Monday, 12 November 2018 00:00

የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ጦር ሰራዊት ማኅበር ተቋቋመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“የሰለጠነ ሰራዊት ማቋቋም ይቻላል”
                    (ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ)     እርስዎ  ስለ ማኅበሩ ምስረታ ምን ይላሉ ?
እኔ ተጋብዤ ነበር የሄድኩት፡፡ በእውነቱ ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ እነዚህ ልጆች፤ ከልጅነት እድሜ ጀምሮ፣ በትንሽ ክፍያ ለሃገራቸው ሲባክኑ የኖሩ ናቸው፡፡ ዛሬ እንደ እቃ ከተጣሉበት በራሳቸው ተፍጨርጭረው ተነስተው፣ ራሳቸውን ችለው፣ ለሃገራቸው አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው። ይሄ ሰራዊት የሚያሳዝነኝ፤ በውስጡ ያለውን ሙያተኛና አዋቂ ሳስብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ነች ያስተማረችው፤ እውቀቱ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባዋል፡፡ የእነዚህን ልጆች እውቀትና ብቃት፣ ይሄ መንግስት መጠቀም አለበት፡፡
እርስዎ የወትድርና ሳይንስ ትምህርት የቀሰሙት የት ነው?
እኔ ወታደር ቤት የገባሁት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ሃረር ወታደራዊ በሚገባ ቀጥቅጬ ነው የተማርኩት፡፡ ጅግጅጋ ለሁለት ዓመት እስራኤሎች በደንብ አስተምረውኛል። እንደገና አሜሪካን ሃገር ሄጄ ለአንድ ዓመት ተኩል ተምሬያለሁ፡፡ ከዚያ ተመልሼም፤ ወደ ሶቭየት ሄጄ፣ ለብርጌድ አዛዥነት  ተምሬያለሁ። ከማልማትም ከስህተትም ደግሞ የተማርኩት ብዙ ነገር አለ፡፡ ታዲያ  ይሄን ሁሉ ትምህርት ይዤ ዝም ብዬ መሬት ልግባ? ማካፈል አለብኝ፤ ለወገኔ፡፡ እኔ የማስበው ደሞዙን አይደለም፤ ለሱ ችግር የለብኝም፤ ዋናው እውቀቱን ማካፈሌ ነው፣ እርካታ የሚሰጠኝ፡፡
 ሰራዊቱ፤ ህዝብ የኔ ነው ብሎ ሊመካበት ይገባል፡፡ ይሄ ሰራዊት የህዝብን ባህልና ጨዋነት መማር አለበት፡፡ በዚህ ለውጥ ውስጥ የኛ እውቀት ለምን ጥቅም ላይ አይውልም? የኛ የጀነራሎቹ ብቻ አይደለም፤ እዚህ ሰራዊት ውስጥ በርካታ ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች----አሉ፡፡ መንግስት ግን ይሄን አቅም አልተጠቀመበትም፡፡
 ኢህአዴግ ሲገባ እኮ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ያሉ ዶክተሮችን አባሮ የራሱን ነው ያስቀመጠው። ይሄ ምን ማለት ነው? እነዚያም እኮ በሀገራቸው፣ በቃል ኪዳናቸው ማገልገል ይፈልጋሉ፡፡ እኔ ወደ ሰራዊቱ የገባሁት፣ ለሃገሬ መስዋዕትነት ለመክፈል እንጂ ከሃገሬ ለመጠቀም አይደለም፡፡ እኛ ውስጥ ይሄ ነገር አሁንም አለ፡፡ እነዚህ ልጆች ጠባብ አመለካከት በውስጣቸው ስለሌለ ነው፣ ዛሬ ይሄን ማህበር የመሰረቱት፡፡ ይሄን መንግስት ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ እኛ ቂም አልያዝንም። እኛ ለሃገር ነው የቆሰልነው፡፡ ለሃገር ነው የተገፋነው፡፡ ኢትዮጵያ ብለን ነው የተሰለፍነው። ስለዚህ መንግስት ይጠቀመን፤ እኛም ማገልገል እንፈልጋለን፡፡


-------------------


            “መንግስት ከጠራን፣ ለሃገራችን የማንሆነው የለም”
             (መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ)


    መጀመሪያ ራስዎን ያስተዋውቁ?
ከ1973 ዓ.ም እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ በተራ ወታደርነት በ21ኛ ክፍለ ጦር ውስጥ አገልግያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም የእጩ መኮንንነት ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ ወርሶ ጦር ትምህርት ቤት ገብቼ ተማርኩ፡፡ እዚያው ተምሬ እዚያው አስተማሪ በመሆን እስከ መጨረሻው ማለትም እስከ 1983 በአስተማሪነት አገልግያለሁ፡፡ አሁን የራሴን የፈርኒቸር ማምረቻ አቋቁሜ፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርቻለሁ። “ቱ አር ኤንድ ሰለሞን ፈርኒቸር” የተሰኘው ድርጅት ባለቤት ነኝ፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊት ማህበር እንዴትና ለምን አላማ ተቋቋመ?
ማኅበሩን ለማቋቋም የተነሳነው ባለፉት 27 ዓመታት አንድ ላይ የነበርን የሰራዊት አባላት መሰባሰቢያ መድረክ አልነበረንም። መደራጀት ስለማይቻል ሳንደራጅ ቆይተናል፡፡ አሁን ግን የተፈጠረውን ለውጥ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊነነታችን መደራጀት አለብን ብለን ነው ማህበሩን የመሰረትነው፡፡ እያንዳንዳችን በሚገባ እንተዋወቃለን፡፡ አሁን ደግሞ ይሄ ማህበር እንደ እድርም እንደ ማህበርም እንደተደራጀ ኃይልም ሆኖ ያሰባስበናል፡፡ እኛ ወታደሮች ነን፡፡ የተደራጀ የተጠንቀቅ ኃይል መሆን አያቅተንም፡፡ ግፋ ቢል የ2 ወር ልምምድ ነው የሚያስፈልገን፡፡ መንግስት በዚህ የሪፎርም ሂደት ውስጥ እገዛ ከፈለገ ዝግጁ ነን፡፡ እኛ ለማኝ እንድንሆን የታሰበልን ሰዎች ነበርን፡፡ ዛሬ በጥንካሬያችን እዚህ ደርሰናል። በዚህ ጥንካሬያችን ላይ ደግሞ ህብረት ሲኖረን የበለጠ ውጤታማ እንሆናን፡፡
በዋናነት የዚህ ማኅበር አላማ ምንድን ነው?
ማህበራዊ ጉዳያችንን ነው የምንከውንበት፤ ነገር ግን መንግስት የኛን እገዛ ከፈለገ ሃገራችንን በቀናነት ለማገዝ ዝግጁ ነን፡፡ እኔ ለምሳሌ ቶፖግራፈር ነኝ፡፡ ከፍተኛ ውጤት ስለነበረኝ ነው ጦር ት/ቤት በአስተማሪነት የቀረሁት፡፡ አሁን እውቀቴ ከተፈለገ ከኢንቨስትመንቱ በላይ እውቀቴን ለማካፈል ዝግጁ ነኝ፡፡ ሃገሬን በዚህ ሙያ ለማገልገል ወደ ኋላ አልልም፡፡ እንደገና ግባና አስተምር ብባል፣ ከሃገሬ የሚበልጥብኝ የለም፡፡ ስለዚህ አገለግላለሁ፡፡
የማኅበሩ መስራቾች ምን ያህል ናችሁ?
ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው የተራራ ክፍለ ጦር አባላት ነን፡፡ 70 ያህል እንሆናለን፡፡ በኋላ ግን ሌሎች የሰራዊቱ አባላት መጥተው፤ “ለምን ሃገር አቀፍ አይሆንም” የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ይሄን ሃሳብ ተቀብለን፣  ሁሉንም የጦር ሰራዊት አባላት የሚያሰባስብ ማኅበር ነው የመሰረትነው፡፡
በምስረታው ላይ ከታዋቂ የሰራዊቱ አባላት እነማን ተገኝተዋል?
በርካታ ትልልቅ የሰራዊቱ አባላት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ ነበሩ፡፡ ለኛ ጀነራል ካሣዬ፤ ጀነራልነታቸው ያንስብናል፣ እሳቸው ለኛ  ማርሻል ናቸው፡፡ ትልቅ ክብር የሚገባቸው ናቸው። በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ታላላቅ ባለሀብቶች አንዱ የሆኑት መቶ አለቃ በላይነህ ክንዴም ተገኝተዋል። መቶ አለቃ በላይነህ ክንዴ፤ የኔ ተማሪ ነው፡፡ እኔ ነኝ ውርሶ ላይ ያስተማርኩት፡፡ በእለቱ ተገኝቶ ለማኅበሩ ምስረታ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ በአስመጪነት የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት መቶ አለቃ እድሜአለም እጅጉና ሌሎችም ዛሬ ጥሩ የሃብት ደረጃ ላይ የሚገኙ በምሥረታው ላይ ነበሩ፡፡  
ማህበራችሁ እነማንን ያካትታል?
የቀድሞ የሰራዊት አባላትን በሙሉ ለማካተት ነው ያቀድነው፡፡ ትልቁ አላማ መረዳዳት ነው። ምናልባት ትልቅ አክሲዮን ለወደፊት ልናቋቁም እንችላለን፡፡ ይሄ ሰራዊት “እምዬ ኢትዮጵያ” ብሎ ለሃገሩ ሲዋጋ የኖረ ነው፡፡ እውነተኛ የሃገር ፍቅር ስሜት ያለው ነው፡፡ እኛ የሃገር ፍቅር ያለን ወታደሮች ነን፡፡ የውጊያ እውቀቱ አለን፡፡ መንግስት አግዙኝ ብሎ ከጠራን፣ ለሃገራችን የማንሆነው የለም፡፡ አሁን ጥሩ አላማ ያለው መሪ ነው ያለን፤ ከጠራን ሁላችንም ዝግጁ ነን፡፡
የዚህ ማኅበር አባል የሚሆኑት እነማን ናቸው ?
መከላከያ ተብሎ የሚጠራው የባህር፣ የምድርና የአየር ኃይል አባላትን ያካትታል፡፡ ፖሊስም ለምን አይካተትም የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ ውይይት ይደረግበታል፡፡


Read 1477 times