Print this page
Saturday, 17 November 2018 11:33

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

 “የሚጠይቁትን ማወቅ በራሱ በግማሽ መልስ ነው”
            
    በጥንት ዘመን በአንዲት ሃገር ላይ ረዥም ዘመን የገዛ አሴረስ የሚባል ግማሽ አምላክ፣ ግማሽ ሰው የሚመስል ንጉሥ ነበር፡፡ አሴረስ የአገሪቱን ሃብት ሙልጭ አድርጎ በመዝረፍ በግምጃ ቤቱ ሳጥኖች አስቀምጧል፡፡ ባለሟሎቹና ሚስቶቹም በፈለጉበት ጊዜ የፈለጉትን ያህል እንዲወስዱ ሲፈቅድ፣ ከሳጥኖቹ ሁሉ ትልቅ የሆነውን ግን የግሉ ስለሆነ እንዳይነኩ አስጠንቅቋል፡፡ ሳጥኑ ውስጥ ካሁን ቀደም ሳጥኑን በመክፈታቸው አንገታቸውን የቆረጣቸው ሚስቶቹ ጭንቅላት አለ ተብሎ ይወራል፡፡ ወሬው እውነት ይሁን ውሸት ለማረጋገጥ ቤተሰቦቹ ሁሌም ይጓጉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አሴረስ ወደ ዘመቻ ይሄዳል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው ቤተሰቦቹ  ሳጥኑን ከፍተው ሲመለከቱ ባዶ ነው፡፡ … ግራ ገባቸው፡፡
አሴረስ ከዘመቻው ሲመለስ ትልቅ ድግሥ ጠበቀው፡፡ በዚህ የድል ቀን ግብር የገባው ሁሉ ከወትሮው የበለጠ ተደሰተ፡፡ አሴረስ ህዝቡ ሲደሰት ካየ ብዙ ዘመናት ስለሆነው ተገረመ፡፡ ለድሉ ክብር ሲልም ቤተሰቦቹ ምን እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው፡፡ እነሱም …”በትልቁ ሳጥን ውስጥ ያስቀመጥከውን አሳየን” አሉት፤ምን እንደሚመልስላቸው ለመስማት አኮብኩበው፡፡ ቃሉን መጠበቅ አለበትና … “እሺ” አላቸው፡፡ ወደ ግምጃ ቤቱም ይዟቸው በመሄድ ሳጥኑን ከፈተው። ወዲያው ግን ደነገጠ፡፡ … ተቆጣ፡፡ ጎራዴውን መዞ…
“እኔ በሌለሁበት ሳጥኔን የከፈተው ማነው?” ሲል አምባረቀ፡፡ እነርሱም በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፤
“እኛ ነን ነገር ግን በውስጡ ምንም አልነበረም” አሉት፡፡
ጭንቅላቱን እየነቀነቀ … “ጥፋታችሁ ከባድ ነው፤ መሄጃዬ ስለተቃረበ ግን ምሬአችኋለሁ” አላቸው፡፡
እነሱም… “ከፈቀድክልን አልማዝና ወርቅ ሌላ የወሰድነው ነገር የለም፤ ጥፋታችን ምንድነው?” በማለት ጠየቁጽ፡፡
አሴረስም… “ጥፋታችሁ ከአልማዝና ከዕንቁ በላይ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ጉዳይ አስመልጣችኋል” በማለት አስረዳቸው፡፡ … ምን ይሆን?
***
ሊቁ፤ “የማውቀው አለማወቄን ነው” ሲል አለማወቅን ማወቅ ትልቅ ዕውቀት መሆኑን እየነገረን ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው አለማወቃችንን ማወቃችን ብቻ ሳይሆን ብናውቅስ ማወቃችንን በምን እናረጋግጣለን? የሚል ነው፡፡ የምንኖረውን እውነት ሌሎች እንዲነግሩን መፈለግ “የለብንም” እንድንል ያሰኛል፡፡ ከኑሯችን ውስጥ የተነጠቅነው፣ ግን ምን እንደሆነ ‹ያላወቅነው› ነገር አለ፡፡ ባለቤቱ እያለ ከጥላው ጋር ጦርነት መግጠም ከነፋስ ጋር መታገል ነው፤ እንደ ዶን ኪፆቴ!!
ወዳጄ፡- በራሳችን ፈልገን የማናገኘውን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለኑሯችን ባዳ ሆነን ምን እየደረሰብን እንደምንገኝ ንገሩን ማለት ግን ድንቁርና ነው። አለሁ እያሉ አለመኖር፡፡ አልሞትኩም ብሎ መዋሸት፡፡ … “የሚጠይቁትን ማወቅ በራሱ በግማሽ መልስ ነው (To know what to ask is already to know half)” ይባላል፡፡ ህመማችንን ካወቅን ትክክለኛውን መድኃኒት መጠየቅና መዳን አያቅተንም፡፡ ሁሌም በህመም ማስታገሻ፣ ሁሌም በእንቅልፍ መድኃኒት መኖር ፍትሃዊ አይደለም። ጥያቄዎቻችንም ሆኑ መልሶቻቸው እኛው ጋ ናቸው፡፡ በተዘጋጁ (ready made) መልሶች ከተዘናጋን፣ከምንሸሸው እውነት ጋር እንላተማለን። ከእውነት ተሸሽቶ መድረሻ የለም፡፡ ለትውልድ ዕዳ ማቆየት ካልሆነ በቀር!!
ወዳጄ፡- ሰው አህያውን ወይም አህያ አህያን ‹አህያ› ቢለው ስድብ አይደለም፡፡ ስድብ የሚሆነው ደደብ፣ አንበሳ፣ ሆዳም ወዘተ የሚል ቅፅል ከተጨመረበት ነው፡፡ አህያው አንካሳ፣ ሆዳም ወዘተ ከሆነ ከእነ ቅፅሉ ቢጠራ --- ሆዳም አህያ፣ አንካሳ አህያ ቢባል ስድብ ሳይሆን እውነት ነው፡፡ ስድብ የሚያሳፍረው ወይም ‹ተሰደብኩ› የሚያሰኘው ያልሆኑትን ስም ሲያሰጥ  ነው፡፡ ሌባ ‹ሌባ› ቢባል፣ ዘረኛ ‹ዘረኛ› ቢባል፣ ውሸታም ‹ውሸታም› ቢባል ስድብ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡
እኛ ግን ጨዋና ባለጌን፣ ጥሩና መጥፎውን፣ መለየት እያቃተን፣ አንዱን ካንዱ እናማታለን ወይ በጅምላ እንፈርጃለን፡፡ ብዕር ያነሳን ሁሉ ገጣሚና ደራሲ፣ መድረክ ላይ የወጣን ሁሉ አርቲስት፣ ሃኪምን ሁሉ መድህን፣ የታጠቀን ሁሉ ጀግና፣ መሪ የጨበጠን ሁሉ ሾፌር፣ ባለስልጣንን ሁሉ የህዝብ ወገን፣ ህግ አስፈፃሚን ሁሉ ፍትሐዊ እንደሆነ እናስመስላለን፡፡ ህዝባችን ለዘረኝነት ጥቃት የተጋለጠበት፣ የህግ የበላይነት ያልተከበረበት ዋነኛ ምክንያትም ማስመሰላችን ነው፡፡ … ለዚህ ነው የጐደለን ነገር አለ የሚያሰኘው!!
ከሰሞኑ እንዳያነውና እንደሰማነው ቀደም ብሎም እንደምናውቀው፣ ምንም እንኳ ነገሩ መች ተነካና ቢሆንም፤ መንግሥት የሚወስዳቸው ፍትሐዊ እርምጃዎች ያበረታታሉ፡፡ ከህግ በላይ ማንም የለም!! ነፃነት፡- ቮልቴር እንደፃፈው፤ በህግና በሥርዓት መኖር መቻል እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይደለም፡፡  (To be free is to be subject to nothing but the laws)
ወዳጄ፡- የአንድ ሃሳብ ዕውነትነት፣ ፍትህም ሆነ ነፃነት የትክክለኛነቱ ዋጋ የሚለካው ወይም መጠኑ የሚታወቀው በማህበረሰቡ ኑሮ ውስጥ ምክንያታዊ ጥቅም ሲኖረው ነው፡፡ ተፈጥሯዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶች በሚከበሩበት አስተዳደር፣ በህግና በስርዓት መኖር የዜጐችን ህልም፣ ተስፋና ምኞት ያለመልማል። ችግሩ እነዚህ መብቶች የሚረጋገጡበት ሥርዓት የትኛው እንደሆነ አለማወቃችን ይመስለኛል። ለነገሩ አገራችን ፓርላማ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ አምቡድአማን፣ ዓቃቤ ህግ ጽ/ቤት፣ ምርጫ ቦርድ ወዘተ የሚባሉ ተቋማት ያሉባት ሀገር ናት፡፡ ተቋማቱ ግን የጨቋኞች መሣሪያ፣ የፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓት አገልጋይና የ”ህቡዕ መንግሥት” (Under ground Government) መመሪያ አስፈፃሚ ከመሆን አላለፉም። ወዳጄ፡- ስድብ አሳፋሪ የሚሆነው፣ ያልሆኑትን ነን ለሚሉ ሰዎች ነው የተባለው ለዚህ ነው!!
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ሳጥኑ ተከፍቶ ሲታይ በውስጡ ምንም አለመኖሩን አሴረስም መናደዱንና … “ከአልማዝና ከዕንቁ የበለጠ፣ የሰው ልጆች ጉዳይ ከሳጥኑ እንዳመለጠ” መናገሩን ተጨዋውተናል። አሴረስ እውነቱን ነበር፡፡ በሳጥኑ ውስጥ ቆልፎ ያስቀመጠው የሚገዛውን ሐገር ህዝብ የወደፊት ተስፋ፣ ህልምና ምኞት ነበር፡፡ ህዝቡ የሚያውቀው ንብረቱ መዘረፉን ብቻ እንጂ ለትውልድ የሚያሸጋግረው ተስፋውና ህልሙም በድንቁርናው ምክንያት እንደተሰለበ አልገባውም ነበር፡፡ አለማወቅን ማወቅ ሌላው ቢቀር ምን እንደተወሰደብን፣ ምን እንደጎደለን እንድንረዳና እንድንታገል አቅም ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ አለማወቅን ካነሳን አይቀር አንድ ከፍተኛ (ወሳኝ የሚባሉ) የአገራችን ባለስልጣን ከዛሚ ራዲዮ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ እየደጋገሙ “ህዝቡ ደንቁሯል!” ሲሉ ነበር፡፡ ተስፋና ህልሙ ላይ ተቆልፎበታል ዓይነት!!
ወዳጄ፡- አንድ ነገር ልጠይቅህ? ነገን ዓይተህ ታውቃለህ?
 ‹አዎ› ካልክ፣ ውሸትህን ነው፡፡  
‹አላየሁም› ካልክም፣ ውሸትህን ነው፡፡
ሠላም!!

Read 1660 times