠር የጀመሩበት ዘመን ነበርና ማህበረሰቡ ከተለምዷዊው ባህልና ሃይማኖት በአያሌው አፈንግጦ ነበር። የተለመደውን የባህልና የሃይማኖት እሴቶችን የሚተካለት ሳይንሳዊ መላምት ባለመሟላቱ ግን ህብረተሰቡ አኗኗር ላይ ከፍተኛ ክፍተት ሊፈጥር ችሏል፡፡ ይህንን ነው ኒቼ በ“በርዝ ኦፍ ትራጀዲ” ድርሰቱ ሊያክመው የሚጥረው፡፡ ሳይንስ በዘመኑ የተሟላ ትንታኔና ሃልዮት ለሰው ልጅ ማቅረብ ቢሳነውም፣ በየጊዜው የሚገኙ የታላላቅ ሳይንቲስቶች ግኝቶች ግን የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ከማተረማመስ አልታቀቡም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ  ማህበረሰቡ ከሃይማኖቱ፣ ከባህሉና ከኑሮው ጋር ግጭቶችን ፈጥሮ ነበር። ጋሼ ኒቼ የነብይነት መንፈስ ያድርባቸውና  ይህንን ማህበረሰብ ሊታደጉት “በርዝ ኦፍ ትራጀዲ” የሚባል ቅዱስ መጽሐፍ አማልክት እንዳጻፏቸው በማሰብ ለህዝቡ እነሆ ይሉታል።
ከ“በርዝ ኦፍ ትራጀዲ” ውስጥ ሦስት ዋና ዋና አመክንዮችን ማንሳት እንችላለን። አንደኛው የትራጀዲን መነሻ የዘረዘረበት ክፍል ሲሆን በዚህም ውስጥ የግሪክ አማልክት የነበሩትን ሁለቱን አፖሎንና ዲያኖዥን ሥያሜዎች በመጠቀም፣ የትራጀዲን መነሻነት በሁለቱ ኃይላት መካከል በሚፈጠር ፍትጊያ የሚከሰቱ ሃይሎችንና መርሆችን ይተነትናል። አፖሎ ስለ ብጽዕና፣ ቅድስና እና ግለኝነት (እራስን፣ አቅምን፣ ልክን ስለማወቅ) የሚጨነቅ አይነት መመሪያ አለው። ስለ ስነምግባር፤ እራስን ስለ መግዛትና ታጋሽነትን የሚያስተምርም ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ዲያኖዥ፤ ለከትን ስለ ማለፍ፣ እንዳሻን ስለ መሆን፣ እራስን አለመቆጣጠር፤ እንደው ባጠቃላይ አጉራው ጠናኝ፣ ቡራ ከረዩ ስለ ማለት የሚያስተምር የትራጀዲ ዘርፍ ነው ይለናል፤ ኒቼ።  
ከባህልና ከሃይማኖት ተነጥሎ ለሚናብዘው የአውሮጳ ማህበረሰብ ደንበኛ ፈውስ የሚሆኑት የአፖሎና ዲያኖዥ ቅልቅል የሆነ የፈጠራ ጥበብ ነው ሲልም ይደመድማል። ዳንሱ፣ ጭፈራው፣ ቀረርቶው፣ ስካሩ ባንድ ወገንና በሌላ በኩል ወገኛነቱ፣ ጨዋነቱ፣ ኩሩነቱ፣ ክብር ጠባቂነቱ ተቀላቅለው ባንድ መድረክ ላይ ሲከወኑ ፈውስን ይሰጣሉ። በሁለቱ መካከል ያለውን የኃይል መሳሳብና ፍትጊያ ወደ ውጤታማ ክንውን ብንለውጠው፣ ይህ ባህሉ ሃይማኖቱ የጠፋበት፤ ዘመናዊነትና ሳይንስ ያናበዙት ያውሮጳ ትውልድ ይታከማል፤ ይድናል -ባይ ነው ኒቼ። ጥንታዊያን ግሪካዊያንም እንዲህ ሁለቱን እያጣመሩና እያጣጣሙ ነው ከዚህ ዓለም ጭንቀት እራሳቸውን ፈውሰው የኖሩት። ትራጀዲ ትልቅ የህይወት መጽናኛ ነው፤ የሰው ልጅ ትርጉም ላጣለት የዚህ ዓለም ኑሮ፣ የትራጀዲ ድራማዊ ትርጉም እየሰጠ ይጽናናል።
በ“በርዝ ኦፍ ትራጀዲ” ሁለተኛው ክፍል ውስጥ ደግሞ ይህ መጣጣምና ጥምረት እንዴት እንደ ደፈረሰ ይነግረናል፤ ዋናው አደፍራሽ ደግሞ ሶቅራጥስ ነው። ሶቅራጥስ እንደ ዲያኖዥያን ዘላለማዊ መጽናናትን አላስገኘልን አሊያም እንደ አፖሎ እራስን ስለ መጠበቅ አላቀነቀነልን፤ እንደው ዝም ብሎ ስለ አመክንዮና ምክንያታዊ ህይወት እያወራ፣ የማይጨበጥ ጥቅል ሃሳብና ሃልዮት ላይ የተመሰረተ እውቀትን አቀንቅኖ ትራጀዲውን አጠፋው። ምክንያቱም ትራጀዲ ምንም እንኳን ብታጽናናንም ኑሮን እንድንገፋ ብታንበረክከንም፣ በዲያኖዥና በአፖሎ ውህደትና ቅንብር የተፈጠረው ትራጀዲ አጥንቱ ያልጠነከረ፣ አናቱ ያልጠና ቅንጅት ነውና በቀላሉ ሊታወክ ይችላል።
በዚህ ወበከንቱ ዓለም ስለ ጥበብ፣ ምክንያትና አመክንዮ መጨነቅ ጥቅም አልባ ነውና፤ ለማይረባ ህይወት ከመጨነቅ ይልቅ እጣ ፈንታ የሚሰጣቸውን ሁሉ በጸጋ እንዲቀበሉ ትራጀዲ እያጽናናች ትመክራቸው ነበር። ይህንን መጽናናት ሶቅራጥስ ምስቅልቅሉን አወጣው። በጥቅል ሃሳቦችና ሃልዮት ላይ በተመሰረት እውቀት፣ ደስታን ማግኘት እንችላለን ይላል - ሶቅራጥስ እንደ ኒቼ ግንዛቤ ከሆነ።
ሦስተኛውና የመጨረሻው የኒቼ ትንታኔ፤ ስለ ሶቅራጥሳዊ አመክንዮ የህይወት ውስንነትና በግዳችንም ቢሆን እንደ ቅድመ ሶቅራጥስ ግሪክ በትራጀዲ መኖር እንዳለብን የሚያስረግጥበት ክፍል ነው። በእርሱ ዘመን (1870 ግድም) የሙዚቃና የፍልስፍና እንደ ገና ማንሰራራት ታሪካዊ ምስክር መሆኑን በመጥቀስ ሃሳቡን ያጠናክራል።

Read 1625 times