Print this page
Sunday, 18 November 2018 00:00

የኢትዮጵያ ትንሳዔና የሽግግር ጉዞ - መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች

Written by  አሰፋ
Rate this item
(0 votes)


    ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በአገራችን እየታዩ ያሉት ሁነቶች በእርግጥም የኢትዮጵያ ትንሣኤ እውን እየሆነ ነው የሚል ተስፋና ጉጉት በብዙዎች ላይ እንዲጭር ምክንያት ሆኖአል፡፡ በመሠረቱ የአሁኑ ዓይነት የፖለቲካ መነቃቃት (political awakening) ሲስተዋል ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ባለፉት 50 እና 60 አመታት አገራችን ሥር ነቀልና ዘላቂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሏት አራት ወይም ከዚያ በላይ ተመሳሳይ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ሳትጠቀምባቸው ወይም የሚፈለገውን ሽግግር ሳያመጡ አልፈዋል፡፡ ይህ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ሁላችንንም ሊያስቆጭ የሚገባ ነገር ነው፡፡ አሁን ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ሌላ ተስፋ፣ ሌላ ራዕይ እንድንሰንቅ  ምክንያት ሆነዋል፡፡ ታዲያ ያሁኑ የለውጥ ነፋስ እንዲሣካ ማበረታታት፣ መሳተፍና ማገዝ አንድ ነገር ሆኖ፤ ለውጡ ይበልጥ እንዲሳለጥ የሚያግዙ ምቹ ሁኔታዎችና ዕድሎችን ከመጠቆም ባለፈ በለውጡ አካሄድ ላይ ገንቢ ትችት ማቅረብና ሕፀፆችን መጠቆም መበረታታት ያለበት እንጂ ከቶውንም የሚነቀፍ ሊሆን አይችልም፡፡
ከዚህ አንፃር አሁን በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ እየተቀነቀነ ያለውን የለውጥ (በእርሳቸው ቋንቋ የመደመር) እንቅስቃሴና ፖለቲካዊ ቅኝት ከተለያዩ መነሻዎች፤ ለምሳሌ ከሠላም እሴቶች ግንባታ፤ ከውጪ ግንኙነት፣ ከተቋም ግንባታ፣ ወዘተ አንፃር መተንተንና ማሰብ ይቻላል፣ ይገባልም፡፡ በዚህ አጭር መጣጥፍ ለማድረግ የምሞከረውም ይህንኑ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የመደመር›› እሳቤ አገራዊ ሽግግሩ ወይም ለውጡ የሚቃኝበት ፍልስፍና ተደርጎ ከተወሰደ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ  አንድምታ የትየለሌ ነዉ፡፡ በዚች ፅሁፍ አንዳንዶቹን  እያነሳን ሃሳብ እንድንለዋወጥ  እኔ በዚህ ጀምሬያለሁ፡፡
1. ብሔራዊ እርቅና የሠላም እሴት ግንባታ
የሠላም መኖር ለተስፋዎቻችን እውን መሆን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ቅድመ ሁኔታዎች አንደኛውና ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። ሠላም ሲባል ብዙዎች እንደሚያስቡት የጦርነት አለመኖር፣ የጥይት አለመጮህ ወይም የሰዎች አለመሞት ብቻ አይደለም፡፡ የመስኩ ተመራማሪዎች ይህን አሉታዊ ሠላም (negative peace) ይሉታል። ሠላም በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለ በጣም ጥልቅ ስሜት ነው። እናም ሰላምን መፍጠር ከራስ ይጀምራል። ማንኛውም ከራሱ የተጣላ ግለሰብ ለሌላው ሰላም ሊሰጥ አይችልም። ሰዎች፣ ቡድኖች ወይም ማህበረሰቦች ሠላም የሚያጡት መቼ ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ዜጎች በተናጠል፣ ቡድኖችና ማህበረሰቦች ወይም እነርሱ የፈጠሯቸው ድርጅቶች የራሳቸውን ሕይወት በሚመለከቱ በአካባቢያዊና በአገራቸው ጉዳይ የመደመጥና የመሳተፍ ዕድል ሲነፈጉ፣ ወይም ከአካባቢያዊና አገራዊ ሐብት በፍትሃዊነት መቋደስ ካልቻሉ፣ ወይም በማንነታቸው ተገለናል፣ ተገፍተናል ብለው ማሰብ ከጀመሩ፣ያን ጊዜ ውስጣዊ ስሜታቸው መደፍረስ ይጀምራል፣ ልባቸውም ይሸፍታል፡፡ ያን ጊዜ አመፅና ግጭት እንቁላላቸውን ይጥላሉ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ስለ ሠላም ግንባታ ስንነጋገር ላይ ላዩን ሳይሆን በጥልቅ ትንተናና ሥልት ላይ የቆመ መሆን አለበት፡፡ ቅን አስተሳሰብ (positive thinking)  በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም ሠላም ስለተመኘን ወይም በስብከት ብቻ ሊመጣ አይችልም፡፡ እንደ ጠ/ሚኒስትሩ ደፋ ቀና ማለት ቢሆን ኖሮ፣ በአሁኑ ሰዓት እንደ እንጉዳይ እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ የሚሉ ግጭቶችና መፈናቅሎች ባላጋጠሙን ነበር። ይህ ሁኔታ የግጭት መከላከል፣ አያያዝና አፈታት ስልታችንን እንድንፈትሽ  ግድ ይለናል፡፡ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በአገራችን እየታዩ ያሉት ግጭቶች፤ ሐገሪቱ ከምትከተለው  ፌደራላዊ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለውን ለጊዜው እናቆየውና መገፋፋት፣ ግጭት፣ መፈናቀል መገዳደል የሕይወታችን አካል ሆኖአል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በጣም እሩቅ ይመስሉን የነበሩት የሩዋንዳና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጭፍጨፋና የእርስ በእርስ ጦርነቶችን የሚመስል ነገር፣ በሐገራችን ላለመደገሙ ዋስትና የለም፡፡ ደግነቱ ከፍተኛ መሸርሸር ቢደርስበትም ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችን፣ ሆደ-ሰፊነታችንና ቁጥብነታችን ጨርሶ ጥሎን ባለመሄዱ፣ የጅምላ ጭፍጨፋ (genocide) አላስተዋልንም፡፡ ምልክቶቹን ግን እያየነን ነዉ፡፡ በቅርቡ በሶማሌ ክልል ተከስቶ ከነበረው ሁኔታ አንፃር፣ የዘር ማጥፋት ባንለው እንኳን የዘር ማጥራት (ethnic cleansing) ሊባል የሚችል ነገር ሲደጋገም እያስተዋልን ነው፡፡ ይህን አደገኛ አዝማሚያ በቁርጠኝነት ካልታገልነውና ካላስቆምነው፣ በሕዝባችን ዉስጥ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ማለፉ አይቀርም፡፡  
ነባሮቹ የግጭት አፈታት ሥልቶቻችን ቀስ በቀስ እየደበዘዙ፤ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ ያላቸው ቅቡልነት እየኮሰመነ ይገኛል፡፡ ዘመናዊ መሰሉ የግጭት አፈታት ሥልታችን ደግሞ በአብዛኛው ከመከላከል ይልቅ ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላ ማስወገድ ላይ ያተኮረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ይበልጡን የኃይል እርምጃን (lethal means) ያስቀደመና ሕግን መደበቂያ ያደረገ (Legalistic approach) አካሄድ ሆኖ መዝለቁ የሚታወቅ ነው፡፡
አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ሊሰፍን የሚችለው በግጭቶች የመከሰቻ መልኮች ላይ ከመረባረብ ባሻገር የግጭት መነሻ የሆኑትን ነገሮች ከምንጫቸው ለማድረቅ በቁርጠኝነት መስራት ስንችል ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ድረስ ከስህተቶቻችን የተማርን አይመስልም፡፡ የፖለቲካ ታሪካችንም በሸር፣ በመሰሪነትና አመጽ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የምንሻ ከሆነ እንደ ሀገር ይቅርታንና እርቅን መለማመድ ይኖርብናል፡፡ ወደፊት መራመድ የምንችለው ያለፉ ቁርሾዎችን በማነብነብና አለመተማመንን በማንገስ ሳይሆን ብሔራዊ እርቅ አውጀን በአዲስ የፖለቲካ ባሕል መንቀሳቀስ ስንችል ነው፡፡ አንዳችን ባንዳችን ላይ ቂም ቋጥረን፣ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እየተመለከተ ትንሹንም ትልቁንም ቅራኔ ከሚገባው በላይ እያጦዝን የሐገራችንን ትንሣኤ እውን ማድረግ አይቻልም፡፡ ወንድም ወንድሙን እየገደለ ሐውልት የሚያቆምበት ሁኔታም መቆም አለበት፡፡ ታዲያ ብሔራዊ እርቅ ሲባል በደምሳሳው አድበስብሶ ማለፍ ሳይሆን፤ ማን ከማን እንደሚታረቅ፣ በየትኛቹ ጉዳዮች መታረቅ እንዳለብን እንዲሁም ሂደቱ ምን እንደሚመስል በውል ተለይተውና ተብራርተው ሊሆን ይገባዋል፡፡ ካልሆነ የይስሙላ ዕርቅ ስለሚሆን ‹‹አለባብሰዉ ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› አይነት ይሆናል፡፡ ይቅርታና ምሕረት ተግባቦትን በመፍጠር ሠላምና መረጋጋት ሊያመጡ ይችላል። የሆነ-ሆኖ ብዙዎች ደጋግመው እንደተናገሩት፤ በሕግ ሥም መብት ረገጣን ማንገስ እንደማይገባ ሁሉ፤ ይቅርታና ምህረትም የህግ የበላይነትን የሚያኮስሱና ወንጀልን የሚያደፋፍሩ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሁን በሐገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተስተዋለ ያለው የዚህ አይነት አዝማሚያ ነው፡፡ የሁለቱን ሚዛን ጠብቆ መራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ነፃነትና ዲሞክራሲን ከሃላፊነትና ግዴታ ጋር ማጣጣም አቅቶን በስሜት እየተነዳን ወደ ሥርዓተ አልበኝነትና ወንጀል ማስፋፋት ከሄድን፤ የምናስበው ጤናማ ሽግግር ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም ወደ ሌላ ያልተፈለገ ትርምስ ሊወስደን ይችላል፡፡
ከዚህ አንፃር በቀዳሚነት መንግስት ሐላፊነት ወስዶ አስፈላጊውን መደላድል መፍጠር ይኖርበታል። የትኛውም ተበደልኩ ባይ ቡድን ወይም ወገን ሃሳቡን በነፃነት የሚያንሸራሽርባቸው፣ በዳይ ወይም አጥፊ የተባለው ወገንም በይፋ ስህተቱን ተቀብሎ ይቅርታ የሚጠይቅባቸው ሁኔታዎችና መድረኮች ሊመቻቹ ያስፈልጋል። በአንዳንድ ምናልባትም በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ሁሉም ወገን የጋራ ተጠያቂነትን መቀበል ሊኖርበት ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የብሔራዊ እርቅ ዋና ዓላማ እውነትን ማፈላለግ፣ የብቀላ ባሕልን ወደ ጎን በማድረግ እውነተኛ ይቅርታና እርቅን ማምጣት ነው፡፡ ብሔራዊ እርቅ መነሻውም መድረሻውም አስተማሪ ፍትህ (restorative justice) የሚባለውን አስተሳሰብ በተግባር ማስረፅ ነው። ተበቃይ ፍትህ (retributive Justice) ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደከተተን እያየን ስለሆነ ሌላ የተሻለ አካሄድ መዘየድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ሐገር በቀል ልምዶችንና ዓለም አቀፍ ተመክሮዎችን ያካተተ ሁሉ አቀፍ የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ሥርዓት ነገ ሳይሆን ዛሬ ያስፈልጋታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብ የመደማመጥ፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህልን ማበልፀግ ይኖርብናል፡፡ የኃይማኖት ተቋሞቻችንና መሪዎቻቸው ከምሽጋቸው ወጥተው ከእነርሱ የሚጠበቀውን ለመፈፀም መትጋት አለባቸው፡፡
2. ብሔራዊ መግባባትና ሐገራዊ  
አንድነትን  መፍጠር
ብሔራዊ መግባባት (national consensus) እና ብሔራዊ እንድነት (national unity) ያንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ አንዱን ያለ ሌላው ማሰብ አይቻልም፡፡ ሌሎች ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ፤ የተሣካ ሐገራዊ ግንባታ (nation building) የሁለቱን በአንድ ላይ መገኘት የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሐገር የረጅም ጊዜ የመንግስትነት ታሪክ ቢኖራትም፣ የሐገር ግንባታ ፕሮጀክቱ በሚፈለገው ደረጃ ተጠናቆአል ማለት አያስደፍርም፡፡ እንደውም በየጊዜው ሙከራ ቢኖርም የሐገር ግንባታ ሂደቱ ተጨናግፎአል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት አሳታፊና አቃፊ እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ በመሰረቱ ያንድ መንግስት ቅቡልነት (legitimacy) ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ደግሞ  ይህ ነዉ፣ ሁሉም ሰው ቤተኛነት እንዲሰማው የሚያደርግ የፖለቲካ ስርዓት ማስፈን። ታዲያ በዚህ ጨንግፎአል በተባለ የሃገር ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የቆመ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት ዛሬ አደጋ ቢያንዣብብበት የሚያስደንቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ብሔራዊ አንድነት መናገርና መፃፍ የሚያሸማቅቅበትን ዘመን  ለመሻገር ገና እየተንደፋደፍን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከትቢያ ሊያነሱት እየሞከሩት ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት ከጉሮሯቸው አልወርድ ብሎ የሚተናነቃቸው  እንዳሉም እያስተዋልን ነው፡፡
ሐገራዊ (ብሔራዊነት) አንድነት መሰረቱ ብሔራዊ (ሐገራዊ) መግባባት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ቁልፍ በሚባሉ ሐገራዊ ጉዳዮች ሳይቀር መግባባት ላይ አልደረስንም። ይህ ከታሪካችን ጀምሮ፣ ሕገ መንግስቱን፣ ሰንደቅ አላማውን፣ የመንግስት አወቃቀርን (form of governance) ሁሉ ያካተተ ነው። ለምሳሌ ከአንድ የስብሰባ አዳራሽ (ሌላ ህዝብ በብዛት የተገኘበት ቦታም ሊሆን ይችላል) ተገኝታችሁ ታዳሚዎቹን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ምን እንደሚሰማቸዉ ብትጠይቁ፣ አራት ዓይነት መልሶች ልታገኙ ትችላላችሁ። ሀ) ከሞላ ጎደል ያለፍንበትን ታሪክ ከእነ ጉድለቱ የተቀበሉና በዚህም የሚኮሩ፣ ለ) ኢትዮጵያዊ ማንነትና ታሪኳን ከእነ አካቴው ለመቀበል የሚያንገራግሩ፣ ሐ) የተምታታባቸውና እውነቱን በመፈለግ ላይ ያሉ፣ መ) ደንታ የሌላቸውና ስደት ናፋቂዎች፡፡ እና ይኼ አያሳስብም ትላላችሁ? እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችን ስኬቶች ሰለባ የሆንን ሕዝብ ነዉ። እንዴት ቢባል? ጥንታዊ ስልጣኔያችንንና ነፃነታችንን አስከብረን በመኖራችን፣ ለዘላለም በእነዚህ ስንኩራራ፣ የጀመርነውን ማስቀጠል ሳንችል ቀርተን ጊዜ ጥሎን ሄዷአል፡፡ አሁን የምንከፍለው ዳፋ ሁሉ የዚህ ውጤት ነው፡፡ የጀመርነውን ለምን ማስቀጠል ተሳነን? ይህ ብዙ ሊፃፍበት የሚችል ራሱን የቻለ ርዕስ ነው፡፡  
የሆነው ሆኖ እንደ ሐገር መቀጠል ካለብን ከሁሉ በፊት ከታሪካችንና ከማንታችን ጋር መታረቅና ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የኩራታችን ምንጭ መሆኑን መቀበል ግድ ይሆናል፡፡ ነባሩን ሁሉ በማጣጣልና በማፍረስ ሳይሆን፤ ያለፈውን  ከእነ ግድፈቱና ውስንነቱ ተቀብሎ፣ ከዚያም ትምህርት እየወሰዱና ባለው ላይ እየገነቡ መሄድ የታላቅ ሕዝብነት መገለጫ ነው፡፡ ልማትና ሥልጣኔ የቅብብሎሽ ሥራዎች ናቸው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ቁም ነገር ያለው ያለፈውን በታሪክነቱና አስተማሪነቱ መዝግበን፣ የጋራ እሴቶቻችንን እያዳበርን ወደፊት መራመድ መቻላችን ላይ ነው፡፡ ሌላ የተሻለ ምርጫ ያለን አይመስልም፤ ሁላችንም የተሳፈርነው በአንድ መርከብ ላይ ነው፡፡ አሁን ‹‹ፈረሱም ይሄው ሜዳውም ይሄው›› እየተባልን ይመስላል፡፡ ፈረሱን እየገራን፣ ሜዳውንም ለግልቢያ ይበልጥ ምቹ እንዲሆን እየሰራን በጋራ መሸምጠጥ የኛ የሁላችን ተግባር እንጂ፤ ለአንድ ሰዉ፣ ለድርጅት፣ ወይም ለመንግስት ብቻ ከቶውንም ልንተወው  አንችልም፡፡
ስለዚህ ‹‹ብዝሃነት ጌጥ ነው፤ አንድነት ሃይል ነው›› የሚለውን ብሂል ከልባችን ተቀብለን በጋራ እየቀዘፍን፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ ተግቶ መስራት ሁላችንንም ሊያግባባን ይችላል ይሆናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ሊያደርጉ እየሞከሩ  ያለው  ይህንኑ ስለሆነ ልናግዛቸው ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙ ነገሮች እጥረት አለ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በግልፅ የመነጋገር፣ የመደማመጥና የመቻቻል ባሕል እጥረት መሆኑን ልብ ብለናል? ሕዝብና ሕዝብ፣ ሕዝብና መንግስት፣ የፖለቲካ ማህበራት፣ ወ.ዘ.ተ ይህንን ባህል ማዳበር ግድ ይላቸዋል። መንግስት ከምንጊዜውም በበለጠ በሆደ-ሰፊነት ልዩነቶችን ማቻቻል፣ ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያግዙ እርምጃዎችን መውሰድ (ሕገ መንግስቱን እስከ ማሻሻል ሊዘልቅ ይችላል)፣ ይህን ተልዕኮ ለማሳካት የጐላ አስተዋፅኦ ያላቸውን የሌሎች ባለድርሻዎችን ተሳትፎ ማበረታታትና ማገዝ፣ ለዚህም የተሳትፎና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ማስፋት ይኖርበታል፡፡ የብሔራዊ አንድነት አልፋና ኦሜጋው ‹‹ዜግነት›› የሚባለው እጅግ ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ ነው። ምንጊዜም የቡድን መብቶች፣ የቡድን ጥቅሞች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የቡድን መብቶች ከሚገባው በላይ ተለጥጠው የዜጋውን ቦታ እንዳያጣብቡ (አሁን ባለው ሁኔታ ጠቅልለው ወስደውታል ማለት ይቻላል) ሚዛኑን አስጠብቆ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡
3. የተቋም ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና የተጠያቂነት አሰራር  ማስፈን
በህግ የተሰጣቸውን ተግባርና ሃላፊነት በብቃት የሚወጡ፣ መንግስትን የሚያነቁና ሲያስፈልግም ሃይ የሚሉና የሕዝብን አመኔታ ያተረፉ ተቋማት መኖር ሌላው የሐገር ግንባታ  መገለጫ መሆኑን ቀደም ብለን አውስተናል፡፡ እነዚህ ተቋማት በዘፈቀደ የሚገኙ (በአዋጅ ብቻ የሚፈጠሩ) ሳይሆን አስቦና አቅዶ መስራትን ይጠይቃል፡፡ የተሳካ የተቋም ግንባታ (state building) የሚባለውም ይህ ነው። በነገራችን ላይ ያገር ግንባታ (nation building) ከተቋም ግንባታ (state building) የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ መልካም አስተዳደር፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብትን ማስከበር፣ ተዓማኒ ምርጫ ማካሂድ ወ.ዘ.ተ ያለ ጠንካራ ተቋማት ከቶውንም አይታሰቡም። ጠንካራ ተቋማት፣ በተለይም የዲሞክራሲ ተቋማት (የሕዝብ እንደራሴ ም/ቤቶች፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ምርጫ ቦርድ) የሚባሉት አሁን የተጀመሩ የተሃድሶና የለውጥ እንቅስቃሴዎች ጥልቀትና ስፋት እንዲያገኙና ዘላቂ እንዲሆኑ የማድረግ ተተኪ የሌለው ሚና አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪዎች እንጂ ጠንካራ ተቋማት ኖረዋት አያውቁም፡፡ ይህ ጥቅል አስተያየት ቢመስልም በዚህ ረገድ ገና ብዙ ርቀት መሄድ እንዳለብን ግን ብዙም የሚያጠያይቅ አይሆንም። አንዳንድ ፀሃፊዎች እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ከተቋም ይልቅ የጠንካራ መሪ (strongmen) ተፅእኖ የተጫጫነው ነው፡፡ ይህ በራሱ መጥፎ ነገር ባይሆንም በሂደት ተቋሞቻችን ቦታውን መያዝ ካልቻሉ እንደገና በአምባገነኖች መዳፍ የመውደቁ ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የተጀመረው የተኃድሶና የለውጥ እንቅስቃሴ እንደገና ላለመጨንገፉ ዋስትና የለም፡፡ ታዲያ ተቋሞቻችን ይህንን የላቀ ተግባር እንዲፈፅሙ ስንጠብቅ፣ አሁን ያለውን አሰራራቸውንና ድርጅታዊ ቁመናቸውን እየፈተሹ ማጠናከር፣ ማብቃትና ተቋማዊ ነፃነታቸውን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ ተግባራት ናቸው፡፡
ከተቋማት ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነገር የሕግ የበላይነትንና የተጠያቂነት አሰራርን የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ በንገራችን ላይ የሕግ የበላይነት (rule of law) እና በሕግ መግዛት (rule by law) ሁለት የተለያዩ ፅንስ ሃሳቦች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሕግ የበላይነት ሁሉም ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት በሕግ ፊት እኩልና ከህግ በታች መሆናቸውን የሚያሳይ ሲሆን፤ በሕግ መግዛት ግን መንግስታት ወይም ገዢዎች የጭቆና ቀንበራቸውን በሕዝብ ላይ ጭነው የሚገዙበት መሳሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ብሔራዊ መግባባትና ሐገራዊ አንድነት ሁሉ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትም ተነጣጥለው የማይታዩ፤ ይልቁንም ተደጋጋፊ መርሆች ናቸው፡፡
ያለ ሕግ የበላይነት ተጠያቂነትን ማሰብ አይቻልም፤ የሕግ የበላይነት ባለበት ሁኔታ ወይም ሐገር ግለሰቦች፤ ቡድኖች፣ መሪዎች እንዲሁም መንግስታት ለሚወስዱት ማንኛውም እርምጃ ወይም ጥፋት ሀላፊነትን ወይም ተጠያቂነትን ይወስዳሉ። የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት በሠፈነበት ሁኔታ አጥፊዎች፣ ሙሰኞች፣ ወንጀለኞች ከድርጊታቸው ይታቀባሉ፤ የዜጎች ደህንነትም የተረጋገጠ ይሆናል። የሕግ የበላይነትና የተጠያቂነት መርሆች በማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ብቻ የሚመዘኑ አይደሉም። ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም ቢያመዝን እንጂ አይተናነስም፡፡ የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት አሰራር መስረፅ፤ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ የኮንትራት አፈፃፀምን በማቀላጠፍ፣ የዜጎችን ንብረት የማፍራት መብት በማረጋገጥ የኢኮኖሚ እድገትን ያፋጥናል፡፡
በእኛ ሐገር ነባራዊ ሁኔታ ጅምሮች ቢኖሩም፣ መሰረታዊ መዋቅሮች ቢዘረጉም፣ የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት አሰራርን በማስረፅ ረገድ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ለሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት መስፈን አንዱ ደንቃራ የፓርቲና የመንግስት አሰራርና ሚና መደበላለቅ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ በሕግ በወረቀት ላይ ተለያይተው የተገለፁ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በተለይም ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ተደበላልቀው  ይታያሉ። በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሕጋዊ አሰራሮች ከመጠምዘዛቸውም ባለፈ የመንግስት ሰራተኞችና ሃላፊዎች ተጠያቂነት አለብን ብለው የሚያስቡት መንግስትን ስልጣን ላይ ላወጣው፣ ደሞዝ ለሚከፍላቸው ሕዝብ ሳይሆን፤ ለፓርቲው  መዋቅር ወይም  የእዝ ሰንሰለት ሆኖ ይታያል፡፡
ሌላኛው ተግዳሮት ሶስቱ የመንግስት ቅርንጫፎች የሚባሉት (ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው) አንዱ ሌላኛውን የመቆጣጠርና ሚዛኑን የማስጠበቅ አሰራር፣ ባህል፣ አቅም አለመዳበር ነው፡፡ በእኛ ሐገር የአስፈፃሚው  አካል (መስተዳደር የምንለው) ስልጣኑ እጅግ ተለጥጦ፣ በሌሎቹ ሁለቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ በጉልህ ይስተዋላል፡፡ ወይስ ራሳቸው ተቋማቱ በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ሃላፊነት ለመፈፀም በሚያበቃ ቁመና ላይ አለመገኘታቸው ነው? የሚለው ጉዳይ ትንሽ ሊያከራክር ይችል ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል የተጠቀሱት የዲሞክራሲ ተቋማትም ቢሆኑ በገዢው ፓርቲና በአስፈፃሚው አካል ተፅእኖ ሥር መውደቃቸውን የሚያመላክቱ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች፤ እነዚህ ተቋማት የሚንቀሳቀሱት አስፈፃሚው  አካል ሰፍቶ በሰጣቸው  ልክ ነው  ሲሉ ይሟገታሉ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ትርጉም ያለው የሶስቱ የመንግስት አካላት የእርስ በርስ ቁጥጥርና የተጠያቂነት አሠራር በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመገኘቱ የሚያከራክር አይደለም፡፡ የዚህ አይነት አዝማሚያ በተለይ የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው ሐገራት የሚያጋጥም ቢሆንም፣ የእኛ ሁኔታ የበለጠ አሳሳቢ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግስታቸው እንዲሁም የገዢው ፓርቲ መሰረታዊ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ሌላ ሳይሆን በተለይ ሁለቱ የመንግስት ቅርንጫፎች (ሕግ አውጭውና ሕግ ተርጓሚው፣ በሌላ አነጋገር ፓርላማውና ፍ/ቤቱ) በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ሐላፊነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በብቃት እንዲወጡ ማብቃት፤ የሙያ ነፃነታቸውን ማክበርና ማስከበር፣ በአጠቃላይ ሲቪል ሰርቪሱ ከፖለቲካ ተሿሚዎች በስተቀር በቴክኖክራቶችና ሙያተኞች ብቻ እንዲመሩ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አስፈላጊ እርምጃ ነው። የፖለቲካና የጎሣ ወገንተኝነት ከእንግዲህ ቦታውን ለተረኛ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ ለማጠቃለል ያህል፤ ሽግግሩን ለማሳለጥ መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል ተቀዳሚዎቹ የሰላምና የዕርቅ ጥረቶችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና ለውጡ ራሱ ቀጣይነት እንዲኖረው፣ ተቋማዊ መሠረት ማስያዝ፤ እንዳስፈላጊንቱም የህግ ከለላ ማበጀት ያስፈልጋል።

Read 1405 times