Sunday, 18 November 2018 00:00

በ3 አገራት መሪዎች የተመረቀው ግዙፍ ተቋም - ጥበበ ግዮን

Written by  ጌትነት ግዛው
Rate this item
(1 Vote)

 ከወራት በፊት ወደ ውቢቷ ከተማ ባህር ዳር ተጉዤ ነበር፡፡ አካሄዴ በባህር ዳር ዘንባባዎች ጥላ ስር ለመንሸራሸር፣ አልያም ከጣና ዳር ቁጭ ብዬ ትኩስ አየሯን እየማግኩ ዘና ለማለት አልነበረም፤ ድንገተኛ የቤተሰብ ጉዳይ ገጥሞኝ እንጂ፡፡ በጠና ታምማ ሆስፒታል የገባችውን የቅርብ ዘመዴን ለመጠየቅ ነበር ወደ ባህር ዳር ያቀናሁት፡፡
ባህር ዳር እንደገባሁ በቀጥታ ያመራሁት ቀበሌ 13 ውስጥ ወደሚገኘው ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ነበር፡፡ ከዋናው በር ገባ ብሎ በስተግራ በኩል የሚገኘው የታካሚዎች መኝታ ክፍል መግቢያ ላይ ስደርስ ግን፣ አንዳች አስደንጋጭ ትዕይንት ተመለከትኩ፡፡ በጽኑ የታመሙ፣ አቅም አንሷቸው የሚዝለፈለፉ፣ የአስታማሚዎቻቸውን ክንድ የተንተራሱ ታካሚዎች እዚህም እዚያም ወለል ላይ ወድቀው ያቃስታሉ፡፡ የሆስፒታሉ አልጋዎች በሙሉ ቀድመው በመጡ ታማሚዎች የተያዙባቸው በርካታ ታካሚዎች፣ የግሉኮስ ከረጢቶችን እንዳንጠለጠሉ ግድግዳ ተደግፈው ያጣጥራሉ፡፡
ልብን በሚሰብርና ሊያዩት በሚዘገንን አሰቃቂ ነገር ዙሪያዬን ተከብቤያለሁ፡፡ አልጋ ለማግኘት ባልታደሉትና አግዳሚ ወንበር ወይም ወለል ላይ ተኝተው ከመታከም ውጭ አማራጭ ባልነበራቸው ታካሚዎች መካከል ክፍት ቦታ እየፈለግኩ እንደምንም አለፍኩና ዘመዴ ወደ ተኛችበት ክፍል ዘለቅኩ፡፡
በዚያች ቅጽበት በፈለገ ህይወት ሆስፒታል የተመለከትኩት ነገር ለቀናት ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ማለዳ ዳግም ወደ ባህር ዳር አቅንቼ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የዶ/ር ፍሬውን ንግግር ስሰማም፣ ቀድሞ ወደ አእምሮዬ የመጣው በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ያየሁት ይሄው አሰቃቂ ትዕይንት ነበር፡፡
“እናት ልጇን በክንዶቿ ላይ አንተርሳ የምታሳክምበት ከተማ” በማለት ነበር፣ ዶ/ር ፍሬው ባህር ዳርን የገለጹዋት - በዕለቱ በተካሄደው የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የምረቃ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ለረጅም አመታት ከባህር ዳርና ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የሚጎርፉ ታካሚዎችን ተቀብሎ ሲያስተናግድ የቆየው ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል፣ የታካሚዎች ቁጥር ከአቅሙ በላይ ከሆነበት ቆይቷል፡፡ የታካሚዎች ቁጥር ከሆስፒታሉ አልጋዎች ቁጥር በእጅጉ የሚልቅ ሆኗል፡፡ በሆስፒታሉ አልጋዎች የተያዙባቸውና አማራጭ የሌላቸው በርካታ ሰዎችን ወለል ላይና አግዳሚ ወንበር ላይ ተኝተው ሲታከሙ መመልከት የተለመደ ነገር ነው፡፡
በ1992 ዓ.ም በሙሉ ዩኒቨርሲቲነት ተቋቁሞ ስራውን የጀመረው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በ8 ካምፓሶች፣ በ5 ኮሌጆች፣ በ4 ተቋማት፣ በ2 ፋኩልቲዎችና በ1 ት/ ቤት የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች አንዱ የሆነው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ለአመታት የመማር ማስተማሩንና የምርምር ስራውን ሲያከናውን የቆየው በፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ ያለው የቦታ ጥበት ያሰበውን ያህል እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖበት የቆየው ኮሌጁ፣ የኋላ ኋላ ግን በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ያለውን የቦታ ጥበት ችግር ለመቅረፍና የህክምናና የምርምር ስራዎቹን በስፋት ለማከናወን የሚያስችለውን ዕቅድ አውጥቶ መትጋቱን ተያያዘው፡፡ የትጋትና ጥረቱ ውጤት ከሰሞኑ ፍሬ አፍርቷል - ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፡፡
ህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም… ማለዳ ላይ…
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ207 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን ግዙፉን ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ለ6ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የህክምና ተማሪዎች የሶስት አገራት መሪዎች በክብር እንግድነት በተገኙበት በአንድነት ባስመረቀበት ታሪካዊና ደማቅ ስነስርዓት ላይ የመገኘት ዕድል ገጠመኝ፡፡
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተገኙበት የተመረቀው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ 500 አልጋዎችና 11 የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡
ለ7 ሚሊዮን ያህል ዜጎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው ሆስፒታሉ፣ በየዕለቱ ሁለት ሺህ ያህል ህሙማንን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም እንዳለውና 51 ስፔሻሊስት ሃኪሞች እንደሚመደቡለት የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሽጌታ ገላው በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ጥበበ ግዮን አንድ ደረጃውን የጠበቀ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማሟላት ያለበትን መስፈርት ያሟሉ የህክምና ክፍሎች እንዳሉት የጠቆሙት ፕሮፌሰር የሽጌታ፣ በቀጣይ የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍሎችን ቁጥር ወደ 15 ለማሳደግና ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን በተሻለ መልኩ ለማሟላት ቢታቀድም የበጀት ጉዳይ እንቅፋት ሆኖ እንደሚገኝ አስምረውበታል፡፡
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘም 172 ተማሪዎች በተመረቁበት በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የበጀትን ጉዳይ በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው አንስተውታል። ሆስፒታሉ በጀት እንዳልተመደበለት በመግለጽ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸውንና ከሌሎች የጤና ተቋማት ለከፍተኛ ህክምና የሚላኩ ታካሚዎች ተቀብሎ እንደሚያክም የጠቆሙት ዶ/ር ፍሬው፤ በተለያዩ የህክምናና የጤና ሳይንስ የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን እየተቀበለ እንደሚያሰለጥን ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ስድስተኛው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሆነው ጥበበ ግዮን፣ በጥራትም ሆነ በአገልግሎት ከሁሉም የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ቢዘጋጅም፣ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች መሟላት ያሉባቸው ነገሮች ይቀሩታል፡፡ የቀሩ ነገሮችን ለማሟላት ደግሞ ከመንግስት በተጨማሪ ለጋሽ አካላትና በዘርፉ የሚሰሩ ወገኖች ድጋፍ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
በእርግጥም ሆስፒታሉ እዚህ ደረጃ የደረሰው በአጋሮችና ለጋሾች ድጋፍና እገዛ ነበር፡፡ ለሆስፒታሉ ከዚህ ደረጃ መድረስ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል በሚል በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ከዩኒቨርሲቲው የዋንጫ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት የተበረከተለት ሂዩማን ብሪጅ የተባለው አለማቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት ከእነዚህ የዩኒቨርሲቲው አጋሮች አንዱ ነው። ተቀማጭነቱ በስዊድን የሆነው ሂዩማን ብሪጅ ለጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁ በርካታ የህክምና መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከዚህ ቀደምም ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ለበርካታ ተቋማት በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁሶችን በመለገስ በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ ሂዉማን ብሪጅ  ለዚህ አዲስ ለተገነባው ሆስፒታል በቁጥር እጅግ የበዙ የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን ለግሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሆስፒታሉ የለገሳቸውን የህክምና መሳሪያዎች ተከላ የተሳካ ለማድረግና የተበላሹትን ለመጠገን  ከሂውማን ብሪጅ ባ/ሜድካል ኮሌጅ ባለሙያዎችን በመውሰድ  ከፍተኛ የሆና የሙያ ድጋፍ አበርክቷል።
ሂውማን ብሪጅ ለጥበበ ግዮን ሆስፒታል ከኢህ ደረጃ መድረስ ላበረከተው አስተዋጽኦና ላደረገው ከፍ ያለ የህክምና መሳሪያዎችና የሙያ ድጋፍ የምስጋና እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡ የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ አዳሙ አንለይ፤ ስራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ላበረከቱት ከፍተኛ ድጋፍና ሆስፒታሉ በጥራትና በብቃት የተሻለ ሆኖ ስራውን እንዲጀምር ላደረጉት ቀና ትብብር ከዪኒቨርሲቲው የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በዕለቱ ለዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ተመራቂዎቹ ትምህርት የማያልቅና የማይቋረጥ መሆኑን ተገንዝበው፣ ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውን በቅንነት በማገልገል ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱና ለሀገር አለኝታ እንዲሆኑ አሳስበዋል። ምሩቃኑ መደበኛ ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ወደ ሶማሊያና ኤርትራ በመሄድ፣ በሙያቸው ለጥቂት ጊዜ በነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ በማቅረብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሁኔታዎችን እንዲያመቻች መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር፡፡ ተመራቂዎቹ ወደ ኤርትራና ሶማሊያ ሄደው የነፃ ህክምና አገልግሎት መስጠታቸው፣ በሀገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ውህደትና የህዝብ ለህዝብ መቀራረብ ለማሳደግ እንደሚረዳም ጠቁመው ነበር።
ይህን ተከትሎ በተደረገ ውይይትም በድምሩ 100 ያህል የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች ወደ ኤርትራና ሶማሊያ አቅንተው በነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ መግባባት ላይ መደረሱ ተነግሯል፡፡ ይህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ከአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰባዊ አገልግሎት ከሚያበረክተው አገራዊ ፋይዳ ባለፈ፣ በአገራት መካከል አንድነትን የሚያጠናክር ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ስራ አገልግሎትን በመጀመር ፈርቀዳጅ ተቋም አድርጎ በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፍረዋል፡፡

Read 1752 times