Saturday, 19 May 2012 11:00

የስልክ ውይይት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

“ሃሳብን የሚገድል ሃሳብ አለ” አለ አቶ 0911…የማያውቀው ስልክ ላይ ከደወለ በኋላ፡፡

“ምን ማለትህ ነው?” ብሎ መለሰ ልጅ እግሩ ሲም 0924 …ሲሙ ከቴሌ የወጣበት ዘመን ልጅ እና አባትነትን ይለያያል፡

“ምን ማለቴ መሰለህ…እምነት አንድ የሀሳብ አይነት ነው፡፡ እውቀት ወይንም ምክንኒያታዊነት ደግሞ ሌላ የሀሳብ አይነት ነው፡፡ እናም… ለምሳሌ ምክኒያታዊነት ራሱ እምነት ነው ካልክ… አንዱን የሀሳብ መንገድ ለማጥፋት እየሞከርክ ነው፡፡ በሀሳብ ማሰብ አይቻልም፤ ካልክ ግን… ሀሳብን የሚገድል ሃሳብ አመንጭተሃል” “እና እኔን ምን አገባኝ?” አለ 0924…ገደል በሚያስገባ ቅላፄ፡፡

“…ልጄ ይሄም ጥሩ ጥያቄ ነውኮ!…ምን ታውቃለህ…አያገባኝም ያልከው ጉዳይ እንደ ህይወት አንተ ባትፈልገውም አግብቶህስ ቢሆን?…ያኔ የትዳር ቀለበታቸውን ደብቀው ለመማገጥ ሲፈልጉ “አላገባሁም” እንደሚሉት የትዳር ሰዎች ሆንክ ማለት አይደለምን?...ስለዚህ ከአንጀትህ የኔ ውይይት እንደማያገባህ እስቲ አሳየኝ”

“ማነው ስልኬን የሰጠህ?… ሳሚ… ነህ አይደል… ድመጽህን አውቄዋለሁ”

“አይ እኔ ሳሚ አይደለሁም ልጄ..እኔ 0911 ነኝ…የሲም ካርድ አባትህ ነኝ”

“…ጭንቅላቴን ወጠወጥሽው እኮ ፍሬንዴ ስልኩን ልዘጋው ነው…እንደዚህ አይነት ፉገራ አይመቸኝም”

“ስልኩን መዝጋት ማለት መክፈት አለመሆኑን እንዴት ታውቃለህ” ልጄ? ለምሳሌ እያደረግን ያለውን ውይይት እስካልዘጋህ ድረስ…ስልኩን በመዝጋትህ ህይወትህ ላይ ብዙ ክፍተቶች ቢፈጠሩስ…? እንደማይፈጠሩስ እንዴት ታውቃለህ?”

“እታባ የላከችህ ሰው ነህ እንዴ” 0924 ለመጀመሪያ ጊዜ የመጨነቅ አዝማሚያ አመለከተ፡፡

“ማን ናት እታባ ልጄ?”

“ዋሽንግተን ያለችው እህቴ”

“ልካኝም…ሳትልከኝም ሊሆን ይችላል…የተላኩትን ተልዕኮ እየተወጣሁ ያለሁት፡፡ እየተወጣሁ ወይንም እየተገባሁ፡፡ ግን ሁለቱንም ቢሆንም አልያም ባይሆን ምን ለውጥ ያመጣል፡፡ ለውጥ ማለት እኮ ራሱ በማይለወጥ የቁልፍ ቀዳዳ ውስጥ የሚዞር የሰረገላ ቁልፍ ማለት ነው?”

ረጅም ትንፋሽ ልጅየው በስልኩ ውስጥ አስተላለፈና “ኧረ ቤተሰብ አጨጨብሽኝ…እታባ የላከችህ ሰው ከሆንክ… በጣም ስጠብቅህ ስለነበር…እንገናኝና የሷን መልዕክት አቀብለኝ፡፡”

“ከአሁን በኋላ “እታባ” ብትል ይሄንን ስልክ እዘጋዋለሁ…የምታገኘውም ነገር ይቀርብሃል፡፡ ለመሆኑ…እህትህን ለምንድነው በትክክለኛ ስሟ የማትጠራት”

“…ወሰኔ ነው ስሟ…ግን ሁላችንም እታባ ነው የምንላት፡፡ ደግሞ እሷም እታባ ስንላት ነው… ደስ የሚላት”

“እንዴት ደስ እንደሚላት አወቅህ?” በቁጣ ጠየቀ 0911

“ምክንያቱም ደስ ይለኛል ስትል ስለሰማሁዋት ነዋ”

“መስማትህን እንዴት እርግጠኛ ነህ? አይ ልጄ!... የዋህ ነህ ልበል?... ለምሳሌ እኔ አሁን አንድ ነገር ልንገርህና ስማኝ…እየሰማኸኝ ነው?”

“አዎ” አለ በትሁት ሽቁጥቁጥነት 0924 ቱ

“እየሰማኸኝ… ‘እኔ አፄ ልብነ ድንግል ነኝ’…ሰማኸኝ አይደል?”

“አዎን”

“አመንከኝ…የተናገርኩትን?”

“አላመንኩም”

“ስለዚህ እህትህ …እታባ እያልክ ስትጠራት ደስ እንደሚላት የነገረችህን እንዴት አመንካት?”

“…እይ መከራዬ…ኧረ ሰውዬው ፍታኝ! …ተቸግሬአለሁ አልኩህ… እቃውን አቀብለኝ!…እኔ ስለምታወራው ነገር አላውቅም”

“እማታውቅ ከሆነ ልጄ ለምን እያወራህ ትመልስልኛለህ…የሚያወራውን ለማያውቅ ሰው የተጣለብኝን አደራ… እንዴት አምኜ ልወጣበት እችላለሁ” በማዘን መለሰ 0911

“…ኧረ ባትሪዬን ጨረስከው ጋሽ ተልእኮ…አሁን የት ነው ያለኸው…ንገረኝና ያለህበት ድረስ እመጣለሁ”

“አሁን ያለሁት በማትፈልገኝ አቅጣጫ ቢሆንስ ልጄ…አየህ ለምሳሌ ታክሲ በጣም ተፈላጊ የሚሆነው ሰው ሁሉ መሄድ ወደሚፈልግበት አቅጣጫ የሚጭን ከሆነ ነው፡፡

በተቃራኒው አቅጣጫ ከሆነ የሚጭነው ማንም አይፈልገውም …ስለዚህ አንተ የት ነው ያለኸው ብለህ የጠየቅኸኝ በየትኛው አቅጣጫ ሆነህ ነው…በሂያጅ ወይንስ በተመላሽ?”

0924 ትግስቱ አለቀ “ወዳጄ እንግዲህ ለእህቴ ደውዬ እነግራታለሁ፡፡ ምን ስትጠጣ ወይንም ስታጨስ እንደቆየህ እኔ አላውቅም፡፡ በኋላ ላይ ስትረጋጋ መልሰህ ደውልልኝ…ቻው!”

በአቶ 0911 የተደወለለትን ስልክ ልጅየው 0924 ዘጋው፡፡ የደዋዩን ቁጥር ከእስክሪኑ ላይ መላልሶ ተመለከተ፡፡

ግራም ቀኝም ተጋብቷል፡፡ ደጅ ወጥቶ ሲያናግር ከቆየበት ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡

…ትንሽ ጋደም ብሎ ነገራትን ለመጨበጥ ሞከረ፡፡ እየሞከረ ስልክ ተደወለለት፡፡ ስልኩን አነሳው፡፡ የቅድሙ ስልክ አልነበረም፡፡ የሚያናግረው ድምጽ ግን የቅድሙ ነው፡፡ 0911ዱ፡፡

“ስልኩን መዝጋት ማለት መክፈት አለመሆኑን እንዴት ታውቃለህ ልጄ?” አለው፡፡

 

 

 

Read 2615 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 11:08