Monday, 12 November 2018 00:00

‘ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንደተመለደው አይደል የሚባለው…እንደተለመደው ምስኪን ሀበሻ ብሶቱን ይዞ አንድዬ ዘንድ ብቅ ብሏል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አኔ ምስኪኑ ፍጥረትህ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— (ይቆጣል)  አሁን ደግሞ ምን ፈለግህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ተቆጣኸኝ እኮ፣ ምን አጠፋሁ?
አንድዬ፡— አሁን ሌላውን ነገር ተወውና፣ ምን ፈልገህ ነው የመጣኸው! እኔን ከልባቸው የሚፈልጉ እየጠበቁኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡—  እኔ ስንቱ ነገር ግራ ገብቶኝ፣ አንተ ዘንድ ብመጣ አመረርክብኝ እኮ፡፡ አንተ አንኳን እዘንልኝ እንጂ! 
አንድዬ፡— አሁንም እንዲሁ ናችሁ፣ አሁንም የሚያዝንላችሁ ነው የምትፈልጉት፣ አሁንም አብሯችሁ ፍራሽ አንጥፎ የሚቀመጥ ነው የምትፈልጉት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ… ከእኔ በፊት ያበሳጨህ አለ እንዴ? እንዲህ ተቆጥተኸኝ አታውቅም፡፡
አንድዬ፡— ለምን እንደሆነ ልንገርህ…የእናንተ ነገር ቆመ ስለው እየወደቀ፣ ተረጋጋ ስለው እየደፈረሰ፣ ተሳሳማችሁ ስል እየተነካከሳችሁ ምን እንደማደርግ ግራ ስለገባኝ ነው፡፡ ምን እንደምትፈልጉ፣ ምን እንደማትፈልጉ ግራ ስለገባኝ ነው፡፡ አሁንስ ገባህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ገብቶኛል አንድዬ፡፡ ለዚህ ነው እኮ አንተን የምንለምነው፡፡
አንድዬ፡— (ወደ ምድር ይመለከታል፡፡ ሁለት ሰዎች አፍ ለአፍ ገጥመው እያወሩ ነው፡፡)  እነኛ ሰዎች የሚሉትን ስማ፡፡
“ስማኝ፣ ምንድነው የምሰማው!”
“ምን ሰማህ?”
“አንተ ትነግረኛለህ ብዬ ጭራሽ እኔን ትጠይቀኛለህ!”
“ጫፉን እንኳን ሳትነግረኝ እንዴት ብዬ ልወቅልህ!”
“ስማ…ሰዎቹ ምን እየሆኑ ነው! አልተስማሙም አሉ…”
አንድዬ፡— አየህ አይደል…ሊተዋችሁ ያልቻለ ችግር ይሄ “አሉ” የምትሉት ነገር ነው፡፡ እኔ ራሴ በዓይኔ አይቻለሁ፣ እኔ ራሴ በጆሮዬ ሰምቻለሁ ስትሉ ሰምቻችሁ አላውቅም፡፡ ሁልጊዜም  “አሉ” ነው.፣ ሁልጊዜ “እነ እከሌ ሲሉ ሰማሁ፣” ነው፡፡ እውነት ይሁን ሀሰት ሳታረጋግጡ በምትበትኑት ወሬ፣ እየተተረማመሳችሁ፣ እኔን ምን ሁን ነው የምትሉኝ! እነኛን ደግሞ እያቸው፡፡
“የሰማሁትን ወሬ ብነግርሽ ኡ! ኡ! ነው የምትዪው።”
“ምን ሰማሽ?”
“ኸረ ጉድ ነው፡፡ ሥራ አስኪያጃችንን ታውቂው የለ…”
“ይሄ አዲስ የተሾመውን ነው የምትዪው?”
“እሱን…”
“ደግሞ ከመምጣቱ ምን ሆነ?”
“ዘሩ ምን እንደሆነ ብነግርሽ አገር ጥለሽ ነው የምትሄጂው፡፡”
አንድዬ፡— አየህ፣ የምለው ገባህ! እሺ ምስኪኑ ሀበሻ ምን ትላለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ስለ ምኑ አንድዬ?
አንድዬ፡— አሁን ስለ ሰማኸው ነዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ አንድዬ…ማለት አሁን እኮ ሰው ሲሾም መጀመሪያ የምንጠይቀው ነው!
አንድዬ፡— እኮ ለምን? ስለ ዘሩ ከመጠየቃችሁ በፊት ለምን ስለ ችሎታው አትጠይቁም! ለምን መጀመሪያ ሰውዬው ለተሰጠው ቦታ ብቁ መሆን አለመሆኑን፣ የተጣለበትን ሀላፊነት ሊወጣ የሚችል ወይም የሚከብደው መሆኑን፣ ባህሪው መልካም መሆን አለመሆኑን፣ ህዝብ የማገለገል ፍላጎት ያለውና የሌለው መሆኑን አትጠይቁም!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱማ ልክ ነህ…አንዱ ችግራችን እሱ ነው፡፡
አንድዬ፡— አየህ አይደል፣ ብዙዎቻችሁ አፍ ለአፍ ገጥማችሁ ስታወሩ ነው ጊዜያችሁን የምታባክኑት፡፡ ወሬ ላይ ነው፡፡ አሉባልታ ላይ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ፣ ብዙ ነገሮች እየተካሄዱ ስለሆነ፣ እንዲህ እያወራን ካልሆነ መረጃ ስለማናገኝ እኮ ነው!
አንድዬ፡— እኔ መረጃ አትለዋወጡ አላልኩም።  የምትለዋወጡት መረጃ አሉባልታና ከሚያፋቅር ይልቅ ለምን የሚያጋጭ ይሆናል እያልኩ ነው፡፡ አሁንማ ይሄ ማህበራዊ ሚዲያ የምትሉት ነገር ጭራሽ አባሰባችሁ መሰለኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እሱ ነገር እኮ የእኛ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ችግር ነው፡፡
አንድዬ፡— አየህ! አየህ አይደል! ሁልጊዜም እንዲሁ ነው፡፡ ራሳችሁን ችላችሁ እንደ መቆም አብሯችሁ የሚወነጀል፣ አብሯችሁ ጣት የሚቀሰርበት ትፈልጋላችሁ፡፡ እኔ እያወራሁ ያለሁት ስለ እናንተ፣ አንተ ደግሞ መላው ዓለም ትለኛለህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለህ፣ እኛም አኮ የዓለም አካል ስለሆንን፣ ሌላ ስፍራ የተደረገው እኛም ዘንድ ቢመጣ አይገርምም፡፡ ጊዜው እኮ የግሎባላይዜሽን ነው፡፡
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ይስቃል፣ ሳቁን መቆጣጠር ያቅተዋል፡፡)
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን እየሆንክ ነው!  ትን እንዳይልህ እኮ ፈራሁ!
አንድዬ፡— ትን ብሎኝ አበቃ እኮ… ግሎባላይዜሽን ነው ያልከኝ! አንድ ተረት አለቻችሁ…  ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አይደል የምትሉት… እናንተ እኮ በቅጡ ለመኮነንም አስቸጋሪ ሆናችሁብኝ፡፡  ግሎባላይዜሽን ነው ያልከኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ ጊዜው እኮ ዓለም አንድ እየሆነች ያለችበት ነው፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ…እንኳን ነገርከኝ፣ የሚገርምህ ይህን ነገር እስከ ዛሬ አላውቅም ነበር፡፡ ስማ…መቼም ዛሬ ተረት፣ ተረት ብሎኛል…ዶሮን ሲያታልሉዋት በመጫኛ ጣልዋት አይደል የምትሉት! የደላው ፈረንጅ የሚሰብካችሁን ሁሉ እየተቀበላችሁ ማስተጋባት የምታቆሙት መቼ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ድሆች ነን፣ ደግሞ ድሃ ምርጫ የለውም፡፡
አንድዬ፡— እስቲ ልጠይቅህ…  ግሎባይዜሽን፣ ግሎባላይዜሽን ትላላችሁ፡፡  መጀመሪያ ነገር እናንተ ራሳችሁ በተራራና መንደር እየተቧደናችሁ፣ አብሮ መኖር እያቃታችሁ ስለ ግሎባላይዜሽን ትነግረኛለህ! (ወደ ምድር ያመለክታል፡፡) እነኛን ተመልከታቸው፡፡
(በርከት ያሉ ሰዎች ቆመጥና የተለያዩ ስለታማ ነገሮች ይዘውና እየጮሁ፣ ወደ አንድ መንደር ውስጥ እየገቡ ነበር፡፡)
አንድዬ፡— እነኚህ ወዴት እየሄዱ ይመስልሀል? እኔ እነግርሀለሁ፣ አብረዋቸው ስንት ዘመን የኖሩና የተጋቡ፣ የተዋለዱ ጎረቤቶቻቸውን፤ ስንት ዘመን ከኖሩበት ቤታቸው ሊያባርሩ ነው፡፡  አንተ ደግሞ ስለ ግሎባላይዜሽን ታወራልኛለህ፡፡ እነኛን ደግሞ ተመልከታቸው…
ምስኪን ሀበሻ፡— ሰብሰብ ያሉ ሰዎች መንገድ መሀል ላይ አጠና፣ ድንጋይና የመሳሰሉ ነገሮች እየደረደሩና እየበተኑ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ምን እያደረጉ ይመስልሀል? እኔ እነግርሀለሁ… መንገድ እየዘጉ ነው፡፡ ሰማኸኝ? የተዘጋ መንገድ እየከፈቱ ሳይሆን፣ የተከፈተ መንገድ እየዘጉ ነው፡፡ ሰው በገዛ አገሩ እንደ ልቡ እንዳይዘዋወር፣   ምግብና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳያልፉ መንገድ እየዘጉ ነው፡፡ ልብ በል፣ አገር የደፈረ፣ ድንበር የጣሰ ወራሪ ጠላት ላይ ሳይሆን ከአንድ ማእድ አብረዋቸው ሲጎርሱ የነበሩ ወገኖቻቸው ላይ ነው እንዲህ የሚደረገው። አንተ ደግሞ እዚህ ግሎባላይዜሽን ትለኛለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ለዚህ፣ ለዚህ ነው እኮ ዘንድሮ ግራ ግብት ያለን!
አንድዬ፡— ስማ ደግሞ ሌላ ነገር፣ የየአገሩን ስም እየጠራችሁ፣ ከእነሱ ጋር አብራችሁ ስለ መኖር፣ ስለ ወንድማማችነት ስታወሩ ምን ይገርመኛል መሰለህ…  ምን ይገርምሀል ብለህ ጠይቀኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ይገርምሀል?
አንድዬ፡— መጀመሪያ እናንተ ራሳችሁ ለስንት ክፍለ ዘመናት የነበራችሁን ወንድማማችነት የሚያፈርሱ ሥራዎች እየሠራችሁ፣ መሬቱን ከፋፍዬ የእድሜ ልክ እርስታችሁ ነው ብዬ የሰጠሁዋችሁ ይመስል “ከመንደሬ ውጣ፣ ወደ መጣህበት ተመለስ” እየተባባላችሁ፣ ድንበር ተሻግራችሁ ከሌላ አገር ጋር ስለ ወንድማማችነት ታወራላችሁ! እርስ በእርስ እየተሳደዳችሁ ስለ ግሎባላይዜሽን ታወራላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ዛሬ አስቆጣሁህ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— ምን አስቆጣኝ! ይልቅ አንድ መልዕክት ለወዳጆችህ ይዘህልኝ ሂድ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— በደስታ አንድዬ፣ በደስታ፡፡
አንድዬ፡— ምን ትላቸዋለህ መሰለህ… ‘ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…’ በላቸው፡፡ በል ደህና ሁን፡፡
(ምስኪን  ሀበሻ፤ ሪፖርቱን ይዞ እሰኪመለስ እየጠበቅነው ነው፡፡)
ደህና ሰንብቱልኛማ!

Read 4407 times