Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 May 2012 11:08

“ማሪዮት በጥራት ጉዳይ ከማንም ጋር አይደራደርም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

* የአምና ገቢው ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው

* በ73 አገሮች 3700 ሆቴሎችና ሎጆች አሉት

* ዋና መ/ቤቱ 300ሺህ ያህል ሰራተኞች አሉ

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው 22ኛው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ስምንት የአፍሪካ መሪዎች የንግድ ሚኒስትሮች፣ ድርጅቶች የአፍሪካ ህብረትና መንግስታቱ ድርጅት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ኢኮኖሚስቶች…. ተሳትፈዋል፡፡ዎልማራት፣ ማሪዮት ኢንተርናሽናል ሚስትቡሽ… የመሳሰሉት ታዋቂ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የቢዝነስ ኩባንያ ኃላፊዎች ቢል ጌትና የመሳሰሉ ታዋቂ የዓለማችን ሀብታሞች የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች… በአጠቃላይ ከ700 በላይ እንግዶች በፎረሙ ታድመዋል፡፡

በኢኮኖሚክ ፎረሙ ላይ ንግግር ካደረጉት የቢዝነስ ሰዎች የማሪዮት ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ፕሬዚዳንትና የአስተዳደር ዳሬክተር ሚ/ር አሌክስ ኪሪያኪድስ አንዱ ናቸው፡፡ ሚ/ር ኪሪያኪድስ “የሆቴል ስራ የቱሪስቶችን ቁጥር በፍጥነት በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ያሳድጋል፤ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወር አዲስ ገቢ ያስገኛል” ብለዋል፡፡ ሚ/ር ኪሪያኪድስ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በኢኮኖሚ ፎረም ለመሳተፍ ብቻ አልነበረም፡፡ 313 ክፍሎች ያላቸው የሁለት ሆቴሎች ግንባታና አስተዳደር ውል ከሰንሻይን ኩባንያ ጋር ለመፈራረም ነበር፡፡ በስምምነቱ መሰረት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን 104 ክፍሎች ያሉት ማሪዮት ኤክስኪዩቲቭ አፓርትመንትና 209 ክፍሎች ያሉት ማሪዮት ኮርትያርድ ሆቴሎች ህንፃ ሲገነባ ሚሪዮት ኢንተርናሽናል ደግሞ በራሱ መስፈርት መሰረት ሆቴሎች ያስተዳድራል፤ የሕንጻዎቹንም የግንባታ ጥራት ይቆጣጠራል፡፡ ሚስተር ኪሪያኪድስ የሆቴሎች ግንባታና አስተዳደር ከሰንሻይን ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከአቶ ሳሙኤል ታፈሰ ጋር ከተፈራረሙ በኋላ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከመግለጫው በኋላ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

 

የሚሰሩት ሆቴሎች የጥራት ደረጃ ምን ይመስላል?

ጥራት አልከኝ? የዚች ዓለም ጥራት ለአንድ ምርት ወይም አገልግሎት መለያ (ብራንድ) ውጤታማነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ዕቃ ለመግዛት ፈለግህ እንበል - ያእቃ ለምሳሌ ቴሌቭዥን ቢሆን በተለያዩ መስፈርቶች ጥራቱ ከፍተኛ ነው ብለህ የምታምንበትን ( ሳምሰንግ፣ ሶኒ፣  ኮንካ፣ ናሽናል … ) ነው የምትገዛው፡፡ በሆቴል ኢንዱስትሪም የጥራት ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡

አንድ ሚስጢር ልንገርህ፡፡ ማሪዮት በመላው ዓለም ተመራጭ ታዋቂና ዝነኛ የሆነው በጥራቱ ነው፡፡ ስለዚህ ለጥራቱ ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ የጥራቱ ትኩረታችን የሚጀምረው ከሰዎቻችንና ከምርቶቻችን ነው፡፡ ሰራተኞቻችንን በአገር ውስጥና በአህጉር ደረጃ  እናሰለጥናለን፡፡ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሰለጠነው ሀገር የማኔጅመንት ደረጃ ወይም ደንበኞቻችን በሚጠብቁት የብራንድ ደረጃና አጠቃላይ የሆቴል ኢንዱስትሪ በሚጠይቀው የሞያ ደረጃ እናሰለጥናለን፡፡

ሆቴሎች የእኛ ስለሆኑ ወይም የእኛን የጥራት ደረጃ ጠብቀው በስማችን (በብራንዳችን) እንዲጠቀሙ ስለፈቀድን (ፍራንቼዝ) ስላደረግን በጥራት መጓደል ስማችን እንዳይነሳ እንግዶቻችን ለሚያርፉበት ክፍል ጥራት ሊኖራቸው ስለሚገባ ፣ ከአስተዳደሩ (አመራሩ) እኩል እንጨነቃለን፡፡ ማሪዮት በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፤ በኤስያም ሆነ በአፍሪካ በጥራት ጉዳይ ከማንም ጋር አይደራደርም፡፡

ሳንሻይን ኮንስትራክሽን የጥራት ደረጃችሁን ያሟላል? እንዴትስ መረጣችሁት?

በሚገባ! ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ አብሮህ የሚሰራው ሸሪክ የጥራት ደረጃ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሰንሻይን ግንባር ቀደም ሪል እስቴት አልሚና የኮንስትራክሽን ኩባንያ ስለሆነ የእኛን የጥራት ደረጃ የሚያሟላ ኩባንያ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዴት መገንባት እንዳለባቸው ያውቃል፡፡ ማሪዮት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከኩባንያው ምን እንደሚጠበቅ ያውቃል፡፡ ጥራት ያለው ምርትም እንዴት ማስረከብ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ስለዚህ እኛ (ማሪዮት) የሚገነባው የምርት የጥራት ደረጃ (ብራንድ) ምን መሆን እንዳለበት የምናውቀው እና ያንን እኛ የምንጠብቀውን (የምንፈልገውን) የጥራት ደረጃ በትክክል ተገንዝቦ የማስረከብ ልምድ ያለው ሰሳሻይን ኮንስትራክሽን ነን በጋራ ለመሥራት የተፈራረምነው፡፡

ቀደም ሲል ትሰሩ የነበረው በአሜሪካና አውሮፓ ነበር፡፡ አሁን ፊታችሁን ወደ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አዙራችኋል፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ነው?

በፍፁም አይደለም፡፡ ይሔ የሆነው በየአገሮቹ ባህል መሰረት ነው፡፡ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ጃፓን ወይም ኢትዮጵያ እያንዳንዱ ባህል የራሱ የሆነ ባህሪይ አለው፡፡ እያንዳንዱ ባህል  ከሀገሬው ባህል ጋር ተመሳስለን እንድንሰራ ይጠይቃል፡፡ ሆቴሎቻችንም መስራት የሚችሉት የአገሬውን ባህል አክብረውና ተመሳስለው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየታየ ያለው የፖሊሲ ለውጥ ሳይሆን ከአገሬው ባህል ጋር ተመሳስለን መሥራታችንን ወይም ምርትና አገልግሎታችንን ከአገሬው ባህል ጋራ ተመሳስለው መስራታቸውን ወይም ከአገሬው ባህል ጋር ማቆራኘታችውን ነው፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ቱሪስት ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት እናተርፋለን ብላችሁ መጣችሁ?

ኢትዮጵያ ወደ ፊት ከፍተኛ የዕድገት ተስፋ ያላት አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ለመሳተፍ ወደ አገሪቷ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቁጥር በየግዜው እየጨመረ ነው፡፡ ይሔው አሁን እንኳ ማሪዮት መጥቷል፡፡ ይህም አገሪቷ በቱሪስትና በጉዞ ድርጅቶች እይታ ያላትን ስፍራ ያሳድገዋል፡፡ ለአገሪቷም በጣም አትራፊ ጉዳይ ነው፡፡

ምናልባትም ሰዎች ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪስት መስህቦች ለማየት ብቻ ሳይሆን በማሪዮት ሆቴል አርፈው ለመዝናናት ሊመጡ ይቻላል፡፡ ይህም አንዱ መስህብ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አይነት ለአገሪቷም ለባለሆቴሎችም ለአስተዳዳሪው ማሪዮትም ጠቃሚ ነው፡፡

ሁለቱም ሆቴሎች የሚሰሩት ቤተክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ የቅዳሴው ድምፅ እንግዶችን ይረብሻል? ለዚህ ምን ታስቧል?

እኛ ለሃይማኖቶች ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት እናደርጋለን፡፡ በመላው ዓለም ከቤተክርስቲያን እና ከመስጊዶች ጎን ሆቴሎች ስላሉን ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ሆቴሎቻችንና ውጤቶቻችን የሰዎችን የግል ነጻነት እንዳይጎዳ ጥንቃቄ እናደርጋለን፡ እንግዶቻችን ከሃይማኖት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በአውሮፕላን በትራፊክ (መኪና ) ጩኸትም እንዳይረብሹ ጥንቃቄ  እናደርጋለን፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ‘ኮ ድምፅ ማጉሊያ ይጠቀማሉ?

ያንን ለመከላከል ሆቴሎቻችን ከውጪ ድምፅ እንዳያስገቡ ተደርገው ነው የሚሰሩት፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት የሚወጣው ድምፅ አውሮፕላን ሲያርፍ ከሚያሰማው ጩኸት አይበልጥም፡፡ እኛ ግን ከአውሮፕላን ማረፊያ ጎንና ስር ሆቴሎች አሉን፡፡ በመላው አረብ ሀገራት ያሉ መስጊዶች አዛን ሲያሰሙ ነው የሚውሉት፡፡ በአረብ አገሮች በርካታ ሆቴሎች አለን፡፡ እንግዶቻችን ግን በድምፅ አይረበሹም፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ በጣም ደካማ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ነው ያያችሁት? የሰለጠነ የሰው ኃይል ከውጪ ልትቀጥሩ ነው?

የለም በሁሉም የሥራ መስክ ስለቱሪስት አያያዝና መስተንግዶ፣ ስለማሪዮት ባህል፣ በስራው እንዴት ማሻሻልና መረዳት እንዳለባቸው እዚሁ እናሰለጥናቸዋለን፡፡ ማሪዮት ኢንተርናሽናል የስራ ዕድል ብቻ ሳይሆን ለዕድገት በር የሚከፍት ሙያዎችን የሚፈጥር አለማቀፍ ድርጅት ነው፡፡ ሰራተኞች ቋሚ የወር ገቢ እንዲያገኙ ከተደረገ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፆኦ ይኖራቸዋል፡፡ በሌሎች አገራት ከመንግስትና ከዩንቨርስቲዎች ጋር በመሆን ወጣቶችን ስለ ቱሪዝምና ጉብኝት ስለ እንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ እንዲሁም ቱሪዝም ስላለው ጥሩ አጋጣሚዎች እያስተማርን ነው፡፡ እንዚህም እናደርገዋለን ብለዋል

ሚ/ር ኪሪያኪድስ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ለምንድን ነው በግብፅ አምስት ሆቴሎች ለመገንባት የወሰናችሁት የሚል ጥያቄ ቀርቦላችው ሲመልሱ

ቢዝነስ ትክክለኛ ጊዜና አጋጣሚ ይፈልጋል፡፡ ይህ ውጤታማ አሰራር ነው፡፡ ግብፅን ያየን እንደሆነ መንግስት ቱሪዝም ለአገሪቷ ዕድገት በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው ብሎ የወሰነው ከብዙ ዓመት በፊት ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ቱሪዝም ብዙ ጥቅም አለው፡፡ የሥራ አጦችን ቁጥር ይቀንሳል የውጪ ምንዛሬን ያመጣል፡፡

ስለዚህ ቱሪዝምን ዘመናዊ ለማድረግ ለመሰረተ ልማት ማስፋፊያና ግንባታ ከፍተኛ ካፒታል አውጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ከአረብ አገሮች ንቅናቄ በፊት በነበረው 2010/11 ዓመት 40 ሚሊዮን ቱሪስቶች ግብፅን ጎብኝተዋል፡፡ እነዚህ ቱሪስቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያለው ማረፊያ፣ ሆቴል፣ ምግብ፣ መዝናኛ ይፈለጋሉ፡፡ አሁን ለምን አምስት ሆቴሎች እየሰራን እንደሆነ ግልፅ ይመስለኛል፡፡

በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ተመሳሳይ ነው፡፡ በዓለም በቀዳሚ ደረጃ ከሚጠቀሱ 50 የቱሪስት መዳረሻዎች 13ቱ ያሉት አፍሪካ ነው፡፡

ከግብፅ ሞሮኮ እስከ ደቡብ አፍሪካ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሆቴል ኢንዱስትሪ ያለው ኢኮኖሚያዊ አቅም ፊታችንን ወደ አፍሪካ እንድንዞር ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች የሚካሂደው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ዛሬ በአፍሪካ ካለው አንድ ቢሊዮን ሕዝብ መካከል 300 ሚሊዮኑ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያለው ነው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሚያሳየው ትንበያም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከ30-50 ባሉት ቀጣይ ዓመታት መካከለኛ ገቢ ያለው የአፍሪካ ሕዝብ በሁለትና ሦስት ደረጃ ያድጋል ይላል፡፡

እነዚህ ሰዎች ገቢያቸው ሲያድግ ማድረግ የሚፈልጉት አገራቸውን እየተዘዋወሩ መጎብኘት ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ የአፍሪካ ሀገሮችን ይጎበኛሉ፡፡ ከዚያም እንደማንኛውም ቱሪስት የተቀረውን አለም መጎብኘት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚያርፉበት የሚዝናኑበት፣ የፈለጉትን አገልግሎት የሚሰጣቸው ሆቴል ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ነው ወደ አፍሪካ እየገባን ያለው በማለት አብራርተዋል ፡፡

ማሪዮት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች 44 ሆቴሎች እያስገነባ ሲሆን በ73 አገሮች ደግሞ 3,700 ሆቴሎችና ሎጆች አሉት፡፡ ያለፈው አመት (2011) ገቢው ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ  ሲሆን በቤተሳዳ ሜሪላንድ -አሜሪካ በሚገኘው ዋና መ/ቤቱ 300 ሺህ ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡

 

 

 

Read 2431 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 14:23