Sunday, 18 November 2018 00:00

የመንግስት ቢዝነስ፣... ከቢሊዮኖች ብር ኪሳራና ከብክነት አዙሪት አያመልጥም!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

• የሜቴክ ታላቅ ውድቀትና ቅሌት፣ ከእድሜው በላይ እጅጉን የገዘፈ ነው። በ8 ዓመታት ውስጥ ብዙ ቢሊዮን ብር ባከነ። ግን...
 • ለዓመታት ያልተጓተተ፣ እጥፍና ድርብ ወጪ ያልፈጀ፣ ቢሊዮኖችን ያላባከነ የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክት የታለ? የለም፡፡
 • የመንግስትን ቢዝነስ፣ “እርም” እንበል። ይቅርታ ጠይቀን፣ ከግል ቢዝነስና ከግል ኢንቨስትመንት ጋር እርቅ እንፍጠር፡፡
       
    ከሜቴክ በፊትም ሆነ ጎን ለጎን፣... ከተንዳሆ እስከ ርብ ግድብ፣... ከኤሌክትሪክ ባቡር እስከ ነፋስ ተርባይን፣... በየአቅጣጫው፣ የቢሊዮን ብሮች ብክነት ሞልቶ ተርፎ! በፌደራልም ሆነ በክልል የውሃ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ ከሜቴክ ጋርም በተናጠልም በርካታ ፕሮጀክቶችን ለበርካታ ዓመታት እያጓተቱ ብዙ ቢሊዮን ብር አባክነዋል።
የግል ኩባንያና የግል ቢዝነስ ላይ፣ ከዓመት ዓመት የማይቋረጥ፣ እንደሜቴክ አይነት ብክነትና ኪሳራ አይፈጠርም። የግል ኩባንያ፣ ተግቶ ስኬታማና ትርፋማ ለመሆን ይጣጣራል። ካልጣረም፣ የራሱን ሃብት አባክኖና ከስሮ ይቀመጣል እንጂ፣ የዜጎችን የታክስ ገንዘብ ከዓመት ዓመት መቀበልም ሆነ እያባከነ መቀጠል አይችልም። የመንግስት ቢዝነስ ግን ይችላል - በየዓመቱ በጀት እየተመደበለት፣ አገር እስኪራቆት ድረስ ክፍያ እየተጨመረለት፣ እስከ ወዲያኛው ጊዜ እየተራዘመለት፣ ከራሱ ኪስ ያልወጣውን ሃብት በከንቱ እየበተነ፣ የዜጎችን የታክስ ገንዘብ እያባከነ ያለ ሃሳብ እድሜ ያስቆጥራል። ምርጫው ግልፅ አይደለም?
ከመንግስት ቢዝነስ ጋር ተጣብቀን የሃብት ብክነትን እንደ እጣፈንታ ተሸክመን የድሃ አገር መከራን መግፋት፣... አልያ ደግሞ የመንግስት ቢዝነስን እርም ብለን በግል ቢዝነስ መተካት ነው ምርጫው። በእርግጥ፣ ከዚህም ከዚያም እያጣቀሱና እየቀየጡ መሞከርም ይቻላል፡፡ አዎ፣ የመንግስት ፕሮጀክቶችን፣ በመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት ከማስገንባት ይልቅ፣ ለግል ኩባንያዎች በኮንትራት መስጠት፣... ለተወሰነ ጊዜ ገሚሱን ብክነት ለመቀነስ እንደሚረዳ፣ በእውን የታየ እውነት ነው። ነገር ግን...
ከቢሊዮን ብሮች ከንቱ ብክነት ለመዳን ከፈለግን ግን፣... መንግስትንና ቢዝነስን ከማለያየት ውጭ ሌላ አስተማማኝ መፍትሄ የለም። ለዚህም ነው፤ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ እንዳሉት፣ የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደርሰውን የብክነትና የኪሳራ ጥፋት ለማስወገድ፣ ለግል ኩባንያ የመሸጥ እቅድ ፍቱን መድሃኒት የሚሆነው። እቅዳቸው ቶሎ ቢሳካ ነው ለአገሪቱ የሚበጃት፣ የሚበጀን። ሁነኛው መፍትሄ፣ ይሄው ነውና።
የእስከዛሬውን ጥፋት በፕራይቬታይዜሽን ማከምና፣ ለዘለቄታውም.. ነፃ የገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት ነው የሚያዋጣን። ምክንያቱም፣... ካሁን በፊትም፣... በስኳር ኮርፖሬሽንና በሜቴክ ፕሮጀክቶች ላይም፣ በግድቦችና በውሃ ሚኒስቴር ፕሮጀክቶች ላይም፣... በኤልፓና በኤሌክትሪክ ባቡር ፕሮጀክቶችም ላይ፣ የዛሬ 10 ዓመትም፣ የዛሬ 8 እና 5 ዓመትም፣... በተደጋጋሚ ለማለት እንደሞከርኩት፣ መንግስት የነካው ቢዝነስ አይሳካም።
በቃ! የመንግስት ቢዝነስ፣... ከቢሊዮኖች ብር ኪሳራና ከብክነት አዙሪት አያመልጥም!
ዋናው ቁምነገር ይሄው ነው። መንግስት የገባበት ቢዝነስ፣ “አንድ ደረጃ፣ 99 ናዳ” እንደሆነ... ከደርግ ዘመን ታሪክ ያልተማረ አገር ሆነና፣ ባለፉት የኢህአዴግ ዓመታትም፣ ተደገመ።
አሁንስ? ዛሬም፣ ወደፊትም ከስህተታችን ካልታረምን፣ ከጥፋታችን ካልተመለስን፣ ከተመሳሳይ መዘዝ አንድንም፡፡ የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ለማዛወር አለመትጋት፣ አለመደገፍና አለመጎትጎት፣... ተመሳሳይ የቢሊዮን ብሮች ኪሳራና ብክነትን እንደመደገስ ነው። ደግሰን ስናበቃ፣ የኋላ ኋላ ዘጠና ዘጠኙ የመዘዝ ናዳ ሲመጣ፣ እሪ ብንል ምን ዋጋ አለው? ጥፋትንና ብክነትን ከደገስን በኋላማ፣ አጥፊ ዘራፊና አባካኝ ሞልቷል፡፡ ቢቀርብን ይሻላል፡፡ ቢበቃን ይበጃል፡፡
ቢያንስ ቢያንስ ለወደፊት እንንቃ፣ እንወቅበት፣ እንማርበት። አዎ፣ ይሄ ሁሉ ብክነትና ኪሳራ መድረስ አልነበረበትም። “መቼስ የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ ነገር! ያለፈውንና የተፈፀመውን ነገር፣ ወደ ኋላ ተመልሶ መለወጥ የሚችል የለም” ሲባል ግን፣... አስቀድሞ ማወቅና መከላከል አይቻልም ነበር ማለት አይደለም። ማወቅም መከላከልም ይቻል ነበር። ማወቅ ለፈለገ፣... ፈቃደኛ ለሆነ።
ጥያቄው ምንድነው?... “እውነታውን ከጅምሩ ለማወቅና ለመከላከል፣... ከምር እንፈልጋለን ወይ?” ነው ጥያቄው። ወይስ እንደወትሮው፣... በአንድ በኩል፣... የግል ኢንቨስትመንትን የማናናቅ፣ የማንቋሸሽና የማጥላላት ነባር ባህል እንዳይቀየር የሙጢኝ መያዝ እንፈልጋለን - አዋቂነት ይመስል። በሌላ በኩልስ በሆታና በጭብጨባ በየቦታው የሚቀፈቀፈው የመንግስት ቢዝነስ፣ ውሎ አድሮ መጨረሻው አያምር ነገር በብክነት ኢኮኖሚውን እየሸረሸረ ሲንድ…ድንገተኛ ዱብዳ የወረደብን እያስመሰልን እንማረራለን፡፡
መንግስት፣ እንደፈቀደው ስልጣኑን እየተጠቀመ፣ አጥፊ የቁጥጥርና የክልከላ ህጎችን እየፈለፈለ የግል ኢንቨስትመንትን ሲያሰናክል፣...  በርካታ ዜጎችም በፊናቸው፣ ከመንግስት የባሱ አምባገነን ጉልበተኞች እየሆኑ ... ንብረት በመዝረፍም ሆነ በማቃጠል፣ በአመፅም ሆነ መንገድ በመዝጋት፣ ስም በማጥፋትም ሆነ ጭፍን አድማ በማነሳሳት የግል ኢንቨስትመንትን በእንጭጩ ለመቅጨት ይረባረባሉ።
የግል ቢዝነስን፣ እንዲያ እንደደመኛ ጠልተን፣ መፈናፈኛ እንዲያጣ ጠምደን ከያዝነው፣... ሌላኛውን አቅጣጫ መርጠናል ማለት ነው - የመንግስትን ቢዝነስ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣... የመንግስት ቢዝነስ... የትም አገር ሆነ በየትኛውም ዘመን፣ ባለስልጣን ቢቀያየርም ሆነ ተሽሮ ቢሾም፣... ከኪሳራ፣ ከብክነትና ከሙስና የማምለጥ እድል የለውም። ብዙም ሳይቆይ፣... በመባቻውና በማግስቱ፣... ሚሊዮን ብሮች፣... አንድ ሁለት እንደዘበት እየተንጠባጠቡ ሲባክኑ፣... በሳምንቱና በወሩ፣... ከመቶ ሚሊዮን ሲያልፍ፣ እናም የቢሊዮን ብሮች ብክነት ሲከማች፣...እንደዘበት እየተንጠባጠበ ብክነት ሲከማች፣ ያኔ ከመነሻው  ማወቅ ይቻል ነበር። አዎ ይቻል ነበር። ለነገሩማ፣... የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች የሚፈጥሩት የሃብት ብክነት፣ መቼ ሚስጥር ሆነና? የዘወትር መደበኛ ተግባራቸው በመሆኑ ማወቅ የሚፈልግ ሰው ማወቅ ይችል ነበር። ግን፣ ፍላጎት ነበር ወይ ነው ጥያቄው?
የመንግስት ቢዝነስን እንደ ስኬታማ መንገድ የማምለክ ነባር ልማድ ውስጥ ተነክረን፣... ውድቀቶችንና ብክነቶችን፣... ገና ከመነሻቸው ለማየትና እውነታውን በግልፅ ለመገንዘብ፣ ቅንጣት ፍላጎት ብናጣና ዳተኛ ብንሆን ምኑ ይገርማል!
በመንግስትና በ”ሕዝብ” ትብብር የግል ቢዝነስ እየተዳከመ፣ እዚህም እዚያም በሆታና በእልልታ የሚፈለፈሉ የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶችም፣... በየጊዜው ከሚዘጋጅላቸው የውዳሴ ሪፖርትና ከሚቀርብላቸው የአዳማቂ ጭብጨባ ጋር፣ በዚያው መጠን በኪሳራ፣ በብክነትና በሙስና የሚጠፋው ሃብት እየጨመረ፣... ከማያቋርጥ የሚሊዮን ብሮች ኪሳራ ጋር፣ የቢሊዮን ብሮች ብክነት ተከታትሎ እየተንሸራተተ፣... በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣... በላይ በላዩ እየተደራረበ እንደጉድ ሲከመር፣... ያኔ፣... የሚንገበገቡ ዜጎች ይበራከታሉ፤... ሆታና አልልታው፣... ውዳሴውና ጭብጨባው ተረስቶ፣... ቁጭት ይበረታል።...
መንገብገብ፣ መቆጨት ባልከፋ። ፋይዳ የሚኖረው ግን፣... ዋናውን ቁምነገር ከምር ለመገንዘብ ፈቃደኛ ከሆንን የተገነዘብነውንም ቁምነገር ነገና ከነገ ወዲያ ካልዘነጋን  ብቻ ነው። አለበለዚያማ ከንቱ ድካም፣ ረብየለሽ ልፋት ይሆናል።... እንደገና የግል ቢዝነስን የማሰናከል ነባር የአገራችንን ባህል ለመለወጥ ካልተጋን፣ እንደወትሮው የግል ኢንቨስትመንትን በስልጣንም ሆነ በአመፅ እያሰናከልን፣ መንግስት ሌሎች አዳዲስ የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን እንዲፈለፍልልን የምንመኝ፣ በሆታና በጭብጨባ የምናጅብ ከሆነ፣... ለከርሞ፣...ለሚቀጥሉት ዓመታትም፣ አዳዲስ የቢሊዮን ብሮች የብክነትና የኪሳራ ጥፋቶች እንዲፈጠሩ እንፈልጋለን ማለት ነው። ታዲያ፣ ባለፉት አመታት ብክነቶች መቆጨታችንና በኪሳራዎች መንገብገባችን ረብየለሽ ከንቱነት አይሆንም?
አዙሪቱም እዚህ ላይ ነው። የግል ቢዝነስንና ኢንቨስትመንትን እያጥላላን የምናሰናክለው፣... የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን በመናፈቅ ነው። ከመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች የምናገኘው ደግሞ፣ የመከራ ሸክም ነው - ኢኮኖሚን የሚያናጋ የቢሊዮኖች ኪሳራና የአገርን ህልውና የሚሸረሽር  የሃብት ብክነት ነው መዘዙ፡፡ ይሄ አንድ ዙር ነው። በዚሁ እየተቆጨንና እየተንገበገብን፣ ነባሩን ፀረ ብልፅግና ባህል ታቅፈን፣ እንደገና የግል ቢዝነስን እያናናቅን፣ እያጥላላን፣... በለመድነው አቅጣጫ፣ የመንግስት ቢዝነስን በሚያወድስ ጎዳና ለመቀጠል እንደገና ሌላ ዙር እንሞክራለን። የሙከራ ዙር ሳይሆን የመከራ ዙር ነው!
ይሄ ነው፣ ለዓመታት የተደጋገመብን የመከራ አዙሪት! እስቲ ዛሬ ይብቃን። የሙስናውን ጉዳይ፣ አቃቤ ህግ፣ ተከሳሾችና ፍርድ ቤት ይጨርሱታል። በትክክል ከተከናወነ፣ ህግና ስርዓትን ለማጠናከር ይረዳል - የህግ የበላይነትን ለማስፋፋት ይሄ አንድ ስራ ነው።
ዋናው ስራ ግን፣ የሜቴክም ሆነ፣ ከሱ ያልተናነሱና በሌሎች የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ የሚከሰቱ አሳዛኝና አንገብጋቢ የሃብት ብክነቶችን ለማስቆም ከምር ከፈለግን፣ ከመንገብገብና ከማዘን ባሻገር ፋይዳ ያለው ትልቅ ቁም ነገር መስራት ከፈለግን፣... ከዛሬ የበለጠ የመማሪያና የመመከሪያ ጊዜ የለም።
የሜቴክ ውድቀትና ቅሌት፣... ትምህርት እና ምክር ይሁነን። የመንግስት ቢዝነስ፣... ከቢሊዮኖች ብር ኪሳራና ከብክነት አዙሪት እንደማያመልጥ እውነታውን ተገንዝበን፣... “እርም” እንበል። ይቅርታ ጠይቀን፣ ከግል ቢዝነስና ከግል ኢንቨስትመንት ጋር እርቅ እንፍጠር።   


Read 5592 times