Monday, 12 November 2018 00:00

“ጋሽ ፍቄ ከነክብሩ ያላረፈበት ምክንያት ለኔ እንቆቅልሽ ነው”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ለኩላሊቱ ጉዳት መጋለጡ ከታወቀ በኋላ ህይወቱን  ለማትረፍ አድናቂዎቹ፣ የሙያ አጋሮቹና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘብ፣ በፀሎትና ኩላሊት ለመስጠት በመዘጋጀት አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ ህዝቡ ለእሱ ያለውን ፍቅርና አክብሮት በህይወት እያለ የማየት ዕድልም ገጥሞታል፡፡
ሆኖም “እኔን ለማሳከም ልመና አትውጡ፤ከእነ ክብሬ ልሙት” በማለት ለህክምናው ወጪ የተጀመረውን ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ አርቲስት ፍቃዱ ቢቃወምም፣ “አይናችን እያየ አትሞትም” በሚል የሙያ አጋሮቹ ዘመቻውን ቀጠሉበት፡፡ የፍቃዱ የቅርብ ወዳጅ አርቲስት ፈለቀ አበበም፤ በወቅቱ በእስር ላይ ለነበሩት የኬኬ ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ ጉዳዩን በመንገር፣ የ1.ሚ ብር ድጋፍ ለማግኘት ተችሏል፡፡   
ይሁንና አርቲስት ፍቃዱ ከዘመናዊ ህክምና ይልቅ መንፈሳዊውን በመምረጡ ወሎ ወልዲያ አቅራቢያ በምትገኘው ሲሪንቃ አርሴማ፣ ፀበል ሲጠመቅ ቆይቶ ህይወቱ አልፏል፡፡ ነገር ግን በሁለት ፈርጅ  ለህክምናው ተብሎ ከተሰበሰበው ገንዘብ ጋር በተያያዘ፣ባለፈው ሳምንት በኮሚቴዎች አለመግባባት የተፈጠረው ውዝግብ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ “አርቲስት ፍቃዱ ለምን ከነክብሩ እንዳላረፈ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው” የሚለው አርቲስት ፈለቀ አበበ፤በሰሞኑ ውዝግብ ቅሬታ እንደተሰማው ተናግሯል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከአርቲስት ፈለቀ አበበ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ  አድርጋለች፡፡

   የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያምን የጤና መታወክ በቅርበት ታውቅ ነበር?
ጤናው መታወኩን የማውቀው ከኩላሊት ህመሙ በፊት በነበረበት የስኳር ህመም ነው፡፡ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ አብረን ስንሰራ፣ ክብርት ባለቤቱ ለመቅሰስ በምትቋጥርለት የምሳ እቃ መነሻ፣ ስለ ስኳር ህመሙ አውርተን እናውቃለን፡፡ ኩላሊቱን እንደታመመ ስሰማ፣ በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ በጣምም አዘንኩ። እርግጥ እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደንግጧል፤ አዝኗልም፡፡ ከእኔ ጋር አብረን  ለመስራት ብዙ አቅድ ነበር፡፡ እንደምታውቂው፤ ጋሽ ፍቄ ተአምረኛ ተዋናይ ነበር፤ አጣነው እንጂ!
በአንድ ወቅት በኢቴቪ “አርሂቡ” ፕሮግራም ላይ በእንግዳነት ቀርበህ፣ ጋሽ ፍቄ ስላንተ ችሎታ ሲመሰክርና እንደሚሳሳልህ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ ትክክል --- ነኝ?
ትክክል ነሽ! እኔም በጣም እሳሳለት ነበር። ከአንጀቴ ነበር የምወደው፡፡ ሁላችንም እንወደዋለን፤ እናደንቀዋለን፡፡ እሱም የሙያ ተከታዮቹንና አዳዲስ ወጣት አርቲስቶችን ይወድና ያበረታታ ነበር፡፡ የ”አርሂቡ” እንግዳነቴን ካነሳሽው አይቀር፣ እኔም ከእርሱ ጋር መድረክ ላይ ስቆም፣ ሀሴት እንደማደርግ በዚያው ፕሮግራም ላይ ተናግሬ ነበር፡፡
በዚህ ቅርበታችሁ ይመስለኛል በታመመ ጊዜ፣ ድጋፍ እንዲያገኝ የታተርከው?
እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ባለሀብቱ ቀድመው ሊረዱት ተዘጋጅተው ነበር፡፡ እኔ እንደ ቧንቧ ነው ያገለገልኩት ማለት ትችያለሽ፡፡
እንዴት?
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የኩላሊት ህሙማን ማህበር፤ አቶ ከተማ ከበደን (የኬኬ ኩባንያ ባለቤት) የክብር አምባሳደር አድርጓቸው ነበር። አቶ ከተማ ከአምባሳደርነታቸውም በተጨማሪ ከቤተሰባቸው በኩላሊት ህመም የተጐዱ ስለነበሩ፣ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት በውል ያውቁት ነበር፡፡ ወህኒ ቤትም ሳሉ ስለ ህሙማኑ ይብሰለሰሉ ነበር።
በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለተቋቋመው “የኩላሊት ህሙማን በጐ አድራጐት ማህበር” 5 ሚሊዮን ብር መለገሳቸውም በአዲስ አድማስ ተዘግቧል ---
ትክክል ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ልጠይቃቸው የታሰሩበት ወህኒ ቤት ሄጄ፣ ብዙ ከተጨዋወትን በኋላ በኩላሊት ህሙማን አምባሳደርነታቸው ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ ጠየኳቸውና፣ እግረመንገዴንም አንዲት እርዳታ የሚያሻት ታዳጊ ወጣት እንዳለች ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም “ዛሬ እንኳን መጣህ፤ ማታ በቴሌቪዥን አይቻት ነበር፤ ሜላት አሰፋ አይደል የምትባለው” አሉኝ፡፡ አክለውም፤” በል ቶሎ አግኛትና ለጊዜው የዲያሊሲስ ህክምና እንዳታቋርጥ እንርዳት፤ ቀጣዩን ከቤተሰቧ ጋር ተነጋግረን እንወስናለን” አሉ፡፡
ጋሽ ፍቄ ከተለገሰው 1 ሚሊዮን ብር ላይ 200 ሺህ ብር ያካፈላት ታዳጊ ናት አይደል?
ትክክል፡፡ ከጋሽ ፍቃዱ እገዛ  በፊት አቶ ከተማ  ሊረዷት መሞከራቸውን አስታውሳለሁ። በኔ ግምት አቶ ከተማ ከበደ፤ እያንዳንዱን የሚያደርጉትን ድጋፍ ሰው እንዲያውቀው የሚፈልጉ አይመስለኝም እንጂ ለሌሎችም በርካታ በኩላሊት ህመም ለተጠቁም ሆነ የተለያየ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ ተገቢ ሆኖ ሲያገኙት፣ የልግስና እጃቸውን ከመዘርጋት ወደ ኋላ አይሉም። ይህንን ደራሽነታቸውን ደግሞ ሁሉም የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡
ለአርቲስት ፈቃዱ ተ/ማርያም ወዳደረጉት ድጋፍ  እንመለስ---
የጋሽ ፍቄን መታመምና የቤተሰቡንና የህዝቡን ድንጋጤ ስመለከት፣ ተነስቼ ወደ እሳቸው ሄድኩኝ - ወህኒ ቤት፡፡ ገና ስንገናኝ “ምነው ፊትህን እንዲህ ክረምት አስመሰልከው?” አሉኝ፡፡ እኔም “የሙያ አባቴ ኩላሊቱን በጠና ታሟል፤ ፊቴን ያጨፈገገው ምክንያት ይሄው ነው፤ እባክዎ አፋጣኝ ህክምና ያስፈልገዋል” ብዬ ሳልጨርስ፤ “እኔም ዜናውን በቴሌቪዥን አይቼ፣ እንደው ምን ባደርግለት ይሻላል እያልኩ ነበር፤ በጣም ያስደነግጣል” አሉኝና፤ “ለመሆኑ ኩላሊትስ የሚሰጠው ያገኝ ይሆን?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ወዲያው፤ “ቶሎ እንዲታከም 1 ሚ. ብር በአስቸኳይ ይሰጠው፡፡ ያን የሚያህል ትልቅ ያገር ሀብት በጭራሽ የሰው ፊት ማየት የለበትም” ብለው እዚያው በቆምኩበት ወሰኑ፡፡ “ይሄ ብር ለህክምናው ይዋል፤ ከዚህ በኋላም የሚያስፈልገውን የትኛውንም ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ ነኝ” በማለት ቃል ገብተውልኝ ተለያየን፡፡
ከዚያስ?
በመጀመሪያ ለጋሽ ፍቄ፤ 1 ሚ. ብር የለገሰው ሰው እንዳለ ነገርኩትና በጣም ተደሰተ፡፡ ያው ጋሽ ፍቄ ማንም ሰው እንደሚያውቀው ትሁት ነው፡፡ በትህትና አመስግኖ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሃይሉ ከበደ መሆኑን ነገረኝና እኔም ደውዬ፣ ሁኔታውን አሳውቅሁት፡፡ ሃይሉ ከበደም በምሳ ሰዓት ከኮሚቴው አባላት ጋር አገናኘኝ፡፡  
አንድ ያልገባኝ ነገር አለ፡፡ አቶ ከተማ ከ1 ሚ. ብሩም በኋላም ተጨማሪ እገዛ እንደሚያደርጉለት ቃል መግባታቸውን ነግረኸኛል፡፡ ለህክምናውም የሚበቃውን ገንዘብ ፈቅደዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ጋሽ ፍቄ፤ “ልመና አትውጡ፤ ከነክብሬ ልሙት” እያለ ለምንድን ነው የኮሚቴ አባላቱ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን የቀጠሉት?
ጋሽ ፍቃዱ ራሱ እንደፈለገው፣ ከእነ ክብሩ እንዳይሞት የሆነበት ምክንያት፣አሁንም ድረስ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በትክክል ለኮሚቴው አሳውቄያለሁ፡፡ ለራሱ ለጋሽ ፍቃዱም ሁሉን ነገር ነግሬው ነበር፡፡ አቶ ከበደ ሁሉንም ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ መሆናቸውን ነግሬው፤ ልመናው እንዲቆም አማክሬው ነበር፡፡ በበኩሌ፤ ያ መልካም አጋጣሚ፣ በአደባባይ እርዳታ ከመጠየቅ የተሻለ አማራጭ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
ታዲያ ጋሽ ፍቄ፤ ስታማክረው ምን አለህ?
“እኔም’ኮ ከእነ ክብሬ ልሙት ብዬ ነበር ፈለቀ” አለኝ፤ በሀዘንና በብስጭት እየተወራጨ፡፡
እንደፈለገው “ከእነ ክብሩ እንዳይሞት” እንቅፋት የሆነበትን ነገር ለማወቅ አልሞከርክም?
ልጠይቀው ፈልጌ ነበር፡፡ ግን ደግሞ በወቅቱ በነበረበት ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ መገዳደርና ገፍቼ መጠየቅ አልቻልኩም፡፡ አሁን ታዲያ ፀፀቱ በውስጤ አለ፤ ምነው ደፍሬ እንቅፋት የሆነበትን ጉዳይ በጠየቅኩት ነበር እላለሁ፡፡ መኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ብቻችንን ስንቀር ነበር የነገርኩት፡፡ በነገራችን ላይ ቼኩ የተፃፈው በጋሽ ፍቃዱ ስም ነበር፡፡ ለራሱ ለጋሽ ፍቃዱ ነው መኖሪያ ቤቱ ወስደን የሰጠነው፡፡
ከማን ጋር ሆናችሁ ነበር ቼኩን ያስረከባችሁት?
እኔ የአቶ ከተማ ከበደ ጓደኛ የሆነው አቶ ሲራክ በትዕዛዙ፣ ወኪሉ አቶ ቴዎድሮስ ቦጋለና አርቲስት አበበ ባልቻ ሆነን ነው ሄደን የሰጠነው። ጋሽ ፍቄም “ሁሉንም ጉዳዬን ለያዘልኝና ለእኔ መስዋዕት እየከፈለ ላለው ኮሚቴ” ብሎ ቼኩን ለኮሚቴው አስረከበ፡፡
ሰሞኑን ለአርቲስቱ መታከሚያ በተሰበሰበው ገንዘብ ዙሪያ በኮሚቴውና በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ መካከል ውዝግብ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ነገሩን  ስትሰማ ምን አልክ?
እንግዲህ እኔ የማውቀው ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ለጋሽ ፍቃዱ መኪና በስጦታ ማበርከቱን ነው። ይልቅ ሰሞኑን  በኮሚቴዎቹ ከተሰባሰበው ገንዘብ ውጭ አስገራሚ መረጃ ሰምቼአለሁ፡፡ የእርሻ በሬያቸውን ሸጠው ጋሽ ፍቄን ለመርዳት የወሰኑ እንዲሁም  ኩላሊት ለመገለስ የተመዘገቡ፣ ባልሳሳት ከ30 በላይ የግለሰቦች ሥም ዝርዝር፣ የጋሽ ፍቄ ወንድም ግርማ ተክለማርያም አሳይቶኛል፡፡ ይሄ በመላው ኢትዮጵያ አድናቂዎቹ፣ ለጋሽ ፍቄ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚመሰክር ነው፡፡  
አቶ ከተማ  ከአርቲስት ፍቃዱ ጋር የመገናኘት እድል ገጥሟቸዋል?
አንድ ጊዜ አቶ ከተማን ለማመስገን፣ ጋሽ ፍቄ ወህኒ ቤት ሄዶ ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ ከተማም፤ “አንተም ታክመህ ድነህ፣ እኔም ከእስር ወጥቼ፣ ቁጭ ብለን እንጫወታለን” ብለውታል፡፡ ጋሽ ፍቃዱም በምስጋና ንግግሩ መሀል፤ “እሳቸው (አቶ ከተማ) ከሚገኙበት ጭንቅ በላይ ለኔ በማሰባቸው ሆድ ይመርቅ” ብሎ ነበር፡፡
በመጨረሻስ የምትለው አለህ----?
እኔ ከዚህ በላይ ብዙ ማለት አልፈልግም። በውስጤ የምፀፀትበትን ነገር ነግሬሻለሁ፡፡ አሁን አደባባይ የወጣው ውዝግብ ደስ አይልም፡፡ የጋሽ ፍቃዱን ነፍስ ይማር፡፡ ለኮሚቴዎቹ ፈጣሪ ብድራቸውን ይክፈላቸው። እንደ አቶ ከተማ ከበደ አይነት ያላቸውን የሚያካፍሉ ለጋሶችንና ባለፀጐችን ያብዛልን እላለሁ፡፡ በደበበ ሰይፉ ስንኝ ብናሳርግስ---
ከሜዳ ከአውድማ አንድ ፍሬ ብትጠፋ
የፍቅር ድምጽ ከፋ እምነት በአፍጢሙ ተደፋ።

Read 1297 times Last modified on Saturday, 10 November 2018 14:02