Monday, 12 November 2018 00:00

ይድረስ ለፖለቲከኞች አክቲቪስቶችና ተከታዮች

Written by  ከያሬድ በላይ
Rate this item
(5 votes)

 ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ብትሆንም፣ በሰው ሰራሽ ችግሮች ስትጎዳ በመቆየቷ ልትበለጽግ አልቻለችም፡፡ የሰው ሰራሽ ችግሮቹ ዋነኛው ምክንያት የፖለቲካና የአስተዳደር መሪዎች መስራት የማይገባቸውን ስለሰሩና መስራት የሚገባቸውን ደግሞ ሳይሰሩ ስለቀሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ሁለቱንም ስህተት እንደ ሰው ሰራሽ ችግር ነው የማየው፡፡ ምሁራን ልሂቃን፣ የሚዲያ ሰዎች፣ አርቲስቶች፣ ጸሀፍት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ዜጎች  መስራት የሚገባንን ሁሉ ሰርተናል ብዬ አላምንም፡፡ በዚህም የተነሳ  ለሰው ሰራሹ ችግር ሁላችንም፣ በመጠኑም ቢሆን አስተዋጽኦ አድርገናል ብዬ አስባለሁ። መልካም የሰሩ፣  ከፍርሀትና ከአድርባይነት ነጻ ሆነው መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖች ፈጽሞ አልነበሩም ማለቴ ግን  አይደለም፡፡
እነሆ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋንና ከባድ ተግዳሮቶችን አጣምሮ በያዘ የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ስለሆነም በዚህ ወሳኝ ወቅት የፖለቲካ መሪዎች፤ አክቲቪስቶችና ተከታዮቻቸው ሁሉ፤ ልባችሁን ከጥላቻ፣ ከእልህ፣ ከቂም- በቀልና ከዘረኝነት አጽድታችሁ.፣ በሰከነ መንፈስ አርቃችሁና አስፍታችሁ ልታስቡ ይገባል። ምክንያቱም የእናንተ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ፣ የኢትዮጵያንና የህዝቧን መጻኢ እድልና ህልውና ይወስናልና፡፡ በሃገራችን ውስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ሁለት በጣም የተለያዩ አስተሳሰቦችንና  አካሄዶችን እመለከታለሁ፡፡ አንደኛው ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ ሰላምንና አንድነትን/ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጥላቻን፣ ዘረኝነትን/ብሄረተኝነትንና መለያየትን መሰረት ያደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁለተኛው አስተሳሰብና አካሄድ ለማንም የማይበጅ ከመሆኑም በላይ አገሪቱን ከአሁን በፊት ታይቶ ወደማይታወቅ አስከፊ የመከራ አዘቅት ውስጥ ሊከታት የሚችል ነው። መጨረሻውም የእርስበርስ ግጭት፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ረሃብና ሀገር አልባነት ሊሆን ይችላል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ፤ በዓለም ላይ ብሄርን/ጎሳን መሰረት ባደረገ ፌዴራሊዝም የተከፋፈለች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህ ህዝብን የሚያራርቅና የሚያለያይ የጎሳ ፌዴራሊዝም ከ27 ዓመት ወዲህ በሀገራችን ፖለቲከኞች የተፈጠረና  በህገ መንግስት የተደገፈ ሲሆን  እነሆ በአሁኑ ወቅት አስከፊ ውጤቱ እየታየ ነው፡- ለብዙዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፤ ሚሊዮኖችን ተወልደው ካደጉበትና ለአመታት ኖረው ሀብት ንብረት ካፈሩበት ስፍራ በጭካኔ ተጨፍጭፈው እንዲባረሩ፣ በገዛ ሀገራቸው ስደተኞች እንዲሆኑ አድርጓል፤ በሀገር ሰላምና ኢኮኖሚ  ላይም አሉታዊ ተጽኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ከዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም “በሽታ” መታከምና መዳን ይገባታል፡፡  
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄሮች/ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ቋንቋ መናገር፤ ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን መጠበቅ፤ ባህላቸውን መጠበቅና  ማዳበር ማንም ሊነፍጋቸው የማይችል፣ ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ መብታቸውና ሃላፊነታቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች ከሁሉም የሀገሪቱ ብሄረሰቦች ጋር እንዲግባቡና በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ እንደ ፍላጎታቸው መማር፣ መስራትና መኖር እንዲችሉ፤ የጋራ ቋንቋ/ቋንቋዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ደቡብ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ዜጋዎች የጋራ ቋንቋ እስካልተናገሩ ድረስ፤ በጋራ ተግባብተው መኖርና ሀገራቸውን በጋራ ማሳደግ ያስቸግራቸዋል፡፡ በመሆኑም ቀስ በቀስ ወደ መራራቅና መለያየት ይሄዳሉ፡፡ ይህ አደጋ፤ “የአማራ ክልል፤ የኦሮሞ ክልል፤ የሱማሌ ክልል፤ የትግሬ ክልል፤ ወዘተ” ብሎ ሀገሪቱን በዘር በከፋፈለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ምክንያት መከሰት የጀመረ ሲሆን ስር ሰዶ ለማስተካከል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በአስቸኳይ ሊታሰብበትና መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ሁለተኛውን የፖለቲካ አቋም የምታራምዱ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች እስኪ ቆም ብላችሁ፤ በሰክነ መንፈስ አርቃችሁ አስቡ፤ ለምን ብላችሁ እራሳችሁን ጠይቁ፤ ምናልባት “የእኔ ብሄር/ብሄረሰብ ባለፉት ስርአቶች ተበድሏል፤ ስለዚህ አሁን እንዲህ መደረግ አለበት፤ ይህ ክልል የኛ ብቻ ነው፤ በአንድነት መኖር አያስፈልገንም-- ወዘተ” ብላችሁ በአጭሩና በጠባቡ የምታስቡ ከሆነ፤ ይህ በጣም የተሳሳተ አክሳሪ አስተሳሰብና አካሄድ፤ እንወክለዋለን ለምትሉት ብሔረሰብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጽሞ የማይበጅ ነው። ምናልባት በስሜታዊነት ተገፋፍቶ ስብከታችሁን በቀላሉ የሚቀበለውን የህብረተሰብ ክፍል ለጊዜው ሊያነሳሳና ተከታያችሁ ሊያደርገው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ የተሳሳተ ተከታያችሁ ከስሜታዊነት ወጥቶ አስተሳሰቡን በሚለውጥና በሚያስተካክል ጊዜ ያዝንባችኋል፤ ያወግዛችኋልም፡፡
እኔ እንደ አንድ ዜጋ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለሀገራችን ይበጃል ብዬ የማቀርበው የመፍትሄ ሃሳብ፡- የፖለቲካ መሪዎችና ተከታዮቻቸው፤ ቂም-በቀልን ሳይሆን  ይቅርታን፤ ጥላቻን ሳይሆን  ፍቅርን፤ መጠላለፍን ሳይሆን መተባበርን፤ መለያየትን ሳይሆን  አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን እንድትመርጡና የማንዴላን መንገድ እንድትከተሉ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ “አንድነት” - የሚለው ቃል ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ “አንድነት ወይም በአንድነት መኖር” ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ ሁሉም ዜጋ እኩል ሁለንተናዊ መብት ኖሮት፤ ተባብሮ፤ ሀገሩን በጋራ እያለማ፤ ተዋዶና ተከባብሮ መኖር ወይም በሌላ አነጋገር “አንድነት በብዝሀነት (Unity in Diversity)” ማለት እንጂ፤ ተጨፍልቆ አንድ አይነት መሆን ማለት አይደለም፡፡ “አንድ አይነት” መሆን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ጽንሰ ሃሳብም አይደለም፡፡ ማንም ብሄር/ብሄረሰብ የራሱን ቋንቋ መናገር፤ ባህሉን መኖርና መንከባከብ ሁልጊዜም የራሱ ሰብአዊ መብት እንጂ ማንም ሊቸረው ወይም ሊነፍገው የሚችል ስጦታ አይደለም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥቂት ብሄረተኛ የፖለቲካ መሪዎች፤ “የኔ ብሄር የተበደለ ነው፤ የሰው መለኪያ ነው፤ ኢትዮጵያን የፈጠረ ነው፤ ወዘተ”  የሚል እጅግ ደካማና አፍራሽ አስተሳሰብ ሲያስተጋቡ እየሰማን ነው፡፡ በእውነቱ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ መስማት በጣም ያሳዝናል፤ ያሳፍራል፡፡ ለዓመታት ስናወግዘው የቆየነውንና ለዚህ አሁን ለሚፈታተነን አደጋ የዳረገንን፤ በዓለም ብቸኛ የሆነውን የሚለያይ የብሄር ፖለቲካ መልሰው በማቀንቀን፣ በስሜታዊነት ተነሳስቶ በቀላሉ ስብከታቸውን የሚቀበለውን የህብረተሰብ ክፍል እያሳሳቱ መሆናቸው ትልቅ ስህተትና በደል ነው፡፡ ይህ አስተሳሰባቸውና አካሄዳቸው ከማንም በላይ እንወክለዋለን የሚሉትን ህብረተሰብ የሚጎዳና የህዝብንና የሀገርን አንድነት የሚያጠፋ ነው፡፡
ሌሎች ጥቂት ዘረኛ ፖለቲከኞች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በፊት አንዱ ብሄር/ዘር ሌላውን እንደ በደለ አስመስለው ከእውነት የራቀ ወሬ በማውራት በህዝብ መካከል ጥላቻንና ግጭትን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር ከ45 ዓመት ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአምባገነን አመራሮች ጋር ተጋጭቷል እንጂ፤ መቼም ቢሆን ህዝብ በህዝብ ላይ ተነስቶ አያውቅም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ከዚህም አልፎ ተከታዮቻቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳይኖራቸውና ብሄር ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራ እንዲታይም አይፈልጉም። አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ዳር ድንበሯን አስከብረው፤ ነጻነቷን ጠብቀው ያስረከቧቸው ታላቅ ሀገር ባንዲራ መሆኑን አለማስተዋላቸው ትዝብት ውስጥ ይጥላቸዋል፡፡ የታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ የጋራ ባለቤቶች መሆናቸውን ባለማስተዋል ወይም ባለመፈለግ፤ ለማይጠቅም የፖለቲካ ትርፍ ብለው፤ በስሜት የተገፋፋ ጊዜያዊ ተከታይ ለማፍራት እንዲያስችላቸው ብቻ፤ ለማንም የማይበጅ፤ ከማንም በላይ እንወክለዋለን የሚሉትን ህብረተሰብ ሊጎዳ የሚችል ከንቱ የጥፋት ፖለቲካ እያካሄዱ መሆናቸው፣ በሃገርና በህዝብ ለይ የሚፈጸም ትልቅ ጥፋትና ስህተት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኛ አይደለም፡፡ አንዱ ዘር ከሌላው ተጋብቶና ተዋልዶ፤ በደምና ስጋ ተዋህዶ ነው የኖረው፤ አሁንም የሚኖረው፡፡ እኔ ስለ ራሴ ማንነት ሳስብ የእግዜር ፍጡር፤ የአዳምና ሔዋን ዝርያ መሆኔንና የዜግነት መለያዬ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን እንጂ ከኦሮሞ አባትና ከአማራ እናት መወለዴን አላስበውም። ምክንያቱም በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዚህ ያለ ጠባብ አስተሳሰብ ከንቱና አክሳሪ መሆኑን እገነዘባለሁና፡፡ እንደ እኔ ከሁለት የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮች/ብሄረሰቦች የተወለዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች፤ በመላው የሃገራችን ክፍሎች እንደሚገኙ ግልጽ ነው፡፡
በዘረኝነትና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ እኩይ ፖለቲካ ከሚያካሂዱ ጥቂት ፖለቲከኞችና በስሜታዊነት እየቀሰቀሱ ለጊዜውም ቢሆን ከሚያሳስቷቸው ተከታዮቻቸው በስተቀር፣ የእትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው አንድነትን፤ ኢትዮጵዊነትን፤ ፍቅርን፤ እኩልነትን፤ ዴሞክራሲን፤ ይቅርታንና ሰላምን ነው፡፡ ለዚህም ነው “ስንኖር ኢትየጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን፤ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው…” ብለው፤ ዘረኝነትን፤ ሌብነትንና ግፍን አውግዘው፤ የተቀደሰ ሀሳብ ይዘው የተነሱትን የለውጥ መሪዎች በሀገራችንና በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ፤ በላቀ ፍቅር የተቀበሏቸውና ከጎናቸው ሆነው ድጋፋቸውን ለመስጠት ብሎም ሀገራቸውን በጋራ ለማልማት በቁርጠኝነት የተነሱት። እኔ ሁልጊዜ ሳየው ልቤን የሚነካኝ ቪዲዮ አለ። በዋሽንግተን አርቲስት ታማኝ በየነ የዶ/ር ዐቢይ ጫማ ላይ ሲወድቅና የደስታ ሲቃ ይዞት እሳቸውንና ክቡር አቶ ለማን የሚያመሰግንበትና የሚያወድስበት ቃላት አጥቶ ሲቸገር ያየሁበት ነው፡፡ እንደምናውቀው አርቲስቱና መሪዎቹ ከተለያዩ የሀገራችን ብሄረሰቦችና አካባቢዎች የመጡ ናቸው፤ ነገር ግን ለነሱ ይህ ምንም ማለት አይደለም፡፡ እነሱን አንድ ያደረጋቸው ዘር/ብሄር አይደለም (ዘረኝነትን የሚጸየፉ ናቸውና)፤ ቁሳዊ ጥቅምም እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ አንድ ያደረጋቸው ትልቁ የጋራ አስተሳሰባቸው ነው፤ ለእናታቸው ለእምዬ ኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ነው፤ ለጋራ ሀገራቸውና ለህዝቧ ያላቸው ትልቅ ራእይ ነው፤ ፍቅርንና አንድነትን መፈለጋቸው ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ትልቅ ሃሳብና ራእይ ከተጋራ፤ ያለ ጥርጥር ሀገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ትለወጣለች ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ትልቅ ሀገር ነች፡፡ በዘመናዊ ግብርና ከተሰራ፤ ከሀገራችን አልፎ ሌሎችን ሊመግብ የሚችል ሰፊና ለም የእርሻ መሬት፤ ወርቅና ከወርቅ በላይ የከበሩ ማእድናት፤ የነዳጅ ዘይት፤ የላቀ የውሀ ሀብት፤ አብዛኞቹ የአለማችን ሀገራት ያልታደሉት ከዓመት እስከ ዓመት የሚዘልቅ ምቹ የአየር ጠባይ ወዘተ...ያላት ሀገር ነች፡፡ ሁሉም የሀገራችን ክፍል የተፈጥሮ ጸጋ አለው፡፡ ለሙ አካባቢ የእርሻ መሬት ሲኖረው፣ ደረቁ አካባቢ ደግሞ ማእድንና የነዳጅ ዘይት አለው፡፡ እልም ያለ አሸዋማ በረሃ ውስጥ የሚኖሩት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የበለጸጉት ለም የእርሻ መሬት ኖሯቸው ሳይሆን፤ በዋነኛነት በነዳጅ ዘይትና በማእድን ነው፤ በተጨማሪም እርስ በርሳቸው ሳይበጣበጡና ሳይከፋፈሉ በሰላም በመኖራቸው ነው። እኛ ኢትዮጵያውያኖች ግን ሁሉም የተፈጥሮ ጸጋ ኖሮን፣ የቸገረንና ያጣነው ፍቅርን፤ አንድነትንና ሰላምን ነው (በላቀ የሀገር ፍቅሯ የምትታወቀው ድምጻዊት ጂጂ ከዓመታት በፊት “እኔስ የራበኝ ፍቅር ነው” አንዳለችውና፤ ተወዳጁ ድምጻዊ ጌቲሽ ማሞ ደግሞ “ለካስ ያጣነው ፍቅር ነበር” እንዳለው)፡፡ ችግራችን ሰው ሰራሽ ነው፤ ከተሳሳተ አስተሳሰብ፤ ከጥላቻ፤ ከዘረኝነትና ከስግብግብነት የሚመነጭ ነው፡፡ ሰው ሰራሹ ችግር ሲፈታ፤ ሀገር ሰላም ስትሆን  እና አሁን የተጀመረው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ሲሳካ (እንደሚሳካም አልጠራጠርም)፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልትበለጽግና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰላም፤ በእኩልነት፤ በፍቅርና፤ በብልጽግና ሊኖርባት የሚችል ሀገር ትሆናለች፡፡
ስለዚህ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች እባካችሁ አርቃችሁና አስፍታችሁ በቅንነት አስቡ፤ ልባችሁን አጽዱ፡፡ በላቀና ጥልቅ አስተሳሰብ  ፍቅርን፤ ይቅርታን፤ መተባበርንና አንድነትን በመከተል፣ ዜጋዎች ሁሉ በአንድነት፤ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት፤ ያልተከፋፈለች፤ የማናፍርባት፤ የተከበረችና፤ የበለጸገች አትዮጵያን እንገንባ፡፡  
ህይወት አጭር ናት፤ የጤነኛ ሰው አማካኝ የህይወት ዘመን ከ70 እስከ 80 ዓመት ቢሆን ነው፤ ከዚህ ላይ የአሁን እድሜያችንን ስንቀንስ፣ ቀሪ ዘመናችን በጣም አጭር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በየዓመቱ ልደታችንን ስናከብር ወደ ሞት እንቀርባለን፡፡ ሁላችንም እናልፋለን፡፡ ስናልፍ ሁሉንም ቁሳዊ ሀብታችንን ትተን ነው የምንሄደው፡፡ ከመቃብራችን በላይ የሚቀረው በህይወት ሳለን የሰራነው ተግባርና ስማችን ብቻ ነው (ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና)፡፡ እኩይ አስባችሁና እኩይ ሰርታችሁ፤ ሲወቀስና ሲወገዝ የሚኖር ስም ትታችሁ አትለፉ፡፡ ይልቁንም ትልቅ አስባችሁ፤ ለሀገራችሁና ለህዝቧ መልካም ስራን ሰርታችሁ፤ በህይወት ስትኖሩ የህሊና እርካታና ሰላም አግኝታችሁ፤ ለትውልድ ታላቅ ሀገርን አስረክባችሁ፤ ስማችሁን በዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ትውልድ ሁልጊዜ የሚያስታውሰውና የሚዘክረው አድርጋችሁ እለፉ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!

Read 4158 times