Monday, 12 November 2018 11:32

ብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ!

Written by 
Rate this item
(7 votes)


    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጡረታ የወጣች አህያና አንድ ከቤት የተባረረ ውሻ አገር ለቀን እንሂድ ተባብለው ሲጓዙ፤
አህያዋ፤
“የማንታወቅበት አገር ሄደን አዲስ ሥራ ብንጀምር ጥሩ ነው” አለች፡፡
ውሻው፤
“መልካም ሃሳብ ነው፡፡ ዕድሜያችንን እንቀንስና እንቀጠር፡፡ ‘በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል’ ማለት ብቻ እኮ ነው የሚያስፈልገው፡፡”
አህያዋም፤
“በጣም ጥሩ፡፡ ግን እግረመንገዳችንን አንድ ጊዜ ላናፋ ፍቀድልኝ” አለ፡፡
ውሻም፤
“ግዴለሽም እንጠንቀቅ፡፡ አያ ጅቦን ትቀሰቅሺዋለሽ”
አህያም፤
“በጣም ብዙ ስለጋጥኩኝ ነፋኝ ቀበተተኝ”
ውሻ፤
“እኔ የለሁበትም- እንዳሻሽ አድርጊ”
አህያ አንድ ጊዜ በከባዱ አናፋችና መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
ጥቂት እንደሄዱም፤ አህያ
“አሁን አንዴ ልጩህ?”
ውሻም፤
“ተይ አህያ፣ የቅድሙ መቀስቀሻ የአሁኑ መቅረቢያ ነው”
አህያ፤
“እንደዚህ ሆዴን ነፍቶኝ፣ ቀብትቶኝ መንገድ መሄድ አልችልም”
ውሻም፤
“እኔ ተናግሬያለሁ፡፡ እንዳሻሽ!”
አህያ አንድ ጊዜ በረዥሙ አናፋች፡፡
ደግሞ ጥቂት እንደሄዱ “እንግዲህ አንድ ብቻ ነው የቀረኝ - አንድ የመጨረሻ ልጩህ” አለች አህያ፡፡
ውሻም፤
“ይሄውልሽ አህይት
የመጀመሪያው መቀስቀሻ፤ ነው፡፡
ሁለተኛው ማቅረቢያ ነው፡፡
ሦስተኛው መበያ ነው፡፡”
አህያም፤
“በምንም ዓይነት ካልጮህኩ አይወጣልኝም” አለችና የመጨረሻ ጮክ ብላ ጮኸች፡፡
ውሻ እንዳለው አያ ጅቦ መጣ፡፡ ውሻ ሮጦ አመለጠ፡፡ አህያን አያ ጅቦ ዘርግፎ ጣላት፡፡ ወዳጆቹን ጠርቶ ተቀራመቷት፡፡
***
የምንጨህበትን ሰዓት እንለይ፡፡ ጥጋባችንን ጋብ እናድርግ፡፡ ለምን ሊዳርገን እንደሚችል እናጢን፡፡ የታገልንለት፣ የሞትንለትና የተሰቃየንለት ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትሕና እኩልነት ትርጉም ባለው መንገድ ፍሬ የሚያፈራው፣ ሰዓትና ጊዜ የለየ ዕቅድና አተገባበር ሲኖረን ነው፡፡
ነፃነት ከልኩ በላይ ሊያስፈነድቀንም ሆነ ከልኩ በታች ሊያደናብረን አይገባም፡፡ አዲስ ነገርን በሆይሆይታ ሳይሆን በጥሞናና በአበክሮ ማየት ብልህነት ነው፡፡ ስለ ጊዜ ያለን ግንዛቤ አጋጣሚዎችን በትክክል መጠቀምንም ሆነ ታግሶ ማለፍን ሊያስተምረን አስፈላጊ ነው፡፡ በ1966 ዓ.ም የተፈጠረውን አብዮታዊ ንፋስ በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ የ1967 -68 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻን ወቅትም ከፈጣን ተምኔታዊ ጉዞ ያለፈ ፋይዳ ላይ አላዋልነውም፡፡
በ1997 ዓ.ም ለውጫዊ ሁኔታ በጥድፊያ እንጂ በሰከነና በተደራጀ መልክ የተቃኘ፣ ጊዜን ከጉዳይ የጣፈ ቅኝት ያልነበረው ነበረና አጋጣሚው እንደ ዘበት አመለጠ፡፡ የአሁኑ ሌላ አጋጣሚ ነው፡፡ ከግርግር ይልቅ የተባና የረባ ድርጅትን መሠረት ያደረገ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ከአቋራጭ ይልቅ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ማቀድን እንልመድ! እንከን ፍለጋ ከመሮጥ ደግ ደጉን እናስተውል፡፡
አፋችን ቅቤ ልባችን ጩቤ ከሆነ፣ የምናመራው ወደ እብሪት ነው፡፡ ወደ ትምክህት ነው። እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል፤ የኔ አበባ ብቻ ናት ዕንቡጥ ማለት አያዋጣንም፡፡ የቆየውንና የተደበቀውን አጀንዳ በሆዳችን ይዘን፣ አዲስ ወይን እየጠመቅን ነው ብንል የለበጣ ጉዞ ነው፡፡ ተስፋችንን አጨላሚ ነው፡፡ ቀና ፉክክር እንጂ ድርጅታዊ የበላይነቴን ያለ ምርጫ አሸንፌያለሁ እንደ ማለት ያለ ጭፍን ግብዝነት የለም፡፡ በርትቶ በዲሞክራሲያዊው መንገድ ማሸነፍንና መሸነፍን እንልመድ እንጂ ብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ እንዳለው አባወራ መሆን ወንዝ አያሻግርም!

Read 7405 times