Sunday, 18 November 2018 00:00

በማዕቀቡ መነሣት ኤርትራውያን ደስታቸውን እየገለፁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የኤርትራው ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ላለፉት ዘጠኝ አመታት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ባለፈው ረቡዕ ማንሳቱን ተከትሎ፣ ኤርትራውያን ደስታቸውን በአደባባይ የገለፁ ሲሆን የሃገሪቱ መንግስት “የትዕግስታችንን ውጤት በመጨረሻ አግኝተናል” ብሏል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ አሸባሪ ከተሠኘው አልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለትና በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሻባብን ትደግፋለች፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ለማተራመስ እየሠራች ነው በሚል ከዘጠኝ አመት በፊት በኤርትራ ላይ የጦር መሣሪያ ግዥና የባለስልጣናት ጉዞ ላይ ማዕቀብ ተጥሎባት እንደነበር ይታወቃል፡፡
ለ20 አመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የዘለቀው ጦርነትና ግጭት በቅርቡ መፈታቱን ተከትሎም በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ እንዲነሣ የኢትዮጵያ መንግስት የፀጥታው ም/ቤት አባል ሀገራትን ሲያግባባ ቆይቷል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በቀጥታ ለፈረንሳይ፣ ለጀርመንና ለእንግሊዝ መንግስታት ማዕቀቡ እንዲነሣ እገዛ ያደርጉ ዘንድ መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ባለፈው  ረቡዕ ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ኒውዮርክ ላይ የተሠበሰበው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በሙሉ ድምጽ ማዕቀቡ እንዲነሳ ወስኗል፡፡
የማዕቀቡን መነሣት ይፋ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ መንግስትና ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን የማዕቀቡ መነሣት ለሁለቱ ሃገራት ቀጣይ ግንኙነትና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና መረጋጋት በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ፤ “ለማዕቀቡ መነሣት ድጋፍ ያደረጉትን በሙሉ እናመሰግናለን ኢ- ፍትሃዊ በነበረው ማዕቀብ በሀገራችን ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነበር” ብሏል፡፡
የሃገሪቱ ዜጐች የማዕቀቡን መነሣት ተከትሎ፣ በጐዳናዎችና አደባባዮች ላይ ሰንደቅ አላማቸውን በማንገብ ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል፡፡
በሌላ በኩል ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚገኙ የሚጠበቁት የሀገረ ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
በዚህም ኤርትራ ዳግም በዚህ ጉባኤ ወደ አፍሪካ ህብረት ንቁ ተሣታፊነት  እንደምትመለስ ተጠቁሟል፡፡  


Read 6113 times