Sunday, 18 November 2018 00:00

እስቲ “ፍትህ ለኢትዮጵያ” እንበል!

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(0 votes)

 እ.ኤ.አ. በ1871 በፈረንሣዊው ዩጂን ፖቲየ የተደረሰውና የግራ-ዘመሞች (በዋናነት የሶሻሊስቶች) መዝሙር የሆነውን “ኢንተርናሲዮናል” በልጅነታችን በትምህርት ቤት የዘመርን ሁሉ እናስታውሰዋለን፡፡ በግጥሙ ውስጥ ካሉት ስንኞች መካከል፡-
“ፍትህ በሚገባ ይበየናል፤
ሻል ያለ ዓለምም ይታያል፡፡”
-- የሚሉ ይገኙበታል፡፡
የሶሻሊስታዊያንና የግራ-ዘመሞች የፍትህ “በሚገባ የመበየን” ምኞት ሙሉ በሙሉ ዕውን ሳይሆን ቀርቶ፣ በምትኩ ፍትህ-አልባነት መገለጫቸው ሆኖ እስከ ኮሙኒዝም ፍጻሜ ድረስ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ቢሆን፣ በግራ ዘመም የፖለቲካ አራማጅ ኃይሎች የሚመሩ በርካታ አገራት ፍትህ-አልባነት ዋነኛ መለያቸው እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያም፣ በተለይ ከ1966 አብዮት አንስቶ “ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነት” የሚሉ መፈክሮች ሲስተጋቡባት የኖረች ብትሆንም፣ ቃልና ተግባር ያልተገናኙባት፣ እንዲያውም በተቃራኒው፣ ከቀደሙት ዘመናት በከፋ መንገድ እነዚህ መብቶች የተረገጡባት ምድር ሆናለች። ለመብቶቹ መረጋገጥ በርካታ ዓመታትን የወሰዱና ከፍተኛ መስዋዕትነት ያስከፈሉ ትግሎች ተካሂደው “ጨቋኝ” የተባሉ አስተዳደሮች ቢወገዱም፣ በምትካቸው የመጡት አሸናፊዎች ከመሻል ይልቅ እየባሱ፣ ከመምራት ይልቅ እየገዙና የጭካኔ መንገዳቸውንም እያከፉ ለሌላ ዙር አመጽና ትግል በር ሲከፍቱ፣ በዚህም ትግል እነርሱም ከወንበራቸው በመፈንገል አዙሪቱን አስቀጥለውታል፡፡
በእያንዳንዱ የአገዛዝና የወንበር ለውጥ ማግሥት፣ የተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎች፣ የተዳፈኑበትን አመድ እያራገፉ ወደ አደባባይ መውጣታቸው የተለመደ ነው፡፡ ዜጎች በተለያዩ አደረጃጀቶች “አሉን” የሚሏቸውን ጥያቄዎች ይዘው “ፍትህ ይሰጠን” በማለት በተለያዩ መንገዶች ድምጻቸውን ያሰማሉ፡፡ ጥያቄዎቻቸው ምንም ያህል የተለያዩ ቢሆኑም፣ ማጠንጠኛቸው በዋናነት “ፍትህ አጣን” የሚል ነው፡፡
ይህ የፍትህ ጥያቄ እጦት ጉዳይ መሬት የረገጠና በተጨባጭ የሚታይ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለያየ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ነው፤ ስለሆነም የፍትህ ጥያቄዎች እዚህም አዚያም ጎላ ብለው ቢደመጡ የሚገርም አይደለም። ለጥያቄዎቹም ምላሽ መስጠት በዋናነት ከመንግሥት የሚጠበቅ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
በዚህ አግባብ ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የሕዝብ ብሶትን መነሻ አድርገው የተቀጣጠሉ ተቃውሞዎች በመንግሥት አመራር ላይ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ለውጥ እንዲፈጠር መንስኤ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ በዚህ ለውጥ ባለፉት ሰባት ወራት “ይሆናሉ” ተብለው ያልተጠበቁ መሻሻሎች በፍጥነት እያየን ነው፡፡ ይህ በራሱ መልካም ጅምር ሆኖ ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ፍላጎት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ መልካም ጅማሮና ከተገኙ ውጤቶች ጎን ለጎን፣ በርካታ ያልተፈቱና ሕዝቡ አሁንም እንዲፈቱለት የሚጠይቃቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ኅብረተሰቡም በተለያዩ መንገዶች ጥያቄውን ማቅረቡን አላቋረጠም፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች ለማቅረብ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎችም መንገዶች ከሚስተጋቡ መፈክሮች መካከል “ፍትህ ለእከሌ፣” ፍትህ ለእነ እንቶኔ፣” “ፍትህ ለዚህ ሕዝብ….” የሚለው ዋነኛው ነው፡፡ ጥያቄዎቹ በዚህ መልክ መነሳታቸው ምንም ክፋት ባይኖረውም፣እንደኔ እምነት፣ ሁሉንም የሚጠቀልል አንድ መፈክር ያስፈልገናል - “ፍትህ ለኢትዮጵያ!”
ለምን “ፍትህ ለኢትዮጵያ!”?
ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት (በተለይም ከ1966 አብዮት ማግሥት አንስቶ) ከፍ ያለ የፍትህ እጦት ከዳር እስከ ዳር ያስተናገደች አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውና አሁንም ሙሉ በሙሉ ያልጠፋው የፍትህ እጦት ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ የኑሮ ደረጃ፣… ሳይለይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የጭካኔ በትሩን ያሳረፈና እያሳረፈ ያለ ክፉ ጠላታችን ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ይመስለኛል፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን “እገሌ ከእገሌ” ሳይባል፣ ደረጃው ቢለያይም እንኳ ስለ ፍትህና ርትዕ መጓደልና አለመኖር የምናማርረው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ በሚገባ የተበየነበት አንድም ክልል የለም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ርትዕ ለሁሉም በእኩል መጠን የሆነለት አንድም ማኅበረሰብ የለም፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እንዲሁም በማኅበራዊው ዘርፍ፣ “የምፈልገውንና የሚገባኝን ሁሉ በሥርዓት አግኝቻለሁ” የሚል የማኅበረሰብ ክፍል ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁሉም “ጎደለብኝ፣ ቀረኝ፣ አነሰኝ” የሚል ቅሬታ አለው፡፡ ይህንን ስናይ፣ ፍትህ የተጓደለው፤ለአንድ ወይም ለተወሰኑ አካባቢዎችና ማኅበረሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ ለመላዋ ኢትዮጵያ ነው፤ ብለን እንድናምን ያስገድደናል፡፡
የአገር ፍትህ ማጣት የሁላችንም ፍትህ ማጣት ነው፣ የአገር ርዕት-አልባ መሆን የሁላችንም ርዕት-አልባነት ነው፡፡ በአንደኛው ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ ወይም ጎጥ የሚታይ የፍትህ እጦት፣ ይዘገይ እንደሆን እንጂ በሁላችንም ቤት መግባቱ አይቀርም፡፡ ይህን ማስቀረት የሚቻለው አገር በሁሉም መስክ ፍትህ በሚገባ ሲበየንባት ብቻ ነው፡፡
ስላጣነው ፍትህና ርትዕ በያለንበት መጮኻችን አግባብ ነው፣ ነገር ግን የፍትህ እጦቱ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት እንደታዘብነው፣ ተቋማዊና አገር-አቀፋዊ መልክና ቅርጽ ያለው፣ አልፎ ተርፎም የፖለቲካ የበላይነት ማረጋገጫ እስከመሆን የደረሰ፣ በአንዳንድ መልኩም የመጨቆኛ መሣሪያ ለመሆን እንደበቃ ተበዳዩ ሕዝብ ሲናገር ይሰማል፡፡ ይህንን አገር-አቀፍ ችግር ለመዋጋት አገራዊ ፍትህ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የየራሳችንን የፍትህ ጥያቄ ብቻ አስመልሰን “ሁሉም ጥሩ ነው” ብለን አርፈን ለመተኛት አንችልም፡፡ የሌላው ችግር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እኛው ጋ  መምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ አገራዊ ፍትህ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፡፡
ስለዚህ፤ የየቡድናችን፣ የየማኅበራችን፣ የየብሔረሰባችን፣ የየብሔራችን፣ የየክልላችን፣… ፍትህ በማያዳግም መልኩ እንዲረጋገጥ፣ እስቲ “ፍትህ ለኢትዮጵያ!” እንበል፡፡ አዎ፤ “ፍትህ ለኢትዮጵያ”!!

Read 599 times