Saturday, 10 November 2018 13:34

አባይ ባንክ 419 ሚሊዮን ብር አተረፍኩ አለ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)


    አባይ ባንክ የአምስት ዓመቱን ስትራቴጂክ ፕላን በጀመረበትና ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁሞ፤ 419 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ የኋላ ገሠሠ ባለፈው ረቡዕ በዋና መ/ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከታክስ በፊት ከፍተኛ የተባለለትን የ419 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰው፣ ይህም ካቻምና ከተመዘገበው ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የ68 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 51 በመቶ ብልጫ ያለው 1.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ መሰብሰቡን፣ የባንኩ የዚህ ዓመት 2.8 ተጨማሪ ተቀማጭ ከወዲያኛው ዓመት ጋር ሲተያይ የ41 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 9.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ እንዲሁም ከሁሉም የገቢ ምንጮች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከካቻምናው ጋር ሲተያይ 33 በመቶ በማደግ 146.3 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አመልክተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ከብድር የተሰበሰበው ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ30 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 2.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የባንኩ አጠቃላይ ብድር 40 በመቶ በማደግ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ብድር 40 በመቶ በማደግ 6 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከቀደመው ዓመት 36 በመቶ ብልጫ በማሳየት 1.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ አጠቃላይ ሀብት ከወዲያኛው ዓመት ጋር ሲተያይ 43 በመቶ በመብለጥ፣ 12.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ባለፈው ዓመት ገንዘብ ነክ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች 18 ተጨማሪ ቅርንጫፎች መክፈቱን፣ እንዲሁም በተለያዩ የቢዝነስ ማዕከላት 17 ተጨማሪ ፖስ ማሽኖች ማስቀመጡንና ለወኪል የባንክ አገልግሎት 51 አዳዲስ “አባይ - ባጃጂ” ወኪሎች መመልመሉን ተናግረዋል፡፡  አባይ ባንክ የራሱን ሕንፃዎች በአዲስ አበባ፣ በባህርዳርና በደሴ ከተሞች ለመገንባት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንም አቶ የኋላ ገሠሠ አክለው ገልፀዋል፡፡    

Read 2944 times