Monday, 12 November 2018 00:00

አስታዋሽ ያጣው የሃገር ሃብት - ቪላ አልፋ!

Written by  ነቢዩ ካሳሁን
Rate this item
(2 votes)


    ብርቅዬው የኢትዮጵያ ልጅ እጅግ የተከበረው የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ ዛሬም በያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ህያው ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ውዱ የኢትዮጵያ ልጅ ህይወቱን በሙሉ ወገኑን ሲያገለግል ኖሮ፣ ወደማይቀረው ቦታ ቢሄድም፣ በሙያው ካበረከተው ባሻገር ከህልፈቱ በኋላ ለወገኑ ጥሎ የሚሄደው ነገር ያስጨንቀውና ያስጠብበው የነበረ ሙያተኛ ለመሆኑ ለህዝቡ አውርሶ ያለፈው ቪላ አልፋ ሙዚየም ቋሚ ምስክር ነው፡፡ ቪላ አልፋ፤ ሰዓሊው የዘመናት ጥበቡና ጥሪቱን ያፈሰሰበት፣ በዓይነቱ አምሳያ የሌለው ታሪካዊና ሥነ ጥበባዊ ሙዚየም ብቻ ሳይሆን በምርጥ የሥነ ጥበብ አጋዥ መጻህፍትና ጆርናሎች የተደራጀ ቤተ መጻህፍትና የምርምር ቦታ ጭምር  ነው፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነቱ ነበርና፣ ቪላ አልፋን ሎሬት በህይወት እያለ በውርስነት ሲረከብ የቀደመው አልነበረም፡፡ ብርቅዬው ቪላ አልፋ ከዛሬ ነገ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ማየት ልንጀምር ነው ብለን ስንጠብቅ ብሎም፣ የሃገሪቱ የሥነ ጥበብ ተማሪዎች ተጨማሪ የመማሪያና የመመራመሪያ  ማዕከል አገኙ ብለን ስንመኝ ብንቆይም፣ ቪላ አልፋን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ታሪካዊው ላሊበላ በጀግና ህዝቡ የድረሱልን ጩኸት፣ ሁሉም በየአቅጣጫው እየተረባረበለት ይገኛል፡፡  
ቪላ አልፋም የሚጮህለት በርካታ የሥነ ጥበብ ክምችት ያለው ሙዚየም ለመሆኑ ውስጡን የሚያውቁ ሙያተኞችና ዜጎች እኔን ጨምሮ ምስክሮች ነን፡፡ በዚህም የተነሳ ጊዜው እየገፋ በሄደ  ቁጥር ሁኔታው እያሳሰበኝ መጥቷል፡፡ ንብረቱና ቅርሱ በብሔራዊ ኮሚቴ አስፈላጊው ምዝገባና ርክክብ ስለተደረገለት የሚያሰጋ ነገር ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን እዚሁ አፍንጫችን ሥር ያለ፣ ለከተማዋ አዲስ ገጽታ ሊጨምር የሚችል መስህብ  ሆኖ ሳለ፣ ለምን የቅርስ ባለሥልጣን በሙሉ ሃይሉ ሰርቶ ሊከፍተው እንዳልቻለ ደንቆኝ፣ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት አድርጌ ነበር፡፡  
በዚሁ መሰረት ሁኔታዎችን ለማጣራትና ለመጠየቅ ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ወደ ቅርስ ባለሥልጣን በመሄድ ይመለከታቸዋል የሚባሉትን ሃላፊዎችና ሙያተኞችን ለመጠየቅ ሙከራ አድርጌ ባገኘሁት ምላሽ፣ ከበላይ ሃላፊው ጀምሮ አንዱ ባንዱ ላይ ከማላከክ ውጭ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት አላገኘሁም። ባጠቃላይ የቅርስ ባለሥልጣን ሃላፊዎች፤ ቪላ አልፋ የያዘው የሃገር ሃብት ምን ያህል እንደሆነ ያልገባቸው መሆኑን ስለተረዳሁም፣ ስጋቴን ለህዝብ ለማጋራት ይቺን ጽሁፍ  ለማቅረብ  ተገድጃለሁ፡፡
መቼም ቪላ አልፋ ውስብስብ ጥንታዊ ዲዛይን ያለው ሙዚየም አለመሆኑን ለመረዳት የግድ አርኪቴክት መሆን አያስፈልግም፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፤ ከ3-5 ዓመት የፈጀብኝ አድሶ ሥራ ላይ ለማዋል መሃንዲሶች ከፓሪስ ማስመጣት ስለነበረብኝ  ወይም እንደ ላሊበላ ሚሊዮን ዶላሮች ባለማግኘቴ  ነው ብሎ ሊደልለን ይሞክራል ብዬ  አላስብም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት፣ የሚመለከተው የመንግስት አካል፣ ሙዚየሙን በአፋጣኝ ለሃገር ጠቀሜታ እንዲውል ያደርግ ዘንድ ላሳስብ እወዳለሁ። እግረ መንገዴንም  መንግስት ትኩረት ካልሰጠውና በሃገሪቱ የቅርስ ሃብት ዙሪያ  ቅርስ ምን እንደሆነ የገባቸው፣ በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በልምዳቸው የተሻሉ የሃገርና የወገን ፍቅር ያላቸው ሰዎች በሃላፊነት እንዲሰሩ ካልተደረገ፣ ሁኔታዎች አሳሳቢ እንደሚሆኑ ስጋቴን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ ከዚህ አንጻር ወደፊት እንደሚከፈት የሚነገርለት የብሔራዊ ቤተ መንግስት ሙዚየም ተጠሪነቱ፤ መብትና ግዴታው ላልገባው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከመሆን ይልቅ  በሙያተኞች አደራ ስር ቢሆን የተሻለ ነው  እላለሁ፡፡


Read 621 times