Saturday, 10 November 2018 13:11

በጋምቤላ ባለሃብቶች፤ የሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር ለሥራችን ማነቆ ሆኖብናል አሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

- የመንግስት ኃላፊዎች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም
 - “መንግስት በወጪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም አለው” - የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ
      
    በጋምቤላ ክልል በወጪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች፤ በክልሉ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና፣ለሥራቸው ማነቆ እንደሆነባቸው ተናገሩ፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግራችንን የማይፈታልን ከሆነ፣ የጀመርነውንና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰስንበትን የልማት ሥራ አቋርጠን ለመሄድ መገደዳችን አይቀርም ብለዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሰሊጥ፣ በጥጥ፣ በማሽላና በበቆሎ ልማት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ አገር በመላክ ላይ የሚገኙት እነዚህ ባለሀብቶች፤ “የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች፤ ከህግና ስርዓት ውጪ ያጉላሉናል፣ ገንዘብ እንድንከፍል ይጠይቁናል፣ ያስሩናል፣ ንብረቶቻችንን ይቀሙናል” ሲሉ በደሎቻቸውን ገልጸዋል፡፡
 ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ የሆነውን፣ ሰሊጥና ማሾ የተባለ የቅባት እህል የሚያመርቱት አቶ ጉአይ ሲሳይ የተባሉ ባለሀብት እንደሚናገሩት፤ በክልሉ አቦቦ ወረዳ ላይ ላለፉት 4 ዓመታት በዚሁ ዘርፍ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በወረዳው የሥራ ኃላፊዎች የሚፈፀሙባቸው የተለያዩ በደሎችና ህገወጥ ተግባራት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በመምጣቱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት ያፈሰሱበትን የእርሻ ልማት  ጥለው ለመሄድ የሚገደዱበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ይገልጻሉ።  
“በማሳው ላይ ያለውን ደን በመመንጠር ለልማት ሥራ ላይ እንዳውለው ከተሰጠኝ 500 ሄክታር መሬት ላይ 240 ሄክታሩን ካለማሁ በኋላ ቀሪውን ማሳ ለማልማት ምንጣሮ ስጀምር አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ” ይላሉ፤ ባለሃብቱ፡፡ በማሳው ላይ የሚገኘው ዛፍ ያለ ጥቅም እየተመነጠረ አመድ ከሚሆን ከሰል በማድረግ ለወረዳው፣ ለህብረሰቡና ለራሳቸውም ጭምር ገቢ ለማስገኘት በማቀድ፣ ከወረዳው ፈቃድ አውጥተው ሥራውን እንደጀመሩ ያስረዳሉ፡፡
በተሰጣቸው ፈቃድ መሰረትም፤ ከሰሉን እያመረቱ መሸጥ ይጀምራሉ። ብዙም ሳይቆይ ግን ችግር ተፈጠረ ይላሉ፤ ባለሃብቱ አቶ ጉአይ። የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች፤ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት በተዘራውና ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ በሚጠበቀው የማሾ ማሳ ላይ፤ በህገወጥ መንገድ ገልባጭ መኪናቸውን እየነዱ በመግባት፣ የከሰል ምርቱን እየጫኑ ይወስዳሉ ሲሉ ከስሰዋል፡፡ እስካሁንም ከ10ሺ ኩንታል በላይ የከሰል ምርት ከማሳቸው ላይ በሃይል መወሰዳቸውን  ተናግረዋል፡፡
በማሾ ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሌላው ባለሃብት በበኩላቸው፤”የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች፣ ከራሳቸው ፍላጐትና ፍቃድ ውጪ የሆነ ማንኛውንም ሃሳብ ለማድመጥም ሆነ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ ፈጽሞ ፍላጐት የላቸውም” ብለዋል፡፡ “ባለሃብቱ ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሰሰበትን የእርሻ ልማት ጥሎ ለመሄድ ስለሚቸገር፣ ክፈል የተባለውንና የታዘዘውን ሁሉ እያደረገ ለመቆየት ይሞክራል፡፡ በዚህ አካባቢ ሙስና ህጋዊ ፈቃድ ያለው ነው የሚመስለው፤ ያለ ገንዘብ የሚፈፀም አንዳችም ነገር የለም” ሲሉ ባለሃብቱ በምሬት ተናግረዋል፡፡   
በወረዳው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው 126 ባለሀብቶች መካከል 34 ያህሉ መሬቱን ተረክበው መጥፋታቸውን የገለፁት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ ባለሃብቶቹ የጠፉበትን ምክንያት ተጠይቀው አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል - “እሱ እናንተን የሚመለከት አይደለም” በማለት፡፡
ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷ እያሽቆለቆለ በመሄድ እጅግ አነስተኛ በሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆሙት የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራአቱ መለስ፤ ለዚህም ምክንያቱ በምርት ጥራት፣ ብዛትና አይነት ተወዳድሮ በማሸነፍ፣ በቂ የሆነ ምርት ለመላክ ባለመቻላችን ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የውጪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለመደገፍ  ቁርጠኛ አቋም ይዟል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤በዚህ የተነሳም ችግሩ በነበረበት ሁኔታ አይቀጥልም ብለዋል፡፡

Read 1192 times