Saturday, 03 November 2018 16:12

***ድንገት*** - (ወግ)

Written by  ከቃል፡ ኪዳን
Rate this item
(2 votes)

 ጥላ ግን ምንድን ነው? ጠሀይ ስትጋረድ መሬት ላይ የሚፈጠር ያኮረፈ ፈዛዛ ምስል? ታድያ ለምን አንዴ ከፊት፤ አንዴ ከኋላ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጎን ይሆናል? ከግርዶሹ ሾልኮ ሊያመልጥ? ቆይ ለምን አንዴ እያጠረ፤ ሌላ ጊዜ እየረዘመ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል? በርዝመቱ አለመቻሉን ሊሸፍን፤ በእጥረቱ ተስፋ መቁረጡን ሊያውጅ?
ድንገት (የድንገት መከሰቻው በጊዜ ቢሰፈር ምን ያህል ነው? አንድ ሰከንድ? ግማሽ ሰከንድ? ከዛ ያነሰ ወይስ የበዛ?)…….
 ‹‹‹ከት!›……ደግመን እንሠራዋለን!›› ሲል ባኮረፈው ፈዛዛ ጥላ ላይ፣ ደምቆ የሚሰማ የሚያስገመግም ድምጽ በቁጣ ተናገረ፡፡
‹‹ጌታዬን! ምንም እየሠራችሁ አይደለም፡፡ ጥቁሮቹ ግን ምን ነካችሁ? አጀማመራችሁ መልካም ነበር እኮ! ቆይ ድንገት (ይኼኛውስ ድንገት ምን ያህል ነው?) ምን ተፈጠረ? እናንተ ነጫጩባዎች ደግሞ ከአቅም በላይ ጉልበት እያባከናችሁ ነው፡፡ ለሁሉም ልክ አለው እኮ! ስንቴ ነው የምነግራችሁ?››
‹‹ኧረ! ለሁሉም ጊዜ አለው ነው የሚባለው፡፡›› ነጮቹ ከሹክሹክታ ከፍ ባለ ድምጽ ተቃወሙ፡፡
‹‹ይሄን እኮ ነው የምለው! ወግ ወጉን እንደው ይዛችሁታል፡፡›› ፊቱን ወደ ቢጫዎቹ አዙሮ ‹‹ደግሞ እናንተ ምን መሆናችሁ ነው? እራሳችሁን ትታችሁ እኮ ነጮቹን ስታዩና ስትኖሩ ነው የምትውሉት፡፡ አሁን ከእነሱ ጋር ፉክክርን ምን አመጣው?›› በቁጣ አፈጠጠባቸውና ፊቱን መልሶ፤ ‹‹አሁን ደግመን እንሠራዋለን!›› አለ፡፡
ሰውዬው ጴጥሮስን ይመስላል፡፡ ለአምላክ ቀኝ እጁ የሆነ፤ ሌላ ሰውም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አምላክ እራሱ እንዳልሆነ ልቦናዬ ነግሮኛል፡፡ እሱ ‹‹ከት›› ካለ ሁሉ ነገር ተቆራረጠ ወይም ተቋረጠ ማለት ነው፡፡
ድጋሚ ድንገት - በሰማይ በአራቱም ማዕዘናት ያሉ መስኮቶች ተከፈቱ፡፡ ነፋሳት ከምሽጎቻቸው ወጥተው እንደ ጠበኛ ጎሾች ግምባር ለግምባር ተላተሙ፡፡ ሲበቃቸው ምድርን አመሷት፡፡ የምድር ቀሚስ ወደ ላይ ተገለበ - ሀፍረቷ ታየ፡፡ ባርኔጣዋ አየር ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ሁሉም እንዳልነበረ ሆነ፡፡
እኔ ግን የቱ ጋ ነው የቆምኩት? ጫፌንስ ያልተነካሁት የቱ ጋ ብሸሸግ ነው? ታላቁ ጦረኛ ዓለምን መገለባበጥ ይችል ዘንድ ፈልጎ ያጣው መቆምያ ላይ ቆሜ ነው? ወይስ እንደ ‹ቪድዮ› ቤት፤ ጠሀይን ጋርጄ -አጨልሜ፤ በፈጠርኩት ጥላ ላይ ድምጽ ያለው ተንቀሳቃሽ ምስል እያየሁ ስለሆነ ነው?
ነፋሳቱ ሲደክሙና ተዝለፍልፈው ሲንሳፈፉ፤ የሰማይ ቧምቧዎች በተራቸው ውሃቸውን ማፍሰስ ጀመሩ፡፡ ማን ከፈታቸው? ደግሞስ ተከፍተው ነው ወይስ ተሠብረው? ወይንስ ፈንድተው? ፈንድተው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ፍሳሹ በከንቱ ውዳሴ፣ እርግማንና ምሬት ጨቅይቶ መልኩን የለወጠ ነበር፡፡
ምድር እስኪያስመልሳት ድረስ ውሃን ተጋተች፡፡ ውቅያኖሶች ተደቅኖ እንደተረሳ ባልዲ ሞልተው ፈሰሱ። በዓለም ወበቅ ሳቢያ ቀልጠው (ቀብጠውም ሊሆን ይችላል) ይሞሏቸው የነበሩትን የሰሜንና የደበቡ ዋልታ ግግር በረዶዎችን ሄደው ዋጡ፡፡ ውሃ ከነፋስ የተረፈውን ጠራርጋ ወሰደች፡፡
ጥንብ ያፀዳ ውሃ
ጥንብ አንሳ ሆነና
ወድቆ እንዳይቀርና
ያመነዥግ ገባ፤ የነፋስ ትራፊን
የነፋስን ትፋት
ያዳቆነው ሰይጣን፤ ሊያቀስሰው ጠልፎት፡፡
ደግሞ ጠሀይቱ ወጣች፡፡ ወጥታም ስስና ማራኪ ፈገግታዋን ቁርጠት ወደ ሚያሲዝ ሣቅ ቀየረች፡፡ ከነፋስና ከውሃ የተረፈውን ልትበላ፤ ድዷን እስከ ሲዖል ደጃፍ በለጠጠች፡፡ በጠሀይ ፊት ማንም ደፍሮ ሊቆም አልቻለም፡፡ ሁለት ‹ድንገቶችን› ተኩሶ፤ ነፋስና ውሃን ተቋቁሞ የነበረው  ሁሉ እንደ ሰም ቀልጦ ፈሰሰ፡፡ እንባ እንኳ ከሽፋሽፍት ላይ እንደ ጉም ተነነ፡፡ ከኔ በቀር አንዳችም የተረፈ የለም፡፡
ሌላ፣ አዲስ ድንገት - በዚህኛው ድንገት፤ ተነቅሎ በተወረወረው የወተት ምድር ምትክ አዲስ ምድር አቆጠቆጠ፡፡ ጴጥሮስ መጣና (ጴጥሮስ ላይሆንም ይችላል፡፡ ግን እግዜሩ እንዳልሆነ ልቦናዬ ነግሮኛል) በእውቀት ዛፍ ቅጠል አዲስ ያቆጠቆጠችውን ምድር ሞረዳት፡፡ ተስተካክላ በቀለች፡፡ በእውቀት ዛፍ ላይም አዋቂዎች በቀሉ፡፡
መልካም የሚመስሉ ሰዎች በምድር ላይ መመላለስ ጀመሩ፡፡ እኔም ስለወደድኳቸዉና ስለመረጥኳቸዉ፤ በእኔ ልክ የሆነና እኔን የሚመስል አንዳች ነገር ጠሀዩ ፊት አቁሜ፤ ጥላውን አስቀጠልኩና አዲሶቹን ተቀላቀልኳቸው፡፡
‹‹አዲስ ነህ?›› አሉኝ፤ አንዲት እናት የመሰሉ፡፡
ከመቼው ተፈጥረው ከመቼው እናት ሆኑ? ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ ምናምን ዓመት ኖረ አሉ - አሉ ነው እንግዲህ፡፡ አያቴ በሰማንያ፤ አባቴ ደግሞ በሠላሳ ሰባት ልክ እንደቸኮሉ ሁሉ ማቱሳላ ወደሄደበት ሄዱ፡፡ እኔም ይኸው በአፍላነቴ ቅፍፍ እንዳለኝ ነው፡፡ እድሜ እንዲህ እያደር ማነሱ ግን ምንድነው ምክንያቱ? ማቱሳላ በዛ ተሰፍሮ የማያልቅ እድሜው የደረሰበት ንቃተ ህሊና ላይ ደርሰን፣ በአንድ ጊዜ ፊጥ እያልን ነው እንዴ? ህጻናቱ ቀድመው አፍ የሚፈቱት፤ አፍ እንደፈቱ መአት የሚያወሩት፤ ሞታቸውን ለማፋጠን ይሆን?
‹‹አዲስ ነህ ወይ?›› ሳይፈጠሩ በፊት፤ ሲፈጠሩና ቀድመውኝ ሲያረጁ ያየኋቸው እናት በድጋሚ ጠየቁኝ።
‹‹እንዲያውም! ካልገረሞት ከእርሶ ብበለጥ ነው!›› አልኳቸው፡፡
ጥቂት መንገደኞች፣ መንገዳቸውን ትተው መጥተው፣ ከበውን ቆሙ፡፡ ከዛም ልክ እንደማልሰማቸው በሹክሹክታ ጸጉረ ልውጥ እንደሆንኩና ከየት አባቴ እንደመጣሁ እርስ በራሳቸው መጠያየቅ ጀመሩ፡፡
ጸጉረ ልውጥ እሆን እንዴ ብዬ አናቴን ብዳብሰው፣ አናቴ ላይ አንዳች ጠጉር የለም፡፡ ስለ ምን ጠጉር እንደሚያወሩ ግራ ገባኝ፡፡ ግራ መጋባቴ፤ ግራ ሲያጋባቸው ሁሉም ትተውኝ ሄዱ፡፡
‹‹አለባበስህ ወጣ ያለ ነዉ›› አለችኝ አንዲት ሴት ከፊቴ መጥታ ቆማ፡፡ አለባበሴ ለየት ያለ እንደሆነ ለማረጋገጥ፣ ከእግር ጥፍሬ እስከ ደረቴ ድረስ እራሴን ተመለከትኩ - እርቃኔን ነበርኩ፡፡
‹‹እንደዚህ ነህ እንዴ?›› ሴቲቱ ጠየቀችኝ፡፡ ብዙ ወንዶች ጉዳያቸውን እየተው መጥተው ከበዋት ቆሙ። ወንዶቹ እሷን እንጂ እኔ ጸጉር የሌለኝ ጸጉረ ልውጥን፤ እኔ እርቃኔን የሆንኩ ወጣ ያለ አለባበስ ለባሽን ሊያዩ ዓይናቸውን አልሰደዱም፡፡
‹‹አይ! እንደዚህ አይደለሁም!›› አልኳት በትህትና። ትንሽ ቆማ ብታዋራኝ ፈቃዴ ነው፡፡ ትንሽ ግን ምንድነው? ከምን አንጻር ተለክቶ ነው፣ ወሬ ትንሽና ረዥም የሚባለው?
‹‹ታድያ እንደዛ ነሃ!›› አለችኝ ፈገግ ብላ፡፡ ፈገግታዋ ዘመድ አገኘሁ ይመስላል፡፡ እሷም እንደዛ ናት መሰለኝ፡፡
‹‹በፍጹም! እውነት ለመናገር እንዴት እንደሆንኩ እራሱ አላውቅም፡፡ ባይገርምሽ እንዴት ለመሆን እንደምሻ እራሱ እስካሁን አልተገለጸልኝም፡፡›› አልኳት፤ ለፈገግታዋ ምላሽ እየሰጠሁ፡፡
እየተመናቀረች ጥላኝ ሄደች፡፡ ከበዋት የቆሙት ወንዶች፤ አስከፋሃት በሚል ገላምጠውኝ ተከትለዋት ሄዱ፡፡ ለምንድነው የሚገላምጡኝ? በእኔ ምላሽ ተከፍታ ቢሆን እንኳን እነሱን አትዩኝ አላለቻቸውም፡፡ ቢገባቸው ቆንጆ አካሏን ይዛ በመሄዷ እኔ ነኝ የቀረብኝ። እኔ ለራሴ በመሄዷ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እንደውም ሊያዝኑልኝ ይገባ ነበር፡፡
ብዙ ድንገቶች አለፉ፡፡ ድንገቶቹ የተከሰቱበትን ጊዜ መስፈርያ እስካሁን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግን መስፈሪያውን እየፈለግሁ ነበር እንዴ? ብቻ ብዙ የማይሆኑ ነገሮች ሆኑ፡፡ የሚሆኑ ደግሞ ሳይሆኑ ቀሩ። አንደኛው ሺህ ካለ፤ ስምንተኛው እንዴት ይቀራል? ጉቶ ይፈጃል እንጂ የትኛው አጥንት ሳይበስል ይቀራል? ያረሰ፤ የገረጀፈ፤ ጥፍር ያበቀለ ሁላ ለሚንተከተከው ውሃ እጅ መስጠቱ አይቀርም፡፡ የሚንተከተው ውሃ እንኳን ተኖ ቢያልቅ እሳቱ እስካልጠፋ ድረስ ለቅቅል የታሰበው ጥብስ ይሆናል፡፡
ሁሉ ነገር ግራ ተጋብቷል፡፡ ወይ ደግሞ ሁሉ ነገር ግራ ገብቶኛል፡፡ አሁንም የቋሚ መንገድ ላይ ቆሜአለሁ፡፡ ከፊቴ ያለው የእግረኛ መንገድ ላይ እግረኞች ይሄዱበታል፡፡ እግር የሌላቸውም ይሄዱበታል፡፡ በርግጥ መቆም የማይችሉትም ከኔ ጋር በቋሚው መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡
‹‹ጊዜ ደጉ!›› አሉ ሁለት አዛውንቶች፤ የዕድሜያቸውን ገሚስ ሲያሳድዱት የነበሩትን ሌባ አፈፍ አድርገው ከያዙ በኋላ፡፡
‹‹ጊዜ ክፉው›› አለ በአሳዳጆቹ እጅ ላይ የወደቀው፡፡
‹‹ስንት ዓመት አሳደዳችሁት?›› አለ ቂጣ-በሌ ፖሊስ ወንጀለኛውን እየተረከባቸው፡፡
‹‹የዕድሜአችንን ግማሽ! በዕድሜአችን አጋማሽ ነው በጋችንን ሰርቆ የጠፋው፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ የምንበላውን ምሳ ትተን ስናሳድደው ነው የኖርነው›› አሉ ሁለቱም በአንድነት፡፡
‹‹የዕድሜአችሁን ግማሽ ያህል ከምታሳድዱት ለምን ዛሬ ብቻ አላሳደዳችሁትም?›› ስል ጠየቅኋቸው፡፡
‹‹እሱ አልመጣልንም ነበር!›› አሉኝ፡፡
‹‹አንተስ የእነሱን ግማሽ ዕድሜ ያህል ከምትሸሽ ለምን ዛሬ ብቻ አልሸሸሃቸውም?›› ስል ጠየቅሁት፡፡
‹‹እኔ የራሴን እንጂ የነሱን ግማሽ ዕድሜ ያህል አልሸሸውም!›› ሲል መለሰልኝ፡፡
‹‹አሁን ለአንድ በግ ምን ያህል ጊዜ ቢታሰር ነው?›› ስል ቂጣ-በሌው ፖሊስን ጠየቅሁት፡፡ ፖሊሱ በሱሪው ቀበቶ ይዞት የነበረውን ሌባውን ለቆ፣ ጣቱን በጣቱ እየቆጠረ፤ ‹‹እንደ ህጉ ከሆነ አንድ ወንድ በግ የሠረቀ፣ አንድ ቀን፡፡ ሁለት ወንድ በግ የሠረቀ፣ ሌላ ሁለት ቀን፡፡ ሦስት ወንድ በግ የሠረቀ፣ ሌላ ሦስት ቀን ይታሠራል፡፡ ለወንድ ግልገል በግ ደግሞ ግማሽ ቀን፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡››
‹‹ሴት በግ የሠረቀስ?›› ስል ጠየቅሁት፡፡
የበጉ ሌባ፣ የፖሊሱን ማብራርያ በሚገባ ከተከታተለና ማስታወሻው ላይ አስፈላጊ ያላቸውን ነጥቦች ካሠፈረ በኋላ ፖሊሱ እንደለቀቀው ሲረዳ እሮጦ አመለጠ፡፡ በጉ የተሠረቀባቸው ሁለቱ ሰዎች እራሳቸውን በትዝብት በመነቅነቅ፤ ‹‹እንግዲህ እኛ አንዴ ለህግ አስረክበነዋል፡፡ አሁን ሄደን ያቋረጥነው ምሳችንን እንጨርስ!›› ተባብለው ወደ ቤታቸው መንገድ ጀመሩ፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሌባው በትህትና መንገድ እንዲለቁለት እየጠየቀ፤ እነሱም እየለቀቁለት፤ ባጠገባቸው እሮጦ ማምለጡን ሲያዩ ተሰባስበው ወደ ፖሊሱ መጡና፤ ‹‹ቆመህ ምን እያደረክ ነው? ሌባውን አባረህ ያዘውና ወህኒ አስገብተህ ዝጋበት እንጂ!›› ሲሉ አፈጠጡት፡፡ ፖሊሱ አፍጥጠው የሚያዩት ሰዎች ላይ አፍጥጦ፤ ‹‹ተረጋጉ! ተረጋጉ! እናንተ እንደምታስቡት አይደለም፡፡ እስር ማስተማርያ እንጂ ቂም በቀል መወጫ አይደለም፡፡››
‹‹ታድያ ሰው ሲበደል ‹መንግስት ይፋረደኝ› የሚለው ለምንድነው?›› አለ አንዱ ከመሀል፡፡
‹‹ማነው እንደዛ ያለው? ተናገር! ማነው እንደዛ ያለው? ፈራጁን መንግስት ተፋራጅ ነው ያለው ማነው?›› ፖሊሱ አፈጠጠ፡፡ የተናገረው አንገቱን አቀረቀረ። ፖሊሱ ከኪሱ አንድ ወረቀት አወጣና በአእምሮው የመጣለትን ምስልን ወረቀቱ ላይ ስሎ ሲያበቃ ከታቹ፤ ‹‹ይፈለጋል! ይህ ሰው ‹ፈራጁን ተፋራጅ› ብሎ ክብረ ነክ የሆነ ነገር በመናገሩና በማስነገሩ ያለበትን የሚያውቅ ወይ ደግሞ እሱን የሚመስል መፍጠር የሚችል ካለ መጥቶ ያስረክበን›› የሚል ጽሑፍ አስፍሮ እንዲያባዛውና በየከተማው መውጫና መግቢያ በሮች ላይ እንዲለጥፍ ቅድም የተናገረውን ሰውዬ ላከው፡፡
ሰዎቹ ሰውየውን ወረቀቱን ተቀብሎ ሊሄድ ሲል ተራ በተራ እየተጠጉ፤ ወረቀቱን ከማባዛቱና ከመበተኑ በፊት፤ እንደዛ ብሎ የተናገረውን ሰውዬ እንዲሸሽ እንዲመክረው በጆሮው ነገሩት፡፡ ሰውዬውም በሀሳባቸው በመስማማት እራሱን ነቅንቆ እየሮጠ ወደተላከበት ሄደ፡፡ መሄዱን ሲያዩ ሰዎቹ መልሰው፤ መልዕክተኛው ወረቀቱን ከመበተኑ በፊት፤ ለተፈላጊው ሰውዬ እንዲሸሽ እንዳይመክረው፣ ህግ ጥንቃቄ ያድርግ ሲሉ ለፖሊሱ አሳሰቡ፡፡
‹‹እና እንዳልኳችሁ የእስር ዓላማው፣ ወንጀለኞች ወንጀል ከፈጸሙበት ማህበረሰብ ተገለው እንዲኖሩና የፈጸሙትን ወንጀል እያሰቡ እንዲጸጸቱ ማድረግ ነው፡፡ እንደውነት ከሆነ ይህ ሰው ለአንድ ወንድ በግ አይደለም ለብዙ ወንድ በጎች የሚሆን ቅጣትን ተቀብሏል፡፡ እንደውም በ‹ደብል ጂዮፓርዲ› ህግ መሠረት፤ በአንድ ወንጀል ሁለቴ ሊጠየቅ ስለማይገባው ከአንድ በላይ ወንድ በግ ሳይሰርቅ እራሱን ከማህበረሰቡ ለብዙ ጊዜ ስላገለለ፤ ከዚህ በኋላ ሌሎች ወንድ በጎችን ቢሠርቅ እንኳን ሊጠየቅ አይገባውም፡፡›› አለ ፖሊሱ፡፡
ሁሉም ማብራርያውን ከተከታተሉ በኋላ እራሳቸዉን በመስማማት ነቀነቁና በየፊናቸው ሄዱ፡፡ እኔና ፖሊሱ ብቻ ቀረን፡፡ ፖሊሱ ዞር ብሎ አይቶኝ፤
‹‹እሺ ጎረምሳው!›› አለኝ፡፡
‹‹ቆይ ግን ሴት በጎችንስ የሠረቀ ምን ያህል ነው የሚቀጣው?›› ስል ያንገበገበኝን ጥያቄ ጠየቅሁት፡፡
‹‹ሴት በግ ሠርቀሀል እንዴ?›› ሲል መልሶ ጠየቀኝ፡፡
‹‹አይ የሴት በጎች መብት ስለሚያሳስበኝ ነው፡፡›› ስል መለስኩለት፡፡ በንቀት ከላይ እስከ ታች ገረመመኝና፤
‹‹ታድያ ሴት ዶሮና ሴት በግ በርካሽ ስትገዛ ለምን ረከሰ ብለህ ከሻጮቹ ጋር አልተከራከርክም?›› ምላሱን አወጣብኝና ጥሎኝ ሄደ፡፡
ፖሊሱ ብዙም ሳይርቅ አብሮ አደግ የሆኑ ሁለት ሴቶች እኔ ያለሁበት ሲደርሱ ቆመው መጣላት ጀመሩ። ከንግግራቸው እንደተገነዘብኩት፤ አንዷ የአንዷን ፍቅረኛ ቀምታታለች፡፡ ቀሚዋ ጓደኛዋን ኃይለ ቃል ትናገራት ጀመር፡፡ ጓደኝየው ደግሞ ስድቧን እየጠጣች፤ በግርምት እራሷን እየነቀነቀች ትስቃለች፡፡ ይድከማት ወይ ሌላ የምትናገረው ትጣ፤ ወይ ደግሞ የጓደኛዋን በንግግሯ አለመናደድ ስታይ፣ ቀሚዋ እያቀዘቀዘች መጣችና ጨርሶ ዝም አለች መሰለኝ፡፡
‹‹ጨረሽ የኔ ጅራፍ?›› አለች ፍቅረኛዋን የተቀማችው ሴት፡፡ ጓደኝየው በአዲስ ኃይል ንግግሯን ልትጀምር ስትል በእጇ ምልክት ሰጥታ አስቆመቻት፡፡
‹‹ስሚ ታስታውሺ እንደሆነ ልጅ እያለሽ፣ እኔ ተጫውቼበት በጣልኩት መጫወቻ ነዉ ተጫውተሸ ያደግሺው፡፡››
‹‹እውነት ብለሻል›› አለች ቀሚዋ፡፡
‹‹ታድያ አሁን እንደማስቲካ ሳላምጠው የነበረውን ፍቅረኛዬን ጣዕሙ ካለቀ በኋላ ካፌ ነጥቀሽ ብትወስጂ እንዴት ልበሳጭብሽ እችላለሁ?›› ስትል ጠየቀቻት፡፡ ጓደኝየው መልስ አጥታ ዝም አለች፡፡
ከዛ ተንደርድረው ተቃቀፉና አንዳቸው በአንዳቸው እቅፍ ለአፍታ ያህል ዓይናቸውን ጨፍነው ቆዩና ተላቀቁ፡፡ ከዛም እጅ ለእጅ ተያይዘው አካባቢያቸውን ዞር ዞር ብለው ሲቃኙ፣ ከእኔ ጋር ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ፡፡ ሰላም ስለማውረዳቸው ደስ እንዳለኝ ፈገግታዬን ልለግሳቸዉ ሳምጥ፤
‹‹ምናባህ ታፈጣለህ?!›› አሉኝና ትከሻ፣ ለትከሻ ተቃቅፈው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
የት ነው ያለሁት ግን? ሰው ራሱ ባጠላው ጥላ ላይ ሲዋልል የሚሰማው ዓይነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ ችግሩ እንደዛ ዓይነት ስሜት ምን ዓይነት፣ ምን፣ ምን እንደሚል ከዚህ ቀደም ቀምሼው አላውቅም፡፡ እራሱ ላይ አጨልሞ እራሱ ጋደም የሚለው ሰው እንደዚህ ዓይነት ስሜት ይሆን እንዴ የሚሰማው? አፍሪቃ እንዲህ ይሆን እንዴ የሚሰማት?
ድንገት መላጣ የገረጀፈ ወጣትና ጸጉሩ እጀርባው ላይ የሚደርስ የታደሰ ሽማግሌ ወደኔ መጡ፡፡ ወጣቱ ወጣትነቱንና ውበቱን ለሽማግሌው ሽጦለት ይሆን? ወይስ የዘመኑ ጤዛ ወጣትነት ኪሣራ ብቻ ሆነ፡፡ ለነገሩ ወጣትነትን መጠበቂያ ከሌለ ወጣትነት ብቻውን ምን ሊፈይድ ነው? በየጉራንጉሩ አልጋ ቤቱ በዝቶ፤ በየትምህርት ቤቱ ደጃፍ ጎረምሳው የመኪናውን ‹ክላክስ› ከትምህርት ቤቱ ደውል በላይ እያስጮኸ ባለበት፣ ባለ ህግ ሴት እንደ መፈለግ ነው፡፡
‹‹ጠፍቶህ ነው አይደል? አይዞህ እኛ እናሳይሀለን፡፡›› አሉኝ ወጣቱና ሽማግሌው በአንድነት፡፡
የወጣቱና የሽማግሌው ድምጽ ሲደባለቅ የአንድ ጠንካራ ጎረምሳ ድምጽ ተፈጠረ፡፡ ድምጻቸው ተደባለቀ እንጂ አልተዋሃደም፡፡ በንግግራቸው መሀል ‹ድንገት› ሊለካበት የሚችል መበላለጥ አለ፡፡ የድንገትን መለኪያ አገኘሁት መሰል!
‹‹ምኑን ነው የምታሳዩኝ?›› አልኳቸው በመጓጓት፡፡
‹‹መነሻህን!/መድረሻህን›› አሉኝ፤ ወጣቱና ሽማግሌው እኩል፡፡
ሽማግሌውና ወጣቱ አንዳቸው የአንዳቸውን መልስ ሲሰሙ ‹እሱ ነገር አንተ ጋር አለ እንዴ?› በሚል በጥያቄ ዓይን ተያዩ፡፡ ከዛም እኩል ፈገግ አሉ፡፡ ወዲያው ስምምነት እንዳደረጉ ሁሉ እጅ ለእጅ ተጨባበጡና ፊታቸውን አዙረው ጥለውኝ ሄዱ፡፡ ሳይጀምር የጨረሰው ወደ መጀመርያው፤ ላይጨርስ የጀመረው ወደ መጨረሻው የሚያደርሳቸውን ተስፋ ሰንቀው ተቃቅፈው ሄዱ፡፡
የሆነ የጉርምስና ጉማጅ ላይ ቁጭ ብሎ የሚተክዝ ዓይነት ሰው ስሜት ተሰማኝ፡፡ እስካሁን ምን እንደምፈልግና ማን እንደሚያስፈልገኝ ሳልረዳ ብቆይም፤ ወጣቱና ሽማግሌው ተያይዘው በመሄዳቸው ግን ቅር አለኝ? በመሄዳቸው  ምን ያጣሁት ነገር አለ? ምቀኝነት ነው? ወይስ ሽማግሌውና ወጣቱን ባልፈልጋቸውም፣ አንዱ አንዱን ለምን ወሰደብኝ ማለቴ ይሆን? እሺ ማን ማንን ነው የወሰደብኝ? ጠሀይ ጠለቀችና ያጠላሁት ጥላ ጠፋ፡፡ ወይ ደግሞ ጥላው ሁሉን ከጉያው ከተተ። ጨለማ የጥላ ታላቅነት ይሆን እንዴ?

Read 1407 times