Sunday, 18 November 2018 00:00

ተቃዋሚዎች፤ መንግስት ፍትህ ለማስፈን የሚወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ህዝቡ ከመንግሥት ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል

  በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦችና የመንግስት ባለስልጣናት ላይ መንግስት ከሰሞኑ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ እንደሚደግፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለፁ፡፡
ባለፉት አመታት የመንግስትና የህዝብ ሃብትና ንብረት ላይ የተደራጀ ዘረፋ የፈፀሙ እንዲሁም በዜጎች ላይ ሰቅጣጭ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙና ከህግ ውጪ የተንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ያደነቀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ አሳስቧል፡፡
“አቃቤ ህግ የወሰደው እርምጃ በእጅጉ የሚደገፍ ነው” ያለው ፓርቲው፤ ከዚህ ቀደም በአባላቱና  በሌሎች መብታቸውን በሚጠይቁ ዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ በርካታ መግለጫዎችን በማውጣት ሲያስገነዝብ ቢቆይም ሰሚ ሳያገኝ መቅረቱን አስታውሷል ሰማያዊ ፓርቲ፡፡
ዛሬ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ህግ ፊት መቅረባቸውን ያደነቀው ፓርቲው፤ ምንም እንኳ የዘገየ ፍትህ ቢሆንም የጠቅላይ አቃቤ ህግ እርምጃ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው ብሏል፡፡
ሰብአዊ መብት ጥሰት በፈፀሙ ሰዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ለቀሪዎቹም አስተማሪ እንደሚሆን የጠቆመው ፓርቲው፤ ከሜቴክ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው “መንግስታዊ ሌብነት” ጊዜውን ጠብቆ መጋለጡ የሚደነቅ ነው ብሏል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሃገርና የህዝብ ሃብት ሲዘርፉና ሲመዘብሩ የነበሩ ሌቦችን ለህግ የማቅረብ ጅማሮውን አጠናክሮ እንዲቀጥልበት የጠየቀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ መላው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለዚህ ተግባር ሙሉ ድጋፉን በመስጠት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፤ “መንግስት በህዝባችን ላይ ተነግሮ የማያልቅና ለመናገር የሚከብድ ዘረኛ ጥቃት የፈፀሙ ወንጀለኞችን በህግ ፊት ለማዋል የወሰደውን እርምጃ እናደንቃለን” ብሏል፡፡
መንግስት ዘርፈ ብዙ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሰማርተው የነበሩ አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ህዝብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም አብን ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የተጀመረው ፍትህን የማስፈን ተግባር በተሟላ መልኩ እንዲከናወን የጠየቀው ንቅናቄው፤ ለዚህ መንግስታዊ ፍትህን የማስፈን እርምጃ የሞራል፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
“የዘር ማጥፋትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ወንጀለኞችን ወደ ፍትህ ለማምጣት የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግፍ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ በመንግስት ደረጃ ይቅርታ እንዲጠየቅና ተመጣጣኝ የልማት ካሳ እንዲከፈለው፣ ህገ መንግስቱ  እንዲሻሻልም ጠይቋል አብን፡፡
አሁን በጥቂቱ ነው የተጀመረው፤ ገና ብዙ እርምጃዎች ይጠበቃሉ ያለው መኢአድ እንዲሁ በሙስና በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚጠየቁ ሰዎችን ለህግ የማቅረቡ ስራ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁሞ፣ መንግስት እርምጃውን በጥልቀት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል፡፡ እንዲህ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይደገም ብቸኛው መፍትሔ፤ ተጠያቂነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ መፍጠር ነው ብለዋል - መኢአድ፡፡     


Read 5862 times