Sunday, 18 November 2018 00:00

“አገሪቱ እንድትቀጥል የፍትህ ሥርአት መሻሻሉ አማራጭ የለውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

· ባለፉት 27 ዓመታት በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመው ወንጀል ከደርግ የሚተናነስ አይደለም
· የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለህግ ማሻሻያ ም/ቤት በራሳቸው ተነሳሽነት አስተዋፅኦ አድርገዋል
· መንግስት በህግ መገዛትን እንዲለምድ ጭምር ማስገደድ አለብን

የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ከተጀመሩ የለውጥ እርምጃዎች አንዱ በፍትህ ስርአቱ ላይ እየተወሰዱ ያሉ ማሻሻያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ እስካሁን በጸረ- ሽብር አዋጁ፣ በሚዲያ ህጉና በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ህጎች ላይ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ለመሆኑ የህግ ማሻሻያዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? በህግ ማሻሻያ ም/ቤት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምንድን ናቸው? ከማሻሻያ እርምጃዎቹ ምን ውጤት ይጠበቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ አመሃ መኮንን ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

የተጀመሩት የህግ ማሻሻያ እርምጃዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አሁን እየተወሰዱ ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎችን ስናነሳ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን እነዚህ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያስፈለገበትን  ምክንያት መዘንጋት የለብንም፡፡ አንደኛ፤ እየተወሰደ ያለው የማሻሻያ እርምጃ ምን ያህል ተመጣጣኝ ነው የሚለውን ለመመዘን ይረዳል፡፡ ሁለተኛ፤ ባለፉት ጊዜያት በተለይ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በዜጎች ላይ የደረሱ እጅግ በጣም አሰቃቂ ጉዳት ያጣነውን ፈርጀ ብዙ ጥቅምና እንደ ሃገር የደረሰውን ጉዳት እየመዘገቡ መሄድ አስፈላጊ በመሆኑ እነዚያን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ሀገሪቷ ሙሉ ለሙሉ በመፈራረስ ደረጃ ላይ የነበረችበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከማህበራዊ ሚዲያዎችና መቀመጫቸውን በውጭ ሃገር ካደረጉ አንዳንድ ሚዲያዎች ብቻ ነበር የምንሰማው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች መንግስትን አሞጋሽና አወዳሽ ብቻ ሆነው፣ ለእነዚህ ችግሮች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነው የኖሩት፡፡ በቅርቡ ነው በመንግስት ውስጥ የነበሩ የለውጥ ኃይሎች ሀገሪቷ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ተረድተው ለመለወጥ የተንቀሳቀሱት፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኋላ ነው የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ የተጀመረው፡፡
ወደ ህግ ማሻሻያ ጉዳዮች ስንመለስ፣ እኔ እስከማውቀው በንባብም ባለኝ መረጃና በስራ ሂደት ባለኝ ተሞክሮ፤ የህግ ስርአቱ እስከ ዛሬ ድረስ ከላይ ወደ ታች ነበር የሚወርደው፡፡ መንግስት የፈለገውን እርሱ የመሰለውን ወይም አላማዬን ያስፈፅምልኛል ብሎ ያመነበትን ህግ አርቅቆ፣ የይስሙላ ውይይት ተደርጎበት፣ በቀጥታ ህዝቡ ላይ የሚጫንበት አሰራር ነበር፡፡ ይሄ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በግልፅ ስናየው የነበረ ነው፡፡ ህዝብን የሚጠቅሙ ሳይሆን የመንግስት ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ ህዝብን መፈናፈኛ የሚያሳጡ ህጎች እየወጡ ነበር ወደ ህዝቡ የሚወርዱት፡፡ አሁን ግን ይሄ ተገልብጦ ህጎች ከታች ወደ ላይ ነው መሰራት ያለባቸው በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያራመዱት ሃሳብ መልካም ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጠ/ሚኒስትሩ፤ በተለያየ ቦታ ተበታትኖ የሚገኝን እውቀት ሰብስቦ ለሃገር እንዲጠቅም ማድረግ ይገባል በሚል የህግ ማሻሻያ ም/ቤት እንዲቋቋም አድርገዋል። የተለያዩ የህግ ባለሙያዎች የተጋበዙበት ምክር ቤት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ም/ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ ጉልህ ተግባራት ምንድን ናቸው?
አሁን ወደ 8 ንኡስ ፕሮግራሞች ተለይተዋል። በእነዚህ ፕሮግራሞች ስር የተለያዩ ግብረ ኃይሎች ተቋቁመው ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከእነዚህ ንኡስ ፕሮግራሞች ውስጥ በተለይም የፀረ ሽብር አዋጁ፣ የሚዲያ ህጉና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ህጎች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተብሎ ሲሰራ ቆይቷል። ባለኝ መረጃ፤ የበጎ አድራጎት ህጉን በተመለከተ ስራው አልቆ የተረቀቀው ህግ ለመንግስት ቀርቧል፡፡ ከዚህ በኋላ በተለመደው የህግ አወጣጥ ስርአት ውስጥ የሚያልፍ ይሆናል፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁም በተመሳሳይ ሁኔታ ስራውን እየሰራ ነው። ረቂቅ እያዘጋጀ ነው፡፡ በቅርቡ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል፡፡ የሚዲያ ህጉም በተፋጠነ ሁኔታ እየተሰራ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ተቋማት ማሻሻያም በፍጥነት እየተሰራ ስለመሆኑ መረጃ አለኝ፡፡ በህግ ስርአቱ በኩል ለዘመናት የቆዩ ብልሽቶች ስለነበሩ በሚፈለገው ፍጥነት፣ በአጭር ጊዜ ሁሉንም ማድረግ ይቻላል የሚል ግምት የለኝም፡፡ የህግ ማሻሻያ በመሰረቱ ቋሚ ስራ ነው፤ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፡፡ የህግ ስርአት ከህብረተሰብ ሁለንተናዊ እድገት ጋር ተያይዞ አብሮ በየጊዜው የሚያድግ ነው፡፡ ለወደፊት በቋሚነት ህጎቻችን ከወቅታዊ ሁኔታዎች፣ ኢትዮጵያ በአለማቀፍ ደረጃ ከገባችባቸው ግዴታዎች ጋር ህጎቻችን ምን ያህል ይጣጣማሉ፣ ምን ያህል ወቅታዊውን የህዝብ ፍላጎት ያሟላል የሚሉትን እየፈተሸ በቋሚነት ማሻሻያዎችን የሚያደርግ ተቋም መፈጠር አለበት፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ግን ጥሩ አካሄድ ላይ ነው የሚል እምነት አለኝ። በአጠቃላይ የህግ ባለሙያዎች በዚህ ሂደት ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆንም አለባቸው፡፡ የህግ ባለሙያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ቢያቀርቡ፣ አሁን ከበፊቱ የተሻለ የመደመጥ እድል ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ህግ የተሻለ የሚሆነው ከታች ወደ ላይ ሲመጣ ነው ብለዋል፤ አሁን ይህ አካሄድ ምን ያህል እየተተገበረ ነው ይላሉ?
ም/ቤቱ ለስራው መቀላጠፍ ሲባል  በጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ውስጥ ሴክሬቴሪያት የተቋቋመለት ቢሆንም በራሱ የቆመ ገለልተኛ አካል ነው፡፡ በሙያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው ስም ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጭምር የተሰባሰቡበት ም/ቤት ነው፡፡ በሂደቱ እየተሳተፉ ያሉ ባለሙያዎች ለሙያቸው ያደሩና ነፃ የሚባሉ ናቸው፡፡ ይሄ ከታች ወደ ላይ የሚለው አሰራር እየተተገበረ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ህጎቹ ማሻሻያ ሲደረግባቸው ዝም ብሎ አይደለም፤ ዝርዝር ጥናት ሲያደርጉ ህብረተሰቡን ያሳትፋሉ፤ ቃለ መጠይቅ ያደርጋሉ፣ የተለያዩ ሰነዶች ይመረምራሉ፡፡ ይሄ አንዱ ከታች ወደ ላይ እየሄደ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በጥናቱ ላይ ተመስርቶ በሚወጡት የህግ ረቂቆች ላይ የተለያዩ የህብረተሰቡን ክፍሎች እያወያዩ ነው፡፡ የሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች በውይይቶቹ እየተሳተፉ ነው፡፡ የሲቪል ማህበራት ህጉ ላይ የነበሩ ችግሮች ለጥናት ሲለዩና ረቂቅ ሲያወጡ፣ በሀገሪቱ በጠቅላላ ሊባል በሚችል ደረጃ ከ10 ያላነሱ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ የፀረ ሽብር ህጉም አሁን በረቂቅ ላይ እያለ እስካሁን ድረስ ከባለሙያዎች፣ ከፓርቲ ተወካዮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከሶስትና አራት ያላነሱ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ በቀጣይም ከአዲስ አበባ ውጪም በክልሎች አካባቢ ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከታች ወደ ላይ እየሄደ ነው ለሚለው ይሄ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዳዩ ወደ ፓርላማ ሲሄድ ደግሞ ህዝብ የሚሳተፍበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡  
እስካሁን ያለው አካሄድ አጥጋቢ ነው ብለው ያምናሉ?
በኔ በኩል እስካሁን አካሄዱ አጥጋቢ ነው፡፡ ግን ሊደርስባቸው የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወሰኑ ናቸው፡፡ መቼም በአንድ የህግ ማሻሻያ ላይ 100 ሚሊዮን ህዝብ ማወያየት አይቻልም፤ ነገር ግን አስተዋፅኦ ማድረግ እንፈልጋለን ለሚሉ ሁሉም አካላት የም/ቤቱ በር ክፍት ነው። የማንኛውንም ሰው ሃሳብ ለመቀበል ችግር የለበትም፡፡ ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነት አስተዋፅኦ እናደርጋለን ብለው አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ አስተዋፅኦዋቸውም ጠቃሚ ነበር፡፡
በፀረ ሽብር ህጉ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?
የበፊቱ ህግ አንደኛ አዋጁ ራሱ ሲወጣ የነበረው ሁኔታ አነጋጋሪ ነው፡፡ እንደምናውቀው ህጉ ከመውጣቱ በፊት መንግስት በተደጋጋሚ የፀረ ሽብር ህግ አያስፈልገኝም፤ ያለኝ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በቂ ነው ሲል ቆይቶ ነው በድንገት ምርጫ 97ን ተከትሎ አዋጁ የወጣው፡፡ አዋጁ ሲወጣ ደግሞ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል፣ ፖለቲከኞች፣ የህግ ባለሙያዎች … ህጉ የህዝብን ነፃነት፣ የፖለቲካ ነፃነትን ለመገደብ የወጣ ነው በሚል ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበር፡፡ ነገር ግን ተቃውሞው ወደ ጎን ተገፍቶ ነው ህጉ የወጣው። ህጉ በብዙ መልኩ አለማቀፍ ደረጃን ያሟላ አልነበረም፡፡
ለሽብርተኝነት የተሰጠው ትርጉም እጅግ ሰፊና ማንኛውም ሰው በሽብር ሊከሰስ የሚችልበትን ሁኔታ የፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ግልፅነት የጎደለበት ህግ ነው፡፡ ለአንዳንድ ተቋማት በተለይ ለደህንነት ኃይሉ የሰጠው ጉልበት ኃይለኛ ነው፡፡ በአዋጁ የሚከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብትን የሚያጣብብ ነው፡፡ መሰረታዊ የሚባሉ የማስረጃ መርሆዎችን የሚጥስ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የግለሰቦች መብት በዚህ ህግ ሲጣሱ መከላከል የሚያስችሉና በቂ ጥበቃ የሚያደርጉ ድንጋጌዎች አልነበሩትም፡፡ በዚህ አዋጅ አፈፃፀም ላይ ሚና ያላቸው ተቋማትም አዋጁን ለማስፈፀም ብቃት አልነበራቸውም። ከደህንነት ኃይሉ እስከ ፍ/ቤት ያሉ ተቋማት ይሄን ህግ ለማስፈፀም ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ኃላፊነትም አይሰማቸውም ነበር። አዋጁ በራሱ የፈጠረው ችግር እንዳለ ሆኖ፣ አዋጁን ለማስፈፀም የተቀመጡት ተቋማት በአተገባበሩ ላይ የፈፀሙት ችግር ቀላል አልነበረም፡፡ ይሄ ደግሞ ሰሞኑን የምንሰማውን ምንጊዜም ተመዝግቦ የሚቀመጥ፣ እጅግ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዜጎች ጥቃትን አስከትሏል፡፡
ህጉ ሲሻሻል አንደኛ የቀድሞ ህግ የፈጠራቸው ችግሮች ድጋሚ እንዳይፈጠሩ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሆን ተሞክሯል፡፡ ትልቅ መነሻ የተደረገው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረትም ደጋግመው በተለያዩ ውሳኔዎቻቸው ሲገልጹ እንደነበረው፣ በየትኛውም ሃገር የሚወጣ የፀረ ሽብር ህግ ሁለት ሁኔታዎችን አቻችሎ እንዲወጣ ይመክራሉ። እውነተኛ የሽብር ህግ፤ ሃገርን በበቂ ሁኔታ ከሽብር የሚከላከልና አስተማሪ የሚሆን ቅጣት የሚጥል መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማይጥስ እንዲያውም ጥበቃ የሚያደርግ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የፀረ ሽብር ህጉ እየተዘጋጀ ያለው፡፡ ከህግ አፃፃፍ አንፃር በፊት የነበሩት ጉድለቶችም እንዲስተካከሉ ተደርጓል፡፡ ህጉ በተቻለ መጠን አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ኢትዮጵያ አለማቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ለመጠበቅና ለማስከበር የገባችውን ቃል ኪዳን የሚያሟላ ሆኖ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በእርግጥ ምንም ያህል የተዋጣለት ህግ ቢሆንም ህግን በመተግበር በኩል ሚና ያላቸው ተቋማትም በዚያው መጠን እስካልተሻሻሉ ድረስ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል ማለት አይቻልም። ስለዚህ የምንጠብቀው ይሄን የሚተገብሩ ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ የሆኑ፣ ለዲሞክራሲያዊ እሴቶች ዋጋ የሚሰጡ ተቋማትና የተቋማት  አመራር ያስፈልጋሉ። ያ እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ ነው ህጉ እየተሻሻለ ያለው፡፡
ብዙዎች የቀድሞው ህግ  ለሰብአዊ መብት ጥሰት በር ከፍቷል ይላሉ …
አሁን ይሄ ጉዳይ ከፖለቲካ ቃል አልፎ በህግ ረገድ ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ አሁን ቢያንስ በአስፈፃሚው አካል ሲደረጉ የነበሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ተረጋግጠዋል፡፡ በዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ የስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይሄ ከመሆኑም በፊት ግን ላለፉት በርካታ አመታት ብዙዎቻችን ይሄ ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን በአደባባይ እየገለፅን፣ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስንጠይቅ ነበር፡፡ በኔ በኩል የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ አካል ተገቢው ምርመራ ቢደረግበት በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ የሚለውን አለማቀፍ ወንጀል መስፈርት የሚያሟላ እንደሚሆን ግምት ነበረኝ፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ስለ ጥሰቱ በሰጡት መግለጫ የተገነዘብኩትም ጥሰቱ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ፣ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ደረጃን የያዘ መሆኑን ነው። በሰብአዊነት የተፈፀመ አለማቀፍ ወንጀል ደረጃ ላይ ያለ ወንጀል ነው የተፈፀመው፡፡
በዚህ ደረጃ ለተፈፀመ ወንጀል ደግሞ ፈፃሚዎቹ በማናቸውም ደረጃ የይርጋ ተጠቃሚ መሆን አይችሉም፤ በማናቸውም የይቅርታ ህግ ከተጠያቂነት ሊያመለጡ አይችሉም፡፡ ምናልባት ይሄን ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች በየትኛውም የአለም ክፍል ቢገኙ፣ በተገኙበት ቦታ ሁሉ ሊከሰሱና ሊጠየቁ የሚችሉበትን መብት የሚያሰጥ ነው። አሁን እየሰማን ያለነው  ወንጀል እነዚህን ሁሉ ያሟላ ነው፡፡ እንግዲህ በደርግ ዘመን በርካታ ዘግናኝ ወንጀሎች በሰብአዊነት ላይ እንደተፈፀመ እናውቃለን፡፡ ባለፉት 27 አመታት ግን በሃገሪቱ የተፈፀመው ተመሳሳይ3 ወንጀል ከዚያ ቢብስ እንጂ የሚያንስ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ስለተፈፀሙ የሠብአዊ መብት ጥሰት ስናነሳ፣ ከፀረ ሽብር አዋጅ ጋር በተያያዘ ስለተፈጸሙት ነው እየተነጋገርን ያለነው፡፡ ነገር ግን ብዙ የደረሱበት የማይታወቁ፤ ቤተሰቦቻቸው ዛሬም ድረስ ፍትህ ያላገኙ አሉ፡፡ እጅግ አሠቃቂ ግድያዎች ተፈጽመዋል፤ የመሠወር ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ በተለይ ይሄ ሰውን የመሠወር ተግባር በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ህግጋት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ ከመግደል ያልተናነሰ ድርጊት ነው። በዚህ መንገድ ብዙ ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም፡፡ ጥሰቱ እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡
በዳኝነት አሰጣጡም ላይ በርካታ አቤቱታዎች ይቀርባሉ፤ በዚህ ረገድ ምን ማሻሻያዎች ለማድረግ ታስቧል?
የህግ ስርአታችን ላይ ችግር አለ ስንል፣ አንዱ የዳኝነቱ ስርአት ነው፡፡ የዳኝነት ስርአቱ ከሌብነት፣ ከነፃነት እጦት፣ ከብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ በጣም ሠፊ ችግር ያለበት ተቋም ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ስናየው፤ ብዙ አይነት ችግር ያለባቸው ዳኞች ያሉበት ተቋም ነው፡፡ ከመብት፣ ከብቃት ማነስ፣ የፅ/ቤትን ነፃነት ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ እጥረት ያለባቸው ብዙ ዳኞች ያሉበት ተቋም ነው፡፡ በዚያው መጠን ግን ለገቡት ቃለ መሃላ፣ ለሙያቸው ቀናኢ የሆኑ ዳኞች የሉም  ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ቢያንስ በጠቅላይ ፍ/ቤት ደረጃ አመራሩ ላይ ለውጥ ተደርጓል፡፡ በከፍተኛና በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ላይ እስካሁን የተደረገ የማሻሻያ ለውጥ የለም፡፡ ፍ/ቤት ከሌላው ተቋም ይለያል፡፡ ዳኝነት ገለልተኛና ነፃ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከዚህ አንፃር ለአስፈፃሚው አካል በቀላሉ አመራሮችን መቀየር ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ በጠቅላይ ፍ/ቤት ደረጃ በተደረገው የአመራር ለውጥ ብዙ ነገር እንጠብቃለን፡፡ እየተሠራ ያለ የለውጥ ጥናትም አለ። ምን ለውጥ ይመጣል የሚለውን እንግዲህ በቀጣይ የምናየው ነው፡፡
በፍትህ ስርአቱ ላይ ከሚደረገው ማሻሻያ ወይም ለውጥ ምን ጉልህ ውጤት ይጠበቃል?
ለውጥ የማድረጉ ጉዳይ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ሃገሪቱ እንድትቀጥል፣ ዜጎቿ በሰላም መኖር እንድንችል የፍትህ ስርአት መሻሻሉ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ የህግ የበላይነት ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት በሀገሪቱ እንዲኖር የማድረግ ጉዳይ ጊዜ ይፈታዋል የሚባል አይደለም፡፡
አሁኑኑ ሊሰራበት የሚገባ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የህግ የበላይነት መከበር አለበት። የህግ የበላይነት ስንል፣ ህዝብን በህግ የመግዛት ብቻ ሳይሆን ገዥውም በህግ የመገዛት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የህግ የበላይነት ፈፅሞ ችላ መባል የለበትም። ይሄ ሃገር የመንግስት ብቻ አይደለም፤ የሁላችንም ነው፤ መንግስት የሚሰጠንን ብቻ መጠበቅ የለብንም፤ መንግስት በህግ መገዛትን እንዲለምድ ጭምር ማስገደድ አለብን፡፡



Read 5636 times