Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Sunday, 18 November 2018 00:00

የፖለቲካዊ ፍረጃና ሽኩቻ መዘዝ

Written by  ገ/ክርስቶስ ኃ/ሥላሴ
Rate this item
(0 votes)


   “ሽኩቻና ፍረጃ” የሚሉት ቃላት ፍቺያቸው ለየቅል ነው፡፡ “ፍረጃ”፤ አንድን ነገር “በምድብ-በምድብ መከፋፈልና መሰየም ወይም ማግለል” ሲሆን፤ “ሽኩቻ” ደግሞ “መታገል፣ መፋለም” ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቃላት፣ በፖለቲካ አውድ ውስጥ ሁነኛ ቦታ ሲያገኙ ደግሞ ምናልባትም ከተራ ፍቺያቸው በላይ ትርጓሜ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንዲያውም ዋናው የፖለቲካ መዘውር በመሆን የአንድን ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ሂደት በማመሰቃቀልና በማንፈር ልሒቃኑን ሳይቀር “የአስተሳሰብ ንጥፈት” ሊያላብሷቸው እንደሚችሉ ከታሪክ ሒደት ተመክሮ መገንዘብ ይቻላል፡፡
እነዚህን ሁለት ቃላት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት አኳያ ላለፉት መቶ ዓመታትና ከዚያም በላይ አገላብጠን ብንመረምራቸው ወይም ብንፈትሻቸው በየመንግሥታቱ ውጣ-ውረድ ውስጥ አይነተኛ ሚናና ቦታ እንደነበራቸው ለማየት አይከብድም። የዘመነ መሳፍንትን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት ካየነው፣ “ከሽኩቻና ከፍረጃ” ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንደነበረው  እንረዳለን፡፡ በዚያ  ዘመን “ፍረጃ” ለፖለቲካው እርካብ መወጣጫ ዋነኛ “የሽኩቻ” አማማጭ ነበር፡፡ ቀድሞውኑ የፊውዳሉ ሥርዓት ማኅበረሰቡን በጥቅሉ ከፋፍሎ ለመግዛት ያግዘው ዘንድ ፍረጃን በሚገባ ተጠቅሞበታል። “ቡዳ፣ የመጫኛ ነካሽ ዘር፡ የባሪያ ዘር፣…ወዘተ” የሚሉትና ሌሎቹም በማኅበረሰቡ ውስጥ የተጠሉና ዝቅተኛ የሆኑ ዜጐች እንዳሉ አመላካች ሲሆን “የባላባት፣ የጨዋ፣ የጠራ ደም ዘር፣… ወዘተ” የሚሉት ደግሞ በከፍታ ላይ ያሉ፣ እንዲገዙና እንዲነዱ የተፈቀደላቸው ወይም አስቀድመው የተመረጡ እንደሆኑ መገለጫ ነበር፡፡
ፍረጃው ወደ አመራር ወይም አገዛዝ አካባቢ ሲደርስ ደግሞ መልኩን ሊቀይር ይችላል። ጀግኖችን ለማንኳሰስ ብልሆችን ለማቃለል፣ መልካም ዝናና ክብራቸውንም ለማዋረድ ይህንኑ የፍረጃ አካሄድ ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በፍረጃ ያልተገባ የግፍ ዋጋ እንዲከፍሉና ለሥልጣን ተሻኳቾቻቸው የስስትና የእብሪት እርምጃዎች መሥዋዕትነት እንዲከፍሉ የተደረጉትን ዐፄ ቴዎድሮስንና አቤቶ ኢያሱን በምሳሌነት መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” የሚለውን ለቴዎድሮስ እንዲሁም “ክርስቲያንነትን የከዳ ወይም የሰለመ” የሚለውን ደግሞ ለኢያሱ ተጠቅመውባቸዋል፡፡
በዘመነ ደርግ፤“ፍረጃና ሽኩቻ” በሚገባ ተንሰራፍተው፣ ልሒቃኑንና በግንባር ቀደምትነት የለውጥ ፈላጊውን ኃይል እንዲሠየፉ፣ ለዘመናት የማይሽር የስቃይ ገፈት እንዲቀምሱ፣ ለመከራና ስደት እንዲዳረጉና ሌሎችም ነፍጥ አንስተው በረሃ እንዲገቡ አስገድደዋቸዋል፡፡
ለፍረጃና ለሽኩቻ እንዲዳረግ የተመቻቸው የለውጥ ኃይል በእጅጉ የተጐዳው ከውስጡ በበቀሉና ሁለቱንም (ፍረጃና ሽኩቻን) እንደ አብዮታዊ መሣሪያ በመጠቀም በሠለጠኑ ጉግ-ማንጉጐች የጥፋት ሒደት እንደነበር አይካድም። እነዚህ “በማርክሲስት-ሌኒኒስት ካባ የተተገኑ እብሪተኞች” ከእነርሱ በላይ አብዮተኛም ሆነ ፍልስፍና ዐዋቂ እንደሌለ በመቁጠር፣ “የፍረጃና የሽኩቻ” መርዛቸውን በመርጨት ተኮፈሱ። የያዙት የፍልፍስፍና መንገድ ከሶሻሊስቱ ዓለም በግልብነት የተኮረጀ እንደመሆኑ፣ በእነዚያ ሀገሮች መሳዮቻቸው የተጠቀሙባቸውን የፍረጃና የሽኩቻ መንገዶች በሙሉ አግበስብሰው በክፋት አእምሯቸው ውስጥ አጨቋቸው። በለስ በቀናቸው መድረኮችና ኃላፊነቶችም ሁሉ በተንኮል ወደ ሕዝቡ ውስጥ ረጩአቸው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው “ፓርቲ” የሚባል ቃል ሲተዋወቅ አንግቦት የመጣው የተደራጀ ኃይል “ደርጊስት፣ ፊዲስት…” በሚል ፍረጃ ታጅሎ ነበር፡፡ ለነገሩማ ደርግም ሥልጣኑን ሲቆናጠጥ “አቆርቋዥ፣ ፊውዳል፣ አድሃሪ፣…” በሚባሉ የፍረጃ ቃላት ታጅቦ ነበር፡፡ ከዚያማ በኋላ የፍረጃ ቃላቱና መንገዶቹ ሁሉ እንደ እንጉዳይ መፍላት ያዙ፡፡ “ቀኝ መንገደኛ፣ ዴማጐግ፣ ትሮትስካይት፣…” የሚባሉት ፍረጃዎች ይዥጐደጐዱ ጀመር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ “ማርክሲስት፣ ሌኒኒስት፣ ማኦይስት፣ ቦልሼቪስት፣…” የሚሉና ዋነኛ የለውጡ መዘውሮች፣ ሐዲዶችና ልሒቃን ሆነው ተፈጠሩ። እነዚህ መፈራረጆች ውለው አድረው ለሥልጣን እርካብ ናፋቂዎች የሽኩቻ ዋነኛ መንስኤዎች ሊሆኑ በቁ፡፡ እናም ሁሉም በየአቅጣጫው ሠይፍን መዘዘ፣ መትረየስ ደገነ፤ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም አስሮ በማሰቃየትና በመረሸን የሽኩቻ ውልፍቱን ተወጣ፡፡ በጊዜው ነፍጥ አንግበው በየበረሃው ደርግን ይፋለሙ የነበሩ ድርጅቶችም ሌላውን ወገን ለማስፈረጅ የተመቻቹ ነበሩ፡፡ “ገንጣይና አስገንጣይ” ዋንኛው የመፈረጃ የማዕዘን ድንጋይ ነበር፡፡ ይኸኛው አፈራረጅ ደግሞ ማለቂያ ለሌለው የእርስ-በርስ ጦርነትና እልቂት፣ ለሀብትም ውድመት ዳርጐናል፡፡ የአንድ አገር ልጆች የምንባል ዜጐች፤ ፖለቲከኞቹ በሚያስጨብጡን የፍረጃና የመሻኮቻ በትሮች እየተዋቃን፣ ለዘመናት ማባሪያ ለሌለው የደም ጐርፍ ሰለባ ሆንን፡፡
በዓለማችን ዙሪያ በመፈራረጅና በመሻኮት ሳቢያ የተከሰቱ እልቂቶች በርካታ ናቸው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፋሽስት ናዚዎች ወይም ሂትለራውያን የአገራቸውንም ሆነ የአካባቢያቸውን ሕዝብ በከፋ የጦርነት እሳት ለመለብለብ “ሰማያዊ ዐይን እና ነጭ ወርቃማ ጠጉር” የምርጥና ዓለምን ሊገዛ የሚገባ ዘር መለያ አድርገው በመፈረጅ ተጠቅመውበታል፡፡ ፍረጃ የራሱንም ተክለ-ሰውነት ወይም የብልጫ ግዝፈት ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆኖ ከቀረበም፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ከፍተኛ አፍራሽነት እንዳለው ከዚሁ ከናዚዎቹ ድርጊት መገንዘብ ይቻላል፡፡ የእብሪተኞችና የከፋፋዮች ዋነኛ የፖለቲካ ማጠንጠኛም፣ ራሳቸውን ከሌላው አስበልጦ መኮፈስ በመሆኑ ይህም አንደኛው የፍረጃ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚቀናቀናቸው ወይም የሚሻኮታቸው መስሎ የታያቸውን ሁሉ ከመንገዳቸውና ዙሪያቸው ጠራርገው ለማስወገድ የማይመለሱ ጨካኞች ናቸው፡፡ ሞሶሎኒም ከዚሁ አኳያ የሚታይ ነው፡፡  
በዘመናችን በፍረጃ ከፍተኛ የሕዝብ እልቂት የተፈጸመው በዚሁ በአህጉረ አፍሪካ በሩዋንዳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ አንደኛው የሕዝብ ወገን (ብሔር) በሌላው ላይ ያካሄደው የረዘመ ጊዜ የፍረጃ ቅስቀሳ ሞልቶ በመገንፈሉ ቱትሲንና ሁቱን ለፍጅት ዳርጓቸዋል፡፡ “በረሮ” የምትባል የማትረባ የነፍሳት ዝርያ የመፈረጃ ስድብ በመደረጓ፣ ያንን ዘግናኝ እልቂት ዓለማችን ለመታዘብ በቅቷል፡፡
የኋላ ኋላ በአገራችን ኢትዮጵያ የመጡት የፍረጃ አባባሎች ከቋንቋ፣ ከዘርና ከማንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው በመሆኑ ሁኔታው በእጅጉ እያሰጋ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ውሎ እያደረ የሚቀጣጠል የመጠቃቃት እርምጃዎች እዚህም እዚያም እየታዩ ሲሆን በቶሎ የመወገዳቸው ነገር እንደራቀም መመልከት ይቻላል፡፡ ፍረጃ የዘመናችን ቅንጡ ሙሰኞችና በሥልጣን የባለጉ ዱርየዎች ዋነኛ ማቀንቀኛ መንገድ ሲሆን፤ ለሥልጣን ሽኩቻና ለብጥብጥ መንገድ ይከፍትላቸው ዘንድ የሙጥኝ የሚሉት ድርጊታቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ፍረጃንም ሆነ ሽኩቻን ከፖለቲካው ማማ ላይ አውርዶና ፈጥፍጦ ለመቅበር ዋነኛው መንገድ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር የሚያቀነቅኑ፣ የሕዝብንም ስሜት የሚገዙ የፖለቲካ አቅጣጫዎች ናቸው። በዓለማችን ለነዚህ ዐበይት የመድኅን ፖለቲካዊ አካሄዶች ዋነኛ አባት መሪ የነበሩትን ማህተማ ጋንዲን መጥቀስ ይቻላል። ጋንዲ፤ ሕንዳውያን ከተጠመዱባቸው የቅኝ ገዥዎች የፍረጃና እርስ በርስ የማሻኮቻ አደገኛ መንገዶች በመታደግ፣ የነፃነታቸውን ልዕልና ያወጀው ለሰላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር ቅድሚያ ሰጥተው አንዲታገሉ የሕንዳውያኑን ልብ በማሸነፉ ነበር፡፡ ጋንዲ በፍቅርና በአንድነት ላይ ያነጣጠረውን ሕንድን ነፃ የማውጣት ፖለቲካዊ ጉዞውን የተለመው በደቡብ አፍሪካ ሳለ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካን የአፓርታይድ ሥርዓት ለማስወገድ የተከፈለውን የዘመናት መሥዋዕትነት ለሃያ ስምንት ዓመታት በአስከፊ አሥር ላይ ሆኖ በሚገባ ያጤነው ኔልሰን ማንዴላም፤በዚያች አገር ላይ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር መሸጋገሪያ ድልድዮችን ለመገንባት ችሏል፡፡
በተለያዩ የመፈራረጅ፣ የመሻኮትና የመዘራረፍ ወንጀሎች የጨቀየን የአንድን አገር የጉስቁልና ፖለቲካዊ ሂደት አጥቦ፣ ሁነኛ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣትና ሕዝብንም በአንድነት በማቆም ለማህበራዊ-ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሰለፍ የፍቅር፣ የሰላምንና የአንድነትን ልዕልና የሚያራምድ የፖለቲካ አውድ እጅግ ወሳኝ ነው። በሀገራችንም ለረዥም ዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን የመፈራረጅ፣ የመሻኮትና የመጠፋፋት የፖለቲካ ሂደት ለጊዜውም ቢሆን የሕዝብን ልብ በመማረክና በአንድነት በማቆም፣ ከከፋ ጥፋት የታገደው የዘመኑ “የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመደመር” አካሄድን የሚሰብከው ፖለቲካዊ ቀመር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
እነዚህ ወርቃማ ሐሳቦች የሥነ ምግባር ልዕልናን የተላበሱና ማንም ሰው በዕለት ተዕለት ተግባሩ ቢኖረው የሚወዳቸው ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር  በተለያዩ የፖለቲካ አሉታዊ ሂደቶች በተሰላቸው ሕዝብ ልቦና ውስጥ ሰርፀው ለመግባትና ለውጥ ለማምጣት ጊዜ የሚፈጁ አይመስለኝም፡፡ በአርግጥም ለሀገር፣ ለእውነተኛ ታሪክ ሂደትና ለወገን የወደፊት የተደላደለ ሕይወት ከልብ የቆመ ዜጋ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በአእምሮው ያጨቃቸውን አፍራሽ የፖለቲካ ሂደቶች በዛሬዎቹ ልዕለ-ኃይል ሐሳቦች እያጠበ፣ አዲሱን የለውጥ ጐራ ሳያቅማማ መደባለቅ እንዳለበት አምናለሁ፡፡
የወቅቱን የፍረጃና የሽኩቻ ዓይነቶችና መገለጫ መንገዶቻቸውን ከማስፈር የተቆጠብኩትም አሁን ያለንበትን የመሻገር ዘመነ-ተስፋ በማክበር ነው፡፡ ባለፉት ረዥም ዓመታት ሀገራችን ያስተናገደቻቸውን እጅግ አስከፊ የመጠፋፋትና የመጠላላት ኩነቶችን የማብቂያ መሥመር በማበጀትና “በይቅርታ” በመሻገር ስለ ወደፊቱ በተስፋ እንደ ማሰላሰል ውስጣዊ ሰላም የሚሰጥ ነገር የለም፡፡
“….ደካሞች (ሰነፎች) በፍጹም ይቅርታ የላቸውም፤ ይልቁንስ ይቅርታ የጀግኖች (የጠንካሮች) ኃያል ተግበር ነው፡፡” ያለው ታላቁ የፍቅርና የአንድነት መሪ ማህተማ ጋንዲ ነበር፡፡ አዎ በእብሪትና በማናለብኝነት ስንፈት የደደበን ልብ በመግራት ይቅርታንና ፍቅርን ማሰብ በእርግጥም “መሸነፍ ሳይሆን ታላቅ የድል አክሊል ነው፡፡” ለመበቃቀል ዳግም ማድባት ወይም መሻት እርባነ-ቢስ ከማድረግ በቀር ፋይዳ የለውም፡፡ ጋንዲ እንዳለው፤ “ዐይን ላጠፋ፣ ዐይኑን ማጥፋት፣ ዓለምን እውር ከማድረግ ውጭ ውጤት የለውም፡፡” የፍረጃና የሽኩቻ ፖለቲካዊ አካሄድ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚቀበለው ተግባር አይደለምና፣ በሐሳብና በክርክር ልዕልና የመሸናነፍን፣ ተሸናንፎም በአንድነት አገርና ትውልድ መገንባትን መምረጥ የሥልጡንነት ሁነኛ መለኪያ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡

Read 1218 times