Monday, 12 November 2018 00:00

የቀድሞው የኢህአፓ የጦር ሠራዊት አመራር ምን ይላሉ? (ስለ ህወሓት በስፋት ይነግሩናል )

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የተወለዱት አዲ - ኢሮብ ትግራይ ነው። የኢሮብ ማህበረሰብ አባል ናቸው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን  እዚያው ኢሮብ የካቶሊክ ት/ቤት ነው የተከታተሉት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲግራት ተማሩ፡፡ በአንድ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የፍልስፍና ትምህርት ጀምረው ነበር፡፡ በ1967 ዓ.ም ግን የኢህአፓ የትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድንን አዲ-ኢሮብ ላይ ተቀላቀሉ፡፡ 20 ያህል የአዲ-ኢሮብ ተወላጆችም፤ በዚያው ዓመት  ኢህአፓን ተቀላቅለዋል፡፡
የኢህአፓን ጦር ሠራዊት ታሪክ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የሚነገርላቸው አቶ በየነ ገብራይ፤ ስለ ሠራዊቱ በርካታ መጣጥፎችን አስነብበዋል። የቀድሞ የኢህአፓ ጦር አመራር አቶ በየነ፤ ድርጅታቸው ከህወሓት ጋር ስለነበረው ቅራኔ እንዲሁም የማሳደድ ታሪክ ይነግሩናል። ድርጅታቸው ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ለምን ተፈረደበት? ኢህአፓ በትግራይ ለምን እንደ ጭራቅ ተሳለ? ስለ ጎሳ ፖለቲካ ምን ይላሉ? የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነትስ በተመለከተ? በእነዚህና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡-

    የኢህአፓን ሠራዊት እንዴት እንደተቀላቀሉት ይንገሩኝ? የሠራዊቱ የመጀመሪያ የጦር እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር?
የመጀመሪያው የኢህአፓ ጦር ሠራዊት ማረፊያው፣ አዲ-ኢሮብ ውስጥ የሚገኘው አሲምባ ተራራ ነበር፡፡ ተራራው በተፈጥሮው ለመሸሸጊያ አስፈላጊ የሚባሉት እንደ ውሃ፣ ፍራፍሬዎችና እጽዋት መገኛ ነው፡፡ ከድሮም ጀምሮ የኢሮብና የአጋሜ አርበኞች ዋነኛ መሸሸጊያ የነበረ ተራራ ነው፡፡ የአዲ- ኢሮብ ነዋሪም በወቅቱ የኢህአፓን ሠራዊት “ኢህአሠ” ብሎ አይጠራም ነበር፤አሲምባ ነበር የሚለው፡፡ ምክንያቱም ኢህአሠ የመጀመሪያ ቋሚ መስፈሪያውን ያደረገው አሲምባ ላይ ነው። አሲምባ የኢህአሠ ታሪክ ጅማሮ ቦታ ነው። ኢህአሠ የመጀመሪያ ተኩስ የተኮሰው ግን ዛላንበሳ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ኦፕሬሽን የተካሄደው የዛላምበሳ ወረዳ አስተዳደርና ፖሊስ ላይ ነው፡፡ በወቅቱ ብዙም ውጤት አልተገኘም፤ ነገር ግን ኢህአሠ ራሱን የሚያስተዋውቅበትን ወረቀት በትኗል። በዚህ ሁኔታ እንግዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ስንንቀሳቀስ ነበር፡፡ በኋላ እኔ ወደ ሱዳን አቀናሁ፤ በ1973 ዓ.ም፡፡
ለምን ነበር የሄዱት?
በሱዳን የኢህአፓ መዋቅር ውስጥ ለመስራት ነው፡፡ አንድ የትጥቅ ትግል የሚያደርግ ቡድን፣ ወደ ውጪ የሚወጣበት ኮሪደር ያስፈልገዋል፡፡ እኛም ከውጪው ጋር ለመገናኘት ሱዳንን ነበር የመረጥነው፡፡ ከውጭ ለሚገኘው ግንኙነት፣ ሱዳን ዋናው መናኸሪያችን ነበር፡፡ ጦራችን በፀለምት አርማጭሆ በሰፊው ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ እኔ በ1973 ወደ ሱዳን ስወጣ ቆስዬ ነበር፡፡ ስለዚህ ሱዳን ሆኜ ከዓለም ሃገራት ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ሳግዝ ነበር፡፡ ሱዳን ደግሞ እንደሚታወቀው፣ ሰፊ የኢትዮጵያን ስደተኛ ይዛ ነበር፡፡ ሱዳን ላይ ሰፊ መዋቅር ነበረን፡፡ ገዳሪፍና ምስራቅ ሱዳን አንድ ዞን፣ ካርቱምና አካባቢዋ ደግሞ ሌላ ዞን ነበር። በሁለቱ ዞኖች ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ አንደኛ፤ ስደተኞችን እናደራጃለን፣ ሁለተኛ፤ ከውጪ አካላት ጋር እንገናኛለን፣ ሦስተኛ፤ ቋራ ላይ ካለው ጦር ጋር እንገናኛለን፡፡ ሱዳን ለትግላችን ምርጥ ቦታ ነበር፡፡ ሱዳን ሆነን ሀገር ቤት ካሉ የተለያዩ ከተሞች ጋር ግንኙነት እናደርግ ነበር፡፡ በወቅቱ ሱዳን የብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች መናኸሪያ ነበረች፡፡
በ1981 ዓ.ም ሱዳን ውስጥ ኢዲዩና ኢህአፓ፣ ከህወሓት ከወጡ አባላትና ከአቶ አረጋዊ በርሄ ጋር ሆነን አንድ ግንባር ፈጥረን ነበር፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ ሀገሪቱ ምን ትሁን በሚለው ላይ ሠፊ ምክክር ስናደርግ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሱዳን አንደኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነበረች፡፡ በኋላ ግን ህወሓት፤”ኢህአፓ የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መታየት የለበትም” በማለቱ፣ ድምጽ ሳይሰማ፣ የሱዳን መንግስት እንዲያጠፋን ተደርጓል፡፡
እንዴት?
ደርግ መውደቁ ሲታወቅ ኢህአፓን  ከህዝቡ ለማጥፋት፣ ለሱዳን መንግስት ህወሓት ገንዘብ ሰጥቶ፣ እኛ እንድንጠፋ ተደርገናል፡፡ ምክንያቱም በውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ ስልጣን ሁሉ ተጠራርጐ ለህወሓት መሰጠቱን፣ ሱዳን ሆነን ስንቃወም ነበር፡፡ ለዚህ ነው ኢህአፓ ድምጽ ሳይሰማ እንዲጠቃ የተፈረደበት፡፡ ኢህአፓ ሱዳን ውስጥ በርካታ ንብረቶች ነበሩት፡፡ ተሽከርካሪዎች፣ ማተሚያ ማሽኖች እንዲሁም ድርጅቱን ለመደጐም ለንግድ ስራ የምንጠቀምባቸው ንብረቶች ነበሩን፡፡ እነሱ ሁሉ እንዲወረሱ ተደረገ፡፡
ማን ነው የወረሰው?
አስወራሾቹ ህወሓት እና ሻዕቢያ ናቸው፡፡ ወራሹ ደግሞ የሱዳን መንግስት ነው፡፡
ከዚያ በኋላ የእናንተ ዕጣ ፈንታ ምን ሆነ?
ይኸ ሴራ ከተጠነሰሰብን በኋላ ንብረታችን ተወርሶ እኛን ማሳደድ ጀመሩ፡፡ እጃቸው የገባነውን አሠሩን፡፡ ሌሊት ላይ ከየቤታችን ታፍነን ታሠርን። ያሣፈነን ህወሓት ነበር፡፡ መተማ ላይ የሱዳን ደህንነታቸው፣ ለህወሓት ደህንነት አስረከቡን፡፡ ከዚያ በኋላ ህወሓት፤ መተማ ላይ ለሶስት ወራት አሠረን፡፡ በኋላም ወደ ትግራይ ባዶ ስድስት እስር ቤት አዘዋወሩን፡፡ በዚያም ለሰባት ወር አሠሩን። ይሄ ሁሉ ሲፈፀም ማንም አያውቅም፤ ክስ አልተመሠረተም፡፡ በኋላ መታሠራችን በአለማቀፍ ደረጃ ሲሰማ መቐሌ በሚገኘው ትልቁ እስር ቤት ውስጥ በግልፅ እንድንታሰር ተደረገ፡፡ በኋላም ወደ ጐንደር አዘዋውረውን፣ ባታ የሚባል እስር ቤት ውስጥ የቀረውን ጊዜ አሳለፍን፡፡
የእስር ቤት  አያያዛችሁ ምን ይመስል ነበር?
ፍ/ቤት ያመላልሱን ነበር፡፡ ለ22 ጊዜ አመላልሰውን፣ ነገር ግን ፍ/ቤቱ የሚለን ነገር የለም፤ ዝም ብለን ደርሰን ወደ እስር ቤት እንመለስ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ “እኛ ከሱዳን ነው ታፍነን የመጣነው” አልን፡፡ ግን የተሠጠን ምላሽ የለም። በኋላ ተስፋ ቆርጠን፣ ኑሮአችንን ሁሉ እስር ቤት ውስጥ ለመመስረት ራሣችንን አሳምነን ሳለ፣ በድንገት አንድ ቀን “ተፈታችኋል፤ ከእስር ቤት ውጡ” አሉን፡፡ ከወጣችሁ በኋላ ወዴት ነው የምትሄዱት ብለው ጠየቁን፤ እኔ “ወደ ትግራይ ሄጄ ቤተሰቦቼን ማየት እፈልጋለሁ” አልኳቸው። ሌሎቹ “ወደ አዲስ አበባ ነው የምንሄደው” አሉ፡፡ እኔን “ወደ ትግራይ አትሄድም አሉኝ። ከለከሉኝ። አዲስ አበባ ከመጣን በኋላም ቀን ከሌት ክትትል ያደርጉብን ነበር፡፡ በሀገሬ ተስፋ አጥቼ፣ ቤተሰቤንና ራሴን ከማሰቃይ አልኩና፣ ወደ ልጆቼ ሄድኩ፡፡  
ለምንድን ነው ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ የተከለከሉት?
በግልፅ አልተነገረኝም፡፡ ነገር ግን ለቤተሰቦቼ እንድታይ አልተፈለገም፡፡ በህይወት አሉ የሚባለው ነገር እንዲሰማ አይፈለግም ነበር፡፡ የኛ መኖርን የትግራይ ህዝብ እንዲያውቅ አይፈለግም። አሁንም ድረስ እንደማይፈለግ፣ ከ24 ዓመት በኋላ ስመጣ ተረድቻለሁ፡፡ ስለ ኢህአፓ የትግራይ ህዝብ የሚያውቀው መጥፎ መጥፎውን ነው፡፡ ግን ኢህአፓን የመሠረቱት በአብዛኛው የትግራይ ልጆች ነበሩ። አሁንም  ኢህአፓ በትግራይ ህዝብ፣ እንደ አውሬ ተስሎ ነው ያለው፡፡ እውነተኛው ማንነቱ እንዲነገር አይፈለግም፡፡
ከውጭ  ከመጡ በኋላ ወደ ትግራይ ሄደዋል? ከሄዱስ ምን ታዘቡ?
በመሃል ሀገር ብዙም የታዘብኩት ነገር የለም፤ ነገር ግን ትግራይ ውስጥ ስለ ኢህአፓ የሚያውቅ ማንም  የለም፡፡ ወጣቱ ትውልድ፤ ሙሉ ለሙሉ “ኢህአፓ ማለት ጭራቅ ነው” በሚል የህወሓት ትርክ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የህወሓትን ውሸት እንደ እውነት ተቀብሎ፣ ኢህአፓን በጭራቅነት ስሎ እንዳለ ለማየት ችያለሁ፡፡ በዚህም በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡ እኔ ወደ አካባቢው መሄዴ እንዲሁም  በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽሑፎች ማቅረቤ  በራሱ ጥሩ ስሜት አልፈጠረም፡፡
ትግራይ ውስጥ ምን  ያህል አንድ አይነት ርዕዮተ አለምና አስተሳሰብ እንደሰረፀ ተረድቻለሁ፡፡ ኑሮ ደግሞ በህብረተሰቡ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳረፈበት ተገንዝቤያለሁ። በዚያው ልክ በአብዛኛው የማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ኢትዮጵያዊነት አሁንም መሠረት የያዘ መሆኑንም ተረድቻለሁ፡፡ እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ኢትዮጵያን ነው የማውቀው፡፡ በጣም ጥቂቶች ናቸው በብሔር ጠበው የነበሩት፡፡ አብዛኛው፤ ያለው ብሔራዊ ጭቆና፣ በኢትዮጵያዊነት ስር ሊፈታ ይችላል የሚል አመለካከት ነበረው፡፡ አሁን ግን ማንኛውም ወጣት መጀመሪያ የሚያየው ብሔሩን ነው፡፡ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ የሚለውን ለመናገር ነው የሚቸኩለው። ይሄ የህወሓት መራሹ መንግስት ውጤት ነው። ህወሓት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ህወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲነግስ ያደረገው የመንግስቱ ኃ/ማርያም (ደርግ) ቡድን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ቅድሚያ ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ሃይል አጥፍቶ ነው፣ አገሪቱን ለብሔርተኞች  የዳረገው። የሃገር ሉአላዊነትን አፍራሽ ሰዎች የበላይነቱን ለማግኘታቸው፣ የመንግስቱ ኃ/ማርያም ቡድን ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡
አሁን በሀገሪቱ የተጀመረውን የፖለቲካ ለውጥ እንዴት ይመለከቱታል?
ለውጡ መምጣቱ ተገቢ ነው፡፡ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡ ሙሉ ለሙሉ በለውጥ ፈላጊዎቹ እጅ ነው ያለው ለማለት ይከብደኛል፡፡ ራሱ ስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ቡድኖች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ትተው፣ በብሔር የተደራጁ ሃይሎች ለለውጡ ፀር ናቸው፡፡ ብሔርተኛ ድርጅቶች ለለውጡ ትልቅ አደጋ እንደሆኑ ይታየኛል፡፡ ከዚህ ለመውጣት ህብረተሰቡ ኢትዮጵያዊነትን እንደገና የሚገነባበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ አንድነትን የሚፈልግና በብሔራዊ መግባባት የሚያምን የተማረው ሃይል የሚበረታ ከሆነ፣ ለውጡን ወደፊት ለማስቀጠል እድሉ አለ፡፡ ያ ካልተደረገ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፤ ተስፋና ስጋት የተቀላቀለበት ስሜት ነው ያለኝ፡፡
በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተጀመረውን አዲስ ግንኙነት የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ስለ ግንኙነቱ ምን ይላሉ?
እኔ በአጠቃላይ የተፈጠረውን ግንኙነት በበጐ ነው የማየው፡፡ የትግራይና የኤርትራ ህዝብ በመሠረቱ፣ በፍፁም በመሃከሉ ልዩነት የሌለው አንድ ህዝብ ነው። በዚያ ህዝብ መካከል አጥር ታጥሮ፣ ሠራዊት ሠፍሮ የነበረበት ሁኔታ ቀርቶ፣ ግንብ መፍረሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአጋጣሚ ኤርትራ ድረስ ሄጄ አይቸዋለሁ። ስሜቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እነ ዶ/ር ዐቢይ ሁኔታዎችን በቀናነት ለማየት እንደሚጥሩ ባምንም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ደንቃራ የነበረው የኤርትራ መንግስት ግን ምን ያህል ቀና ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ግን ትልቅ ግንብ ከህዝቡ መሃል መነሣቱ ትልቁ ቁም ነገር ነው፡፡ የኔ መሠረታዊ ጥያቄ፤ በግንኙነቱ ላይ ህዝቡ መማከር አለበት የሚል ነው፡፡ እነ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ፤ አሁን ድንበር ለማካለል አለመንቀሳቀሳቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ምን ድረስ ሊዘልቅ ይችላል የሚለውን  ከወዲሁ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በኤርትራ  በርካታ ንጹሃን ገበሬዎች አሉ፤ እነሱ የት ናቸው? መጠየቅ አለበት፡፡
እርስዎ ከኢሮብ ማህበረሰብ ነው የወጡት። ማህበረሰቡ በግንኙነቱ ላይ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
እንግዲህ የኢሮብ ማህበረሰብ ላለፉት 700 እና 800  አመታት የሚኖርበት ቦታ ይታወቃል። ያ ቦታ አሁን የአልጀርሱ ቡድን የተሠጠበት ነው። አንድ ሦስተኛ የሚሆነው መሬቱ፣ በሄግ ውሣኔ ወደ ኤርትራ ተካልሏል፡፡ አሁን ወደ ኤርትራ የተካለለው መሬትና ህብረተሰብ በአስተሳሰቡም፣ በስሜቱም፣ በስነልቦናውም አንድም ቀን ስለ ኤርትራዊነት አስቦ የማያውቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከደሙ የሠረፀን ማህበረሰብ፤ ወደ ኤርትራ ተከለል ማለት ከባድ ነው። ቢያንስ ከ10ኛው በላይ የሚሆነው በዚህ ውሣኔ ኤርትራዊ ሆኖ፣ የተቀረው ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል። ይሄን አናሣ ብሔር ለሁለት ይከፍለዋል። ያ ደግሞ በህልውና ላይ ትልቁን አደጋ ያመጣል፡፡
ለዚህ ነው እኔም ያለሁባቸው ሠላማዊ ሠልፎች በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱት፡፡ አሁንም በዚህ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ላይ የኢሮብ ማህበረሰብ ያለውን ጥያቄ አጠናክሮ ይገፋበታል። ለኢትዮጵያዊ አንድነት የተደረገው ትግል የተጀመረው ኢሮብ ነው፡፡ ኢህአፓን ከመሠረቱት አንዱ የሆነው ተስፋዬ ደበሣይ ኢሮብ ነው፡፡ አብዛኞቹ የኢህአፓ መስራቾች ኢሮቦች ናቸው። በርካቶችም በአባልነት በኢትዮጵያዊነት ትግል ላይ ተሠልፈው ተዋድቀዋል፡፡ ማንኛውም ኢሮብ ኢሮብነቱን ይወዳል፤ ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቅናል፡፡ ለዚህ ነው አሁን የተፈፀመው ስምምነት ስጋት ያጫረበት፡፡
ስለ ሀገርዎ ምን ያልማሉ? ምንስ ተስፋ ያደርጋሉ?
አሁን ኢትዮጵያን ለማዳንም ሆነ ለማጥፋት እድሉ ያለው በእጃችን ነው፡፡ የተሻለውን መምረጥ ነው ያለብን፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ምን አይነት ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው ብለን፣ የመፍጠር እድሉ በእጃችን ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መጠናከር ካለበት። ዘረኞችና ቡድንተኞች አሁንም የሚያሸንፉበት እድል ስለሚኖር፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ትግሉ ላይ ጠንክረው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ቂም በቀልነት አያስፈልግም፤ ይቅር ለእግዚአብሔር ብለን፣ ሁሉን  ትተን፣ ወደፊት መራመድ አለብን። ህወሓት የሄደበትን የጽንፈኝነት መንገድ መልሰን መጓዝ የለብንም፡፡ የህወሓትን መንገድ መሄድ ማለት፣ ሃገሪቷን የበለጠ ወደ ቁልቁለት መውሰድ ነው፡፡

Read 1952 times