Saturday, 17 November 2018 11:11

በእርግጥም የጀግኒት ዘመን!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ፤ 50 በመቶ የሚኒስትርነቱን ድርሻ ለሴቶች መስጠታቸው ከፍተኛ ውዳሴን  የተቀዳጀው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ በአፍሪካ እንዲሁም በመላው ዓለም በእጅጉ ተደንቋል፡፡
ሴቶችን ወደ ከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን የማምጣት እርምጃ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ኢትዮጵያ ከንግስት ዘውዲቱ ወዲህ የመጀመሪያዋን ሴት ርዕሰ ብሄር አግኝታለች፡፡ ሴት ፕሬዚዳንት በመሾም በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች - ኢትዮጵያ፡፡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ የመጀመሪያዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተሹመዋል፡፡ ሰሞኑን የተሾሙት የጠ/ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬተሪ ሃላፊ (ቃል አቀባይ) እና ምክትላቸውም እንዲሁ ሴቶች ናቸው፡፡ በእርግጥም የጀግኒት ዘመን ነው፡፡  
የተባበሩት መንግስታት ሴቶች ዋና ዳይሬክተር ፉምዚሌ ምላምቦ፣ ሴቶች የአመራር ዕድል ከተሰጣቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ ሲመሰክሩ፤ ‹‹የሴቶች አመራር ሰጪነት በጎ ተጽዕኖዎችን የሚያሳዩ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ሴቶች አገሮችን፣ ከተሞችን፣ኢኮኖሚዎችንና ጠንካራ ተቋማትን ስኬታማ በሆነ መንገድ ገንብተዋል፣ መርተዋልም›› ይላሉ፟።
 በሴቶች ወደ ከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን መምጣት የማይበርዳችሁም ሆነ የማይሞቃችሁ ሰዎች፣ ለአገራችን ትልቅ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም፡፡
እንኳን ለእኛ የዲሞክራሲ እናት ነኝ ለምትለዋ አገረ አሜሪካም ጭምር። ለዚህ ነው ሰሞኑን በአሜሪካ በተካሄደው የአማካይ ዘመን ምርጫ፤ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር ለኮንግረስ መመረጣቸው፣ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተው፡፡ የሴቶች መብት ተሟጋቾች፤ “ምርጫው ለሴቶች ድል ነው” ብለውታል፡፡ እናላችሁ፤ “ኢት  ኢዝ ኤ ቢግ ዲል!” ለማለት ነው። በዚያ ላይ አገሪቱ የጀመረችው ሁለንተናዊ የለውጥ እርምጃ አካልም መሆኑን አትዘንጉት፡፡  
የኢትዮጵያ ሴቶች በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ቁልፍ የመንግስት ሥልጣኖችን መቆጣጠራቸው በራሱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተው፣ብቃታቸውን እንደሚያሳዩንም  አልጠራጠርም። በነገራችን ላይ ከሰሞኑ የሴቶች ሹመት ጋር ተያይዞ፣ ለዘመናት በወንዶች ብቻ በሞኖፖል ተይዞ የቆየውን የመንግስት ስልጣን የተነጠቁ የመሰላቸው አንዳንድ ወንዶች፤ “የወንዶች መብት ተሟጋች” ድርጅት ለማቋቋም ማሰባቸውን ፍንጭ  ሰምቼ ፈገግ ብያለሁ፡፡    
ወደ ቁምነገሩ ስንመጣ፣ የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ከፍተኛ የሴት ሹማምንት ቁጥር ምን ያህል እንደደረሰ ታውቁ ይሆን? ባታውቁም አትጨነቁ፤ ዝርዝራቸውን  እነሆ፡-
ወ/ሮ ሙፈረያት ካሚል - የሠላም ሚኒስትር
ኢንጅነር አይሻ ሞሃመድ - የመከላከያ ሚኒስትር
ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር - የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር
ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ   - የትራንስፖርት ሚኒስትር
ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም - የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
ወ/ሮ ያለም ጸጋዬ  አስፋው - የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር
ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ - የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር
ዶ/ር ሂሩት ካሣው - የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር
ወ/ሮ አዳነች አበበ - የገቢዎች ሚኒስትር
ዶ/ር ፍጹም አሰፋ - የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሚኒስትር
አምባሳደር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ - ርዕሰ ብሔር
ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ - የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት
ወ/ሪት ቢልለኔ  ሥዩም - የጠ/ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪ ሃላፊ
ወ/ሪት ሄለን ተስፋዬ   -  የጠ/ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪ ምክትል ሃላፊ

Read 1827 times