Saturday, 24 November 2018 12:08

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር ኃይሏን ልታቋቁም ነው ለማስጠበቅና ራሷን

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ መካከል የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ልትገነባ መሆኑን የመከላከያ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ፡፡ የባህር ኃይል ጦር ሰፈሩ የሚገነባው ከቀይ ባህር ዳርቻ ወደ ውስጥ 60 ኪ/ሜትር ገብቶ በውሃው አካል ላይ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድና ኤርትራን ጨምሮ በርካታ አገሮች የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ለመገንባት መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት ጀነራሉ፤ “ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም የግዴታ የባህር ኃይል ጦር ያስፈልጋታል፤ ይህን እውን ለማድረግም እየተንቀሳቀስን ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን የቀይ ባህርን ለሸቀጥ ማጓጓዣ ብቻ ስትጠቀምበት ነው የኖረችው ያሉት ጀነራሉ፤ ይህ ሁኔታ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ይቀየራል፤ በቀይ ባህር ላይ የራሷ የባህር ኃይል ይኖራታል ብለዋል፡፡
በቀይ ባህር ላይ የባህር ኃይል መገንባቱ ሃገሪቱ በአካባቢው ላይ ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅና ራሷን ከሚቃጡባት የውጭ ጥቃቶች ለመከላከል በእጅጉ አጋዥ መሆኑንም ጀነራሉ ገልፀዋል፡፡
አሁን  የሚገነባው የባህር ኃይል ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ያሟላ፣ በእጅጉ የዘመነና የ100 ሚሊዮን ህዝብ ኃያል ሃገር መሆኗን የሚያሳይ ይሆናል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን የባህር ኃይል እንደገና የማቋቋም ውጥን እንዳላቸው መግለፃቸው ይታወሳል፡፡  

Read 8777 times