Saturday, 03 November 2018 16:13

የፀሃይቱ እንባ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(11 votes)


        (ከ“ACRES OF DIAMONDS!” ….. ዶ/ር ራሴል ኮንዌል በጥቂቱ ተሻሽሎ የተተረጎመ፡፡)
             
     ልቤ በዚህች በምጎበኛት አገር ማለለ፤ ወደድኳት። በርሃ ብትሆንም ቅሉ፣ በርሃ ውበት እንዳለው ማየት የቻልኩት አሁን ነው፡፡  በልቤም ‹ከጉብኝቴ መልስ ወደ አባት አገር አልመለስም› ስል ማልኩ! እዚህ ሰርቼ መለወጥ እችላለሁ፡፡ አገሬ በእኔ፣ እኔም በአገሬ ተስፋ ቆርጠናልና አልሔድም! እያልኩ ከራሴ ጋር ተማማልኩ፡፡
ከግመሊቱ ኮርቻ ላይ ተቀምጬ ውዝዋዜዋ እየናጠኝ ተዳክሜያለሁ፡፡ የጢግሪስን ወንዝ ዳርቻ እየጎበኘሁ ነበር፡፡ ሽማግሌው አረብ አስጎብኚዬ የግመሊቱን መሳቢያ ገመድ ይዞ እየጎተተ ይለፈልፋል። አንድም ቁምነገር የምሰማው ባጣ እርሱን ማዳመጡን ተውኩትና ወንዙንና ዳርቻዎቹን፣ አሸዋውንና ንፋሱን ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡
ድንገት ቆም አለና እንዲህ ሲል ጮኸ … ‹‹ ጌታው! እንደ እርስዎ ላለና ለተከበረ ወዳጅ የምነግረው አንድ አስደናቂ ታሪክ አለኝ፡፡ ታዲያ ይገርምዎታል … ይህንን ጨዋታ ለተከበሩ ወዳጆች ብቻ ነው የማወራው።›› ፍልቅልቅ ገፁን እያሳየኝና  ላቡን እያንጠፈጠፈ እንዲሁም ኮፍያውን ከጭንቅላቱ ላይ አውልቆ እያወዛወዘ መልሴን ጠበቀ፡፡ ጥቂት ከታገሰ በኋላ ወጉን ይጠርቅ ያዘ፡፡
***
‹‹….አሊ ሃፌድ ያልተማረ ነገር ግን የትልቅ እርሻ ባለቤት ነበር ይባላል፡፡ ሃብታም ነበር አሉ። ከብቶች በበረቱ፣ አዝርዕት በማሳውና ኮረዳ ከእቅፉ ስር የማያጣ፤ ሁሉ የሞላለት ሃብታም ነበር ይባላል - አሊ ሃፌድ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ታዲያ አንድ ጎብኚ ወደ ቤቱ መጣ። ይህ እንግዳ ቡድሂስት መነኩሴ ነበር። እናም ከሻይ በኋላ ከአሊ ጋር በእሳቱ ዳር ቁጭ ብለው ሲጨዋወቱ ስለ አለም አፈጣጠር እንዲህ ሲል አጫወተው አሉ… ›› ብሎ ግመሊቱን ይዞ ቆመና ሽቅብ ያጤነኝ ጀመር፡፡
በጣም ስለተናደድኩ የሚናገረውን ሙሉ በሙሉ አልሰማሁትም፡፡ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ግመሊቱን ሲያስቆማት ግዜ ‹‹ኧረ ባክህ ወደ ፊት እየጎተትክ! … አታስመሽብኝ እንጂ!›› ስል ገሰፅኩት፡፡
‹‹…ግድ የለዎትም ጌታዬ! ተረክና ታሪክ ህይወት ይለውጣልና ሲነገርዎ ለእኔ ብለው መስማት ይኖርብዎታል፡፡ ያው መቼም እውነት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህንን ተረክ እርስዎም ለልጆችዎና ለወዳጆችዎ ቢነግሩ ግሩም ነው!…›› ሲል ምክር ብጤ ጣል አድርጎ፣ ድጋሚ ያፈጥብኝ ጀመር፡፡ ፀሃይቱ ከአናቴ እየተንበለበለች ቢሆንም ይህ አረብ ካላወራኝ የማይተወኝ ስለመሰለኝ እንዲቀጥል ጭንቅላቴን በአዎንታ አወዛወዝኩ፡፡
ከንፈሩን ካሞጠሞጠ በኋላ ቀጠለ … ‹‹…እና መነኩሴውም እንዲህ ሲል ነገረው ይላሉ … አሊ ወዳጄ፣ ይህ የምታየው አለም ሁሉ የሆነ ወቅት ጭጋግ ብቻ የሞላበት ኦና ነበር፡፡ (ጣቶቹን ከፊት ለፊቱ እያወናጨፈና በክብ ቅርፅ እያንቀሳቀሰ…) … ፈጣሪ ይህንን ጭጋግ መሰል ነገር በክብ አንቀሳቀሰው፡፡ እናም ለጥቆ የእሳት ኳስ ተፈጠረ።  ይህ የእሳት ኳስ በጠፈር ውስጥ እየዞረ ያገኘውን ሁሉ እያቃጠለና እያጠቃለለ ተንቀሳቀሰ፡፡ ሌሎቹን ጭጋጎች እየበተነ ነጎደ፡፡ በውጪኛው አካል አካባቢና በአየር ለውጥ ደግሞ ቅዝቃዜው የዝናብ ነጠብጣብ እየሰራ እየተጠቀለለ ይኖር ነበር፡፡ በመጨረሻም ውስጣዊው እሳት ፈንድቶ ተራሮችንና ሸለቆዎችን… ኮረብታዎችንና…. ጉብታዎችን እየፈጠረ፤ በመሬት ፊት ላይ የቀለጡ አለቶችንና የከበሩ ማዕድናትን እያስቀመጠ … ኮፐር፣ ብር ፣ ወርቅ …. እና በመጨረሻም ውዱንና ጠንካራውን አልማዝ አንጥሮ በጥቂቱ እያወጣ፣ እያንጠባጠበ (…አሊ አፉን ከፍቶ ያዳምጣል … መነኩሴውም ከጥቂት ዝምታ በኋላ ይለጥቃል …)
ወዳጄ ለዚህ‘ኮ ነው አልማዝን የፀሃይ እንባ የምንለው፣ (ሳይንሱም ዳይመንድ (አልማዝ) ከፀሃይ የመጣ የካርቦን ጥርቅም ነው ይላልና!) … እናም አሊ ይገርምሃል፤ አንዲት የአልማዝ ሉል ቅንጣት ብታገኝ … ይህንን ቀበሌ መግዛት ያስችልሃል፡፡ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ ቢኖርህማ እስከ ልጅ ልጅ ልጆችህ በሃብት ትንቆጠቆጣለህ። … (እያለ እያስተማረውና አሊም እየሰማ ለሊቱን አጋምሰው ወደ የመደባቸው ተለያዩ…) ድካም ተጫጭኗቸው ምሽቱን በየመደቦቻቸው ተፈነደሱ።
አሊ ግን ይህንን ተረክ ከሰማ በኋላ ፈፅሞ እንቅልፍ አልያዘውም፡፡ አይኑን ከድንኳኑ ጣራ እንደተከለ ሲያሰላስል አነጋ፡፡ ስለ ማዕድኑ ከሰማ በኋላ እንቅልፍ አልወስድ አለው፡፡
ሳይነጋ በጠዋት ተነስቶ መነኩሴውን  ቀሰቀሰውና ያስለፈልፈው ጀመር፡፡ ‹‹…የአልማዝ ፈርጥ የት ነው የማገኘው!…›› ሲል አፋጠጠው...
‹‹…አልማዝ! … አልማዝ ምን ያደርግልሃል!›› ይላል መነኩሴው፤ አይኖቹን እየጠራረገ፡፡
‹‹…ሃብታም መሆን እፈልጋለሁ! በጣም እፈልጋለሁ፡፡ እናም ከእንግዲህ ወዲያ የአልማዝ ፈርጥ ካላገኘሁ ሰላም የለኝም፡፡ እባክህ ወዳጄ ንገረኝ!…›› እያለ አስጨነቀው…
‹‹…እንዲያ ከሆነ፣ በተራሮቹና በሸለቆዎቹ መሃል አስስ፡፡ ሩቅም ቢሆን ተጓዝ፡፡ ወንዞችንና ነጫጭ አሸዋዎችን ፈትሽ፡፡ በነሱ መሃል አንድ ቦታ አታጣውም!…›› ሲል መከረውና ተገላገለ፡፡
እናም አሊ በማግስቱ እንግዳውን ካሰናበተ በኋላ በሳምንት ውስጥ ንብረቱን ሁሉ ሸጦ ወደ ጉዞው ቀጠለ። በተራሮች  በሸለቆዎች፣ በአሸዋዎች መሀል፣ በበረሃና በውቅያኖስ ዳርቻዎች ሁሉ ለወራት፣ እንዲሁም ለአመታት ፈለገ፡፡ በመጨረሻም በባርሴሎና ካለ አንድ ወንዝ ዳርቻ ወድቆ ሞተ ይላሉ….››
(…ይህ የመንገድ መሪዬ የነገረኝ የሚገርም ታሪክ ይመስላል፡፡ በድብርት ውስጥ ብሆንም ታሪኩን ሰማሁት፡፡ ይህንን አወራኝና ቆሞ ከአንዱ ግመል ላይ ያለውን የተጫነ ሻንጣ እስር በፀጥታ ያጠባብቅ ጀመር። ሆሆይ!... በአለም ላይ እንዲህ ያለ አክተሩ ተንገላቶ የሚሞትበት እርባና ቢስ አሳዛኝ ታሪክ ሰምቼም አላውቅ፣ … ደግሞስ ይህንን ታሪክ ነው ለተለዩ ወዳጆች እያለ የሚጎርርብኝ፡፡ በአንድ ምዕራፍ ተወልዶ የሚያበቃ ታሪክ … ኤጭ! … ፊቴን አጨማደድኩ። እኔ ነኝ ጥፋተኛ … እንደ አሊ ሃፌድ አፌን ከፍቼ ማዳመጤ!… )
***
መንገድ መሪዬ ከፊት ተመልሶ የግመሌን ገመድ እየጎተተ፣ ወሬውን እንደ አዲስ ያወራ ጀመር … (ኤጭ!)
‹‹…እናም የአሊን መሬት የገዛው ሰው አንድ ዕለት ከማሳው መካከል ወደምትገኘው ምንጭ ግመሉን ሊያጠጣት ሄደ፡፡ ግመሉም ኩልል ብላ የምትወርደውን ምንጭ ለመጠጣት አሸዋውን ገፋ ገፋ ስታደርግ የሚያንፀባርቅ ነገር ከውሃው ውስጥ አየ፡፡ ሲያወጣው … በዙሪያው ሁሉ ቀስተ ደመና የሚረጭ ድንጋይ ነበር። የሚያምር ፈርጥ፡፡ ወደ ቤቱ ወስዶ ጠረጴዛው ላይ አኖረውና ሁሉን ረስቶ ወደ ዕለት ህይወቱ ገባ፡፡
ከወራት በኋላ፤ ያ የድሮው መነኩሴ አሊን ሊጎበኘው መጣ፡፡ እናም ወደ ጎጆው ገብቶ እንደቆመ ከጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን ድንጋይ በመገረም አስተዋለ፡፡
ሳያስበው እንዲል ሲልም ጮኸ … ‹‹ኦው! ፈጣሪ ሆይ! … የአልማዝ ፈርጥ እነሆ! አቶ አሊ አገኘኸው ማለት ነውን!››
የቤቱ ባለቤትም እንዲህ ሲል መለሰ … ‹‹…ይህ ድንጋይ ነው እንጂ አልማዝ አደለም፡፡ አቶ አሊም ከዚህ ቤት የለም…›› (በመቀጠል የሆነውን ሁሉ አጫወተው…)
‹‹…ነገር ግን…›› አለ መነኩሴው በሰማው ነገር እያዘነ... ‹‹…ነገር ግን እኔ ፈርጥን በማየት ብቻ አውቃለሁ ጌታው፡፡ እምልልዎታለሁ ይህ የአልማዝ ፈርጥ ነው! … እስኪ ያገኙበትን ቦታ ያሳዩኝ!›› ሲል ጠየቀው፡፡ አንድ ላይ ሆነው ወደ ምንጯ ሄዱ፡፡ እናም አካባቢውን በጥንቃቄ ቢያስተውሉ በከበረ ድንጋይ ተሞልታ አገኟት። በአልማዝ የተሞላች ምንጩን ጥሎ አሊ ውቅያኖሶችን ሊያስስ እንደወጣ ሲያስብ፣ መነኩሴው በጸጸት እንባ ተሞላ፡፡
***
የግመሌ ጎታች በመቀጠል እንዲህ ሲል አስረግጦ አስረዳኝ … ‹‹…በታሪክ እንደሚታወቀው ይህ የነገርኩዎ ታሪክ እውነት ይመስለኛል፡፡ … በዓለም ውዱና ታዋቂው የጋልኮንዳ የአልማዝ ቦታ የተገኘው እንዲህ ባለ ሂደት ነው ይባላልና!…››
የተራኪዬን ታሪክ ክፍል ሁለት ስሰማ ወደ ልቤ ተመለስኩ፡፡ አሁን ታሪኩ ሙሉ ነበር፡፡ የታሪኩ ሞራል ምንድነው ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ እነዚህ ሞራል አልባ አረቦች ምን ሞራል ያስተምሩኛል ስል አሰብኩ። ታሪኩ በየወንዙና በየበረሃው የተንከራተቱና የተሰቃዩ ወገኖቼን አስታወሰኝ፡፡ ነገር ግን ለተራኪዬ ምንም አላወራሁትም ነበር፡፡ ይልቅስ ሌላ ታሪክ ነበር የታሰበኝ። እናም እንዲህ አልኩት ‹‹…ጌታው እባክህ ቶሎ ቶሎ ወደ ድንኳኔ አድርሰኝ!...››
…በልቤም ... ‹እምዬ አገሬ! ስስቴና ጓዳዬ! የእንቁ ምንጬ!› እያልኩ ሽቅብ ጋለብኩ፡፡ ልቤንም አልኩት፤ ‹ተው! በፈጣሪ ብለህ  ሀብትህን በጓሮህና በምንጭህ ዙሪያ ፈልግ!›

Read 4634 times