Saturday, 17 November 2018 11:32

ህመምና መስዋዕትነት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(4 votes)

 ልሒድ ልሒድ አለች ወደ ህልሟ ኬላ
ስጋ ሐር ልብሷን ነብሴ አውልቃ ጥላ ….
 (ተይ አይሆንም ነብሴ፣ ደበበ ሰይፉ! … 1992)
***
ክራውን ሻይነስ ታውቃላችሁ! (ካላወቃችሁ ላጫውታችሁ እፈልጋለሁ፡፡)
***
ጨዋታ -1
ትናንትና ማታ ሲደብረኝና ጭንቀት አናቴ ላይ ሲወጣ፣ ከፊት ለፊቴ እንደ እንቅፋት ሁልጊዜ ከሚያጋጥመኝ ዶዶ ባር ዘው ብዬ ገባሁ፡፡ ቤቱ በሙዚቃ ጩኸት የተናወጠና እኔም ጩኸት የማልወድ ቢሆንም ለዛሬ ከባሬስታው ፊት ለፊት ከሚገኘው የከፍታ ወንበር ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ ቤቱ ውስጥ ብዙ ሰው የለም፡፡ መሃል ላይ አንድ ጠረጴዛ ሞልተው የተቀመጡ ትላልቅ ሰዎችና እኔ ብቻ፡፡ ሰዎቹ ሞቅ ብሏቸዋል፡፡ ሁለት ሴትና ሶስት ወንዶች ናቸው፡፡ ሁሉም ጎልማሶች፡፡
በመሃል የሙዚቃው ስልተ ምት በተቀየረ ቁጥር የሚጨፍር አንድ ሰው አለ፡፡ የእኔን ቀልብ የሳበችው ግን ሌላኛዋ ሴት ናት፡፡ ነጭ የሞላው ከፊት ያለው ፀጉሯን ወደ መሃል ስባ እንደ ፈረስ ጭራ ያሰረች ሲሆን ከማጅራቷ ጀምሮ እስከ መሃል አናቷ ያለው ፀጉር ደግሞ በጣም በአጭር ተቆርጦ ፓንክ ነው፡፡ አለባበሷ የወጣትና ሸንቃጣ ሰውነቷን የሚያሳይ ነው፡፡
ወጣት ልጆች እንደምታደርስ ብገምትም በሚገርም ሁኔታ አይኔን ከእርሷ ማንሳት ተስኖኛል፡፡ በጣም ቀበጥ ትመስላለች፡፡ መቅበጥም ያምርባታል ስል ብቻዬን አስባለሁ፡፡  በመሃል በመሃል በሚመጡ የድሮ ዘፈኖች ስትደንስ ሳይ አፌን መግጠምና ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ። ኦህ … ጌታየዋ፡፡ ዛሬ እዚህ መገኘቴን ወደድኩት። ቀኑን ሙሉ ያሳሰበኝ ነገር ለጊዜውም ቢሆን ጠፋ፡፡ ይህቺ ሴት ግን …. ስል አስባለሁ!  አስር ልጆች ይኖሯት ይሆን! … ጡረታ ወጥታ ይሆን! … የየትኛው ሚስት ትሆን!  አብሬሽ ልደንስ ብላት ምን ይፈጠር ይሆን!  ሴትየዋን ግን ወድጃታለሁ! ምን ዋጋ አለው፡፡ እኔ ‹‹የክራውን ሻይነስ ታማሚ ነኝ!››
ጨዋታ - 2
በ1950 ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ሊው የሚሉት የ 19 አመት ቻይናዊ ወጣት ነበር፡፡ ሊው የ 29 አመቷን፣ የአንድ ልጅ እናት የሆነችውንና ባሏ የሞተባትን ዙን አፈቀራት፡፡ ማፍቀር ደግ ነው። ሆኖም በዘመኑ አንድ ቻይናዊ ወጣት በእድሜ የምትበልጠውን ሴት ማፍቀርም ሆነ ማግባት አይችልም ነበር፡፡ ወጣቱ ሊው ግን መፍትሔ ነበረው፡፡ እሷም አፍቅራው ነበርና ተመካከሩበት፤ ስለዚህ ህግ ወደማያገኛቸውና ወደማይረብሻቸው ቦታ ለመሰደድ ወሰኑ፡፡ ወደ ቾንግኪንግ ጥቅጥቅ ጫካ ገቡና በዋሻ መኖር ጀመሩ፡፡ (ይህ ተረት አይደለም!)
በጫካ ውስጥ ዋሻ ቆፍረው በፍቅር አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ መብራት የለ (በርግጥ በኋላ የላምባ ኩራዝ ይጠቀሙ ነበር)፣ ውሃ ከምንጭ፣ ምግብ እንኳን አልነበራቸውም፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ሳር፣ ቅጠልና ስራስር ይመገቡ ነበር፡፡ በኋላ ሊው በባህላዊ መንገድ መቆፈርና ማልማት ጀመረ፡፡
በዚያም መኖር በጀመሩ ከሁለተኛው አመት ጀምሮ ተራራውን ለመውጣትና ለመውረድ ከባድ ስለነበር ሊው ለሚስቱ ምቾት ሲል በተራራው ላይ ደረጃዎችን እየጠረበ መስራት ጀመረ፡፡ እናም 50 አመት ሙሉ ከሌሎች ስራዎቹ ጋር በትጋት ሰራ፡፡ ደረጃዎቹን ከላይ እስከ ታች ….  አ-ነ-ጠ-ፋ-ቸ-ው፡፡
ከግማሽ ክፍለ ዘመን (ከ50 አመት) በኋላ በ2001 ተራራ ወጪ ጀብደኞች በዚያ ጫካ ወደ ተራራው ሲገቡ፣ እነዚያ ሊው ለባለቤቱ መወጣጫ የሰራቸውን 6000 የተጠረቡ ደረጃዎች አገኟቸው። 6000! ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት ሊው የ72 አመት አዛውንት ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ አንድ ቀን ሊው ከእርሻ ስራው እንደተመለሰ ወዲያውኑ በህመም ተዝለፍልፎ ከሚስቱ እቅፍ ወደቀ፡፡ እሷም እጆቹን እንደጨበጠች አብራው መጸለይ ጀመረች፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ አዛውንቱ ሊው እስከ ወዲያኛው አሸለበ፡፡ ፍቅረኛውና ሚስቱን በግማሽ ክፍለ ዘመን ዕድሜ፣ ለቀናት ሳይለያት ኖሮ እስከ መጨረሻው ተለያት፡፡ በወቅቱ እጅግ በጣም አስቸግሮ የነበረው ነገር፣ በዚያች በመጨረሻዋ ሰአት የተያያዙ እጆቻቸውን ማላቀቅ ነበር፡፡
አሁን ይህንን አካባቢ የቻይና መንግስት አጥሮ ይጠብቀው ጀምሯል፡፡ እንደ ሙዚየምም ይንከባከቡታል፡፡ ደረጃዎቹም ‹‹የፍቅር መሰላል!›› ተብለው ተሰይመዋል፡፡
የጨዋታ - 1 - ሀተታና ማብቂያ!
ቁጭ ብዬ ሳስበው እንዲህ እላለሁ፡፡
የጀግናዬን የሊውን ልብ ይዤ ብፈጠር እንዲህ አደርግ ነበር፡፡ … በሙዚቃው መሃል ተንደርድሬ እነሳና፣ እንባ ያቆረዘዙ አይኖቼን፣ ፍርሃት የሚያንደቀድቀው ልቤንና ብቸኛዋን ነፍሴን ሸክፌ ከባሩ መሃል ላይ በምርጥ የዳንስ ስልት ከምትወዛወዘው ቆንጅዬ ሴትዮ እግር ስር ተንበርክኬ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ … ‹‹ እንዴት ያለሽው ውብ ሴት ነሽ! … ላደንቅሽ ቃላት አይበቁኝም፡፡ ወድጄሻሁ ! …›› እያልኩ መጮህ፡፡
የአስተማሬዬን የጋሼን ልብ ይዤ ብፈጠር ኖሮ ቀጥታ ወደ ጠረጴዛቸው እሄድና … ‹‹ክቡራትና ክቡራን፤ ይህቺን ምርጥ ዘፈን ከዚህች ውብ ፅጌረዳ ጋር ብደንስ ይከፋችኋልን!…›› እላቸዋለሁ። መቼም አያሳፍሩኝም፤ እነዚያን የሚያማምሩ መዳፎች ለአምስት ደቂቃ ያህል በጨበጥኩ ነበር!
ምናልባት በመገረም … ‹አንተን የሚያካክሉ ወጣት ልጆች አድርሻለሁኮ!›› ትለኝ ይሆናል፡፡
እኔም እላለሁ፤ ‹‹እመቤት ቀድመሽ ስለተፈጠርሽ እንጂ አፍቃሪሽስ እኔ መሆን ነበረብኝ፣ ለባለቤትሽም ሚስቱን እንፈልግለታለን።›› …  ሆ! ብለው ሊስቁ ይችላሉ፡፡ ወይም የዚያ የግዙፉ ሰውዬ ቡጢ ፊቴ ላይ ይፈነዳል፡፡
ግና ራሴን ብቻ በመሆኔ እንዲህ ያልቃል፡፡ ለሰከንድ ያህል የሙዚቃው ጩኸት ፀጥ ሲል ወደ ቀልቤ ተመልሼ ዙሪያዬን ብቃኝ በቤቱ የቀረሁት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ሰዎቹ ወጥተው ሄደዋል፡፡ እኔም ከሞቅታዬ ጋር ሳስብ የነበረውን እያሰላሰልኩ ሂሳቤን ከፍዬ ስወጣ ካፊያ ጀምሮ ነበር፡፡ በእውነት ግን እንዲህ አይነት አያሌ ህልማዊ ምሽቶችን ለማሳለፍ የተገደድኩት ‹ … የክራውን ሻይነስ!›..› ተጠቂ ስለሆንኩ አይደለምን!?

የጨዋታ - 2 – (እንዲሁም የሁለቱም) መደምደሚያ!
ረጃጅሞቹ ካኖፒ ዛፎች በልጅነታቸው ተቀላቅለው ያበቅሉና በኋላ ሲያድጉ ግን ይነጣጠላሉ፡፡
በጭራሽ ስለሚተፋፈሩ ቅርንጫፎቻቸው አይነካኩም፡፡ ከአናታቸው ተራርቀው ነው የሚኖሩት፡፡ ይህ የቅርንጫፋቸው አለመነካካት ‹ክራውን ሻይነስ!› ይባላል፡፡
እኔ ደግሞ በጭራሽ ሴቶችን መንካትና መጠጋት ስለማፍር ክራውን ሻይነስ ይዞኛል እላለሁ፡፡ ለራሴ በሽታ የሰጠሁት ስም ነው፡፡ ደግሞም አሁን ይህቺን ሴት ባፈቅር ምን ይፈጠር ይሆን! መቼም አገር ጉድ ይላል!  በውኑ አንዲት ዳንስን በማየት ብቻ ሰው ማፍቀር ይቻላልን! መቼም ነገ ማታም እዚሁ እገኛለሁ፡፡ ምናልባትም ለወራት ከዚሁ አልጠፋም!

Read 2106 times