Saturday, 17 November 2018 11:33

እቅጯን! ‹‹በቤቱ ላይ ደም አለበት፡፡››

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

 እነሆ ፤ ፈጣሪ ምድሪቱን ይገዛ ዘንድ የመረጠው ንጉሥ፤ ለሕዝቡ የሚበጀውን ከማድረግ የሚያውከው፡ ፀጋውን ቀምቶ መርገምትን የሚያስታቅፍ ምን ተግዳሮት ገጠመው ይሆን? ይኸ ፈታኝ ጥያቄ ነበረ፡፡ ንጉሡም መፍትኼውን ሲባጅ ሌት ተቀን በጸሎት ተጠምዶ ከረመ። በእርሱ የንግሥና ዘመን ምድሪቱን ክፉ አበሳ ተጋርጦባታልና፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች መካከል ተጽፎ የሚገኘው ሕያው ፍትኃዊ ገድል እንዲህ ይላል . . .
‹‹በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ራብ ሆነ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፡፡ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስሪያውስ ምንድር ነው? አላቸው። ንጉሡንም እኛን ካጠፋ ፥ በእስራኤልም ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት።››
ሳኦል የገባኦንን ሰዎች መግደሉ ከመሀላ ያፈነገጠ ነበር፡፡ አስቀድሞ በኢያሱ ዘመን የእስራኤል ሕዝብ ወደ (ገባዖን) ከተማቸው በደረሱ ጊዜ ‹‹የሕዝቡም አለቆች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም።›› ሆኖም ግን ሰነባብተው የገባኦን ሰዎች ለፈጸሙት የማታለል ተግባር እያሱም ሊገድላቸው ተነስቶ ነበር፡፡ የገባኦን ሰዎች ግን ስህተታቸውን አምነው እጅ ነሱ... ‹‹እኛ ባሪያዎችህ ምድሪቱን ሁሉ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ ያጠፋ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፥ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን፥ ይህንንም ነገር አድርገናል። አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ውስጥ ነን ለዓይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን አሉት። እንዲሁም አደረገባቸው፥ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፥ አልገደሉአቸውምም። በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠውም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቈራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው።››
የቃል ኪዳን ሕዝቡን ወደ ተስፋው ምድር ሲመራ በየመሀሉ ለገጠማቸው ጦር እግዚአብሔር በምን ተአምር እንደረዳቸው ገባኦያውያን ያውቁ ነበረ፡፡ ለምሳሌ ከአማሌቅ ጋር ሲዋጉ ሙሴ እያሱን ወደ ጦርነቱ ልኮ እርሱ ኮረብታው ላይ ወጥቶ የተፈጸመውን ኩነት፡፡ ‹‹ሙሴም ኢያሱን፦ ጕልማሶችን ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው። ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። እንዲህም ሆነ፡- ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ። ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ።እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ ተናገር አለው። ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም ይህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፡፡ እርሱም፦ እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ።››
የገባኦን ሰዎች ቅን ወዳጅ ታማኝ አገልጋዮች ሳሉ የተሰጣቸው መሀላ ፈርሶ የደረሰባቸው ግፍ በምድሪቱ ላይ መከራ እስኪያመጣ፡ ገዢውን እስኪያስጨንቅ እና እግዚአብሔር ‹‹እቅጯን!›› ምክንያቱን ለገዢው እስኪናገር ደረሰ፡፡ እናም እንደ ሳኦል የቤት ባዳ በሆነ፣ ለነባር የእምነት ቃል ባልተገዛ ንጉሥ በተፈጸመ ያልተገባ ፍርድ፤ ከአምናው ግፍ የተረፈ መገረን እዳው ለዘንድሮው አዲስ የተቀባው ንጉሥ ሲተርፍ፤ የግፉአኑ በደል በፍትህ ካልተቃና፤ እንባቸው በወግ ካልታበሰ፤ ደሙ ካልደረቀ፡ መዘዙ ለምድሪቱና ሕዝቧ ሁሉ የሚተርፍ በጠኔ የመደቆስና መሰል መባረክን በመርገምት የሚውጥ፤ ይኸውም አንዳች ማስተሰርያን ግድ የሚል የውዴታ ግዴታ ወይም የግዴታ ውዴታ አባዜና ትካዜን ያከናንባል። በተለይ የበደል ካሳው እንዲህ እንደ ገባኦን ለመስማት የሚከብድ ጥያቄ ሲሆን ደግሞ ጉዳዩን እጅግ ያጦዘዋል፡፡ ንጉሥ ዳዊት የምድሪቱ በረከት ይፋፋ፤ መርገምቷ ይሰበር ዘንድ በማስተሰረያነት የተጠየቀው ከአማቾቹ ቤተሰብ መካከል ሰዎችን አሳልፎ ለሞት እንዲሰጥ ነበራ!
የሕዝብ እንባ እንዲታበስ መመኘት፤ መወጠንና መከወን ለየቅል ናቸው፡፡ እናስ ንጉሥ ዳዊት ምን ወሰነ? ‹‹ንጉሡም እሰጣችኋለሁ አለ። ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ።››
እናም በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ‹‹እንደ ልቤ›› ብሎ በጠራው በ‹ልበ አምላክ ዳዊት› ላይ እንኳን ከቁጣው ያልተመለሰው። ዳኝነቱ የማያዳላው። ደሀ አደጉንና ምንዱባኑን እሚታደገው፡ የፈጣሪ ፍርዱ፤ ለምድሪቱ መከራ ማብቂያ የሆነው ፍትኃዊ ገድል ይኸ ነበር፡፡ እውነት ነው፤ በእርግጥ በአዲሱ ኪዳን አስተምህሮ ይቅርታና ምህረት እንጂ ‹‹መግደል መሸነፍ ነው››። ግን ደግሞ ቋት ሞልቶ የፈሰሰ መሪር በደልም እንባዋ ይታበስ ዘንድ በአደባባይ ትጮሀለች። አይን ላወጣ አይኑን eye for an eye ቀርቷል ማለት፤ እግዚአብሔር መቸም የማይደራደርበትን የደሀውን መበደል ላፍታም መዘንጋት ከቶም አይቻልም። ደግሞም ‹‹በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል።›› እንዲል አሁንም ወንጌሉ ፤ በይቅርታና ምህረት መደገፍም ሁሉን በእኩል አይን በሚያየው የሕግ ጥላ ስር ሲዳኝ፤  እውነት ነጻነት ያወጣችኋል የተስፋ ቃል ሲፈጸም በአይኑ ለማየት እስኪበቃ በየሰዉ ልቦና ውስጥ አንዳች እረፍት የሚነሳ ጎትጓች ሀሳብ መብላላቱም እንዲሁ ይቀጥላል...ዘላቂ መፍትኄን መራብ መጠማቱ፤ የምድሪቱን መከራ ማብቂያ በጽኑ መቃተቱ፡፡
‹‹ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ። እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፥ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ።››
እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት የመዝሙር ድርሳኑን መክፈቻ ምዕራፍ እንዲህ በሚል ዘላለማዊ፣ ህያውና የእውነት ቃል ጀመረ . . . ‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም። እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።››
ፈጣሪ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ይባርክ!!

Read 687 times